ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግያለሁ
ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግያለሁ
ጆሴፊን ኤሊአስ እንደተናገረችው
ባለቤቴ በእስር ቤቱ የብረት አጥር በኩል በሹክሹክታ “አትጨነቂ፤ ሊገድሉኝ ወይም ሊፈቱኝ ይችላሉ፤ እኔ ግን ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ እቀጥላለሁ” አለኝ። እኔም ታማኝ ሆኜ ለመቀጠል ቆርጬ ነበር። ዛሬም ቢሆን የሚሰማኝ እንደዚያው ነው።
በምዕራብ ጃቫ፣ ኢንዶኔዥያ በምትገኝ ሱከቡሚ የምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ በ1916 ተወለድኩ። ወላጆቼ ሀብታም ቻይናውያን የነበሩ ሲሆን ትልቅ ቤትና በርካታ አገልጋዮች ነበሯቸው። ሦስት ታላላቅና ሁለት ታናናሽ ወንድሞች ነበሩኝ። በቤታችን ያለሁት ሴት ልጅ እኔ ብቻ ስሆን ነገረ ሥራዬ ሁሉ እንደ ወንድ ነበር። ጣሪያ ላይ መውጣት እንዲሁም ስፖርት መሥራት እወድ ነበር። ሆኖም በጣም የሚያሳስበኝ አንድ ነገር ነበር።
ገና ለገና በሲኦል ውስጥ እቃጠል ይሆናል ብዬ እጨነቅ ነበር። አስተማሪዬ በጥባጭ ልጆች ሲኦል እንደሚገቡ ትናገር ነበር። እኔ ደግሞ ረባሽ ስለነበርኩ ሲኦል እንደምገባ ይሰማኝ ነበር። በኋላም ጃካርታ ውስጥ (በዚያን ጊዜ ባታቪያ ትባል ነበር) የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በመከታተል ላይ እንዳለሁ ታመምኩ። ሐኪሙ የምሞት መስሎት ስለነበር ቤት ያከራየችኝ ሴት በቅርቡ ወደ ሰማይ እንደምሄድ በመናገር ልታጽናናኝ ሞከረች። ይሁን እንጂ አምላክ ሲኦል እንድገባ ወስኖብኛል ብዬ ስላሰብኩ ፈርቼ ነበር።
እናቴ ካንግ ኒዮ እና ታላቅ ወንድሜ ዶዶ ወደ ቤት ሊወስዱኝ በፍጥነት ጃካርታ መጡ። ወደ ቤት እየሄድን ሳለ ዶዶ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሳታማ ሲኦል እንደማያስተምር ታውቂያለሽ?” ብሎ ጠየቀኝ።
እኔም “እንዴት አወቅህ?” ብዬ ጠየቅሁት። በዚህ ጊዜ እናቴ ሙታን ምንም እንደማያውቁና ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙ የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አነበበችልኝ። (መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ከዚያም “እነዚህን ነገሮች ያስተማሩን የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው” አሉኝ። “ሙታን የት ናቸው?” የሚል ርዕስ ያለውን ቡክሌት የሰጡኝ ሲሆን እኔም ወዲያውኑ ማንበብ ጀመርኩ። * እቤት ከመድረሳችን በፊት “ይህ እውነት ነው!” አልኩ።
ስለ እምነቴ ለሰዎች መናገር
ቤተሰቦቼ በዚህ ወቅት ባንዶንግ ወደሚባል በምዕራብ ጃቫ ወደሚገኝ ትልቅ ከተማ ተዛውረው ነበር። እዚያም ቀስ በቀስ ከሕመሜ አገገምኩ። መጋቢት 1937 ክሌም ዴሾምፕ የተባለ በጃካርታ የሚያገለግል አውስትራሊያዊ የይሖዋ ምሥክር ሊያነጋግረን መጣ። በጉብኝቱ ወቅት እኔና እናቴ እንዲሁም ፌሊክስ፣ ዶዶ እና ፔንግ የተባሉት ታላላቅ ወንድሞቼ ሕይወታችንን ለአምላክ መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን። በኋላም ታናናሽ ወንድሞቼ ሃርታንቶ እና ዩሳክ እንዲሁም አባቴ ታን ጊም ሆክ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። *
ከተጠመቅን በኋላ ለዘጠኝ ቀን በተደረገው ልዩ የስብከት ዘመቻ ላይ ከክሌም ጋር የመሥራት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ክሌም የምሥክርነት መስጫ ካርድ በመጠቀም እንዴት መስበክ እንደምንችል አሳየን፤ ይህ ካርድ በሦስት ቋንቋ የተጻፈ ቀለል ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የያዘ ነበር። በተጨማሪም ለዘመዶቻችንና ለጓደኞቻችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንመሠክር ነበር። ብዙም ሳይቆይ በባንዶንግ የነበረው ትንሹ ቡድናችን በኢንዶኔዥያ ውስጥ ሁለተኛ ጉባኤ ሆነ።
