ከጦር አዛዥነት ወደ ‘ክርስቶስ ወታደርነት’
ከጦር አዛዥነት ወደ ‘ክርስቶስ ወታደርነት’
ማርክ ሉዊስ እንደተናገረው
“እንደምን አደሩ ግርማዊነትዎ።” “እንደምን ዋሉ ክቡርነትዎ።” “እንደምን አመሹ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር።” እነዚህ አባባሎች፣ የአውሮፕላን አብራሪና የአውስትራሊያ ንጉሠ ነገሥት አየር ኃይል ልዩ ቡድን አዛዥ በነበርኩበት ወቅት ባለ ሥልጣናትን ሰላም ለማለት ከምጠቀምባቸው አባባሎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። መሪዎችንና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን እዚያው አውስትራሊያ ውስጥም ሆነ ከአገር አገር በአውሮፕላን አጓጉዝ ነበር። አሁን ግን ከዚህ የበለጠ የሚያረካ ሥራ እየሠራሁ ነው። ይህ ሥራ ምን እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።
የተወለድኩት በ1951 ምዕራብ አውስትራሊያ፣ ፐርዝ ውስጥ ሲሆን ያደግኩት በወታደር ቤተሰብ ውስጥ ነው። ገና የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ የሞተር አልባ አውሮፕላን አብራሪዎች (gliding) ክበብ አባል ሆንኩ። በጣም የምወደውንና ሕይወቴን ሙሉ ልሠራው የምፈልገውን የአብራሪነት ሙያ ሀ ብዬ የጀመርኩት በዚህ መንገድ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ ተለያዩና ቤተሰባችን ተበታተነ። የአየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች አዛዥና ቤተሰቡ ከእነሱ ጋር እንድኖር የጋበዙኝ ሲሆን እዚያ እየኖርኩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ። አዛዡ በሰጠኝ ማበረታቻ መሠረት እኔም በአውስትራሊያ ንጉሠ ነገሥት አየር ኃይል ተቋም ውስጥ ገብቼ በእጩ መኮንንነት ለመሠልጠን ፍላጎት አደረብኝ።
በአብራሪነት ተመረቅኩ
ከስድስት ዓመት ገደማ በኋላ በፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በመያዝ የአየር ኃይል መኮንን ከመሆኔም በላይ በአብራሪነት ተመረቅኩ። የመጀመሪያ ሥራዬ በአውስትራሊያ ውስጥ እንዲሁም ከአገር ውጪ ወደ ደቡብ ፓስፊክና ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚጓዙ የአየር ኃይል አውሮፕላኖችን ማብረር ነበር። ብዙውን ጊዜ በትላልቅ ተራሮች መካከልና ጥልቅ በሆኑ ሸለቆዎች ውስጥ በመብረር አውሮፕላናችንን ሜዳ ላይ እናሳርፍ ነበር። በእርግጥ ሥራው አደገኛ ነበር። በእነዚያ ዓመታት የአየር ኃይል ቡድናችን በርካታ አውሮፕላኖችንና ጥሩ ልምድ ያላቸውን አንዳንድ ሰዎች አጥቷል። ሆኖም ገለልተኛ ወደሆኑ አካባቢዎች በመብረር በዚያ የሚኖሩ ሰዎችን የሚጠቅሙ ሥራዎችን አከናውነናል። ድልድይ ለመሥራት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን፣ ለመንገድ ሥራ የሚያስፈልጉ አነስተኛ ቡልዶዘሮችን፣ አስቸኳይ የምግብ እርዳታዎችንና የሕክምና ቡድኖችን እናጓጉዝ ነበር። አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ያጓጓዝንባቸው ጊዜያትም አሉ።
በ1978 የበረራ ትምህርት ለመስጠት የሚያስፈልገውን ብቃት በማሟላቴ ወደ ተቋሙ ተመልሼ አስተማሪ ሆንኩ። ወደ ተቋሙ መመለሴ፣ የሦስት ዓመት ሴት ልጅ ካላት ዳያን ከምትባል ባሏን በሞት ካጣች ወጣት ሴት ጋር የነበረኝን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ ፈጠረልኝ። የዳያን ባል አብሮኝ ተምሮ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በደረሰበት የአውሮፕላን አደጋ ሕይወቱ አልፏል። ለዳያን የጋብቻ ጥያቄ ሳቀርብላት በጉዳዩ ላይ ለማሰብ ጊዜ እንድሰጣት ጠየቀችኝ። በድጋሚ የአውሮፕላን አብራሪ ለማግባት ያመነታች ይመስላል።
ከጊዜ በኋላ ለ12 ወራት ለአንድ የአውስትራሊያ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለ ሥልጣን የቅርብ ረዳት ሆኜ እንድሠራ ተሾምኩ። ካምቤራ በሚገኘው የባለ ሥልጣኑ መኖሪያ ቤት ያሳለፍኩት ሕይወት ፖለቲካዊ አሠራሮችን በቅርብ እንዳውቅ ያስቻለኝ ከመሆኑም ሌላ ከሲቪልና ከወታደራዊ ባለ ሥልጣናት እንዲሁም ከሃይማኖት መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረኝ አድርጎኛል።
