ባይካል—የዓለም ትልቁ ሐይቅ
ባይካል—የዓለም ትልቁ ሐይቅ
ሩሲያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ዛሬ ደቡባዊ ሳይቤሪያ በመባል በሚታወቀው ገጠራማ ክልል የሚኖሩት የሞንጎልያ ጎሣዎች ከጥንት ጀምሮ ለዚህ ሐይቅ አምልኮ አከል ክብር ሲሰጡት ኖረዋል። በስፋት የሚበልጡት በርካታ ሐይቆች ቢኖሩም በዓለም ላይ ካሉ ጨዋማ ያልሆነ ውኃ ከሚገኝባቸው ሐይቆች ሁሉ በጥልቀቱ ተወዳዳሪ የለውም፤ ከዚህም በላይ ከየትኛውም ሐይቅ ይበልጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ይዟል። ከሐይቁ መጠሪያዎች እስካሁን ሳይጠፋ የቆየው ባይካል የሚለው ሲሆን ትርጉሙም “ባለጠጋ ሐይቅ” ወይም “ባሕር” ማለት እንደሆነ ይታመናል። እንዲያውም ሐይቁ “በጣም ትልቅና በቀላሉ የሚተን” ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ባሕረኞች በሐይቁ ዳር ሆነው “ወደ ባሕር ስለመሄድ” ሲናገሩ ይሰማል።
ስለ ባይካል ሐይቅ ሲነሳ ሩሲያውያን ልዩ ስሜት ያድርባቸዋል። ከሞስኮ የመጡ አንዲት የሳይንስ ሊቅ ይህን ሐይቅ “ሁሉም ሰው በልጅነቱ የተማረው ውብ ሙዚቃ” በማለት ጠርተውታል። የሙዚቃው “ኖታዎች” ማለትም የባይካል ሐይቅ ገጽታዎች በርካታ ናቸው፤ እጅግ ማራኪ የሆኑት የሐይቁ ዳርቻዎች፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ ኩልል ያለው የሐይቁ ውኃ እንዲሁም በውስጡ የሚገኙት ብርቅዬ ፍጥረታት ከእነዚህ መሃል የሚጠቀሱ ናቸው።
ርዝመቱ 636 ኪሎ ሜትር፣ ወርዱ ደግሞ ሰፊ በሆነው ወገን ሲለካ 80 ኪሎ ሜትር የሆነው የባይካል ሐይቅ ከሕዋ ላይ ሆኖ ሲታይ ገርበብ ብሎ የተከፈተ ሰማያዊ ቀለም ያለው ዓይን ይመስላል። በምድር ላይ ካለው ጨዋማ ያልሆነ ውኃ አንድ አምስተኛው የሚገኘው በዚህ ሐይቅ ውስጥ ሲሆን የሰሜን አሜሪካ አምስት ታላላቅ ሐይቆች የያዙት ውኃ አንድ ላይ ቢዳመር እንኳ የባይካል ሐይቅ ይበልጣቸዋል! የባይካል ሐይቅ ከ1,600 ሜትር በላይ ጥልቀት አለው። የባይካል ሐይቅ በድንገት ቢደርቅ፣ በዓለም ላይ ያሉት ወንዞች ሁሉ ይህን ሐይቅ መልሰው ለመሙላት አንድ ዓመት ይፈጅባቸዋል!
