በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ እምነቴ ለሌሎች መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

ስለ እምነቴ ለሌሎች መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ እምነቴ ለሌሎች መናገር የሚያስፈራኝ ለምንድን ነው?

“በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ ለመናገር የሚያስችሉኝ ግሩም አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር። ያም ሆኖ በአጋጣሚው አልተጠቀምኩበትም።”—ካሌብ *

“በክፍል ውስጥ መምህራችን ስለ ዝግመተ ለውጥ ምን አመለካከት እንዳለን ጠየቀችን። ይህ ስለ እምነቴ ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ባውቅም በጣም ስለፈራሁ የምናገረው ጠፋኝ። በኋላ ግን በሁኔታው በጣም አዘንኩ።”—ጃዝሚን

አንተም ክርስቲያን ወጣት ከሆንክ እንደ ካሌብና ጃዝሚን ተሰምቶህ ያውቅ ይሆናል። እንደ እነዚህ ወጣቶች ሁሉ አንተም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የምትወዳቸው ከመሆኑም ሌላ የተማርካቸውን ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ትፈልጋለህ። ያም ሆኖ እምነትህን ለሌሎች ስለ ማካፈል ስታስብ በፍርሃት ትርድ ይሆናል። ይሁን እንጂ በድፍረት የመናገር ችሎታ ማዳበር ትችላለህ። እንዴት? ከዚህ በታች የቀረቡትን ነጥቦች ተግባራዊ በማድረግ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ራስህን ማዘጋጀት ትችላለህ።

1. የሚያስፈሩህን ሁኔታዎች ለይተህ እወቅ። እምነትህን ለሌሎች ስለ መናገር ስታስብ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ሊያጋጥምህ የሚችለው መጥፎ ነገር ሊሆን ይችላል! ይሁንና የሚያስፈሩህን ነገሮች በጽሑፍ ማስፈርህ በራሱ ፍርሃትህ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል።

የሚከተለውን ዓረፍተ ነገር ለማሟላት ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ሐሳብህን አስፍር።

▪ በትምህርት ቤት ስለ እምነቴ ብናገር ሊፈጠር የሚችለው ሁኔታ፦

․․․․․․

አንተን የሚያስፈሩህ ነገሮች ሌሎች ክርስቲያን ወጣቶችንም ሊያስፈሯቸው እንደሚችሉ ማወቅህ ያበረታታህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የ14 ዓመቱ ክሪስቶፈር “ልጆቹ እንዳያፌዙብኝና የተለየሁ ሰው እንደሆንኩ አድርገው እንዳያስወሩብኝ እፈራለሁ” በማለት ተናግሯል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ካሌብም “አንድ ሰው ጥያቄ ቢጠይቀኝና መልሱን ባላውቀውስ የሚለው ሐሳብ ያስጨንቀኛል” ብሏል።

2. ፈተናዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉ አምነህ ተቀበል። እንደዚህ ያለው ፍርሃት ጨርሶ መሠረት የሌለው ነው ሊባል ይችላል? እንደዚያ ማለት አይቻልም። አሽሊ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ልጆች ስለ እምነቴ ማወቅ የሚፈልጉ በመምሰል ቀርበውኝ ነበር። በኋላ ግን የተናገርኩትን ነገር በማጣመም በሌሎች ልጆች ፊት አሾፉብኝ።” የ17 ዓመት ወጣት የሆነው ኒኮል ያጋጠመውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ልጅ እኔ በያዝኩት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኝን አንድ ጥቅስ ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲያወዳድር ቃላቱ እንደሚለያዩ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ የያዝኩት መጽሐፍ ቅዱስ እንደተለወጠ ተናገረ። እኔም ምን ማለት እንዳለብኝ ስላላወቅኩ ክው ብዬ ቀረሁ!” *

እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች በጣም እንደሚያስፈሩ ሊሰማህ ይችላል! ይሁንና በፍርሃት ተሸንፈህ ከመናገር ወደኋላ ከማለት ይልቅ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ሊያጋጥሙህ የሚችሉ ነገሮች እንደሆኑ አምነህ ተቀበል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) የ13 ዓመቱ ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ስደት እንደሚደርስባቸው ተናግሯል፤ ስለዚህ ሁሉም ሰው እኛንም ሆነ እምነታችንን እንደሚወድ መጠበቅ አንችልም።”—ዮሐንስ 15:20

3. ስለምታገኛቸው ጥቅሞች አስብ። መጥፎ ሁኔታ ሊያጋጥምህ እንደሚችል ታስብ ይሆናል፤ ይሁንና ከዚህ ሁኔታ መልካም ውጤት ሊገኝ ይችላል? የ21 ዓመት ወጣት የሆነችው አምበር እንደዚህ ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ለሌላቸው ሰዎች ስለ እምነታችሁ ማስረዳት ከባድ ነው። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችሁ እግረ መንገዳችሁን የራሳችሁን አቋም ለመመርመርና ለማወቅ አጋጣሚ ይሰጣችኋል።”—ሮም 12:2

በተራ ቁጥር 1 ሥር ባለው ክፍት ቦታ ላይ አስፍረኸው የነበረውን ሐሳብ እስቲ በድጋሚ ተመልከተው። ሊፈጠር ይችላል ብለህ ያሰብከው ይህ ሁኔታ ሊያስገኛቸው የሚችላቸውን ቢያንስ ሁለት ጥቅሞች ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ከታች ባለው ባዶ ቦታ ላይ ጻፋቸው።

1 ․․․․․․

2 ․․․․․․

ፍንጭ፦ ስለ እምነትህ መናገርህ እኩዮችህ የሚያሳድሩብህ ተጽዕኖ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችል ይሆን? ስለ እምነትህ መናገርህ በራስ የመተማመን ስሜትህ እንዲጎለብት የሚያደርገው እንዴት ነው? ለይሖዋ አምላክ ያለህን አመለካከትስ የሚነካው እንዴት ነው? እሱስ ስለ አንተ ምን እንዲሰማው ያደርጋል?—ምሳሌ 23:15

4. ዝግጅት አድርግ። ምሳሌ 15:28 “የጻድቅ ሰው ልብ የሚሰጠውን መልስ ያመዛዝናል” ይላል። ስለ እምነትህ ምን ብለህ እንደምትናገር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሊያነሷቸው የሚችሉ ጥያቄዎችንም ለማሰብ ሞክር። በእነዚህ ርዕሶች ላይ ምርምር አድርግ፤ እንዲሁም በራስህ አገላለጽ ልትሰጠው የምትችለውን መልስ ተዘጋጅ።—በገጽ 25 ላይ የሚገኘውን  “ምን መልስ እንደምትሰጥ ተዘጋጅ” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

5. እንዴት እንደምትጀምር አስብ። ስለ እምነትህ ለመናገር ዝግጅት ካደረግህ በኋላ እንዴት እንደምትጀምር ታስብ ይሆናል። የተለያዩ አማራጮች አሉህ። ስለ እምነትህ መናገር ከመዋኘት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፦ አንዳንዶች ወደ ውኃው የሚገቡት ቀስ ብለው ነው፤ ሌሎች ደግሞ ዘሎ መግባትን ይመርጣሉ። ወደ ውኃው ቀስ ብለው እንደሚገቡ ሰዎች ሁሉ አንተም ከሃይማኖት ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ጉዳዮች በማንሳት ውይይት ከጀመርክ በኋላ የግለሰቡን ስሜት እየተመለከትክ ውይይቱ ቀስ በቀስ በመንፈሳዊ ነገር ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ትመርጥ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን ገና ለገና መጥፎ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ በጣም የምትጨነቅ ከሆነ የተሻለው አማራጭ፣ ልክ ውኃ ውስጥ ዘለው እንደሚገቡ ሰዎች በቀጥታ ስለ እምነትህ መናገር ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 12:11, 12) የ17 ዓመቱ አንድሩ እንዲህ ብሏል፦ “ምንጊዜም ቢሆን እምነቴን ለሌሎች ከማካፈል ይበልጥ የሚከብደኝ፣ እንዲህ ለማድረግ ማሰቡ ነው። አንድ ጊዜ ውይይት ከተጀመረ በኋላ ግን ስለ እምነቴ መናገር ካሰብኩት የበለጠ ቀላል ይሆንልኛል።” *

6. አስተዋይ ሁን። ጥልቀት የሌለው ውኃ ውስጥ ዘለህ እንደማትገባ ሁሉ ትርጉም የሌለው ክርክር ውስጥ ላለመግባትም ተጠንቀቅ። ለመናገርም ሆነ ለዝምታ ጊዜ እንዳለው አስታውስ። (መክብብ 3:1, 7) ኢየሱስም እንኳ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 26:62, 63) ከዚህም በተጨማሪ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስታውስ፦ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን . . . [“ሰተት ብሎ ወደ መከራ ከገባ በኋላ እንደገና ይጸጸታል፣” የ1980 ትርጉም]።”—ምሳሌ 22:3

ስለዚህ ውይይቱ ወደ ክርክር እያመራ እንደሆነ ካስተዋልክ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ‘ሰተት ብለህ አትግባ።’ ከዚህ ይልቅ አጠር ያለና ማስተዋል የሚንጸባረቅበት መልስ ስጥ። ለምሳሌ ያህል፣ ከክፍልህ ተማሪዎች አንዱ እያፌዘ ‘ለምን ሲጋራ አታጨስም?’ ቢልህ ‘ሰውነቴን መበከል አልፈልግም!’ ብለህ መመለስህ በቂ ሊሆን ይችላል። ልጁ የሚሰጥህን ምላሽ ካየህ በኋላ ስለ እምነትህ የበለጠ ማብራራት ይኖርብህ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ትችላለህ።

ከላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች ስለ እምነትህ “መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ” እንድትሆን ያስችሉሃል። (1 ጴጥሮስ 3:15) እርግጥ ዝግጁ መሆንህ ፈጽሞ ፍርሃት እንዳይሰማህ ያደርጋል ማለት አይደለም። የ18 ዓመቷ አላና እንዲህ ብላለች፦ “ፍርሃት እየተሰማህም እንኳ ስለ እምነትህ መናገርህ አንድ ነገር እንዳከናወንክ እንዲሰማህ ያደርጋል፤ ፍርሃትህን ማሸነፍ እንዲሁም ሊሳካም ላይሳካም እንደሚችል እያወቅህም እንኳ በድፍረት መናገር ችለሃል። መናገርህ መልካም ውጤት እንዳስገኘ ስትመለከት ደግሞ የበለጠ ጥሩ ስሜት ይሰማሃል! በድፍረት መናገር መቻልህ ያስደስትሃል።”

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.11 የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንድን ሐሳብ ለመግለጽ የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ትርጉሞች በተቻለ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሐሳቡ ከተገለጸበት መንገድ ሳይርቁ ቃል በቃል ለመተርጎም ጥረት ያደርጋሉ።

^ አን.19 በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን  “ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ሐሳቦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

በምትማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ልጆች እንደሚከተለው ብለው ያስቡ ይሆን?

‘የይሖዋ ምሥክር እንደሆንሽ አውቃለሁ። ምናልባት ታሾፍብኛለች ብለሽ ታስቢ ይሆናል፤ እኔ ግን በጣም አከብርሻለሁ። በዓለም ላይ ይሄ ሁሉ ችግር እያለ አንቺ ግን የመረጋጋት ስሜት ሊታይብሽ የቻለው እንዴት ነው? እኔ በበኩሌ ፍርሃት ይሰማኛል። ሌላ ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን? ወላጆቼ በፍቺ ይለያዩ ይሆን? ሌሎች ልጆች ሳይደበድቡኝ በሰላም ትምህርት ቤት ደርሼ መምጣት እችል ይሆን? በአእምሮዬ የሚመላለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፤ አንቺ ግን በሕይወትሽ ውስጥ ምን ለማድረግ እንደምትፈልጊ በሚገባ የምታውቂ ይመስላል። ለመሆኑ እንደዚህ እንድትሆኚ ያደረገሽ ሃይማኖትሽ ነው? ስለዚህ ጉዳይ መወያየት ብፈልግም ነገሩን አንስቶ ውይይት መጀመር ግን ያስፈራኛል። ውይይቱን አንቺ መጀመር ትችያለሽ?’

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“ስለ እምነቴ ስናገር የሚስቁብኝ አንዳንድ ልጆች ነበሩ። ይሁንና ሲያሾፉብኝ እንደማልበሸቅ ሲገነዘቡ ብዙውን ጊዜ ትተውኝ ይሄዳሉ።”—ፍራንቼስካ፣ ቤልጅየም

“ስለ እምነትህ ለሌሎች የማትናገር ከሆነ ክርስቲያን መሆንህን ልትዘነጋና እንደ ሌሎቹ መሆን ልትጀምር ትችላለህ። ዝም ብለህ ሌሎችን አትከተል፤ ከዚህ ይልቅ የራስህ አቋም ይኑርህ።” —ሳማንታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ልጅ እያለሁ ከሌሎች ልጆች የተለየሁ ሆኜ መታየት አልፈልግም ነበር። ከፍ እያልኩ ስሄድ ግን እምነቴ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረኝ እንደረዳኝ መገንዘብ ጀመርኩ። ይህም ይበልጥ በራሴ እንድተማመን ረድቶኛል፤ በማምንበት ነገር ኩራት እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”—ጄሰን፣ ኒው ዚላንድ

 [በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ሐሳቦች

“በሚቀጥሉት ወራት ምን ለማድረግ አስበሃል?” [የሚሰጥህን ምላሽ ካዳመጥክ በኋላ አንተ ስላወጣሃቸው መንፈሳዊ እቅዶች ንገረው፤ ለምሳሌ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሊያም አገልግሎትህን በስፋት ለማከናወን ማሰብህን ልትነግረው ትችላለህ።]

▪ በዜና ስለሰማኸው አንድ ጉዳይ ከጠቀስክ በኋላ እንዲህ በማለት ጠይቅ፦ “ስለዚህ ጉዳይ ሰምተህ ነበር? ታዲያ ምን ተሰማህ?”

