ከምሥራቅ ቲሞር ሕዝብ ጋር ተዋወቅ
ከምሥራቅ ቲሞር ሕዝብ ጋር ተዋወቅ
አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ምሥራቅ ቲሞር ወይም ቲሞር ሌስተ የቲሞርን ደሴት ምሥራቃዊ አጋማሽ የምትሸፍን ትንሽ አገር ነች። ከማላይ ቋንቋ የተወሰደው “ቲሞር” የሚለው ቃልም ሆነ ሌስተ የሚለው የፖርቹጋልኛ ቃል “ምሥራቅ” የሚል ትርጉም አላቸው። እንግሊዝኛ ተናጋሪ የሆኑ አገሮች በአብዛኛው ኢስት ቲሞር (ምሥራቅ ቲሞር) በማለት ይጠሯታል። አገሪቱ በኢንዶኔዥያ አካባቢ ከሚገኙት ደሴቶች በምሥራቃዊ ጫፍ ላይ ስለምትገኝ በሦስቱም ቋንቋዎች የተሰጣት ስያሜ ተስማሚ ነው።
ምሥራቅ ቲሞር 14,800 ካሬ ኪሎ ሜትር ገደማ የቆዳ ስፋት ያላት ሲሆን ይህ መጠን ከጅቡቲ ግማሽ የቆዳ ስፋት ትንሽ በለጥ ቢል ነው። ምሥራቅ ቲሞር በመጠን ትንሽ ብትሆንም እንኳ የእስያንና የአውስትራሊያን ተፈጥሯዊ ገጽታዎች አጣምራ የያዘች አገር ናት። በዚህች ደሴት ላይ የሐሩር ክልል ጥቅጥቅ ደንም ሆነ ደረቅ የባሕር ዛፍ ቁጥቋጦ እንዲሁም የሣር ምድር ይገኛል። የዱር እንስሳቷም ቢሆኑ የአውስትራሊያና የእስያ ዝርያዎች ድብልቅ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ማርሱፒያል የሚባሉት የአውስትራሊያ የካንጋሮ ዝርያዎችና ወፎች ከእስያ ጦጣዎችና የጨዋማ ውኃ አዞዎች ጋር በአንድነት ይኖራሉ። ስለ ምሥራቅ ቲሞር ሕዝብስ ምን ማለት ይቻላል? ከእነርሱ ጋር መተዋወቅ ትፈልጋለህ?
በቅኝ ግዛት ያሳለፈችው ጊዜ
የፖርቹጋል አሳሾች መጀመሪያ ምሥራቅ ቲሞር የደረሱት በ1514 ገደማ ሳይሆን አይቀርም። በዚያን ጊዜ የነበሩት ተራሮች በአብዛኛው ሰንደልዉድ በተባለ ዛፍ ተሸፍነው ነበር። የዚህ ዛፍ ንግድ በጣም አትራፊ በመሆኑ ፖርቹጋላውያን በዚህች ደሴት ላይ የንግድ ማዕከል ለመመሥረት ጥሩ ምክንያት ሆኗቸዋል። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ አካባቢ ላይ ዓይኗን ጥላ ስለነበር ሚስዮናውያንን በመላክ የአገሬውን ተወላጅ የመለወጥ ፍላጎት አደረባት። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ፖርቹጋላውያን በ1556 ደሴቷን ቅኝ ግዛት አደረጓት።
ይሁን እንጂ ምሥራቅ ቲሞር ገለልተኛና የተረሳች ቅኝ ግዛት ሆና ቆይታለች። ሆላንዳውያን በ1656 የደሴቷን ምዕራባዊ ክፍል ሲቆጣጠሩ ፖርቹጋላውያን ወደ ምሥራቁ ክፍል አፈገፈጉ። በመጨረሻም ፖርቹጋላውያን አካባቢውን ከ400 ለሚበልጡ ዓመታት በቅኝ አገዛዝ ካስተዳደሩ በኋላ በ1975 አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ለቀው ወጡ።
በዚያው ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። ከዚያ ለቀጣዮቹ 24 ዓመታት በዘለቀው ግጭት አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ማለትም ወደ 200,000 የሚገመቱ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ተቀስቅሶ የነበረው የዓመጽ ማዕበል በ1999 በመላ አገሪቱ በፍጥነት ተዛምቶ 85 በመቶ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችንና አብዛኞቹን የመሠረተ ልማት ተቋማት አውድሟል። በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ተራራ ለመሸሽ ተገደዋል። በመጨረሻም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጣልቃ በመግባት የሚደርሰውን ውድመት ማስቆምና አገሪቱን ማረጋጋት ጀመረ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቲሞራውያን የወደመችውን አገራቸውን መልሰው ለመገንባት ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል። በግንቦት 2002 ምሥራቅ ቲሞር ወይም የቲሞር ሌስተ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ እንደ አንድ አገር ሕጋዊ እውቅና አገኘች።
የተለያዩ ባሕሎች ያሉባት አገር
ለምዕተ ዓመታት የዘለቀው የንግድ ልውውጥ፣ የእስያና የአውስትራሊያ ስደተኞች እንዲሁም የአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት በምሥራቅ ቲሞር በርካታ አስደሳች ባሕሎችና ቋንቋዎች እንዲኖሩ ምክንያት ሆነዋል። የፖርቹጋል ቋንቋ የንግድና የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ ቢቀጥልም 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውንና ብዙ የፖርቹጋል ቃላት የያዘውን ቴቱም የተባለ ቋንቋ ይጠቀማል። በመላ አገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ጎሣዎች የሚናገሯቸው በትንሹ 22 የሚያህሉ ሌሎች ቋንቋዎችም አሉ።
በገጠራማ አካባቢዎች የጎሳ መሪዎች አሁንም በነዋሪው የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። እነዚህ መሪዎች ከክብረ በዓላት፣ ከመሬት ክፍፍልና ከሌሎች ባሕላዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን አመራር ይሰጣሉ። አስተዳደራዊ መዋቅሩን በበላይነት የሚመራው ግን በሕዝብ የተመረጠ ግለሰብ ነው።
ሕዝቡ የሚከተለው ሃይማኖት ሕይወት ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው ነገሮች ነፍስ አላቸው የሚለውን ጥንታዊ እምነትና ከውጪ የመጣውን የካቶሊክ እምነት ቅልቅል ነው። የቀድሞ አባቶች አምልኮ፣ ጥንቆላና መናፍስትነት የማይነካው የሕይወት ዘርፍ የለም። አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ፣ ከሕመማቸው ለመፈወስ ወይም ከክፉ መናፍስት ጥበቃ ለማግኘት በአካባቢው ወደሚገኝ ማታን ዶክ ወይም ጠንቋይ መሄዳቸው የተለመደ ነው።
የማወቅ ጉጉት ያለውና እንግዳ ተቀባይ የሆነ ሕዝብ
የምሥራቅ ቲሞር ሕዝቦች በተፈጥሯቸው ደስተኞች፣ የማወቅ ጉጉት ያላቸውና እንግዳ ተቀባዮች ናቸው። የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዣናና ጉሽማኦ “እርስ በርሳችንም ሆነ ከእንግዶች ጋር የመማማር፣ የመጨዋወት፣ የመግባባትና የመቀራረብ ከፍተኛ ፍላጎት አለን” በማለት ተናግረዋል።
ወደ ቲሞራውያን ቤተሰብ ቤት በእንግድነት የተጋበዘ አንድ ሰው ለገበታ የሚቀርበው ከቤተሰቡ አባወራ ጋር ነው። የአባወራው ሚስትና ልጆች እንግዳውን ያስተናግዱና ከመሸ በኋላ እራታቸውን ይበላሉ። እንግዳው መጀመሪያ ላይ ትንሽ ምግብ ይወስዳል። ከዚያም ምግቡ በጥሩ ሁኔታ እንደተሠራ ለማሳየት እንዲጨመርለት ይጠይቃል።
አብዛኞቹ ቲሞራውያን አትክልቶችንና ቅጠላ ቅጠሎችን የሚመገቡ ሲሆን ሩዝ፣ በቆሎ ወይም ካሳቫ ከእነዚህ ምግቦች ጋር አብሮ ይቀርባል። ቲሞራውያን ሳቦኮ የሚባል ተወዳጅ ባሕላዊ ምግብ ያላቸው ሲሆን ይህም ከሰርዲን፣ በታማሪንድ ፍሬ ከተሠራ ስጎና ከሌሎች ቅመማ ቅመሞች ተዘጋጅቶ በዘንባባ ቅጠል ተጠቅልሎ የሚቀርብ ነው። ሆኖም ሥጋ በጣም ውድ ነው።
በልጆች ጫጫታ የደመቁ መንደሮች
ምሥራቅ ቲሞር በርካታ ወጣቶች የሚገኙባት አገር ነች። ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ ወደ ግማሽ የሚጠጉት ልጆች ሲሆኑ በርካታ ቤተሰቦች ከ10 እስከ 12 የሚደርሱ ልጆች አሏቸው።
ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ወንዶች ከወንዶች ጋር ሴቶች ደግሞ ከሴቶች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው እየሳቁና እየዘመሩ ነው። በየትምህርት ቤታቸው ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ሥነ ምግባር ይማራሉ።
አንድ የቲሞራውያን ልጅ ከጎረቤት ልጆች ጋር ካልሆነ በስተቀር ብቻውን ወይም በዝምታ ሲጫወት ማየት የተለመደ አይደለም! ልጆች በጣም የሚወዱት ጨዋታ ዱዱ ካሬታ ወይም መኪና መንዳት ነው። መኪና ብለው የሚያሽከረክሩት የብስክሌትን ቸርኬ ሲሆን ይህን ነገር ከኋላ ሆነው በእንጨት እየገፉ በየመንገዱ ላይ እየተሯሯጡ ይጫወታሉ።
ይሁን እንጂ ይህ ሲባል ልጆች ከመጫወት ሌላ ምንም አያውቁም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከባድ የሆነውን በቆሎ የመፍጨት ሥራ እንዲያከናውኑ ሊታዘዙ ይችላሉ። ይህን ሥራቸውን ሲያከናውኑም ቢሆን ፈገግታ ከፊታቸው ላይ አይጠፋም። ደስተኛ ሆነው ላያቸው በዓለም ላይ በጣም ድሃ ከሆኑት አሥር አገሮች መካከል በአንደኛዋ ውስጥ መወለዳቸው ግድ የሚሰጣቸው አይመስሉም።
የአገሪቱ ራስ ምታት
ቲሞራውያን ሥር በሰደደ ድህነታቸው ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ለመምራት ተገደዋል። ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል 40 በመቶ የሚሆነው የቀን ገቢው ከ1.5 የአሜሪካ ዶላር በታች ነው፤ ይህ ደግሞ ከምግብና መሠረታዊ ከሆኑ የቤት ውስጥ ወጪዎች አያልፍም። የመሠረተ ልማት ተቋማቷም ቢሆኑ የረቡ አይደሉም። መንግሥት ይፋ ያደረገው አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “በመላ አገሪቱ ከሚገኙ አራት ሰዎች መካከል ሦስቱ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አይደሉም፤ ከአምስቱ መካከል ሦስቱ ተስማሚ የመጸዳጃ ቤት የላቸውም በተጨማሪም ግማሽ የሚሆነው ሕዝብ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኝም።”
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ በርካታ የጤና ችግሮች ይከሰታሉ። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ወባ፣ ሳንባ ነቀርሳ እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች የሰዎችን አማካይ ዕድሜ ከ50 እንዳይበልጥ አድርገውታል። ከ10 ልጆች መካከል አንዱ አምስት ዓመት ሳይሞላው ይሞታል። በ2004 ወደ 800,000 ለሚጠጋ ሕዝብ የጤና አገልግሎት የሰጡት ሐኪሞች ብዛት 50 አይሞላም ነበር።
በርካታ የውጪ አገር መንግሥታት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመተባበር ቲሞራውያን የፈራረሰችውን አገራቸውን መልሰው ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በቲሞር ባሕር ውስጥ የሚገኘው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ደካማ የሆነውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያሻሽለዋል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል። ከምንም በላይ ግን የምሥራቅ ቲሞር ትልቁ ሀብት መንፈሰ ጠንካራና ትሑት የሆነው ሕዝቧ ነው። አንዲት ቲሞራዊት ሴት ለንቁ! መጽሔት አዘጋጆች “ድሆች ብንሆንም እንኳ ደስታ የራቀን ሰዎች አይደለንም!” በማለት ተናግራለች።
“መልካም ዜና”
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች ለምሥራቅ ቲሞር ሕዝብ ‘መልካም ዜና እያበሰሩ’ ነው። (ኢሳይያስ 52:7፤ ሮሜ 10:14, 15) በ2005 በአገሪቱ የሚገኘው ብቸኛ ጉባኤ ስለ መጪው ምድራዊ ገነት የሚናገረውን አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሌሎች በመስበክ ወደ 30,000 የሚጠጋ ሰዓት አሳልፏል።—መዝሙር 37:10, 11፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
አንዳንድ ነዋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማራቸው ከመናፍስት ቀንበር ነፃ አውጥቷቸዋል። ጃኮብ የሚባለውን የአምስት ልጆች አባት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ሰው በአካባቢው በጣም በተለመዱት መናፍስታዊ ድርጊቶች ከመጠን በላይ ተጠላልፎ ነበር። ዘወትር ለሙታን መናፍስት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ይህ ልማድ በቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ አስከትሎበታል። የዶሮ መሥዋዕት ለማቅረብ የቀን ገቢውን ማውጣት የሚኖርበት ሲሆን የፍየል ወይም የአሳማ መሥዋዕት ለማቅረብ ደግሞ የበርካታ ሳምንታት ደሞዙን ማውጣት ያስፈልገው ነበር።
ከጊዜ በኋላ የጃኮብ ሚስት ፍራንሲስካ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙታን ምንም እንደማያውቁና በሕያዋን ላይ ጉዳት ማድረስ እንደማይችሉ የሚያረጋግጡ ጥቅሶችን ለጃኮብ እያሳየች አስረዳችው። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4) ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በመቀበል ለመናፍስት መሥዋዕት ላለማቅረብ ወሰኑ። በዚህም ምክንያት ዘመዶቻቸው ከእነርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋረጡ እንዲሁም በቅርቡ እነዚህ መናፍስት የበቀል እርምጃ ወስደው እንደሚገድሏቸው ነገሯቸው። ያዕቆብና ፍራንሲስካ ግን “ይሖዋ ይጠብቀናል” በማለት በአቋማቸው ጸኑ።
ከዚያም ጃኮብ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ከቤተሰቡ ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ይህም በሕይወቱ ውስጥ ተጨማሪ ለውጦችን እንዲያደርግ ረዳው። ለበርካታ ዓመታት በየቀኑ ፓኬት ሲጋራ ይጨርስ የነበረ ቢሆንም ማጨሱን አቆመ። ማንበብና መጻፍም ተማረ። በዚህ ወቅት ፍራንሲስካ ከዘንባባ ፍሬ የሚዘጋጀውን ሱስ የማስያዝና የማደንዘዝ ኃይል ያለውን ቢተል ነት የተባለ ፍሬ መብላቷን አቆመች። በመጨረሻም በ2005 ያዕቆብና ፍራንሲስካ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። እነዚህ ባልና ሚስት በዛሬው ጊዜ ገንዘባቸውን ልጆቻቸውን ለማስተማርና የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን በጥበብ ይጠቀሙበታል።
በእርግጥም ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተነበየው የአምላክ መንግሥት ምሥራች “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” በመሰበክ ላይ ሲሆን መልእክቱ የማወቅ ፍላጎት ላላቸው፣ እንግዳ ተቀባይና ደግ ለሆኑት የምሥራቅ ቲሞር ሕዝቦችም እየተዳረሰ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ ማቴዎስ 24:14
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“ፈትልና ቀሰም አገኛችሁ”
ቲሞራውያን በአንድ ወቅት ሴት ልጅ መወለዷን ለመናገር “ፈትልና ቀሰም አገኛችሁ” የሚል አባባል ይጠቀሙ ነበር። አባባሉ ቲሞራውያን ሴቶች በሽመና ሙያ የተካኑ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። የዚህ የሽመና ሙያ ውጤት ታይስ ተብሎ ይጠራል። ይህ ጨርቅ በልዩ ልዩ በዓላት ላይ የሚለበሱ የተለያየ ዲዛይን ያላቸውን ልብሶች፣ ብርድ ልብሶችንና ቤተሰቡ እንደ ቅርስ የሚያያቸውን ሌሎች ነገሮች ለመሥራት ያገለግላል። አረጋውያን ለወጣት ሴቶች እንዴት ጥጥ መዝራት፣ መልቀም፣ መፍተል፣ ቀለም መንከር እንዲሁም በቀለማት ያሸበረቀ ታይስ መሥራት እንደሚችሉ ያስተምሯቸዋል። እንደ ዲዛይኑ ዓይነት፣ አንድን ታይስ ሠርቶ ለመጨረስ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል። እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ የታይስ ዓይነት ስለሚኖረው ይህንን ሥራ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው አንድን ታይስ አይቶ የት እንደተሠራ በቀላሉ መለየት ይችላል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
ኢንዶኔዥያ
ምሥራቅ ቲሞር
አውስትራሊያ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሕላዊ ጎጆ ቤት
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ዱዱ ካሬታ”—ተወዳጁ የልጆች ጨዋታ
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጃኮብና ቤተሰቡ