እዚያ የምሠራበት ጊዜ ሲያበቃ ወደ በረራ አስተማሪነት ተመለስኩ። ብዙም ሳይቆይ በ1980 እኔና ዳያን ተጋባን።በ1982 የበረራ ደህንነት ኃላፊና የአውሮፕላን አደጋ መርማሪ በመሆን ለሁለት ዓመት የሚቆይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመሄድ አጋጣሚ አገኘሁ። ሥራው በመላው ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም እስከ ሰሜን አየርላንድ መጓዝ የሚጠይቅ ነበር። በተጨማሪም ሥራው የበረራ ደህንነትን ለማሻሻል ሲባል የአውሮፕላን አደጋዎችን መመርመርን እንዲሁም የአውሮፕላኑን ንድፍና የበረራ እንቅስቃሴዎቹን መገምገምን ያጠቃልላል።
ወደ አውስትራሊያ ተመለስኩ
ወደ አውስትራሊያ ከተመለስኩ በኋላ ሴት ልጃችን ካሪ ተወለደች፤ በዚህ ጊዜ የቤተሰባችን ቁጥር ወደ አራት ከፍ አለ። የሥራ ጫና ስለነበረብኝ ዳያን ሴት ልጆቻችንን እንደ እናትም እንደ አባትም በመሆን መንከባከብ ግድ ሆኖባት ነበር፤ ይህ ደግሞ በቤተሰብ ሕይወታችን ላይ ጉዳት ማስከተሉ አልቀረም። ከሦስት ዓመት በኋላ በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት ልዩ የአየር ኃይል ቡድን አዛዥ የመሆን ሥልጣን አገኘሁ። በ1991 የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት በፈነዳበት ወቅት የእኔ ክፍል ለተባበሩት መንግሥታት ጦር ድጋፍ ሰጥቶ ነበር። ከዚህም በላይ የተባበሩት መንግሥታት በፓኪስታን፣ በአፍጋኒስታን፣ በአፍሪካና በእስራኤል ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ተካፍለናል።
በ1992 የመከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ የቅርብ ረዳት ሆንኩ። በአውስትራሊያ ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ የጦር አዛዥ ለሆነ ሰው የቅርብ ረዳት ሆኜ ማገልገሌ በውትድርና፣ በፖለቲካና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዳስተውል ረድቶኛል። ከዚህም በላይ የተባበሩት መንግሥታት ብዙ ጉድለቶች አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ እንድደርስ አድርጎኛል። ያም ሆኖ ግን የተሻለ ዓለም ለማምጣት ብቸኛው ተስፋችን የተባበሩት መንግሥታት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሁንና በቤታችን ውስጥ የተከሰቱት አንዳንድ ነገሮች የነበረኝን አመለካከት እንደገና እንድመረምር አደረጉኝ።
የዳያን ጥያቄዎች መልስ አገኙ
የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረችው ዳያን የመጀመሪያ ባሏ ከሞተ በኋላ ለጥያቄዎቿ መልስ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም። ትልቋ ልጃችን፣ ሬኒ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች የማወቅ ፍላጎት እያደረባት በመጣ ጊዜ ደግሞ ሁኔታዎች ይበልጥ እየከበዱ መጡ። ዳያን ወደ አንዲት ጓደኛዋ ቤት ሄዳ ሳለ በቀጣይ እትሙ ላይ ስለ ሰይጣን አምልኮ * የሚናገር ርዕስ እንደሚወጣ የሚጠቁም ሐሳብ ያለው አንድ ንቁ! መጽሔት ተመለከተች። ዳያን ከዚያ በፊት ንቁ! መጽሔት የሚባል አይታ አታውቅም ነበር። ቤቷ እስክትደርስ ድረስ ‘ይህን እትም ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?’ እያለች ታስብ ነበር።
ከሦስት ቀን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ፤ በዚህ ጊዜ ዳያን የምትፈልገውን መጽሔት አገኘች። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ የተቀበለች ሲሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይም መገኘት ጀመረች። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በመጀመሯ ደስ ብሎኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ በስብሰባዎች ላይ አብሬያት እገኝ ነበር፤ ሆኖም የሃይማኖት ሰው እሆናለሁ የሚል ሐሳብ ስላልነበረኝ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚያስፈልገኝ አልተሰማኝም። በአምላክ መኖር አምናለሁ፤ ይሁን እንጂ ግብዝነት የሚንጸባረቅባቸው በርካታ ድርጊቶችን ስለምመለከት ሃይማኖትን በቁም ነገር ለመያዝ አስቤ አላውቅም። ለምሳሌ ያህል፣ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የታቀፉ ቀሳውስት በአንድ በኩል ስለ ፍቅርና ሰላም እየሰበኩ ለምን ጦርነትን እንደሚደግፉ አይገባኝም ነበር።
ዳያን፣ እንዳነብባቸው በማሰብ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማየት በምችልበት ቦታ ላይ በዘዴ ታስቀምጥ ነበር። አንዳንዶቹን ካነበብኳቸው በኋላ በጥንቃቄ የነበሩበት ቦታ መልሼ አስቀምጣቸዋለሁ። ፍላጎት አድሮበታል ብላ እንድታስብ አልፈልግም ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት እያደገ ሲሄድ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይረብሹኝ ጀመር። አንዱ፣ ወፎች “የጦር አዛዦችን ሥጋ” እንደሚበሉ የሚናገረው የራእይ 19:17, 18 ጥቅስ ሲሆን ሌላው ደግሞ ስለ አንድ “ቀይ አውሬ” የሚጠቅሰው ራእይ 17:3 ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ይህ አውሬ የተባበሩት መንግሥታትን ይወክላል የሚል አመለካከት አላቸው፤ ይህ ደግሞ እኔ ለዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከነበረኝ አመለካከት ጋር ይቃረናል። * ይሁንና ስለዚህ ጉዳይ በፍጹም ላለማሰብ እሞክር ነበር።
በ1993 ዳያን በጥምቀት ሥነ ሥርዓቷ ላይ እንድገኝ ጠየቀችኝ። ጥያቄዋ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነበር። “ከይሖዋ ወይም ከእኔ አንዱን መምረጥ ቢኖርብሽ ማንን ትመርጫለሽ?” በማለት ጠየቅኳት። ዳያን፣ “የምመርጠው ይሖዋን ነው፤ ሆኖም
እንዲህ ያለ ምርጫ እንደማይቀርብልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ሁለታችሁም ታስፈልጉኛላችሁ” በማለት መለሰችልኝ። በዚህ ጊዜ በዳያን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ስላለው ስለዚህ አካል የበለጠ ማወቅ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ዳያን በምትካፈልበት ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር ግብዣ አቀረበልኝ፤ እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ።በተለይ ከወታደራዊ ኃይልና ከመንግሥታት ታሪኮች ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ይበልጥ ትኩረቴን እየሳቡት መጡ። ለምሳሌ ያህል፣ በአየር ኃይል ውስጥ ሥልጠና በምወስድበት ወቅት የጥንቶቹ ግሪኮች ስላገኟቸው ወታደራዊ ድሎች ተምሬ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ በኋላ የዚህ ታሪክ አብዛኛው ክፍል ከብዙ ዘመናት በፊት በዳንኤል ምዕራፍ 8 ላይ ተመዝግቦ እንደነበር ተረዳሁ። ይህና ሌሎች ትንቢቶች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን ቀስ በቀስ አሳምነውኛል።
ስለ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የነበረኝ አመለካከትም ተለወጠ። በወታደራዊ ኃይል አማካኝነት የሰውን ዘር ችግሮች መፍታት እንደማይቻል፣ ጦርነት እውነተኛ ሰላም እንደማያመጣ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ለጦርነት መንስኤ የሚሆነውን የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የዘር ልዩነት ማስወገድ እንደማይችል አወቅሁ። ለሰው ዘር ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣው አምላክ ብቻ መሆኑን ተገነዘብኩ። እንዲያውም እነዚህ ችግሮች በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች የወንድማማች ኅብረት ውስጥ አለመኖራቸው ይሖዋ አሁንም ቢሆን ይህን ማድረግ እንደጀመረ በግልጽ ያሳያል። (መዝሙር 133:1፤ ኢሳይያስ 2:2-4) ‘የሆነ ሆኖ አምላክን ለማገልገል ከውትድርና መውጣት ይኖርብኝ ይሆን?’ እያልኩ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።
በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለመመራት የወሰድኩት አቋም
በ1994 ሲድኒ ውስጥ ተደርጎ በነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ አንድ ውሳኔ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ። በዚያ ስብሰባ ላይ ጥንታዊ አለባበስ የተንጸባረቀበት የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ቀርቦ ነበር። ድራማው የጥንት እስራኤላውያን ከይሖዋና የከነዓናውያን አምላክ ከሆነው ከበኣል አንዱን በማገልገል ረገድ ተደቅኖባቸው ስለነበረው ምርጫ የሚናገር ነበር። የይሖዋ ነቢይ የነበረው ኤልያስ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ እውነተኛው አምላክ፣” NW] ከሆነ እሱን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” በማለት ለእስራኤላውያን ምርጫ አቅርቦላቸው ነበር። (1 ነገሥት 18:21) በእነዚህ ቃላት ልቤ በጥልቅ ተነካ። እንደ እስራኤላውያን ሁሉ እኔም በሁለት ሐሳብ እየዋለልኩ ነበር። አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ማለትም ይሖዋን ለማገልገል ወይም በውትድርናው መስክ ለመቀጠል መምረጥ ይኖርብኛል።
ያን ዕለት ምሽት በመኪና ወደ ቤት እየተመለስን እያለ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ስል አየር ኃይልን ለመልቀቅ እንዳሰብኩ ለዳያን ነገርኳት። ድንገት ያደረግኩት ውሳኔ ቢያስገርማትም ሐሳቤን ሙሉ በሙሉ ደግፋልኛለች። በርካታ ቀናት ቢያልፉም ውሳኔዬ ግን አልተለወጠም፤ በመሆኑም የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገባሁ።
በወቅቱ በዋና ከተማዋ በካንቤራ በሚገኘው የአውስትራሊያ የመከላከያ ኃይል ተቋም ውስጥ የአንድ የጦር መኮንኖች ብርጌድ አዛዥ ነበርኩ። ወታደራዊ ሥልጠናና የቀለም ትምህርት በመውሰድ ላይ የነበሩ 1,300 የሚያህሉ የምድር ጦር፣ የባሕር ኃይልና የአየር ኃይል እጩ መኮንኖችን እንዲሁም ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞችን በበላይነት አስተዳድር ነበር። በዓመቱ የትምህርት ዘመን ማብቂያ ላይ 400 ለሚሆኑ የመጨረሻ ዓመት ሠልጣኞችና ሌሎች ሠራተኞች ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ስል የውትድርናውን ዓለም ልለቅ እንደሆነ ነገርኳቸው። አቋሜን በይፋ መናገሬ ከአንዳንዶቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለማድረግ አስችሎኛል።
የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ
ያስገባሁት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት ባገኘ ማግሥት በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ከሦስት ወር በኋላ ሚያዝያ 1995 ተጠመቅኩ። ከዚያም ሁኔታዎች ሲመቻቹልኝ ወዲያው የዘወትር አቅኚ በመሆን ሙሉ ጊዜዬን በአገልግሎት ማሳለፍ ጀመርኩ።
ከጦር አዛዥነት ወደ ‘ክርስቶስ ወታደርነት’ ያደረግኩት ለውጥ ብዙ ማስተካከያዎችን ማድረግ ጠይቆብኛል። (2 ጢሞቴዎስ 2:3) በጉባኤ ውስጥ የተሰጠኝ የመጀመሪያ ኃላፊነት በስብሰባ ወቅት ድምፅ ማጉያ ማዞር ነበር። ትእዛዝ በመስጠት ፋንታ አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን ፈቃድ መጠየቅን መማር ነበረብኝ። ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር አንድን ሥራ እንከን በማይወጣለት መንገድ ማከናወን ሳይሆን ለሰዎች አሳቢነትና ፍቅር ማሳየት ነው፤ እርግጥ አሁንም እነዚህን ባሕርያት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማንጸባረቅ እየታገልኩ ነው። የማገኘው ገቢ በመቀነሱ ምክንያት ቤተሰባችን አኗኗሩን ቀላል ማድረግ ነበረበት።
አሁንም ቢሆን በስብከቱ ሥራ መካፈል በጣም ያስደስተኛል። በአንድ አጋጣሚ በወቅቱ የዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ካላት