በዚያው ዓመት ትንሽ ቆየት ብሎ ቤተሰባችን 80,000 ቻይናውያን በሚኖሩባት በጃካርታ ለመስበክ ወደዚያ ተዛወረ። እኔ፣ እናቴና ፌሊክስ አቅኚዎች በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን። በተጨማሪም እኔ በባንዶንግ፣ በሱረባየ እና በሌሎች ቦታዎች አገልግያለሁ። አብዛኛውን ጊዜ የምሰብከው ብቻዬን ነበር። ያኔ ወጣት እንዲሁም ጠንካራ የነበርኩ ከመሆኑም ሌላ አምላክን ማገልገል ያስደስተኝ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የጦርነት ደመና አጥልቶ ስለነበር እምነቴ የሚፈተንበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም።
በጦርነቱ ጊዜ ፈተና አጋጠመን
ታኅሣሥ 1941 እስያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትርምስ ውስጥ ተዘፈቀች። የጃፓን ንጉሠ ነገሥት ሠራዊት ኢንዶኔዥያን በቁጥጥር ሥር አዋላት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችን የታገዱ ሲሆን እኛም በይፋ መስበክ አልቻልንም። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመጠየቅ ስሄድ የቼስ መጫወቻ ስለምይዝ ሰዎች ቼስ ለመጫወት የምሄድ ይመስላቸው ነበር።
በ1943 አንድሬ የሚባል ደፋር አቅኚ አገባሁ፤ አንድሬ ድምፁ ኃይለኛ ስለነበር የሰዎችን ትኩረት በቀላሉ መሳብ ይችል ነበር። እኔና አንድሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመላው ጃቫ ለሚገኙ ጉባኤዎች በድብቅ እናደርስ ነበር። እንዲህ ስናደርግ ብንያዝ የሚጠብቀን ሥቃይና ሞት ብቻ ነበር። ለበርካታ ጊዜያት ከመያዝ ያመለጥነው ለጥቂት ነው።
በአንድ ወቅት እኔና አንድሬ በሱከቡሚ ባቡር ልንሳፈር ስንል ኬምፔይታይ ተብሎ በሚጠራው በጃፓን ወታደራዊ ሠራዊት ውስጥ የሚሠራ አንድ ፓሊስ ያዘን። እኔም ሻንጣዬ ውስጥ ከልብሶቼ ሥር የታገዱ ጽሑፎችን ይዤ ነበር። ፖሊሱ “ሻንጣው ውስጥ የያዛችሁት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ።
በዚህ ጊዜ አንድሬ “ልብስ ነው” በማለት መለሰ።
ፖሊሱ “ከልብሶቹ ሥር ያለውስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ።
አንድሬም “ሌላ ልብስ” አለው።
“ግን ከታች በኩል ያለው ምንድን ነው?” በማለት ፖሊሱ በድጋሚ ጠየቀ። እኔ በጣም ብጨነቅም ትንፋሼን ዋጥ አድርጌ በልቤ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በዚህ ጊዜ አንድሬ “ለምን ራስህ ፈትሸህ አታረጋግጥም?” አለው።
ከዚያም የፖሊሱ ረዳት ሻንጣውን ለመፈተሽ እጁን ወደ ውስጥ ከተተ። ወዲያውኑ በጣም ጮኸና እጁን ከሻንጣው ውስጥ አወጣ። ለካ ጣቱን እስፒል ወግቶት ኖሯል። በሁኔታው ያፈረው ፖሊስ ሻንጣውን ዘግተን በአፋጣኝ ወደ ባቡሩ እንድንገባ አዘዘን።
ሌላ ጊዜ ወደ ሱከቡሚ ባደረግነው ጉዞ ኬምፔይታይ ፖሊስ አየኝና የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስላወቀ በአካባቢው ወዳለው የፖሊስ ዋና መምሪያ እንድሄድ አዘዘኝ። አንድሬና ወንድሜ ፌሊክስ ተከትለውኝ መጡ። እዚያ እንደ ደረስን መጀመሪያ ለጥያቄ የቀረበው አንድሬ ነበር። ከዚያም የጥያቄ ናዳ አዥጎደጎዱበት። “የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው? የጃፓንን መንግሥት ትቃወማላችሁ? ሰላይ ነህ?”
