ጥሩ ጤንነት የማይፈልግ ሰው የለም!
ጥሩ ጤንነት የማይፈልግ ሰው የለም!
ከዛሬ 2,700 ዓመታት በፊት አንድ ነቢይ በሽታ የማይኖርበት ዘመን እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር። በኢሳይያስ ጥንታዊ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው ይህ ትንቢት እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ ቆይቶልናል። ኢሳይያስ በዚህ ጽሑፍ ላይ ‘ታምሜአለሁ የሚል የማይኖርበት’ ዘመን እንደሚመጣ ከተናገረ በኋላ “በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤ የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ። አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) እንዲህ ስላለው ጊዜ የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው የዮሐንስ ራእይ አምላክ ሥቃይን ወይም ሕመምን ስለሚያስወግድበት ዘመን ይገልጻል።—ራእይ 21:4
ታዲያ እነዚህ ተስፋዎች ይፈጸሙ ይሆን? የሰው ልጅ ጥሩ ጤና አግኝቶ የሚኖርበትና በሽታ የሚባል ነገር የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የሰው ልጆች ካለፉት ትውልዶች የተሻለ ጤንነት አግኝተው እንደሚኖሩ አይካድም። የተሻለ ጤንነት አላቸው ሲባል ግን በጣም ጥሩ ጤንነት አግኝተዋል ማለት አይደለም። አሁንም ቢሆን በሽታ ከባድ ሥቃይና መከራ ማስከተሉ አልቀረም። ያመኝ ይሆናል የሚለው ፍርሃት ብቻ እንኳ ከባድ ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል። በዚህ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ዓለም ውስጥም እንኳ በአካላዊና በአእምሯዊ በሽታዎች ከመሠቃየት ነጻ የሆነ ሰው የለም።
የጤና መጓደል የሚያስከትለው ኪሳራ
የጤና መጓደል የሚያስከትለው ጫና ብዙ ገጽታዎች አሉት። በዛሬው ጊዜ በበሽታ ምክንያት የሚደርሰው የገንዘብ ኪሳራ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአውሮፓ 500 ሚሊዮን የሚያህሉ የሥራ ቀናት በጤና ችግር ምክንያት ባክነዋል። በሌሎች አካባቢዎችም ችግሩ ተመሳሳይ ነው። በሥራ ቦታ በሚደርሰው የምርታማነት መቀነስ ላይ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደው የሕክምና ወጪ ሲታከልበት በሁላችንም ላይ የኢኮኖሚ ጫና መፈጠሩ አይቀርም። ሁኔታው ታላላቅ የንግድ ድርጅቶችንና መንግሥታትን ለኪሳራ ይዳርጋቸዋል። እነዚህ የንግድ ድርጅቶች ኪሳራውን ለማካካስ የምርቶቻቸውን ዋጋ ከፍ ሲያደርጉ መንግሥታት ደግሞ ግብር ይጨምራሉ። ይሁንና ይህ ሁሉ ጫና ዞሮ ዞሮ የሚያርፈው በአንተው ላይ ነው።
በጣም የሚያሳዝነው በድህነት ሥር የምትኖር ከሆነ በቂ ሕክምና ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንብሃል። በጣም ውስን የሆነ፣ አሊያም ምንም ዓይነት የሕክምና አገልግሎት በማይሰጥባቸው በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ከአንተ የተለየ አይደለም። በበለጸጉ አገሮችም ቢሆን ጥሩ ሕክምና ማግኘት ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅባቸው ሰዎች አሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የጤና ኢንሹራንስ ከሌላቸው 46 ሚሊዮን ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ነው።
በሽታ የሚያስከትለው ጫና በገንዘብ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ቀሳፊ በሆነ በሽታ እንዲሁም ፋታ በማይሰጥ ከባድ ሕመም እንሰቃያለን፣ ሌሎች በከባድ ሕመም ሲሰቃዩ እያየን ለመኖር እንገደዳለን አልፎ ተርፎም የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ መሪር ሐዘን ይሰማናል።
በሽታ የሚባል ነገር በማይኖርበት ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋ በጣም የሚማርክ ነው። መቼም ቢሆን ጥሩ ጤንነት ማግኘት የማይፈልግ ሰው የለም! እንዲህ ያለው ተስፋ የማይታመን ቢመስልም እንኳ እውን መሆኑ እንደማይቀር የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ደግሞ በሰው ሠራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካኝነት ውሎ አድሮ ማንኛውም ዓይነት ሕመምና በሽታ ሊጠፋ እንደሚችል ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሰዎች በሽታ የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ የሚናገረውን ጥንታዊ ትንቢት አምላክ እንደሚፈጽመው በእርግጠኝነት ያምናሉ። ታዲያ የሰው ልጅ በሽታ የማይኖርበት ዘመን እንዲመጣ ሊያደርግ ይችላል? አምላክስ? ወደፊት ምን ዓይነት ጊዜ ያመጣ ይሆን?