ዓለምን በካርታ ያስቀመጠው ሰው
ዓለምን በካርታ ያስቀመጠው ሰው
ቤልጂየም የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው
በ1544 መጀመሪያ ላይ ጌራርዲየስ መርኬተር በጣም በሚቀዘቅዝ ጨለማ ክፍል ውስጥ ታስሮ ነበር። በ16ኛው መቶ ዘመን የኖረው ይህ ታላቅ ሰው እገደላለሁ ብሎ አስቦ ነበር። ካርታ አዘጋጅ የነበረው መርኬተር እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሊገኝ የቻለው ለምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት የዚህን ሰው ሕይወትና በእሱ ዘመን የነበሩትን ሁኔታዎች ጠለቅ ብለን እንመርምር።
መርኬተር ቤልጂየም ውስጥ አንትወርፕ አቅራቢያ በምትገኘው ሩፕልሞንዴ የምትባል አነስተኛ የወደብ ከተማ በ1512 ተወለደ። ትምህርቱን የተከታተለው በሉቨን ዩኒቨርሲቲ ነበር። ከዩኒቨርሲቲው ከተመረቀ በኋላ የአሪስቶትልን ትምህርቶች አጥንቷል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ፣ የአሪስቶትል ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር መጋጨታቸው ይረብሸው ጀመር። መርኬተር እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “ሙሴ ስለ ዓለም አፈጣጠር የጻፈው ነገር ከአርስቶትልና ከሌሎቹ ፈላስፎች አመለካከት ጋር በብዙ መንገድ እንደማይጣጣም ስገነዘብ ሁሉም ፈላስፎች የሚያስተምሩት ነገር እውነት ስለ መሆኑ ጥርጣሬ አደረብኝ፤ በዚህም የተነሳ ተፈጥሮን ማጥናት ጀመርኩ።”
መርኬተር ፈላስፋ መሆን ስላልፈለገ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይከታተል የነበረውን ተጨማሪ ትምህርት አቆመ። ይሁን እንጂ ቀሪ ሕይወቱን ያሳለፈው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በመፈለግ ነበር።
ወደ ጂኦግራፊ ፊቱን አዞረ
መርኬተር በ1534 ጀማ ፍሪሲየስ በተባለው የሒሳብ ሊቅ አማካኝነት ሒሳብ፣ ሥነ ፈለክና ጂኦግራፊ ማጥናት ጀመረ። በተጨማሪም ቅርጽ የማውጣትና ሉል የመሥራት ሞያ ከነበረው ከጃስፐር ቫን ደር ሄይደን ቅርጽ የማውጣት ጥበብን ሳይማር አልቀረም። በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የካርታ አዘጋጆች የጎቲክ ፊደላትን ማለትም ደመቅ ተደርገው የሚጻፉ ፊደላትን መጠቀም የጀመሩ ሲሆን ይህም በካርታዎች ላይ የጽሑፍ መግለጫ ለማስፈር የሚያስችል በቂ ቦታ እንዳይኖር አድርጓል። ይሁን እንጂ መርኬተር ጣሊያኖች ይጠቀሙበት የነበረውን አይታሊክ ተብሎ የሚጠራ አዲስ የአጻጻፍ ስልት መከተል ጀመረ፤ በዚህ ዘዴ መሠረት ፊደላትን መቀጣጠልና ጋደል አድርጎ መጻፍ የሚቻል ሲሆን ለሉል ሥራም ጠቃሚ ነው።
በ1536 መርኬተር፣ ከፍሪሲየስና ከቫን ደር ሄይደን ጋር የመሬትን አቀማመጥ የሚያሳይ ሉል ያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ሥራ ላይ ቅርጽ አውጪ በመሆን አገልግሏል። መርኬተር የሚያምር ቅጥልጥል የእጅ ጽሑፍ ያለው መሆኑ ለሥራው መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በዘመናችን የመርኬተርን የሕይወት ታሪክ የጻፈው ኒኮላስ ክሬን እንደገለጸው፣ አንድ ሌላ የካርታ አዘጋጅ “በአሜሪካ የሚገኙ ሃምሳ ቦታዎችን የአንድ ሰው ቁመት የሚያክል ስፋት ባለው የግድግዳ ካርታ ላይ ሲያሰፍር መርኬተር ግን ስልሳ ቦታዎችን ሁለት ስንዝር የሚያህል ዲያሜትር ባለው ሉል ላይ ማስፈር ችሏል!”
የካርታ አዘጋጅ ተገኘ
በ1537 መርኬተር ያለማንም እርዳታ የመጀመሪያው የሆነውን ካርታ የሠራ ሲሆን ይህም ቅድስቲቱን ምድር የሚያሳይ ካርታ ነው፤ ካርታውን ያዘጋጀው “[ብሉይና አዲስ] ኪዳንን በተመለከተ የተሻለ ማስተዋል” ለማግኘት እንዲረዳ ብሎ ነው። በ16ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁት ቅድስቲቱን ምድር የሚያሳዩ ካርታዎች ብዙ ስህተት ነበረባቸው። በአንዳንዶቹ ካርታዎች ላይ የተጠቀሱት ቦታዎች ከ30 የሚያንሱ ሲሆን አብዛኞቹም የተቀመጡት በትክክለኛው ቦታ ላይ አልነበረም። መርኬተር ያዘጋጀው ካርታ ግን ከ400 በላይ የሆኑ ቦታዎችን ያሳያል! በተጨማሪም ካርታው እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው በምድረ በዳ የተጓዙበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። በዚህ ካርታ ላይ የሠፈሩት ትክክለኛ መረጃዎች በመርኬተር ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች አድናቆታቸውን እንዲገልጹ አድርገዋቸዋል።
መርኬተር ባገኘው ስኬት በመበረታታቱ በ1538 የዓለምን ካርታ አዘጋጀ። ከዚህ ጊዜ በፊት የነበሩት የካርታ አዘጋጆች ስለ ሰሜን አሜሪካ የሚያውቁት ነገር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ይህን አካባቢ ‘የማይታወቅ ሩቅ አገር’ ብለው ይጠሩት ነበር። ከዚያ ቀደም “አሜሪካ” የሚለው ስም የነበረ ቢሆንም ይህንን ስም ተጠቅሞ ሰሜንና ደቡብ አሜሪካን በካርታ ላይ ያመለከተው የመጀመሪያው ሰው መርኬተር ነው።
መርኬተር በኖረበት ዘመን አሳሾች የተለያዩ የዓለም ውቅያኖሶችንና በርካታ አዳዲስ አገሮችን ያገኙ ነበር። መርከበኞች የሚያስተላልፉት መረጃ እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑ ካርታ በማዘጋጀቱ ሥራ ላይ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር፤ በመሆኑም ካርታ የሚያዘጋጁ ሰዎች አንዳንድ መረጃዎችን በግምት ማስቀመጥ ግድ ሆኖባቸዋል። እንደዚያም ሆኖ መርኬተር “እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተዘጋጁት ሁሉ የሚሻል ሉል” የመሥራት ግቡን በ1541 ማሳካት ችሏል።
በመናፍቅነት ተከሰሰ
መርኬተር በኖረበት በሉቨን ከተማ ብዙ የሉተራን እምነት ተከታዮች ነበሩ። በ1536 መርኬተር የሉተራን እምነት ደጋፊ ሆነ፤ ከጊዜ በኋላ ሚስቱ የዚህ እምነት ተከታይ እንደሆነች ይታመናል። በየካቲት 1544 መርኬተርና የሉቨን ነዋሪ የሆኑ 42 ሰዎች “ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ደብዳቤዎችን” ጽፋችኋል
በሚል ተከሰው ታሰሩ። ይሁን እንጂ መርኬተር የታሰረው የሉቨን ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት ምሑራን የሆኑት ታፐርና ላቶመስ እሱ ያዘጋጀውን ቅድስቲቱን ምድር የሚያሳየውን ካርታ ስለተጠራጠሩም ሊሆን ይችላል። እነዚህ ምሑራን የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነውን የዊልያም ቲንደልን ጉዳይ ለማየት በተሰየመው ችሎት ላይ ነበሩ፤ ቲንደል በ1536 የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በቤልጅየም ተገድሏል። ታፐርና ላቶመስ፣ ዊሊያም ቲንደል እንዳዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሁሉ መርኬተር የሠራው ቅድስቲቱን ምድር የሚያሳየው ካርታም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ያበረታታል የሚል ስጋት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ መርኬተር የትውልድ ከተማው በሆነችው በሩፔልሞንዴ ውስጥ በሚገኝ ወህኒ ቤት ታሠረ።ለፍርድ ከቀረቡት ሰዎች መካከል አንዷ የነበረችው አንቶይኔት ቫን ሩዝሜልስ፣ መርኬተር ፕሮቴስታንቶች በሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ እንደማያውቅ መስክራለች። ይሁን እንጂ አንቶይኔት ራሷ በእነዚህ የንባብ ፕሮግራሞች ላይ ትገኝ ስለነበር ታፍና እንድትሞት በቁሟ ተቀብራለች። መርኬተር ከሰባት ወር በኋላ ከእስር የተለቀቀ ቢሆንም ንብረቱ በሙሉ ተወርሶበት ነበር። በ1552 መርኬተር ሃይማኖታዊ መቻቻል ባለባት ጀርመን ውስጥ በምትገኘው ዱይስበርግ ከተማ መኖር ጀመረ።