አንድሬ “እኛ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አገልጋዮች ነን፤ የሠራነውም ምንም ጥፋት የለም” በማለት መለሰለት። አዛዡ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ የነበረውን ሳሙራይ የሚባሉት የቀድሞ የጃፓን ጦረኞች የሚጠቀሙበትን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣ።
“አሁን ብገድልህስ?” በማለት አንድሬ ላይ አንባረቀበት። ከዚያም አንድሬ ጠረጴዛው ላይ ተደፍቶ በልቡ መጸለይ ጀመረ። ከረዥም ጊዜ ጸጥታ በኋላ ቢሮው በሳቅ ተሞላ። አዛዡ “ደፋር ነህ!” በማለት ተናገረ። ከዚያም አንድሬን አስወጣና እኔንና ፌሊክስን አስገባን። አዛዡ ለቀረበልን ጥያቄ የሰጠነው መልስ ከአንድሬ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ሲመለከት “ሰላዮች አይደላችሁም፤ ሂዱ ከዚህ!” በማለት ጮኸብን።
ሦስታችንም በደስታ ይሖዋን እያመሰገንን ወደ ቤታችን ሄድን። ይሁን እንጂ ከፊታችን ከዚህ የባሰ ፈተና ያጋጥመናል ብለን አላሰብንም ነበር።
ተጨማሪ የእምነት ፈተናዎች
አያሌ ወራት ካለፉ በኋላ “ሐሰተኛ ወንድሞች” አንድሬን ስለ ከሰሱት ካምፔይታይ ፖሊስ አሰረው። (2 ቆሮንቶስ 11:26) ልጠይቀው ወኅኒ ቤት ስሄድ ከስቶና አቅም አጥቶ አገኘሁት። ሕይወቱን ያቆየው ከእጣቢ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ያገኘውን የምግብ ፍርፋሪ እየለቃቀመ በመብላት ነበር። የወኅኒ ቤቱ አዛዦች ይህን ሁሉ ቢያደርጉም የአንድሬን እምነት ማስካድ አልቻሉም። በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት በእስር ቤቱ የብረት አጥር በኩል በሹክሹክታ “አትጨነቂ፤ ሊገድሉኝ ወይም ሊፈቱኝ ይችላሉ፤ እኔ ግን ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ እቀጥላለሁ። ከዚህ ቤት ሬሳዬ ይወጣል እንጂ ክጄ አልወጣም” አለኝ።
አንድሬ በእስር ቤት ስድስት ወር ከቆየ በኋላ በጃካርታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ችሎቱ የሚካሄድበትን ክፍል ሞልተውት ነበር። ሁላችንም በጭንቀት ተውጠን ነበር።
ዳኛው፣ አንድሬን “በጃፓን ጦር ሠራዊት ውስጥ ገብተህ የማታገለግለው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቁት።
አንድሬም “እኔ የአምላክ መንግሥት ወታደር ነኝ፤ አንድ ወታደር ደግሞ በአንድ ጊዜ በሁለት ሠራዊቶች ውስጥ ማገልገል አይችልም” በማለት መልስ ሰጠ።
ዳኛውም “ሌሎች ሰዎች የጦር ሠራዊቱ አባል እንዳይሆኑ ታበረታታለህ?” ብለው ጠየቁት።
አንድሬ “በፍጹም፤ ውሳኔው የራሳቸው ነው” አለ።
አንድሬ በርካታ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ መከላከያ ማቅረቡን ቀጠለ። ዳኛው አጥባቂ ሙስሊም ቢሆኑም በአንድሬ መልስ ተገረሙ። “እምነታችን የተለያየ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሕሊናውን እንዲጥስ አላስገድድም” አሉ። አክለውም “አሁን ነፃ ነህ” አሉት።
በችሎቱ ላይ የተገኘነው በሙሉ ከጭንቀታችን ተገላገልን፤ እኔም በደስታ ፈነጠዝኩ። አንድሬ ወደ እኔ መጣና እጄን ያዘኝ። ከዚያም ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ከበውን ደስታቸውን ይገልጹልን ጀመር።
ስለ እውነተኛው ነፃነት መስበክ