ኬሪ ከተባለችው ሴት ልጃችን ጋር ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የምናነጋግራቸው ሰዎች የሚያንጸባርቁትን ስሜት እንድታጤን ነገርኳት። የተወሰኑ ሰዎችን ካነጋገርን በኋላ አብዛኞቹ መልእክታችንን ለመስማት ፈቃደኞች ባይሆኑም አንዳንዶቹ ጥሩዎችና ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ለመገንዘብ ቻልን። ይህ ደግሞ ሁለታችንንም አበረታትቶናል። ሌላዋ ልጃችን ለተወሰነ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናች ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ላለማገልገል መርጣለች።እኔም ሆንኩ ዳያን፣ ልጃችን ኬሪ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ እንዲኖራት እናበረታታት ነበር። በቅርቡ ከልጄ ጋር የአቅኚዎች ኮርስ በመውሰዴ በጣም ተደስቻለሁ። ኮርሱ ለእሷ የመጀመሪያዋ ሲሆን ለእኔ ደግሞ ሁለተኛዬ ነበር። ኬሪና ሌሎች ወጣቶች በመንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ራሳቸውን ሲያስጠምዱ ማየት እንዴት የሚያስደስት ነው!—መዝሙር 110:3
ያገኘኋቸው የተትረፈረፉ በረከቶች
ስላሳለፍኩት ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ በጦር ሠራዊት ውስጥ ማገልገልና የክርስቶስ ወታደር መሆን በርካታ የሚያመሳስሏቸውም ሆኑ የሚያለያዩዋቸው ነገሮች እንዳሉ እገነዘባለሁ። ለምሳሌ፣ ሁለቱም ኃላፊነቶች ታማኝነትን፣ ታዛዥነትን፣ የአቋም ጽናትን፣ ራስን መገሠጽንና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃሉ። ይሁንና በውትድርናው ዓለም የተሰማሩ በርካታ ሰዎች ለአገራቸውና ለጦር ጓዶቻቸው ሲሉ ለመሞት ፈቃደኞች ሲሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ጠላቶቻቸውን እንኳ እንዲወዱ ይጠበቅባቸዋል። (ማቴዎስ 5:43-48) የጦር ሜዳ ጀግኖች በድፍረት ተነሳስተው አንድ ጊዜ ለፈጸሙት ጀብዱ የሜዳልያ ሽልማት ያገኛሉ፤ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን የአምላክን ሞገስ የሚያገኙት በአገልግሎታቸው ታማኝ ሆነው እስከ ጸኑ ድረስ ነው። ይህ ደግሞ ከዓመት ዓመት ተቃውሞ፣ ፌዝና ሌሎች ፈተናዎች ቢደርስባቸውም እንኳ ድፍረት ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ ሊጠይቅባቸው ይችላል። (ዕብራውያን 10:36-39) ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮችን የመሰሉ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን የሚከተሉ ሰዎች አይቼ አላውቅም።
በመግቢያው ላይ ከተጠቀሱት አባባሎች በተቃራኒ አሁን ሰላም የምለው “እንደምን አደርሽ እህት” እና “እንደምን አመሸህ ወንድም” በማለት ነው። አምላክን ከልብ ከሚወዱ ሰዎች ጋር በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! ከሁሉ የላቀው ክብር ግን ልዑል ይሖዋን ማገልገል ነው! ሕይወቴን ከዚህ ይበልጥ እርካታ በሚያመጣ መንገድ እጠቀምበታለሁ ብዬ አላስብም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.15 የጥቅምት 22, 1989 እትም ገጽ 2-10
^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለ መጽሐፍ ገጽ 240-243 ተመልከት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በውትድርናው ዓለም የተሰማሩ በርካታ ሰዎች ለአገራቸውና ለጦር ጓዶቻቸው ሲሉ ለመሞት ፈቃደኞች ሲሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ጠላቶቻቸውን እንኳ እንዲወዱ ይጠበቅባቸዋል
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካንቤራ በሚገኘው የፓርላማው ምክር ቤት አናት ላይ አንድ ልዩ የአየር ኃይል ጄት ሳበር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1994 ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ውስጥ ተደርጎ በነበረ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የቀረበ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአቅኚዎች ትምህርት ቤት ከኬሪ ጋር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ከዳያን እና ከኬሪ ጋር