የአህጉራት መላተም
የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ከብዙ ዘመናት በፊት አንድ ክፍለ አህጉር ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመንሸራተት ከእስያ ጋር እንደተላተመ የሚገልጽ ጽንሰ ሐሳብ አላቸው። ይህ ክስተት ግዙፍ የዓለት ንጣፎች እንደ ወረቀት እንዲጨረማመቱ ያደረገ ሲሆን የምድርን ገጽ ወደላይ በመግፋት የሂማልያ ተራሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። አንዳንዶች እንደሚያምኑት አህጉሮች እርስ በርስ ሲላተሙ የተፈጠረው ኃይል በሳይቤሪያ በርካታ ስምጥ ሸለቆዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ከእነዚህም መካከል በአሁኑ ጊዜ ባይካል ስምጥ ሸለቆ በመባል የሚጠራው ይገኝበታል። ከጊዜ በኋላ በአካባቢው ካሉት ተራሮች የሚወርደው ጎርፍ ሰባት ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆነውን የስምጥ ሸለቆውን ክፍል በደለል ሞላው፤ ከዚያም ውኃ ሲሞላው የባይካል ሐይቅ ተፈጠረ። በአሁኑ ጊዜ ከ300 በላይ ወንዞችና ጅረቶች ወደ ሐይቁ የሚፈሱ ሲሆን ከሐይቁ ወጥቶ የሚፈሰው ግን አንገራ የሚባለው ወንዝ ብቻ ነው።
በዓለም ላይ ካሉት አብዛኞቹ ጥንታዊ ሐይቆች በተለየ መልኩ ባይካል በደለል አልተሞላም ወይም ወደ ረግረግነት አልተለወጠም። የሳይንስ ሊቃውንት ይህ የሆነው ከሐይቁ ሥር ያለው መሬት መንቀሳቀስ (tectonic plates) አሁንም መሬቱን እየሰነጠቀውና ስምጥ ሸለቆውን እያሰፋው በመሆኑ ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም ምክንያት ሐይቁ በጊዜ ሂደት በደለል በመሞላት ፈንታ በየዓመቱ ጥልቀቱ እየጨመረ ነው! በተጨማሪም ከሐይቁ በታች ያለው መሬት መንቀሳቀስ ከሥሩ ፍል ውኃዎች እየተወረወሩ እንዲወጡ አድርጓል።
የባይካልን ሐይቅ ውስጡን መቃኘት
አንዳንዶች የባይካልን ሐይቅ መሃል ለመሃል በጀልባ ማቋረጥ ያስፈራቸዋል፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ኩልል ያለውን ውኃ ወደታች ከተመለከተ እስከ 50 ሜትር ድረስ ወለል ብሎ ይታየዋል! እጅብ ብለው የሚኖሩ ኤፒሹራ ተብለው የሚጠሩ ጥቃቅን ክረስቴሽኖች (የሸርጣን ዝርያዎች) የሐይቁን ውኃ የሚያጣሩ ሲሆን ብዙ ሐይቆች ጥርት ብለው እንዳይታዩ የሚጋርዱትን አልጌዎችና ባክቴሪያዎች ያስወግዳሉ። ሕይወት ካላቸው ነገሮች የሚወጡትን ብስባሽ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቆሻሻዎችን በሐይቁ ውስጥ እየተዘዋወሩ የሚመገቡ ክሬይፊሽ የሚባሉ በርካታ የውኃ ውስጥ ፍጥረታትም ሐይቁን በማጽዳት ያግዟቸዋል። በዚህም ምክንያት ውኃው በጣም ንጹሕ ከመሆኑ የተነሳ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ለምርመራ የተወሰደው የውኃው ናሙና በተቀመጠበት የቤተ ሙከራ ጠርሙስ አማካኝነት ሊበከል ችሏል!
የባይካል ሐይቅ ውኃ ውስጡን ወለል አድርጎ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በኦክስጅን እጅግ የበለጸገ ነው። ጥልቅ የሆኑ አንዳንድ ሐይቆች ከተወሰነ ጥልቀት በኋላ ኦክስጅን ስለማይኖራቸው በውስጣቸው ከሚኖሩት የውኃ ውስጥ ፍጥረታት ውስጥ አብዛኞቹ በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥልቀት በሌለው የሐይቁ ክፍል ለመኖር ይገደዳሉ። በባይካል ሐይቅ ውስጥ ግን ከላይ ወደታች ቀጥ ብለው የሚወርዱትና አግድም የሚሄዱት ሞገዶች ጥልቅ እስከሆነው የሐይቁ ክፍል ድረስ ኦክስጅን ይዘው በመሄድ ውኃውን በደንብ ያቀላቅሉታል። በዚህም የተነሳ በሐይቁ ውስጥ ከላይ እስከ ታች ሕያዋን ፍጥረታት ይርመሰመሱበታል።
ቀዝቃዛና ንጹሕ በሆነው ውኃ ውስጥ ደን መሳይ ጥሻ ይበቅላል። ልክ እንደ ኮራሎች ቅርንጫፎቻቸውን የዘረጉት አረንጓዴ ሰፍነጎች ስፍር ቁጥር ለሌላቸው የውኃ ውስጥ ፍጥረታት መጠለያ ይሆናሉ። ሙቀት ወዳድ የሆኑ ብዙ ሕያዋን ፍጥረታት ፍል ውኃ በሚፈልቅባቸው የሐይቁ ክፍሎች አካባቢ ይኮለኮላሉ። በሐይቁ ውስጥ ከሚኖሩት ከ2,000 በላይ የሚሆኑ የውኃ ውስጥ ፍጥረታት መካከል 1,500 የሚያህሉት በሌላ ቦታ አይገኙም።
ዓሣ አጥማጆች በጣም የሚወዱት ኦሙል የሚባል በአርክቲክ ክልል የሚገኝ ጣፋጭ ነጭ ዓሣ የሚኖረው በባይካል ሐይቅ ነው። እዚህ ቦታ ለየት ያሉና ግራ የሚያጋቡ ሌሎች ፍጥረታትም አሉ። አንድ ጠፍጣፋ የትል ዝርያ ርዝመቱ ከ30 ሴንቲ ሜትር በላይ ሲሆን የሚመገበውም ዓሣ ነው። በአሸዋ ቅንጣቶች መሃል የሚኖሩ ባለ አንድ ሕዋስ ፍጥረታትም አሉ! ሐይቁ፣ ጎሎሚያንካ ተብሎ የሚጠራ በባይካል ሐይቅ ብቻ የሚገኝና ምናልባትም በዚያ ካሉት ሁሉ በጣም ለየት ያለ የዓሣ ዝርያ መኖሪያ በመሆኑም ዝና አትርፏል።
በጣም ትንሽ የሆነው ጎሎሚያንካ የሚባለው የዚህ ዓሣ ሰውነት ብርሃን የሚያስተላልፍ ከመሆኑም በላይ በርካታ ደማቅ
ቀለማትን ያንጸባርቃል። ይህ የዓሣ ዝርያ የሚኖረው በሐይቁ ጥልቅ አካባቢ ሲሆን እንደ አብዛኞቹ ዓሦች ዕንቁላል ከመጣል ይልቅ አምሳያውን ይወልዳል። ከአካሉ ውስጥ አንድ ሦስተኛው በቪታሚን ኤ በበለጸገ ስብ የተገነባ ነው። ከ200 እስከ 450 ሜትር ጥልቀት ላይ ሊገጥመው የሚችለውን ኃይለኛ የአየር ግፊት ቢቋቋምም ለፀሐይ ብርሃን ሲጋለጥ ግን ሰውነቱ ይቀልጥና አጥንቱና ስቡ ብቻ ይቀራል። ጎሎሚያንካ፣ በባይካል ሐይቅ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ዝነኛ ለሆነው ኔርፓ ወይም የባይካል አቆስጣ ለሚባለው የውኃ ውስጥ እንስሳ ተወዳጅ ምግብ ነው። በዓለም ላይ ጨዋማ ባልሆነ ውኃ ውስጥ የሚኖረው የአቆስጣ (seal) ዝርያ ኔርፓ ብቻ ነው።የሚለዋወጡት ወቅቶች
በዓመት ውስጥ ለአምስት ወራት ያህል የባይካል ሐይቅ በበረዶ ይሸፈናል። በጥር ወር ማብቂያ አካባቢ የበረዶው ውፍረት አንድ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ይሆናል። በበረዶው ላይ የሚታዩት መሥመሮች በጠጠር የተሠራ የሚመስል ቅርጽ የሚያበጁ ከመሆኑም በላይ ፀሐይ ስትወጣ እንደ መስተዋት ያንጸባርቃል። በተጨማሪም በረዶው በላዩ ላይ የሚሄዱ ሰዎች በሐይቁ የታችኛው ክፍል ያሉትን ድንጋዮች ማየት እስኪችሉ ድረስ በጣም ጥርት ያለ ከመሆኑ የተነሳ ስስና በቀላሉ የሚሰበር ሊመስል ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አብዛኛውን ጊዜ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ በጣም ጠንካራ ነው። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በሩሲያና በጃፓን መካከል ጦርነት በተደረገበት የክረምት ወቅት የሩሲያ ሠራዊት በዚህ በረዶ ላይ የባቡር ሐዲድ በመዘርጋት 65 ባቡሮችን ማሻገር ችሏል!
ከሚያዝያ ማብቂያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ በረዶው እንደ ነጎድጓድ ኃይለኛ ድምፅ እያሰማ ይሰባበራል። በዚህ ጊዜ ከሐይቁ የሚሰማው የማያቋርጥ ውካታ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የተለመደውን “የበረዶ ሙዚቃ” ይፈጥራል። የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ የሆኑት ጀራልድ ዱረል፣ በረዶው ‘እንደ ትናንሽ ጸናጽሎች የሚያንቃጭልና ድመቶች ሲያንኮራፉ የሚያሰሙት ዓይነት’ ድምፅ እንደሚያሰማ ጽፈዋል። ብዙም ሳይቆይ አየሩ እየሞቀ ሲሄድ ነፋሱና ማዕበሉ በረዶውን እየገፉ አንጸባራቂ ቁልሎች በመሥራት ከሐይቁ ላይ ጠራርገው ወደ ዳርቻው ይጥሉታል።
የሐይቁ ውኃ መታየት ሲጀምር ወፎች ይመለሳሉ። ዲፐር እንደሚባለው ዝርያ ያሉት አንዳንዶቹ የባይካል ሐይቅ ወፎች ክረምቱን በሙሉ በአንጋራ ወንዝ መነሻ ላይ ይከርማሉ፤ ምንጊዜም ወደ በረዶነት የማይለወጠው ይህ የሐይቁ ክፍል ብቻ ነው። አየሩ ሞቅ እያለ ሲሄድ እነዚህ ወፎች እንደ ዳክዬ፣ ዝይ፣ ሁፐር ስዋን
የሚባሉ የዳክዬ ዝርያዎችና ሳቢሳ ካሉት ሌሎች የውኃ ወፎች ጋር ይቀላቀላሉ።በሰኔ ወር ሐይቁን ሊጎበኙ የሚመጡ ሰዎች በውኃው ዳር ባሉት ድንጋዮች ላይ በብዛት የሚፈለፈሉትን ካዲስ ፍላይ የተባሉ ነፍሳትን ዕጮች ለመብላት የሚመጡትን ድቦች ማየት ይችላሉ። ድቦቹ በዙሪያቸው የሚበሩት ነፍሳት የሚያሰሙትን ድምፅ ከቁብ ሳይቆጥሩ ዕጮቹን በምላሳቸው እየላሱ በደስታ ይመገቧቸዋል። ድቦቹ የነፍሳቱን ዕጮች ለመብላት በሐይቁ ዳርቻ በብዛት መታየታቸው ብዙ እንስሳትና ወፎችም በዚህ ወቅት ወደዚህ አካባቢ እንዲመጡ ያደርጋል።
በጸደይ መጀመሪያ ላይና በበጋ ወራት ሐይቁ ለጥቂት ጊዜ ያህል በአልጌ ይሸፈናል፤ እነዚህ አልጌዎች ለጥቃቅን ሸርጣኖች ምግብ ከመሆናቸውም በላይ ውኃው አረንጓዴ መልክ እንዲኖረው ያደርጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን የባይካል ሐይቅ ውኃ ከዳርቻው ላይ ሆኖ ሲታይ ወደ አረንጓዴ ያደላ ሰማያዊ መልክ ሲኖረው ወደ መሃል ያለውና ጥልቅ የሆነው ክፍል ደግሞ ልክ እንደ ውቅያኖስ ደማቅና ጠቆር ያለ ሰማያዊ ቀለም አለው።
በሐይቁ ዳርቻ የአሸዋ ክምሮችና የሚያምሩ ቋጥኞች ይገኛሉ። በአካባቢው የሚገኙት በርካታ ማራኪ የባሕር ወሽመጦችና ባሕረ ገብ መሬቶች በጣም ደስ የሚል እይታ ይፈጥራሉ። አንድ ጸሐፊ ይህንን ቦታ “እንደሚያብረቀርቅ ዕንቁ ተለዋዋጭ ገጽታ ያለው የተንጣለለ ምድር” በማለት የጠራው ሲሆን አካባቢው ውኃና ሰማዩ የሚታይበት የተለያየ ዓይነት ገጽታ የተላበሰ መልክዓ ምድር ነው።
በዓመቱ ማብቂያ ላይ ሐይቁ ብዙውን ጊዜ ሞገዳማ ይሆናል። በመከር ወቅት ነፋስ የሚኖር ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በሐይቁ ላይ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ይፈጠራል። ይህም ጸጥ ያለውን ውኃ በማናወጥ ከ4 እስከ 6 ሜትር ከፍታ የሚደርስ ኃይለኛ ማዕበል ያስነሳል። በሌሎች የዓመቱ ወቅቶችም ቢሆን ነፋሱ ትላልቅ የመንገደኛ መርከቦችንና የዓሣ ማስገሪያ ጀልባዎችን ያሰጠመባቸው አጋጣሚዎች አሉ።
የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው መሬት
ሳይቤሪያ ለመኖሪያ አስቸጋሪ አካባቢ በመሆኑ ባይካል ቀዝቃዛና ጭር ያለ ግዙፍ ሐይቅ ይመስል ይሆናል፤ እውነታው ሲታይ ግን ሐይቁ ብዛት ባላቸው የዱር እንስሳት የተከበበ ከመሆኑም በላይ በዙሪያው የተለያየ መልክዓ ምድር ይታያል። ሐይቁን የከበቡት አራት ትላልቅ የተራራ ሰንሰለቶች፣ የደጋ አጋዘኖችና ዝርያው ከምድር ሊጠፋ የተቃረበው የሳይቤሪያ የተራራ ፍየል መኖሪያ ናቸው።
በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ደግሞ በሣር የተሸፈኑ ሜዳዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ በሣር የተሸፈኑ ሜዳዎች አንዳንዶቹ በሚያስገርም ሁኔታ ዓይነታቸው የበዛ የሜዳ አበቦች ስለሚገኙባቸው የሳይቤሪያ የአበባ ቦታዎች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። በሜዳው ላይ ከሚኖሩት ብርቅ የሆኑ የወፍ ዝርያዎች መካከል ረጅም እግርና አንገት ያላት ዴሞይሰል ክሬን የምትባለው የምታምር ወፍ እንዲሁም በእስያ በትልቅነቷ ተወዳዳሪ የሌላት በስታርድ የምትባለው ወፍ ይገኙበታል።
በባይካል ሐይቅ ዙሪያ የሚገኘው ምንጊዜም ቅጠሉ የማይረግፍ ጥቅጥቅ ያለ ደን ለሐይቁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ደን ስፋቱ ከብራዚሉ የአማዞን ዝናባማ ደን በሁለት እጥፍ ይበልጣል። እንደ ብራዚሉ የአማዞን ዝናባማ ደን ሁሉ ይሄኛው ደንም የዓለም ሥነ ምህዳርና የአየር ንብረት ሚዛኑን እንዲጠብቅ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። እዚህ ደን ውስጥ ካፐርኬይሊ የሚባለውን የጅግራ ዝርያ ጨምሮ በርካታ የአእዋፍ ዝርያዎች ይኖራሉ፤ ካፐርኬይሊ ተጓዳኝ ለማግኘት ሲፈልግ የሚያሳየው ትርዒትና የሚያሰማው ዝማሬ አስደናቂ ነው። በገጽ 17 ላይ የምትታየው እጅግ የተዋበችው ትንሿ ዳክዬም ይህን ሐይቅ ታዘወትራለች።
ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት አጥቢ እንስሳ ደግሞ ዝነኛው የባርጉዚን ሳብል ነው። በአንድ ወቅት ለሚያብረቀርቀው ፀጉሩ ሲባል ያላንዳች ምሕረት ሲታደን የነበረው ይህ እንስሳ ለተፈጥሮ ሀብት ተንከባካቢዎች ምስጋና ይግባቸውና አሁን ቁጥሩ እየጨመረ ነው። ይህን ውብ ፍጥረት ለማዳን የተደረጉት ጥረቶች በ1916 በባይካል ሐይቅ ዳርቻ ላይ የባርጉዚን የተፈጥሮ እንክብካቤ ተቋም እንዲቋቋም ምክንያት ሆነዋል። በአሁኑ ጊዜ ከሐይቁ ዳርቻዎች ጋር የሚዋሰኑ ሦስት የተፈጥሮ እንክብካቤ ተቋማት እንዲሁም ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ሦስት ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ።
ጥልቅ በሆነው የፍጥረት ሥራ ላይ ማሰላሰል
ባይካል ሐይቅ፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ያሰፈረውና ታዋቂ የቱሪስት መስህብ የሆነ ሥፍራ ነው። በየዓመቱ ከ300,000 የሚበልጡ ጎብኚዎች ከመላው ዓለም ወደዚህ ቦታ ይጎርፋሉ። ስለ ጉዞ መረጃ የሚሰጥ አንድ ምንጭ “ባይካል በአሁኑ ጊዜ ስለ ተፈጥሮ ለሚያጠኑ ሰዎች በጣም አስደሳች ከመሆኑም ሌላ እጅግ ማራኪ የሆነ የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ቦታ ነው” በማለት ዘግቧል። “ባይካል ማራኪ የሐይቅ ዳርቻዎችና፣ የእግር ጉዞ ለማድረግ ግሩም የሆነ አካባቢ ያለው መሆኑ እንዲሁም ወፎችን ለማየት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩና በጀልባ ለመዝናናት ማስቻሉ በእስያ ውስጥ እጅግ በጣም ማራኪ ከሚባሉት የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ቦታዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል።”
ሐይቁ ወደር በሌለው የአምላክ ጥበብና በፍጥረቱ ግርማ ላይ ለማሰላሰል የሚያስችል ተስማሚ ቦታ ነው። በውስጡ ይህን ያህል ብዛት ያለው ልዩ ልዩ ዓይነት ሕይወት መኖር እንዲችል አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ አስደናቂ ተፈጥሯዊ ሂደቶች የሚከናወኑበት እንዲህ ዓይነት ድንቅ ሐይቅ ሊፈጥር የሚችል ከአምላክ በቀር ማን ይኖራል! በባይካል ሐይቅ ዳርቻ ላይ የቆመ ሰው “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው!” በማለት የተናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሐሳብ መልሶ ለማስተጋባት መገፋፋቱ አይቀርም።—ሮሜ 11:33
[በገጽ 16 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ጨዋማ ባልሆነ ውኃ ውስጥ ብቻ የሚኖረው አቆስጣ
የባይካል ሐይቅ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኔርፓዎች ወይም የባይካል አቆስጣዎች መኖሪያ ነው፤ እነዚህ እንስሳት ዓመቱን ሙሉ የሚመገቡት ጥልቀት ባለው የሐይቁ ክፍል የሚኖሩትን ዓሦች ነው። እነዚህ እንስሳት መሃል ሳይቤሪያ እንዴት ሊመጡ እንደቻሉና በሌላ አካባቢ ያልኖሩት ለምን እንደሆነ የሚያውቅ ሰው የለም። የቅርብ ዘመዳቸው የሚኖረው 3,220 ኪሎ ሜትር ርቆ ነው።
ኔርፓዎች በጠፍጣፋ ፊታቸው ላይ ተቀራርበው የተቀመጡ በጣም ትላልቅ ዓይኖች ያሏቸውና 1.4 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ከዓለም በጣም ትናንሽ የሆኑት የአቆስጣ ዝርያዎች ናቸው። እንደ አብዛኞቹ አቆስጣዎች እርስ በርስ ሳይነካከሱና ሳይጎነታተሉ ብዙውን ጊዜ በቡድን መልክ ሆነውና ተቀራርበው በትልቅ ቋጥኝ ላይ ፀሐይ ሲሞቁ ይታያሉ። በእርግጥም ገራሞቹ ኔርፓዎች በምድር ላይ ካሉት አቆስጣዎች ሁሉ በጣም ተግባቢዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።
ስለ አቆስጣዎች የሚያጠኑ አንድ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ እንደገለጹት ኔርፓዎች “ለዘብተኛ ከሆነው ባለቀለበቱ አቆስጣ የበለጠ ገራሞች ናቸው፤ ሳይንሳዊ ምርምር ለማድረግ በመረብ በሚያዙበት ጊዜ አይናከሱም።” አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ጠላቂ ዋናተኞች በጥልቅ ውኃ ውስጥ በሚዋኙበት ጊዜ እንቅልፍ የወሰዳቸው አቆስጣዎች ያሉበት ቦታ ደርሰው እንደነበረ ይጠቅሳል። እነዚህ ጠላቂ ዋናተኞች የተኙትን አቆስጣዎች ሲነኳቸው አልፎ ተርፎም ሲያገላብጧቸው እንኳን ከእንቅልፋቸው እንዳልነቁ ተናግረዋል።