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ኢንዶኔዥያን በቅኝ ግዛት ይዞ በነበረው የደች መንግሥት ላይ ለአራት ዓመት የዘለቀ ዓመፅ ተቀሰቀሰ። በዚህ ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በየመንደሩ የሚኖሩ ሰዎች ቀያቸውን ለቅቀው ተሰደዱ። አርበኞቹ “ነፃነት” የሚል ትርጉም ያለውን “መርዴካ” የሚለውን መፈክር እንድናሰማ ሊያስገድዱን ሞከሩ። ይሁንና እንዲህ ካሉት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ገለልተኞች መሆናችንን ነገርናቸው።
በአካባቢው ዓመፅ ነግሦ የነበረ ቢሆንም ከቤት ወደ ቤት መስበካችንን ቀጠልን። በአገልግሎት ላይ የምሥክርነት መስጫ ካርዶችንና ከጦርነቱ በፊት የነበሩንን ጽሑፎች እንጠቀም ነበር። ዓመፁ በረድ ካለ በኋላ ግንቦት 1948 እኔና አንድሬ እንደገና አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን፤ በወቅቱ በኢንዶኔዥያ ውስጥ አቅኚ የነበርነው እኛ ብቻ ነን። ከሦስት ዓመታት በኋላ በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ 14 የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጃካርታ ሲመጡ የተሰማኝን ደስታ መግለጽ ያቅተኛል። ከእነሱ ያገኘነው ሥልጠና ተጨማሪ ኃላፊነት መሸከም እንድንችል አስታጥቆናል።
ሰኔ 1952 እኔና አንድሬ በማዕከላዊ ጃቫ በምትገኘው ሰማራንግ ከተማ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። በቀጣዩ ዓመት እኛ ራሳችን በጊልያድ ትምህርት ቤት 22ኛውን ክፍል ተካፈልን። ከተመረቅን በኋላ ወደ ኢንዶኔዥያ ተመለስን፤ ከዚያም በኩፓንግ፣ ቲሞር እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያ በኋላ በደቡብና በሰሜን ሱላዌሲ አገልግለናል። እዚያም ሌሎች የእምነት ፈተናዎች አጋጥመውናል።
ሥራችን እንደገና ታገደ
በ1965 መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ የተደረገው ሙከራ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ የገቡ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች ኮሚኒስቶች ናቸው ብለው ይከሱ ጀመር። ደግነቱ ባለሥልጣናቱ አላመኗቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ቀሳውስቱ ምንም ተስፋ ሳይቆርጡ በይሖዋ ምሥክሮቹ ላይ የጀመሩትን የስም ማጥፋት ዘመቻ ገፉበት። በመጨረሻም ታኅሣሥ 25, 1976 የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታገደ።
እገዳው ይፋ ከተደረገ ብዙም ሳይቆይ በመናዶ የሚገኘው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አንድሬን ወደ ቢሮው አስጠራው። ከዚያም “የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ መታገዱን ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀው።
አንድሬም “አዎን” ብሎ መለሰለት።
ባለሥልጣኑም “አሁን ሃይማኖትህን ለመቀየር ተዘጋጅተሃል?” በማለት ጠየቀው።
አንድሬ ትንሽ ጎንበስ አለና ደረቱን መታ መታ እያደረገ “ደረቴን ቀድደህ ልቤን ማውጣት ትችላለህ። ሃይማኖቴን ግን ፈጽሞ ማስቀየር አትችልም” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ።
በዚህ ጊዜ ዐቃቤ ሕጉ በጣም ደንግጦ “ታዲያ በሪፖርቴ ላይ ምን ብዬ ልጻፍ?” ብሎ ጠየቀው።