የመጀመሪያው አትላስ
መርኬተር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ ትክክል ስለ መሆኑ ያለውን እምነት መግለጹን አላቆመም። አብዛኛውን ዕድሜውን ያሳለፈው “የሰማይና ምድር [አፈጣጠር]፣ ከጥንት እስከ ዛሬ” ብሎ ለሰየመው ፕሮጀክት የሚሆኑ ሐሳቦችን በመጻፍ ነበር። ይህ ጽሑፍ ስለ ጊዜ ቅደም ተከተልና ስለ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የሚገልጹ መረጃዎችን የያዘ ነው።
በ1569፣ መርኬተር ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ የተከናወኑትን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ታሪካዊ ክስተቶች የያዘ ዝርዝር አሳተመ፤ ይህ ዝርዝር የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ክፍል ሲሆን ክሮኖሎጂያ የሚል ርዕስ ሰጥቶታል። መርኬተር ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀበት ዓላማ የሰው ዘር ታሪክ ምን ያህል ጊዜ እንዳስቆጠረና ቀደም ባሉት ጊዜያት የተከናወኑትን ታላላቅ
ታሪካዊ ክስተቶች አንባቢዎቹ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ነበር። መርኬተር በመጽሐፉ ውስጥ ሉተር ገንዘብ በመክፈል የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት ይቻላል የሚለውን የካቶሊክ ትምህርት በ1517 መቃወሙን አስፍሮ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ክሮኖሎጂያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንዳይነበቡ እገዳ ከጣለችባቸው መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ተፈረጀ።መርኬተር ቀጣዮቹን ዓመታት ያሳለፈው ራሱ ያዘጋጃቸውን አዳዲስ ካርታዎች ለማተም የሚያገለግሉ ፕሌቶችን በማዘጋጀት ነበር። በ1590 መርኬተር በጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመርጋቱ የግራ ጎኑ ሽባ የሆነ ሲሆን የመናገር ችሎታውንም አጣ፤ ይህ ደግሞ ሥራውን መቀጠል እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆንበት አድርጓል። ይሁን እንጂ ዕድሜውን ሙሉ የደከመበትን ሥራ ለማጠናቀቅ ቆርጦ ስለነበር በ1594 በ82 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ሥራውን ቀጥሏል። የመርኬተር ልጅ ሩሞልድ አባቱ ጀምሯቸው የነበሩትን አምስት ካርታዎች ሠርቶ አጠናቋል። መርኬተር የሠራቸው ካርታዎች ስብስብ በ1595 ለሕትመት የበቃ ሲሆን አትላስ የሚል ስያሜም አግኝቷል።
መርኬተር ያዘጋጀው አትላስ የዘፍጥረትን መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚያብራራ ክፍል ያለው ሲሆን ይህ ክፍል ፈላስፎች የአምላክን ቃል ትክክለኛነት አስመልክቶ የሚሰነዝሩትን ተቃውሞ ውድቅ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ይዟል። መርኬተር ይህን ጥናት “የልፋቴ ውጤት” በማለት ጠርቶታል።
“የዘመናችን ታላቁ የመልክዓ ምድር ሊቅ”
በ1606 ዮዶከስ ሆንዲየስ መርኬተር ያዘጋጀውን አትላስ በትልቁ አሳትሞታል፤ ይህ አትላስ በበርካታ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ በብዛት ተሽጧል። በ16ኛው መቶ ዘመን የነበረው አብርሃም ኦርቴሊየስ የተባለ ካርታ አዘጋጅ መርኬተርን “የዘመናችን ታላቁ የመልክዓ ምድር ሊቅ” በማለት አወድሶታል። በቅርቡ ደግሞ ኒኮላስ ክሬን የተባለው ፀሐፊ መርኬተርን “ፕላኔቷን በካርታ ያስቀመጠ ሰው” በማለት ጠርቶታል።
መርኬተር ትቶልን ያለፈውን ነገር አሁንም ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንጠቀምበታለን። ለምሳሌ ያህል፣ አትላስ ስንመለከት ወይም ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም በተባለው መሣሪያ ስንጠቀም ከመርኬተር የልፋት ውጤት ጥቅም እያገኘን ነው። መርኬተር በአምላክ የፍጥረት ሥራ ውስጥ ያለውን ቦታ ለማወቅ ዕድሜውን ሙሉ ሲደክም የኖረ ታላቅ ሰው ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መርኬተር—ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ
መርኬተር ምድር ጽድቅና የሰላም የሰፈነባት እንዲሁም ብልጽግና የሚኖርባት ቦታ እንደምትሆን ያምን ነበር። ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው የካልቪን ትምህርት ስህተት እንደሆነ ለማረጋገጥ በሮም ምዕራፍ 1 እስከ 11 ላይ የተመሠረተ ሳይታተም የቀረ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ነበር። የሚገርመው ነገር መርኬተር ለመዳን እምነት ብቻ ሳይሆን ሥራም እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ከማርቲን ሉተር ሐሳብ ጋር እንደማይስማማ አሳይቷል። መርኬተር በጻፈው አንድ ደብዳቤ ላይ ኃጢአት “የመጣው ከፕላኔቶች [አስትሮሎጂ] ወይም አምላክ በፈጠረው በማንኛውም ፍጥረት ላይ እንከን ስለኖረ ሳይሆን ሰው በነፃ ምርጫው ያመጣው ነገር” እንደሆነ ገልጿል። ከሌሎች ጋር ያደርግ በነበረው የደብዳቤ ልውውጥ ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የምስጢረ ቁርባን ቀኖና እንደማይቀበለውና “ይህ ሥጋዬ ነው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ቃል በቃል መወሰድ ያለባቸው ሳይሆኑ ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው እንደሆኑ ገልጿል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የመርኬተር የካርታ አሠራር ዘዴ
የብርቱካንን ልጣጭ ቀጥ አድርገህ ለመዘርጋት ሞክረህ ታውቃለህ? ልጣጩን ሳትቆራርጠው ባለበት ሁኔታ ይህን ማድረግ እንደማትችል የታወቀ ነው። ይህ ምሳሌ፣ ካርታ የሚያዘጋጁ ሰዎች ክብ የሆነችውን ምድር በጠፍጣፋ ነገር ላይ ለመሳል በሚያደርጉት ጥረት የሚገጥማቸውን ችግር ለመረዳት ያስችላል። መርኬተር ይህን ችግር ለማስወገድ የሚያስችል አንድ ዘዴ የፈጠረ ሲሆን ይህም የመርኬተር የካርታ አሠራር ዘዴ (The Mercator projection) ተብሎ ይጠራል። በዚህ ዘዴ መሠረት በምድር ወገብና በዋልታዎች መካከል ባሉት የኬንትሮስን ዲግሪዎች በሚያመለክቱት መሥመሮች መካከል ያለው ርቀት ተመጣጣኝ ነው። ምንም እንኳን ይህ ዘዴ ርቀትንና መጠንን (በተለይ ደግሞ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ዋልታዎች አካባቢ) ሊያዛባ ቢችልም በካርታ ሥራ ውስጥ የታየ ትልቅ እመርታ ነው። መርኬተር በ1569 ያዘጋጀው ግድግዳ ላይ የሚሰቀል ካርታ ድንቅ ሥራ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይህ ሰው በካርታ ሥራ ረገድ ከፍተኛ ዝና እንዲያተርፍ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲያውም እሱ የፈለሰፈው ዘዴ ከውቅያኖሶች ካርታና ዘመናዊ ከሆነው ግሎባል ፖሲሺኒንግ ሲስተም ከተባለ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ይሠራበታል።
[ሥዕል]
የመርኬተር የካርታ አሠራር ዘዴ የዓለም ካርታ ተስሎበት ተሰንጥቆ ከተዘረጋ ሲሊንደር ጋር ሊመሳሰል ይችላል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መርኬተር በ1537 ያዘጋጀው ቅድስቲቱን ምድር የሚያሳየው ካርታ ከ400 በላይ የሆኑ ቦታዎችን ይዟል
[በገጽ 20 እና 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መርኬተር በ1538 ያዘጋጀው የዓለም ካርታ
በሁለቱም የአሜሪካ አህጉሮች ላይ “አሜሪ ኬ” የሚል ስም መስፈሩን ልብ በል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Antwerpen, Stedelijk Prentenkabinet
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁለቱም ካርታዎች፦ From the American Geographical Society Library, University of Wisconsin-Milwaukee Libraries