“በዓለም ላይ የተፈጠረው የገንዘብ ቀውስ [ሌላም ችግር ሊሆን ይችላል] የሚስተካከል ይመስልሃል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] እንደዚህ ሊሰማህ የቻለው ለምንድን ነው?”

“ሃይማኖትህ ምንድን ነው?”

“ከአምስት ዓመት በኋላ ምን ዓይነት ሕይወት የሚኖርህ ይመስልሃል?” [የሚሰጥህን ምላሽ ካዳመጥክ በኋላ አንተ ስላወጣሃቸው መንፈሳዊ ግቦች ንገረው።]

 [በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ምን መልስ እንደምትሰጥ ተዘጋጅ

ቆርጠህ አውጣው!

የሚከተለውን ሐሳብ እናቀርብልሃለን፦ ይህን ሠንጠረዥ ከወላጆችህና ከጓደኞችህ ጋር ተወያይበት። በተሰጠህ ምሳሌ መሠረት ሠንጠረዡን ሙላው። ከዚያም የክፍልህ ተማሪዎች ሊያነሷቸው የሚችሉ ሌሎች ጥያቄዎችን ለማሰብ ሞክር።

ሥነ ምግባር

ጥያቄ

ስለ ግብረ ሰዶም ምን አመለካከት አለህ?

መልስ

ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሰዎችን አልጠላቸውም፤ ይሁንና በድርጊታቸው አልስማማም።

ሌላ ጥያቄ

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ምክንያታዊነት የጎደለው አይሆንም?

ምርምር

1 ቆሮንቶስ 6:9, 10ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ጥራዝ 2 ምዕራፍ 28 *

መልስ

በፍጹም፤ ምክንያቱም እኔ ግብረ ሰዶምን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግናዎች እጠላለሁ።

የፍቅር ጓደኝነት

ጥያቄ

የፍቅር ጓደኛ የማትይዘው ለምንድን ነው?

መልስ

ዕድሜዬ እስኪደርስ ድረስ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት ላለመመሥረት ስለወሰንኩ ነው።

ሌላ ጥያቄ

ይህን የማታደርገው የይሖዋ ምሥክር ስለሆንክ ነው?

ምርምር

ማሕልየ መሓልይ 8:4የወጣቶች ጥያቄ፣ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 1

መልስ

አዎ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት የምንመሠርተው ለማግባት ስናስብ ብቻ ነው፤ እኔ ደግሞ ለዚህ አልደረስኩም!

የገለልተኝነት አቋም

ጥያቄ

ብሔራዊ መዝሙር የማትዘምረው ለምንድን ነው?

መልስ

ለአገሬ አክብሮት አለኝ፤ ይሁን እንጂ አገሬን አላመልክም።

ሌላ ጥያቄ

ስለዚህ ለአገርህ አትዋጋም ማለት ነው?

ምርምር

ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 13:35ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ገጽ 148-151 *

መልስ

በፍጹም አልዋጋም። በሌሎች አገሮች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችም አገራችንን ለመውጋት አይነሱም።

ደም

ጥያቄ

ደም የማትወስደው ለምንድን ነው?

መልስ

በኤድስ እንደመያዝ ያሉ አደጋዎችን የማያስከትሉ ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን እቀበላለሁ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከደም እንድርቅ ስለሚያዝ ደም አልወስድም።

ሌላ ጥያቄ

እሺ፣ ደም ባለመውሰድህ ምክንያት የምትሞት ቢሆንስ? አምላክ ይቅር ሊልህ አይችልም?

ምርምር

የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29፤ ዕብራውያን 11:6የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ገጽ 129-131

መልስ

የግል ምርጫ

ጥያቄ

የእናንተ እምነት አባል የሆነው እገሌ እንዲህ ሲያደርግ አይቼዋለሁ። አንተስ ለምን እንደዚህ አታደርግም?

መልስ

አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ተምረናል፤ ይሁን እንጂ የተማርነውን ተግባራዊ እንድናደርግ አንገደድም። ሁላችንም የራሳችንን ምርጫ ማድረግ አለብን።

ሌላ ጥያቄ

ታዲያ እያንዳንዱ ሰው የሚመራበት የተለያየ መሥፈርት አለ ማለት ነው?

ምርምር

መልስ

ፍጥረት

ጥያቄ

በዝግመተ ለውጥ የማታምነው ለምንድን ነው?

በዝግመተ ለውጥ እንዳምን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለ? እውቀት አላቸው የሚባሉት ሳይንቲስቶች ራሳቸው እንኳ በዚህ ጉዳይ እርስ በርሳቸው አይስማሙም!

ሌላ ጥያቄ

ምርምር

መልስ

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.56 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

^ አን.78 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ መናገር ከመዋኘት ጋር ይመሳሰላል። ውይይቱ ቀስ በቀስ በእምነትህ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አሊያም በቀጥታ ስለ እምነትህ መናገር ትችላለህ!