ልትተማመንበት የሚገባ የወደፊት ተስፋ!
ልትተማመንበት የሚገባ የወደፊት ተስፋ!
መንታ መንገድ ላይ ደረስክ እንበል። የአንደኛው መንገድ ምልክት “በሰዎችና እነሱ በሚሰጡት ተስፋ ተማመን” ይላል። የሌላኛው ምልክት ደግሞ “በአምላክና በመንግሥቱ ተማመን” ይላል። በየትኛው መንገድ ላይ ለመሄድ ትመርጣለህ?
ማስተዋል የታከለበት አካሄድ በአምላክ መተማመን ነው። አምላክ “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል” ብሏል። (ምሳሌ 1:33) ፈጣሪያችንን የምናዳምጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን አውቀን ተግባራዊ በማድረግ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንዲህ ያለው እምነት ጥሩ መሠረት ያለው ነው? እንዴታ! ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው ርዕሰ ትምህርት ላይ ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው በመግዛት ረገድ ስኬታማ መሆን የማይችሉበትን ምክንያት በትክክል የሚያብራራው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንደሆነ ተመልክተናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚናገረው ሐሳብ እውነት እንደሆነ አትስማማም?
መጽሐፍ ቅዱስን ከትንቢት አንጻር ከተመለከትነውም የሚናገረው ሐሳብ ትክክል እንደሆነ እንረዳለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ‘የመጨረሻ ዘመን’ ልዩ የሚያደርጉ አስከፊ ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። እነዚህን አስከፊ ሁኔታዎች እኛም በገዛ ዓይናችን ማየት እንችላለን። (ማቴዎስ 24:3-7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የፕላኔቷ ምድራችንን ደኅንነት እንኳ ሳይቀር ስጋት ላይ እንደሚጥሉ ተንብዮ ነበር። ራእይ 11:18 አምላክ ‘ምድርን ያጠፏትን የሚያጠፋበት ዘመን እንደሚመጣ’ ይናገራል።
እነዚህ ቃላት ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት በተጻፉበት ወቅት የአየር፣ የባሕርና የምድር መበከል፣ የምድር ሙቀት መጨመር፣ የተለያዩ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች በሰዎች አማካኝነት ከምድር ገጽ መጥፋትና የመሳሰሉት ነገሮች የሚከሰቱበት ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነበር። አሁን ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች ሲከሰቱ እያየን ነው! አዎን፣ አምላክ ፈጽሞ አይዋሽም። በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ አንድም እንኳ ሳይቀር ፍጻሜውን እያገኘ ነው። * (ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:18) እንዲያውም የአምላክ ስም ትርጉም ቃሉን የሚፈጽም ከመሆኑ ጋር የተሳሰረ ነው።
እምነት ልትጥልበት የምትችለው ስም
በአንድ ቼክ ላይ የሰፈረ ፊርማ የሰነዱን ሕጋዊነት እንደሚያረጋግጥ ሁሉ ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስምም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተመዘገቡት ተስፋዎች ሁሉ ዋስትና የሚሰጥ ነው። * የአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ ተለይቶት የማያውቅ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “በቅዱስ ስሙ ታምነናልና” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 33:21፤ 34:4, 6
ምሳሌ 18:10 የአምላክን ስም ከአባታዊ እንክብካቤው ጋር በማያያዝ “[የይሖዋ] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” በማለት ይናገራል። በተመሳሳይም ሮሜ 10:13 “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ይላል። ይህ ሲባል ግን የአምላክ የግል ስም ክፉውን የሚያርቅ ምትሐታዊ ኃይል ያለው ነገር ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የማዳን እርምጃውን የሚወስደው አምላክ ራሱ ነው፤ ይህ ጥቅስ እንደሚለው ሰዎች እሱን የሚጠሩት እንከን የለሽ አምላክ መሆኑን አውቀው ሙሉ በሙሉ ስለሚተማመኑበት ነው። መዝሙር 91:14 “[እኔን ይሖዋን] ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ” ይላል።
እንግዲያው ‘እምነት የጣልኩት በማን ላይ ነው? በአምላክ ወይስ በሰው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክንና መንግሥቱን የመረጡት በስሜት ወይም በጭፍን እምነት ተነሳስተው ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት ስላላቸው ነው። (ዕብራውያን 11:1፤ 1 ዮሐንስ 4:1) በመሆኑም ከፊታቸው በሚጠብቃቸው ‘ተስፋ ይደሰታሉ’ እንጂ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ፍርሃት አይሰማቸውም። አንተም ይህንን ብሩሕ ተስፋ እንድትጋራቸው ይጋብዙሃል።—ሮሜ 12:12
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 የኅዳር 2007 ንቁ! መጽሔትን ተመልከት፤ ይህ ልዩ እትም ሙሉ በሙሉ ያተኮረው “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?” በሚለው ጥያቄ ላይ ነው።
^ አን.7 በዚህ ገጽ ላይ የሚገኘውን “መጠሪያም ዋስትናም ነው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአንድ ቼክ ላይ የሰፈረ ፊርማ የሰነዱን ሕጋዊነት እንደሚያረጋግጥ ሁሉ የአምላክ ስምም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተመዘገቡት ተስፋዎች ሁሉ ዋስትና የሚሰጥ ነው
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጠሪያም ዋስትናም ነው
ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም መጠሪያ ብቻ አይደለም። * እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። በአጭር አነጋገር፣ አምላክ ዓላማውን ከግቡ ለማድረስና ቃሉን ለመፈጸም ሲል አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን ማንኛውንም ነገር ለመሆን የሚያስችለው ፍቅር፣ ኃይልና ጥበብ አለው። ይሖዋ የፈለገውን ሁሉ፣ ለምሳሌ ያህል ጻድቃንን የሚታደግና ክፉውን የሚያጠፋ አምላክ፣ ጸሎት ሰሚ፣ ወይም አፍቃሪ አባት መሆን ይችላል።
ይሖዋ “እኔ አምላክ ነኝ፤ . . . የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ . . . ተናግሬአለሁ፤ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:9, 10) አምላክ ምንጊዜም ዓላማውን ከመፈጸም ወደኋላ ስለማይልና ስሙ እንዲህ ከማድረጉ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። “ይሖዋ ይዋሽ ዘንድ ሰው አይደለም።”—ዘኍልቍ 23:19 NW
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.17 ይሖዋ የሚለው ስም ሁሉን ቻይ፣ ፈጣሪ፣ አምላክና ጌታ ከሚሉት የማዕረግ ስሞች የተለየ ነው። ይህ ስም መጀመሪያ በተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰባት ሺህ ጊዜ ያህል ይገኛል። ይህን ስም ለራሱ ያወጣው አምላክ ራሱ ነው። ዘፀአት 3:15 “ይሖዋ . . . ለዘላለሙ ስሜ ነው” ይላል።—አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን