የጀልባ ሽርሽር በኬረለ ሐይቆች ላይ
የጀልባ ሽርሽር በኬረለ ሐይቆች ላይ
ሕንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በሚያማምሩ ዕቃዎች በተሞላ የጀልባ ቤት ውስጥ ሆነህ 44 ወንዞች ወደ ውቅያኖስ የሚገቡበትን ቦታ እያየህ ስትንሸራሸር ይታይህ። ይህን ማድረግ የሚቻለው በሕንድ ደቡባዊ ምዕራብ በምትገኘው የኬረለ ግዛት ባሉት 900 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላቸው የተያያዙ ሐይቆችና ወንዞች ላይ ነው። እንዲህ ያለ ልዩ አጋጣሚ ብታገኝ በጣም እንደምትደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። ጀልባህ በዝግታ እየቀዘፈ ሲሄድ በዘንባባ ዛፎች የተከበቡ ትልልቅ ኩሬዎችን፣ ለምለም የሩዝ ማሳዎችን፣ የተፈጥሮ ሐይቆችንና ጀልባ መሄጃ ቦዮችን እያየህ ማድነቅህ አይቀርም። ናሽናል ጂኦግራፊክ ትራቭለር፣ ኬረለን “‘አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊያያቸው ከሚገቡ’ 50 ቦታዎች መካከል አንዱ” በማለት የመዘገበው በእነዚህ ሐይቆች ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ሌላው ነገር ደግሞ በሐይቆቹ ዳርቻ የሚኖሩት ሕዝቦች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች በአካባቢያቸው ቱሪስቶችም ሆኑ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ያልነበሩበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ የእነሱ አኗኗር እምብዛም አልተለወጠም። ምንም እንኳ አንዳንዶቹ አዲስ በተሠሩት ሆቴሎች ወይም ከቱሪዝም ጋር ዝምድና ባላቸው ሌሎች ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ ቢሆኑም ባጠቃላይ ሲታይ ባሕላቸውና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንደ ቀድሞው ነው። የሩዝ ማሳዎቻቸውንና የኮኮናት እርሻቸውን ይንከባከባሉ፤ እንዲሁም ለዕለት ጉርሳቸው ተጨማሪ ነገር ለማግኘትና ኑሯቸውን ለመደጎም ዓሣ አጥምደው ይሸጣሉ።
በሐይቆቹ ላይ ዓሣ ማጥመድ
በዚህ አካባቢ ዓሣ ማጥመድ የተለመደ የሕይወት ክፍል ነው። ሆኖም በሌላ በማንኛውም ቦታ የማታየው አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ሴቶች ካሪሚን የሚባሉ ዓሦችን በእጃቸው ሲይዙ ትመለከታለህ። በኬረለ ሐይቆች ብቻ የሚገኘው ካሪሚን የሚባለው ዓሣ ለሕንዶችም ሆነ ለውጭ አገር ዜጎች ተወዳጅ የቅንጦት ምግብ ነው። ሴቶቹ ይህን ዓሣ ፍለጋ የኒኬል ዕቃዎቻቸውን ከኋላቸው አስከትለው ውኃ ውስጥ ይሄዳሉ። ዓሣው፣ ሴቶቹን ሲያይ ወደ ውኃው ውስጥ ይጠልቅና ጭንቅላቱን በደለሉ ውስጥ ይደብቃል። ሴቶቹም ቀስ ብለው በእግራቸው እየዳሰሱ ዓሣው የተደበቀበትን ቦታ ያገኛሉ። ከዚያም በፍጥነት እጃቸውን ውኃው ውስጥ ሰደው ያልጠረጠረውን ዓሣ ከያዙ በኋላ ለማምለጥ ሲንፈራገጥ ኒኬላቸው ውስጥ ይጨምሩታል። የሚበቃቸውን ያህል ካጠመዱ በኋላ ዓሣ የሚገዙ ሰዎች በጉጉት ወደሚጠባበቁበት ወደ ባሕሩ ዳርቻ ይሄዳሉ። ትላልቆቹና ውድ የሆኑት ዓሣዎች ብዙ ገንዘብ መክፈል ለሚችሉ ሰዎች ምግብ እንዲሆኑ ለትልልቅ ሆቴሎች ይሸጣሉ፤ ትንንሾቹ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ይሸጣሉ።
የቻይናውያን መረቦች
በሐይቆቹ ዳርቻዎች ላይ የቻይናውያን ዓይነት ዓሣ ማጥመጃ መረቦችን ማየት የተለመደ ነው። እነዚህም ቢሆኑ ትልቅ የቱሪስት መስህብ ናቸው።
እነዚህን መረቦች ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ1400 በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮቺን (የአሁኗ ኮቺ) ያመጡት ከኩብላይ ካን ቤተ መንግሥት የመጡ ቻይናውያን ነጋዴዎች እንደሆኑ ይታመናል። መረቦቹን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙባቸው ቻይናውያን ሲሆኑ በኋላም የፖርቹጋል ሠፋሪዎች ይገለገሉባቸው ጀመር። ከ600 ዓመታት በፊት እንደነበረው ሁሉ የቻይናውያን መረብ ዛሬም ለብዙ ሕንዳውያን ዓሣ አጥማጆች መተዳደሪያ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሕዝቦች ደግሞ ምግባቸውን ያገኙበታል። የሚገርመው ነገር አንዱ መረብ የሚይዘው የዓሣ መጠን አንድ መንደር
ሊመግብ የሚችል መሆኑ ነው። ብዙ ቱሪስቶች፣ እንዲደርቁ ተብለው የተሰጡ መረቦችን ፀሐይ በምትጠልቅበት ጊዜ ፎቶግራፍ ማንሳት በጣም ያስደስታቸዋል።ቱሪስቶቹ ወደ እነዚህ ሐይቆች የሚመጡት የቻይናውያንን መረቦች ፎቶግራፍ ለማንሳት ብቻ አይደለም። በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ባሕላዊውን የእባብ ጀልባ ውድድር የመሰሉ የውኃ ላይ እንቅስቃሴዎች ለማየት ይጎርፋሉ።
የጀልባ ውድድር በሐይቆቹ ላይ
እባብ ጀልባዎች የሚባሉት ቀጠን ያሉ ረጃጅም ታንኳዎች ናቸው። የጀልባዎቹ የኋለኛ ክፍል የኮብራ ራስ የሚመስል ቅርጽ ስላለው እባብ ጀልባ የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። ጥንት በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩ እርስ በርስ የሚዋጉ ነገሥታት ከመከር ወቅት በኋላ በሚያደርጓቸው ጦርነቶች በእነዚህ ጀልባዎች ይጠቀሙ ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ ጦርነቶች ሲቀሩ የጀልባዎቹ አስፈላጊነትም እየቀነሰ መጣ። እነዚህ ግርማ ሞገስ ያላቸው የጥበብ ውጤቶች በውኃዎቹ ላይ ሲመላለሱ የሚታዩት በቤተ መቅደስ በዓላት ወቅት ብቻ ነበር። ከፍተኛ ድምቀት በሚኖራቸው በእነዚህ በዓላት ወቅት ጀልባዎቹን ካስጌጧቸው በኋላ የአካባቢውን ባሕል ለማስተዋወቅ ይጠቀሙባቸዋል። እንዲሁም ለበዓሉ በቦታው ለተገኙት ሹማምንት ክብር ሲባል የጀልባ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። የዛሬ አንድ ሺህ ዓመት ገደማ የተጀመረው ይህ ባሕል አሁንም ድረስ ይዘወተራል።
በዚህ ውድድር ላይ እያንዳንዳቸው ከ100 እስከ 150 ሰዎች የያዙ 20 የሚሆኑ ጀልባዎች ይካፈላሉ። አጫጭር መቅዘፊያዎችን የያዙ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች በሁለት ረድፍ ተደርድረው ይቀመጣሉ። ረጃጅም መቅዘፊያዎችን የያዙ አራት የጀልባው መሪዎች ከኋላ ቆመው ይቀዝፋሉ። ሁለት ሰዎች ደግሞ በጀልባዋ መሃል ላይ ቆመው ውድድሩን ለመጨረስ ምን ያህል እንደቀራቸው ለመጠቆም ከበሮ በእንጨት ይመታሉ። ከዚህ በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ቀዛፊዎቹ ፍጥነታቸውን እንዳይቀንሱ ለማበረታታት ያጨበጭባሉ፣ ያፏጫሉ፣ ይጮኻሉ፣ እንዲሁም የባሕረተኞችን ዘፈን ይዘፍናሉ። ወጣቶቹ ለተወሰነ ጊዜ እኩል ሲቀዝፉ ከቆዩ በኋላ
ውድድሩን ለመጨረስ ሲቃረቡ ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስበው ይቀዝፋሉ።በ1952፣ የመጀመሪያው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ጃዋሀርላል ኔህሩ፣ በሐይቆቹ አካባቢ በምትገኘው አሌፔይ የተባለች ቁልፍ ከተማ ተገኝተው በተመለከቱት የጀልባ ውድድር በጣም ተደስተው ነበር። እንዲያውም በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ ለጥበቃ የተደረገውን ዝግጅት ችላ ብለው በአሸናፊው ጀልባ ውስጥ ዘለው በመግባት ከቀዛፊዎቹ ጋር ሲያጨበጭቡና ሲዘፍኑ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ዴልሂ ከተመለሱ በኋላ ፊርማቸውና “የማኅበረሰብ ሕይወት ልዩ ገጽታ ለሆነው የጀልባ ውድድር አሸናፊዎች” የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት የእባብ ጀልባ ምስል በብር አስቀርጸው ላኩላቸው። ከዚያ በኋላ ይህ የብር ጀልባ በዓመታዊው የኔህሩ ሽልማት ውድድር ላይ ለአሸናፊዎች የሚሰጥ ዋንጫ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። እንዲህ ዓይነቱን ውድድር ለማየት በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ይጎርፋል። በሌሎች ወቅቶች ብዙ እንቅስቃሴ የማይታይባቸው ሐይቆች ውድድሮቹ በሚካሄዱበት ጊዜ ይደምቃሉ።
ተንሳፋፊ ሆቴሎች
በሐይቆቹ ላይ የቱሪስት መስህብ የሆኑት እባብ ጀልባዎቹ ብቻ አይደሉም። ወደ ቤትነት የተቀየሩት የድሮ የሩዝ ጀልባዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳጅነታቸው እየጨመረ መጥቷል።
በአሁኑ ጊዜ ቱሪስቶች የሚጠቀሙባቸው አብዛኞቹ የጀልባ ቤቶች አዲስ የተሠሩ ቢሆኑም ከመቶ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩና ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው የተሠሩ የሩዝ ጀልባዎችም አሉ። እነዚህ ጀልባዎች መጀመሪያ ላይ ኬቱቨለም ማለትም “ባለ ቋጠሮ ጀልባ” በሚል ስም ይታወቁ ነበር። ጠቅላላው ጀልባ የሚሠራው ከጣውላ ሲሆን አንድ ላይ የተያያዘው ያላንዳች ምስማር በገመድ ነው። እነዚህ ጀልባዎች ሩዝና ሌሎች ሸቀጦችን ከአንድ መንደር ወደ ሌላው ለመውሰድና ቅመማ ቅመሞችን ወደ ሩቅ ቦታዎች ለማጓጓዝ ያገለግሉ ነበር። ዘመናዊ ማጓጓዣዎች ከመጡ በኋላ ግን እነዚህ ጀልባዎች ተፈላጊነታቸው እየቀነሰ መጣ። ከዚያም አንድ ብልህ ነጋዴ እነዚህ ጀልባዎች ለቱሪስት ኢንዱስትሪው የሚያገለግሉ የጀልባ ቤቶች ተደርገው ቢቀየሩ ጥሩ እንደሚሆን ተሰማው። እነዚህ የጀልባ ቤቶች ሰገነት፣ መታጠቢያ ቤት ያለው ምቹ መኝታ ቤትና ውብ በሆኑ እቃዎች የተሞላ ሳሎን ስላላቸው ተንሳፋፊ ሆቴሎች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። ጀልባህን ወደፈለግክበት ቦታ የሚነዱልህና ያማረህን ምግብ የሚያዘጋጁልህ አስተናጋጆች ይመደቡልሃል።
ሲመሽ ጀልባዎቹ በሐይቁ ዳርቻ ላይ አሊያም የበለጠ ጸጥታ ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ደግሞ በሐይቁ መሃል መልሕቃቸውን ይጥላሉ። በሐይቁ መሃል ለማደር የመረጠ ሰው፣ አልፎ አልፎ እንቅልፍ ያጣ ዓሣ ሲምቦራጨቅ ካልረበሸው በቀር ጸጥ ረጭ ባለው ሐይቅ ላይ አስደሳች ምሽት ማሳለፍ ይችላል።
ይሁን እንጂ በሐይቁ ዙሪያ ከመዝናኛ በቀር ምንም ነገር
የለም ማለት አይደለም። በአካባቢው የሚገኙ ንቁ የሆኑ ‘ሰው አጥማጆች’ በቅንዓት ይንቀሳቀሳሉ።በሐይቆቹ ዙሪያ የሚካሄድ ‘ሰዎችን የማጥመድ’ ሥራ
‘ሰውን ማጥመድ’ የሚለውን አገላለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ኢየሱስ ነው። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ለሆኑት ዓሣ አጥማጆች “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲል ሰዎች የእሱ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ስለሚካሄደው ሥራ መናገሩ ነበር። (ማቴዎስ 4:18, 19፤ 28:19, 20) የይሖዋ ምሥክሮች፣ በኬረለ ሐይቆች ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች ጨምሮ በመላው ዓለም ይህን ተልእኮ እየፈጸሙ ነው።
በሐይቆቹ ዙሪያ ያሉትን 13 ጉባኤዎች ጨምሮ በመላው ኬረለ 132 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች አሉ። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወንድሞች የሚተዳደሩት ዓሣ በማጥመድ ነው። አንድ ወንድም ዓሣ በማጥመድ ላይ ሳለ ለሌላ ዓሣ አጥማጅ ስለ አምላክ መንግሥት ነገረው። ሰውየው በእሱ ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደበትም። ባለቤቱና አራት ልጆቻቸውም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት አደረባቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። በጥናታቸው ፈጣን ዕድገት ያደረጉ ሲሆን ከስድስቱ የቤተሰብ አባላት መካከል አራቱ ተጠምቀዋል። የተቀሩት ሁለት ልጆች ደግሞ ወደ መጠመቅ ደረጃ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ናቸው።
የአንድ ጉባኤ አባላት በአንድ ትንሽ ደሴት ላይ ለመስበክ በጀልባ ሄደው ነበር። ወደ ደሴቱ የሚመላለስ ጀልባ እንደ ልብ ስለማይገኝ የአካባቢው ሰዎች ደሴቱን ካዳማኩዲ ማለትም “ከገቡ አይወጡ” እያሉ ይጠሩታል። እዚህ ደሴት ላይ ወንድሞች ጆኒንና ባለቤቱን አግኝተው አነጋገሯቸው። እነዚህ ባልና ሚስት ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ካቶሊኮች የነበሩ ቢሆኑም ሰዎች ለማሰላሰል ወደሚሰበሰቡበት አንድ ማዕከል ይሄዱ ነበር፤ እንዲሁም ማዕከሉን ለመርዳት የቻሉትን ያህል ገንዘብ ይለግሱ ነበር። ጆኒ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መማር የጀመረ ከመሆኑም በላይ ስለ አዲሱ እምነቱ ለሌሎች መናገር ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማሩ ትምባሆ ከማጨስና አልኮል ከመጠጣት ልማድ እንዲላቀቅ ረድቶታል!
የጆኒ ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ ስላልነበረ በቤተሰቡ ላይ የገንዘብ ችግር ያስከተለበት ቢሆንም እንኳ ሥራውን ተወ። ብዙም ሳይቆይ ጆኒ ሸርጣን እየያዘ በመሸጥ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ማሟላት ቻለ። ጆኒ በመስከረም 2006 የተጠመቀ ሲሆን ባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቁ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳላቸው ማወቃቸው ስለ ሕይወት ያላቸውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ለውጦታል።—መዝሙር 97:1፤ 1 ዮሐንስ 2:17
በእርግጥም በኬረለ የሚገኙትን ሐይቆች መጎብኘት አስደሳች ተሞክሮ ነው። ይህ የሆነው ውብ የሆኑትን የቻይናውያን መረቦች፣ የእባብ ጀልባዎችና የጀልባ ቤቶች ማየት ስለሚቻል ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ‘ሰው አጥማጅ’ የሆኑ ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች በመኖራቸው ጭምር ነው።
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሕንድ
ኬረለ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኬረለ ዓሣ ማጥመድ የዕለት ተዕለት ሕይወት ክፍል ነው
[ምንጭ]
የላይኛው ፎቶ:- Salim Pushpanath
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሴቶች በእጃቸው ዓሣ ሲያጠምዱ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእባብ ጀልባዎች ውድድር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ኬቱቨለም”
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጀልባ ቤቶች
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆኒና ባለቤቱ ራኒ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Salim Pushpanath