በልጆች ላይ የሚታይ ጤናማ ያልሆነ ውፍረት—ምን ማድረግ ይቻላል?
በልጆች ላይ የሚታይ ጤናማ ያልሆነ ውፍረት—ምን ማድረግ ይቻላል?
በበርካታ አገሮች ውስጥ ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ በዓለም ዙሪያ ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው 22 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ልጆች ከልክ ያለፈ ውፍረት ይታይባቸዋል።
በስፔን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ3 ልጆች መካከል አንዱ ከመጠን በላይ ወፍራም ነው አለዚያም ጤናማ ያልሆነ ውፍረት ይታይበታል። በአውስትራሊያ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ (1985-1995) ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል። በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ከ6 እስከ 11 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ ጨምሯል።
በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ልጆችም እንኳ ሳይቀር ጤናማ ያልሆነ ውፍረት እየታየባቸው ነው። በዓለም ዙሪያ ጤናማ ያልሆነ ውፍረትን ለመከላከል የተቋቋመ አንድ ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለባቸው ሕፃናት ይልቅ ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ይበዛሉ። በ2007 ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች በብዛት ከሚገኙባቸው አገሮች መካከል ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ሜክሲኮ ሁለተኛውን ደረጃ ይዛ ነበር። በሜክሲኮ ሲቲ ብቻ 70 በመቶ የሚሆኑ ልጆችና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከመጠን በላይ ወፍራሞች ናቸው አሊያም ጤናማ ያልሆነ ውፍረት ይታይባቸዋል። የሕፃናት የቀዶ ሕክምና ባለሞያ የሆኑት ፍራንሲስኮ ጎንሳሌስ “ጤናማ ያልሆነ ውፍረት በሚያስከትላቸው በሽታዎች ሳቢያ ከወላጆቹ ቀድሞ ለሞት የሚዳረገው የመጀመሪያው ትውልድ” በአሁኑ ጊዜ ያለው ሳይሆን እንደማይቀር አስጠንቅቀዋል።
ጤናማ ባልሆነ ውፍረት ሳቢያ የሚመጡት በሽታዎች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ በሽታዎች መካከል የስኳር ሕመም፣ ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊትና የልብ ችግር ይገኙበታል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በእነዚህ የጤና ችግሮች በአብዛኛው የሚጠቁት አዋቂዎች ነበሩ። የዩናይትድ ስቴትስ የሕክምና ተቋም እንደገለጸው ከሆነ በ2000 በዩናይትድ ስቴትስ ከተወለዱት ወንዶች ልጆች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት እንዲሁም ከሴቶቹ ልጆች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በሕይወታቸው ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ ጤናማ ካልሆነ ውፍረት ጋር ተያይዞ በሚመጣው፣ ዓይነት ሁለት በተባለው የስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በልጆች ላይ እየታየ ያለው አዝማሚያ በጣም አስደንጋጭ ነው። ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ልጆች ቁጥርም እየተበራከተ ይሄዳል። በአትላንታ፣ ጆርጂያ የሚገኘው ሞርሃውስ የሕክምና ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሪቤካ ዲን-ድዚትኸም እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፦ “ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ወጣቶች ቁጥር በዚህ ሁኔታ እየጨመረ ከሄደ ከልብ በሽታ ጋር ለተያያዙ ችግሮች የሚጋለጡ ወጣቶችና አዋቂዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሻቅብ ይችላል።”
አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች
ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የሚታይባቸው ልጆች ቁጥር በዓለም ዙሪያ እየተበራከተ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? ልጆች በዘር የሚወርሱት ነገር ጤናማ ላልሆነ ውፍረት እንዲጋለጡ ሊያደርጋቸው ቢችልም ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ይህ ችግር ያለባቸው ልጆች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡ መንስኤው ከዘር ውርስ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልሆነ ይጠቁማል። እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የክሊኒካል ባዮኬሚስትሪና ሜዲስን ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ኦራሂሊ እንዲህ ብለዋል፦ “ጤናማ ያልሆነ ውፍረት እየተበራከተ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው የዘር ውርስ ብቻ አይደለም። በ30 ዓመት ውስጥ በጂኖቻችን ላይ ይህን ያህል ትልቅ ለውጥ ሊከሰት አይችልም።”
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የማዮ ክሊኒክ ለዚህ ችግር መንስኤ የሆኑትን ነገሮች አስመልክቶ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “ከጂንና ከሆርሞን ጋር የተያያዙ ነገሮች በተወሰነ ደረጃ ልጆች ጤናማ ላልሆነ ውፍረት እንዲጋለጡ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ችግር መንስኤ የሚሆነው ልጆች ከልክ በላይ መብላታቸውና እምብዛም እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው ነው።” በአሁኑ ጊዜ ያለው የአመጋገብ ልማድ እየተለወጠ እንደመጣ የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሥራ ዓለም የተሠማሩ ወላጆች ምግብ ለመሥራት በቂ ጊዜና ጉልበት ስለማይኖራቸው በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የመመገብ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዘወተረ መጥቷል። በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን የሚያቀርቡ ምግብ ቤቶች በመላው ዓለም በእጅጉ ተበራክተዋል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው በዩናይትድ ስቴትስ ከ4 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ልጆች መካከል አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን በየቀኑ ይመገባሉ። እንዲህ ያሉ ምግቦች በአብዛኛው ከፍተኛ የስኳርና የቅባት ይዘት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ለመብላት በሚያጓጓ ሁኔታ ትልቅ መጠን እንዲኖራቸው ተደርገው ይዘጋጃሉ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከወተትና ከውኃ ይልቅ ለስላሳ መጠጦች ይበልጥ ተወዳጅነት እያገኙ መጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የሜክሲኮ ነዋሪዎች በየዓመቱ ለለስላሳ መጠጦች በተለይ ደግሞ ለኮላ መጠጦች የሚያወጡት ወጪ መሠረታዊ ለሆኑ አሥር የምግብ ዓይነቶች ከሚያወጡት አጠቃላይ ወጪ ይበልጣል። ኦቨርካሚንግ ቻይልድሁድ ኦቢሲቲ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ በቀን ውስጥ 600 ሚሊ ሊትር (ሁለት ጠርሙስ) ለስላሳ መጠጥ የሚጠጣ ሰው በዓመት ውስጥ ከ11 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ሊጨምር ይችላል!
አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግን በተመለከተ ደግሞ በስኮትላንድ የሚገኘው የግላስኮ ዩኒቨርሲቲ ያካሄደው አንድ ጥናት እንደጠቆመው አብዛኞቹ የሦስት ዓመት ልጆች በቀን ውስጥ “ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ አካላዊ እንቅስቃሴ” የሚያደርጉት ለ20 ደቂቃ ብቻ ነው። በኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጄምስ ሂል ይህን ጥናት አስመልክተው ሲናገሩ “በብሪታንያ እምብዛም እንቅስቃሴ የማያደርጉ ልጆች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይህ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች ውስጥ እየታየ ነው” ብለዋል።
መፍትሔው ምንድን ነው?
ጤናማ አመጋገብን በተመለከተ ምክር የሚሰጡ ባለሞያዎች በልጆች የአመጋገብ ልማድ ላይ ገደብ ማበጀት በእድገታቸውና በጤንነታቸው ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ። ከዚህ ይልቅ የማዮ ክሊኒክ እንደገለጸው “ልጆቻችሁ ከመጠን በላይ እንዳይወፍሩ ልትከላከሉ የምትችሉበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመላው ቤተሰባችሁን የአመጋገብም ሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልማድ ማሻሻል ነው።”—በዚህ ገጽ ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ቤተሰባችሁ በቂ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግና ጤናማ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖረው አድርጉ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁ ካደጉም በኋላ ይህንኑ ልማድ ይከተላሉ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?
1 በፍጥነት ከሚዘጋጁ ምግቦች ይልቅ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በብዛት ተመገቡ።
2 ለስላሳ መጠጦችን፣ ጣፋጭ ነገር ያለባቸው መጠጦችን እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የቅባትና የስኳር መጠን ያለባቸውን ቀላል ምግቦች ቀንሱ። ከዚህ ይልቅ ውኃ ወይም አነስተኛ የቅባት ይዘት ያለው ወተት ብትጠጡ እንዲሁም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ቀላል ምግቦችን ብትመገቡ ይመረጣል።
3 ምግብ በምታዘጋጁበት ጊዜ ከመጥበስ ይልቅ እንደ መጋገር፣ መቀቀልና በእሳት መለብለብ ያሉ ብዙ ቅባት ማድረግ የማይጠይቁ የማብሰያ ዘዴዎችን ተጠቀሙ።
4 የምታቀርቧቸውን ምግቦች መጠን አታብዙ።
5 ልጆቻችሁ አንድ ነገር እንዲሠሩ ለማድረግ ምግብን እንደ ሽልማት ወይም እንደ ማባበያ አድርጋችሁ አትጠቀሙ።
6 ልጆቻችሁ ቁርስ ሳይበሉ እንዲቆዩ አታድርጉ። ቁርስ አለመብላታቸው በኋላ ላይ ከመጠን በላይ እንዲበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።
7 ቴሌቪዥን እየተመለከታችሁ ወይም ኮምፒውተር ላይ እየሠራችሁ ምግብ ከመብላት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጣችሁ ተመገቡ፤ አለዚያ ሳይታወቃችሁ ከመጠን በላይ ልትበሉ ትችላላችሁ።
8 ልጆቻችሁ ብስክሌት መንዳትን፣ ኳስ መጫወትንና ገመድ መዝለልን የመሳሰሉ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠይቁ ስፖርቶችን እንዲያዘወትሩ አበረታቷቸው።
9 ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ኮምፒውተር በመጠቀምና የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ረዘም ያለ ሰዓት እንዳያጠፉ ገደብ አብጁላቸው።
10 በቤተሰብ ደረጃ ሆናችሁ የዱር አራዊት የሚጠበቁባቸውን ፓርኮች ለመጎብኘት፣ ዋና ለመዋኘት፣ በመናፈሻ ቦታዎች ለመጫወትና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ለማከናወን እቅድ አውጡ።
11 ልጆቻችሁ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠይቁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሠሩ አድርጉ።
12 ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ልማድ በመከተልና በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኑ።
[ምንጭ]
ምንጭ፦ ብሔራዊ የጤና ተቋማትና የማዮ ክሊኒክ