የመንፈስ ጭንቀት ምን ስሜት ይፈጥራል?
የመንፈስ ጭንቀት ምን ስሜት ይፈጥራል?
“የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ተነስቼ በአልጋዬ ጫፍ ላይ ቁጭ ካልኩ በኋላ ‘ዛሬ የምሞትበት ቀን ነው እንዴ?’ ብዬ አሰብኩ” በማለት ጄምስ * ከዓመታት በፊት የተሰማውን ስሜት ተናግሯል። በዚያን ወቅት ጄምስ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ጀምሮት ነበር። “እያንዳንዱን ቀን ከዚህ የስሜትና የአእምሮ ሕመም ጋር ስታገል ኖሬያለሁ” በማለት ከ30 ዓመታት በኋላ ተናግሯል። ጄምስ ወጣት ሳለ የከንቱነት ስሜት ይሰማው ስለነበር የልጅነት ፎቶግራፎቹን እንኳን ቀዳዷቸው ነበር። “መታወስ የሚገባኝ ሰው እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር” በማለት ተናግሯል።
ሁላችንም አልፎ አልፎ በሐዘን ስሜት ስለምንዋጥ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ከምን ዓይነት ስሜት ጋር እየታገለ እንዳለ የምናውቅ ይመስለን ይሆናል። ይሁንና ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች የሚሰማቸው ስሜት ምንድን ነው?
ዱብ ዕዳ
ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ የሐዘን ስሜት ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዳያከናውን እንቅፋት የሚሆን አሳሳቢ የመረበሽ ስሜት ነው።
ለምሳሌ ያህል፣ አልቫሮ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት “በፍርሃትና ግራ በመጋባት ስሜት እንዲሁም በከፍተኛ የአእምሮ ሥቃይና በመሪር ሐዘን” ሲሠቃይ ኖሯል። እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “የመንፈስ ጭንቀት ስላለብኝ ሰዎች ስለእኔ የሚሰጡት ሐሳብ ይጎዳኝ ነበር። ለተፈጠረው ስህተት ሁሉ ምንጊዜም ራሴን እኮንን ነበር።” አልቫሮ የመንፈስ ጭንቀት ምን ስሜት እንደሚያሳድር ሲገልጽ “የት ቦታ እንደሚያምህ ሳታውቅ በኃይለኛ ሕመም ትሠቃያለህ፤ ለምን እንደሆነ ሳታውቅ ትፈራለህ፤ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ፈጽሞ ስለ ችግሩ ማውራት አትፈልግም” በማለት ተናግሯል። አሁን ግን አልቫሮ የችግሩን ምንነት ማወቁ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ አስገኝቶለታል። “እንደ እኔ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ ማወቄ ብቻ እንኳ ረድቶኛል” ሲል ተናግሯል።
በብራዚል የምትኖር ማሪያ የተባለች የ49 ዓመት ሴት የመንፈስ ጭንቀት ባስከተለባት የእንቅልፍ ማጣትና የሕመም ስሜት ትሠቃይ የነበረ ከመሆኑም በላይ በትንሽ ትልቁ ትነጫነጭ ነበር፤ እንዲሁም “ማባሪያ የሌለው የሚመስል የሐዘን ስሜት” ነበረባት። ማሪያ ተመርምራ ሕመሟ ምን እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ስታውቅ እፎይታ ተሰማት። “በኋላ ላይ ግን ይበልጥ ስጋት አደረብኝ፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች ስለመንፈስ ጭንቀት ጥሩ ግንዛቤ የላቸውም፤ እንዲሁም አሳፋሪ ነገር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል” በማለት ገልጻለች።
ያለምንም ምክንያት ማዘን
የመንፈስ ጭንቀት አንዳንድ ጊዜ ግልጽ የሆነ መንስኤ ቢኖረውም ብዙውን ጊዜ ሕመሙ የሚጀምረው በድንገት ነው። በደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ሪቻርድ እንዲህ ብሏል፦ “ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳታውቅ ሕይወትህ በድንገት የሐዘን ደመና ያጠላበታል። የምታውቀው ሰው አልሞተብህም፤ ምንም የሚያሳዝን ነገር አልደረሰብህም። ሆኖም በከባድ ሐዘን ትዋጥና ሐሞትህ ፍስስ ይላል። ይህን የሐዘን ደመና ሊገፍልህ የሚችል ምንም ነገር የለም። ምክንያቱን ሳታውቀው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ትዋጣለህ።”
አንድ ሰው የመንፈስ ጭንቀት ያለው መሆኑ ሊያሳፍረው አይገባም። ሆኖም በብራዚል የምትኖር አና የምትባል ሴት የመንፈስ ጭንቀት እንዳለባት ሲነገራት የኀፍረት ስሜት ተሰማት። “ስምንት ዓመት አልፎም እንኳ አሁንም ሁኔታው ያሳፍረኛል” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። በተለይም የሚሰማትን ከፍተኛ የሐዘን ስሜት መቋቋም አስቸጋሪ ሆኖባታል። “አንዳንድ ጊዜ ሥቃዩ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ አካላዊ ሕመም ይሰማኛል። የሰውነቴ ጡንቻዎች በሙሉ ይተሳሰራሉ” በማለት ገልጻለች። በዚህ ጊዜ ከአልጋ መነሳት እንኳ ከባድ ሊሆን ይችላል። አና ያለማቋረጥ የምታለቅስባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲያውም “ስቅስቅ ብዬ ከማልቀሴ የተነሳ
ሰውነቴ ሁሉ ይዝልና ደሜ ራሱ መዘዋወር እንዳቆመ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ተናግራለች።መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች መንፈሳቸው በጣም ሊደቆስ እንደሚችል ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አንድ ሰው የተሰማውን ስጋት ሲገልጽ ይህ ሰው ‘ከልክ በላይ በሐዘን ሊዋጥ [“ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዘው፣” ጂዊሽ ኒው ቴስታመንት]’ እንደሚችል ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 2:7) የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች በጣም ከማዘናቸው የተነሳ ሞትን ይመኛሉ። ብዙዎች “ከምኖር መሞት ይሻለኛል” ብሎ እንደተናገረው እንደ ነቢዩ ዮናስ ይሰማቸዋል።—ዮናስ 4:3
ታዲያ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ምን ዓይነት ሕክምና ማግኘት ይችላሉ? እንዲህ ያለውን ሕመም መቋቋም የሚችሉትስ እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ ያሉት ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳታውቅ ሕይወትህ በድንገት የሐዘን ደመና ያጠላበታል”