አንድሬም “አሁንም የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩና ምንም የሠራሁት ጥፋት እንደሌለ ጻፍ” አለው።
ዐቃቤ ሕጉ ደግሞ “ጽሑፎቻችሁን ሁሉ መውረስ አለብኝ” አለው።
ያን ዕለት ማታ አንዳንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻችንን ከቤታችን አውጥተው ወደ ሌላ ሥፍራ በመውሰድ ሣጥኖቹን ባዶ አስቀሯቸው። እኛም መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም
መስበካችንን ቀጠልን። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ከዚያ በኋላ አስቸግሮን አያውቅም።ሕይወቴ አስደሳች ነበር!
ከዚያ ወዲህ እኔና አንድሬ በጃቫ ደሴት ላይ በምትገኘው በሱረባየ ከተማ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ ሱማትራ ባለችው ባንግከ ደሴት በአቅኚነት አገልግለናል። ይሁንና አንድሬ የጤና ችግር ስላጋጠመው በ1982 ወደ ጃካርታ ለመመለስ ተገደድን። በ2000 አንድሬ ጃካርታ እያለን ሞተ፤ አንድሬ በ85 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በቅንዓት የሚያገለግል አቅኚ ነበር። እሱ ከሞተ ከአንድ ዓመት በኋላ በሥራችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሳ።
ያሳለፍኩት ሕይወት በጣም አስደሳች ነበር! በአሁኑ ጊዜ ዕድሜዬ 93 ዓመት ሲሆን ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት አገልግያለሁ። በ1937 ስጠመቅ በኢንዶኔዥያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 25 ብቻ ነበር። አሁን ግን ወደ 22,000 ይጠጋል። እንዲህ ያለው እድገት እንዲገኝ የበኩሌን አስተዋጽኦ በማበርከቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ! ይሁን እንጂ የሕይወት ጉዞዬ ገና መጀመሩ ነው። አምላክን ለዘላለም በታማኝነት ማገልገል እፈልጋለሁ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.7 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተሙን አቁሟል።
^ አን.9 መላው ቤተሰብ እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ ነበር። ከቤተሰቡ መካከል ዛሬ በሕይወት የቀሩት ጆሴፊንና ዩሳክ ሲሆኑ አሁንም በጃካርታ በቅንዓት እያገለገሉ ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እኔ የአምላክ መንግሥት ወታደር ነኝ፤ አንድ ወታደር ደግሞ በአንድ ጊዜ በሁለት ሠራዊቶች ውስጥ ማገልገል አይችልም”
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ደረቴን ቀድደህ ልቤን ማውጣት ትችላለህ። ሃይማኖቴን ግን ፈጽሞ ማስቀየር አትችልም”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የኖርንባቸውና ያገለገልንባቸው ቦታዎች
ኢንዶኔዥያ
ሱላዌሲ
መናዶ
ሱማትራ
ባንግከ
ጃቫ
ጃካርታ
ሱከቡሚ
ባንዶንግ
ሰማራንግ
ሱረባየ
ቲሞር
ኩፓንግ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1970ዎቹ ዓመታት ከአንድሬ ጋር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ “ሙታን የት ናቸው?” የሚል ርዕስ ያላትን አንዲት ትንሽ ቡክሌት በማንበብ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተረዳሁ