ከግብረ ሰዶም እንዴት መራቅ እችላለሁ?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከግብረ ሰዶም እንዴት መራቅ እችላለሁ?
“የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ በትምህርት ቤት ውስጥ ካለች ልጅ ጋር ፍቅር ያዘኝ። ሌዝቢያን ሆንኩ እንዴ ብዬ በማሰብ በጣም ተጨነቅኩ።”—አና *
“በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ሌሎች ወንዶችን የመውደድ ስሜት ያስቸግረኝ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ያለው ስሜት ትክክል እንዳልሆነ አውቅ ነበር።”—ኦሌፍ
“ከሴት ጓደኛዬ ጋር አንድ ሁለት ጊዜ ተሳስመን እናውቃለን። ወንዶችንም አፈቅር ስለነበር ‘ለሴትም ለወንድም የጾታ ፍላጎት ያለኝ ሰው ነኝ ማለት ነው?’ ብዬ አስብ ነበር።”—ሴራ
ለሥነ ምግባር ንጽሕና ግድ የሌለው ይህ ዓለም በርካታ ወጣቶች ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲጀምሩ ይገፋፋቸዋል። የ15 ዓመት ወጣት የሆነችው ቤኪ እንዲህ ትላለች:- “በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ልጃገረዶች ሌዝቢያን (ከሴቶች ጋር ወሲብ የሚፈጽሙ ሴቶች) እንደሆኑ ወይም ከሁለቱም ጾታዎች ጋር ወሲባዊ ግንኙነት የመፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው አሊያም ከሁለቱም ዓይነት ጾታዎች ጋር የሚደረግ ወሲብ የሚፈጥረውን ስሜት ለማወቅ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።” የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ክሪስታም በትምህርት ቤቷ ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ትናገራለች። “አብረውኝ የሚማሩ ሁለት ልጃገረዶች ከእነርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት እንድፈጽም ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር” ብላለች። “እንዲያውም አንዷ ከሴት ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ ምን እንደሚመስል ማየት እፈልግ እንደሆነ የሚጠይቅ ወረቀት ጽፋልኛለች።”
ተመሳሳይ ጾታ ባላቸው ሰዎች መካከል ስላለው ወሲባዊ ግንኙነት እንዲህ በግልጽ የሚወራ በመሆኑ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘ግብረ ሰዶም መፈጸም በእርግጥ ስህተት ነው? ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ጾታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት ቢያድርብኝስ? ይህ ሁኔታ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንደሆንኩ ያመለክታል?’
አምላክ ግብረ ሰዶምን እንዴት ይመለከተዋል?
በዛሬው ጊዜ፣ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ግብረ ሰዶምን አቅልለው ይመለከቱታል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ግልጽ የሆነ ሐሳብ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ ወንድና ሴትን እንደፈጠረ እንዲሁም የአምላክ ዓላማ የጾታ ግንኙነት በትዳር ጓደኛሞች መካከል ብቻ እንዲፈጸም መሆኑን ይነግረናል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:24) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን ማውገዙ ምንም አያስደንቅም።—ሮሜ 1:26, 27
እርግጥ ነው፣ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ሊገልጹ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ማገን የተባለች የ14 ዓመት ወጣት “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉት አንዳንድ ሐሳቦች ዛሬ በሚገኘው ዓለም ውስጥ ምንም ቦታ የላቸውም” በማለት ተናግራለች። ሆኖም አንዳንዶች እንዲህ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ከእነርሱ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ነው። የአምላክ ቃል እነርሱ ለማመን ከሚፈልጉት ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ስለሚያስተምር አይቀበሉትም። የአምላክ ቃል ጊዜ ያለፈበት ነው የሚለው አመለካከት የተዛባ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ጠባብ አመለካከት እንድናስወግድ ያበረታታናል! እንዲያውም ይሖዋ አምላክ ትእዛዛቱን የሰጠን ለእኛው ጥቅም ሲል መሆኑን ልብ እንድንል በቃሉ ውስጥ ያበረታታናል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) እንዲህ መባሉም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም አፈጣጠራችንን በተመለከተ ከፈጣሪያችን የተሻለ ማን ሊያውቅ ይችላል?
ወጣት እንደመሆንህ መጠን የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቁብህ ይሆናል። ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ጾታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት ቢያድርብህስ? ግብረ ሰዶም ፈጻሚ ሆንክ ማለት ነው? አይደለም። አንተ ባትፈልገውም የጾታ ስሜትህ በሚያይልበት “በአፍላ ጉርምስና” ዕድሜ ላይ መሆንህን አስታውስ። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) ለተወሰነ ጊዜ ከአንተ ጋር ተመሳሳይ ጾታ ባለው ሰው ልትማረክ ትችላለህ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንደሆንክ አያመለክትም። አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ብዙውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ በሂደት ይጠፋል። ይሁንና ‘መጀመሪያውኑም ቢሆን እንዲህ ያለው ስሜት የሚቀሰቀሰው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
አንዳንዶች ግብረ ሰዶም የመፈጸም ስሜት በሰው ልጆች ጂን ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ከጊዜ በኋላ የሚዳብር ስሜት ነው ይላሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የግብረ ሰዶምን መንስኤ በተመለከተ የሚሰነዘሩትን ተጻራሪ ሐሳቦች አንስቶ ማብራሪያ መስጠት አይደለም። በእርግጥም የግብረ ሰዶም መንስኤ ይህ ነው ማለት ጉዳዩን ከልክ በላይ ማቃለል ሊሆን ይችላል። እንደ ማንኛውም ባሕርይ ሁሉ አንድ ሰው ግብረ ሰዶም ፈጻሚ እንዲሆን የሚያደርገው ምክንያትም በጣም የተወሳሰበ ነው።
መንስኤው ምንም ይሁን ምን ዋናው ቁም ነገር፣ ግብረ ሰዶም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ድርጊት መሆኑን መገንዘቡ ነው። በመሆኑም ተመሳሳይ ጾታ ላለው ሰው ከሚሰማው ተገቢ ያልሆነ ስሜት ጋር የሚታገል ሰው ሊደረስበት የሚችል ግብ ተቀምጦለታል፤ ይኸውም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንዲህ ባለው ስሜት ላለመሸነፍ መምረጥ ይችላሉ። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው “ግልፍተኛ” ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 29:22) መጽሐፍ ቅዱስ ከማጥናቱ በፊት ቁጣውን ለመቆጣጠር አይሞክር ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ ራስን መግዛት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ይጀምራል። ይህ ሲባል ግን በውስጡ የንዴት ስሜት ፈጽሞ አይሰማውም ማለት ነው? እንዲህ ማለት አይደለም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በቁጣ መገንፈል ስለሚያስከትለው ችግር የሚናገረውን ስለሚያውቅ ስሜቱ እንዲያሸንፈው አይፈቅድም። ተመሳሳይ ጾታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት ያድርበት የነበረ ግለሰብን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህ ሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ያለውን አመለካከት ከተማረ በኋላም አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ያልሆነ ስሜት ሊሰማው ይችላል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል በዚህ ምኞቱ ተሸንፎ መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም ሊቆጠብ ይችላል።
እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ማስወገድ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አይካድም። ሆኖም ሥር የሰደዱ መጥፎ ምኞቶችን እንኳ ማሸነፍ እንደሚቻል እርግጠኛ ሁን። (1 ቆሮንቶስ 9:27፤ ኤፌሶን 4:22-24) ዞሮ ዞሮ አኗኗርህን የምትቆጣጠረው አንተ ነህ። (ማቴዎስ 7:13, 14፤ ሮሜ 12:1, 2) አንዳንዶች በዚህ ሐሳብ ባይስማሙም ስሜትህን እንዴት መቆጣጠር እንደምትችል መማር ወይም ቢያንስ ድርጊቱን ከመፈጸም መራቅ ትችላለህ።
መጥፎ ድርጊቶችን ከመፈጸም ተቆጠብ
ግብረ ሰዶም ከመፈጸም እንድትቆጠብ ምን ሊረዳህ ይችላል?
▪ አንደኛ ይሖዋ ‘ስለ አንተ እንደሚያስብ’ በመተማመን የሚያስጨንቅህን ሁሉ ለእርሱ በጸሎት ንገረው። (1 ጴጥሮስ 5:7፤ መዝሙር 55:22) ይሖዋ “ከማስተዋል በላይ የሆነ” ሰላም በመስጠት ሊያበረታታህ ይችላል። ይህ ደግሞ ‘ልብህንና አሳብህን ይጠብቅልሃል’ እንዲሁም መጥፎ ምኞቶችን ከመፈጸም እንድትቆጠብ የሚረዳህን “እጅግ ታላቅ ኀይል” ይሰጥሃል። (ፊልጵስዩስ 4:7፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7) ለሁለቱም ዓይነት ጾታዎች ይሰማት የነበረውን ወሲባዊ ስሜት ለማሸነፍ ትጥር የነበረችው ሴራ እንዲህ ትላለች:- “እንዲህ ያለው ስሜት ሲመጣብኝ እጸልያለሁ፤ ይሖዋ ደግሞ ያበረታኛል። እርሱ ባይረዳኝ ኖሮ ይህንን ችግር መወጣት አልችልም ነበር። ጸሎት በጣም ረድቶኛል!”—መዝሙር 94:18, 19፤ ኤፌሶን 3:20
▪ ሁለተኛ አእምሮህን ገንቢ በሆኑ መንፈሳዊ ነገሮች ሙላው። (ፊልጵስዩስ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብብ። የአምላክ ቃል፣ በአእምሮህም ሆነ በልብህ ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ፈጽሞ አቅልለህ አትመልከተው። (ዕብራውያን 4:12) ጄሰን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ይላል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እንደ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 እና ኤፌሶን 5:3 ያሉ ጥቅሶች ለውጥ እንዳደርግ በጣም ረድተውኛል። መጥፎ ስሜት በሚሰማኝ ቁጥር እነዚህን ጥቅሶች አነባለሁ።”
▪ ሦስተኛ ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችን እንድናውጠነጥን ከሚያደርጉን ወሲባዊ ሥዕሎችና ግብረ ሰዶምን የሚያበረታቱ ፕሮፖጋንዳዎች ራቅ። * (መዝሙር 119:37፤ ቈላስይስ 3:5, 6) አንዳንድ ሲኒማዎችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ግብረ ሰዶምን ምንም ችግር የሌለው አማራጭ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። አና እንዲህ ትላለች:- “ዓለም ያለው የተዛባ አመለካከት በአእምሮዬ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ ለጾታ ያለኝን አመለካከት አዛብቶብኛል። አሁን ግን ግብረ ሰዶምን ከሚያበረታታ ከማንኛውም ሰው ወይም ሁኔታ እርቃለሁ።”—ምሳሌ 13:20
▪ አራተኛ ምስጢረኛህ ለሆነ ሰው ስሜትህን አውጥተህ ንገረው። (ምሳሌ 23:26፤ 31:26፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:1, 2፤ 3:10) ኦሌፍ፣ የአንድን ክርስቲያን ሽማግሌ ምክር የጠየቀበትን ሁኔታ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “የሰጠኝ ምክር በጣም ጠቃሚ ነበር። እንዲያውም ቀደም ብዬ አነጋግሬው ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር።”
ተስፋ አትቁረጥ!
እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ለማስወገድ ብዙ መድከም አያስፈልግም፤ እንዲያውም ከጾታ ጋር በተያያዘ የውስጥ ስሜትህና ፍላጎትህ የሚልህን በመስማት ማንነትህን መቀበል እንዳለብህ ይናገሩ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግ እንደምትችል ይናገራል! ለምሳሌ፣ አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ቀድሞ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ የነበሩ ቢሆንም እንደተለወጡ ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ምንም እንኳ አንተ እዚህ ደረጃ ላይ የደረስክ ባትሆንም በልብህ ውስጥ ያለውን እንዲህ ዓይነቱን ስሜት በመዋጋት ማሸነፍ ትችላለህ።
እንዲህ ያለው ስሜት አሁንም የሚያስቸግርህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ፤ ወይም ደግሞ ራስህን እንደማይሻሻል ሰው አድርገህ አትቁጠር። (ዕብራውያን 12:12, 13) ሁላችንም ብንሆን አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ዝንባሌዎችን እንዋጋለን። (ሮሜ 3:23፤ 7:21-23) በመጥፎ ምኞቶች ተገፋፍተህ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን የማትፈጽም ከሆነ በጊዜ ሂደት ስሜቱም ሊጠፋ ይችላል። (ቈላስይስ 3:5-8) ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ እንደሚረዳህ በእርሱ ታመን። እርሱ የሚወድህ ከመሆኑም በላይ አንተን የሚያስደስትህ ምን እንደሆነ ያውቃል። (ኢሳይያስ 41:10) አዎን፣ “በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ . . . የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።”—መዝሙር 37:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.19 በአሁኑ ጊዜ ወንዶች ለራሳቸው በተለይ ደግሞ ለውበታቸው ከሚገባው በላይ ትኩረት በመስጠት የሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ (ሜትሮሴክሽዋሊቲ) ግብረ ሰዶም ፈጻሚ በሆኑና ባልሆኑ ወንዶች መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ እንዲመጣ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ሜትሮሴክሽዋሊቲ የሚለውን ቃል እንደፈጠሩ የሚነገርላቸው ሰው እንዳሉት ከሆነ ይህ ስያሜ የሚሰጠው ግለሰብ “ግብረ ሰዶም ፈጻሚ ወይም ከተቃራኒ ጾታ ጋር የጾታ ግንኙነት የሚያደርግ አሊያም ከሁለቱም ጾታዎች ጋር ወሲብ የሚፈጽም ሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከራሱ ጋር ፍቅር የያዘው ከመሆኑም በላይ የጾታ ፍላጎቱን የሚያረካለትን ማንኛውንም ዓይነት ወሲባዊ ግንኙነት ይፈጽማል።” ይህ ስያሜ በስፋት እየተሠራበት የመጣው ለምን እንደሆነ አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሰዎች እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ተደርገው በመታየታቸው እንዲሁም ግብረ ሰዶም እንደ ነውር መታየቱ እየቀረ በመምጣቱና እውነተኛ የወንድነት መገለጫ የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ያለው አመለካከት በመለወጡ ነው።”
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ አምላክ ግብረ ሰዶምን የሚያወግዘው ለምንድን ነው?
▪ ተመሳሳይ ጾታ ካለው ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት የመጀመር ስሜት የሚያስቸግርህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
▪ ግብረ ሰዶም እንድትፈጽም ከሚገፋፋህ ስሜት ጋር እየታገልክ ከሆነ ለማን ማማከር ትችላለህ?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጎለመሰ ክርስቲያን ምክር እንዲሰጥህ ጠይቅ