በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ጥሩ ወላጅ ለመሆን የሚረዱ ሰባት ነጥቦች (ነሐሴ 2007) ይህ መጽሔት ለጸሎቴ መልስ ሰጥቶኛል። ይሖዋን የምትወድ የአራት ዓመት ልጅ ያለችኝ ሲሆን የወላጅነት ኃላፊነቴን ስወጣ ስህተት እሠራለሁ ብዬ እሰጋለሁ። በመሆኑም እሷን ማሠልጠን እንድችል እንዲረዳኝ ይሖዋን በየዕለቱ እለምነዋለሁ። ለእኛ ለወላጆች ስለምታስቡልን ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

ዋይ. ኤም. አ.፣ ሜክሲኮ

በዚህ መጽሔት ላይ የወጣው ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ለቤተሰባችን ጠቃሚ መመሪያ ሆኖልናል! በጣም ሲያሳስቡኝ ለነበሩ በርካታ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥቶኛል። ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደሚያስብ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ሆኖልኛል። ይሖዋ ጸሎቴን የሰማ ከመሆኑም ሌላ እንባዬን አይቷል፤ እንዲሁም ይህ ርዕሰ ትምህርት በጣም እንደሚያስፈልገኝ አውቋል።

ጄ. ኤም.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ጠቃሚ መመሪያዎችንና ትምህርቶችን በጥቂት ገጾች ላይ አስፍራችሁልናል። ከእኛ የሚጠበቀው እነዚህን መመሪያዎች መታዘዝ ብቻ ነው!

ኢ. ኤል.፣ ፊንላንድ

ብሩህ አመለካከት መያዝ ጤንነትህ እንዲሻሻል ይረዳህ ይሆን? (መስከረም 2007) ብዙ ጊዜ ችግሮች ሲነሱ ራሴን ተወቃሽ አደርግ ስለነበር ይህ ርዕስ በጣም ጠቅሞኛል። ጥሩ እናት እንዳልሆንኩ ስለሚሰማኝ በጭንቀት እሠቃይ ነበር። ብሩህ አመለካከት መያዝ ለእኔ ቀላል ባይሆንም እንኳ ይህን ርዕስ ማንበቤ ጭንቀቴን ቀንሶልኛል። ለእኛ በማሰብ እንዲህ የመሰሉ ርዕሶችን ስለምታወጡልን በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ኣ. ኤስ.፣ ኢኳዶር

ለዘመናት ሰዎችን ሲያሠቃይ የኖረው የጥርስ ሕመም (መስከረም 2007) የጥርስ ሐኪም ስሆን ስለ ጥርስ ሕክምናም አስተምራለሁ። ለመረዳት ቀላልና ማራኪ የሆነው ይህ ርዕስ በጣም አስደንቆኛል። የጥርስ ሕክምናን አስመልክቶ በአጭሩ የቀረበው ታሪክ እጅግ ግሩም ነው። ከዚህ ርዕስ ያገኘሁትን መረጃ ለጓደኞቼና ለሥራ ባልደረቦቼ አካፍያቸዋለሁ።

ኬ. አር.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ተጠያቂው አምላክ ነው? (መስከረም 2007) እኔና ጓደኞቼ ድንገተኛ አደጋን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን ለመወያየት ተሰብስበን ነበር። በዚህ ጊዜ “ለመሸሽ ተዘጋጅተሃል?” በሚለው ሣጥን ውስጥ በቀረቡት ጥሩ ሐሳቦች ላይ ሻይ ቡና እያልን ተወያየን። ከዚያም አንዳንዶቻችን ለድንገተኛ አደጋ ብለን ያዘጋጀናቸውን ዕቃዎች ተመለከትን። ለድንገተኛ አደጋ ጊዜ መዘጋጀትን አስመልክቶ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አስፈላጊ እንደሆነም ተወያይተናል። የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ዋናው ሥራችን ለአደጋ ጊዜ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብ እንዳልሆነ ተገንዝበናል። ከዚህ ይልቅ ዋናው ሥራችን የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክና ምድር ያላትን አስደናቂ ተስፋ ይኸውም ምድር ማንኛውም ሰው ሠራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ አደጋ ፈጽሞ እንደማያሰጋት ለሰዎች መናገር ነው።

አር. ጂ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ልጆቻችሁን ከጥቃት ጠብቋቸው! (ጥቅምት 2007) በልጅነቴ በጾታ የተነወርኩ ሲሆን ሁኔታውን እስከ ዛሬ ድረስ ለወላጆቼ አልነገርኳቸውም። በመሆኑም እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች በጣም አጽናንተውኛል። ወላጆች ይህንን መጽሔት እንደሚያነቡትና ልጆቻቸውን ከጥቃት እንደሚጠብቁ ሙሉ እምነት አለኝ። ይህን አስፈላጊ ትምህርት ስለሰጠን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። እነዚህ ርዕሰ ትምህርቶች የጾታ ጥቃት የተፈጸሙባቸውን ሰዎች በእጅጉ እንደሚያጽናኗቸው እርግጠኛ ነኝ።

አር. ኢ.፣ ጃፓን