[ምንጭ]
Dr. Konstantin Mikhailov/Naturfoto-Online
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የግዞት ቦታ
በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ለመካድ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ምክንያት ከ1951 እስከ 1965 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ባይካል ሐይቅ አካባቢ በግዞት ተወስደው ነበር። በ1951 ፕራስኮቪያ ቮሎሲያንኮ የባይካል ትልቁ ደሴት ወደሆነው ኦልክሆን ተወስዳ ነበር። በግዞት ከተወሰዱ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን የዕለት ጉርስ ለማግኘት ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ተሠማራች። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱሷን በመጠቀም ለሌሎች የኦልክሆን ነዋሪዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማካፈል ሌላ ዓይነት “ዓሣ የማጥመድ” ሥራም ለማከናወን ትጥር ነበር።
በ1953 ፕራስኮቪያ እና ሌሎች ስድስት የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ሥራቸው ምክንያት ተይዘው ታሠሩና እሷ የ25 ዓመት እሥራት ተፈረደባት። ከእሥር ከተለቀቀች በኋላ በ2005 በሞት እስካንቀላፋችበት ጊዜ ድረስ በኢርኩትስክ ክልል ኡሶልዩሲቢርስካይ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉባኤ በታማኝነት ስታገለግል ቆይታለች። በአሁኑ ጊዜ በባይካል ክልልና በአቅራቢያው ባለው የኢርኩትስክ ከተማ 30 የሚያህሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያደረጉ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ይገኛሉ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሩሲያ
የባይካል ሐይቅ
[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የባይካል ሐይቅና የሳያን ተራሮች
[ምንጭ]
© Eric Baccega/age fotostock
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የባይካል ትንሿ ዳክዬ
[ምንጭ]
Dr. Erhard Nerger/ Naturfoto-Online
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Dr. Konstantin Mikhailov/Naturfoto-Online
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
© Eric Baccega/age fotostock; Boyd Norton/Evergreen Photo Alliance