የተማረችውን ነገር ወዳዋለች
የተማረችውን ነገር ወዳዋለች
አንዲት ሴት ግንቦት 2004 በካንሰር ከመሞቷ በፊት የጻፈችው አንድ ደብዳቤ በቅርቡ ተገኝቶ ነበር። ይህች ሴት ጤንነቷ ድንገት በማሽቆልቆሉ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ደብዳቤውን ጽፋ አልጨረሰችውም። ይሁን እንጂ ለማንም ያልተላከውን ይህን ደብዳቤ ያነበቡ ሰዎች ልባቸው ስለተነካ አንብተዋል፤ እንዲሁም በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት ተጠናክሯል።
ደብዳቤውን የጻፈችው ሱዛን የምትባል ሴት ስትሆን በከነቲከት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሽማግሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልክ ስትደውል ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እንደነበረች በደብዳቤዋ ላይ ገልጻለች። ቀጥላም በእነዚያ የወጣትነት ዓመታት ያጋጠማትን ሁኔታ በዝርዝር ጽፋለች። የሱዛን እናት ይህን ልብ የሚነካ ደብዳቤ ያገኘችው ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር። በኋላም የደብዳቤውን አንድ ቅጂ ኒው ዮርክ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ላከችው።
ሱዛን በ1973 በከነቲከት የሚኖረውን የዚህን የጉባኤ ሽማግሌ ስልክ ቁጥር ከስልክ ማውጫ ላይ እንዳገኘች ጽፋለች። ሁኔታውን በሚመለከት እንዲህ ብላለች:- “በዚያን ጊዜ 14 ዓመቴ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ካነበብኩ በኋላ ይህ እውነት መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። ከዚያ በፊት ከአንድም የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኝቼ ስለማላውቅ በስልክ ማውጫ ላይ አድራሻቸውን መፈለግ ጀመርኩ። ከዚያም ከእኔ ስልክ ጋር ተመሳሳይ መነሻ ያለውን ስልክ ቁጥር መርጬ ደወልኩ። ስልኩን ያነሳው ወንድም ጀንሪክ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝቼ የማላውቅ መሆኑ በጣም አስገረመው።” *
አሳዛኝ ሁኔታ
ሱዛን በደብዳቤዋ ላይ እንደገለጸችው የአሥር ዓመት ልጅ ሳለች ከእናቷ እህት ጋር እንድትኖር ወደ ከነቲከት ተላከች። መጀመሪያ ወደዚያ የሄደችው ለጥቂት ጊዜ እንድትቆይ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ሱዛን አክስቷ ጋር መቆየት እንደምትፈልግ ብቻዋን በፍሎሪዳ ለምትኖረው ለእናቷ ነገረቻት። ሱዛን ሁኔታዋ “አንድ ሰው በጣም ከሚበድሉት ሰዎች መለየት እንዲከብደው ከሚያደርገው ስቶክሆልም ሲንድሮም ከሚባለው ችግር” ጋር እንደሚመሳሰል ጽፋለች። * ይህ ነው የማይባል በደል ይፈጸምባት ነበር።
ሱዛን እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች:- “አክስቴና አብሯት የሚኖረው ሰው በጣም ይበድሉኝ ነበር። ከዚህም በላይ ቤታችን ሰው መጥቶ አያውቅም ማለት ይቻላል። እናቴ በቂ ገንዘብ ትልክ የነበረ ቢሆንም እንኳ ትምህርት ቤት እንድገባ ከተፈቀደልኝ በኋላ ምሳ ተሰጥቶኝ እንዲሁም የረባ ልብስ ተገዝቶልኝ አያውቅም ነበር። ከእኔ ትንሽ የሚያንሱት ሁለቱ የአክስቴ ልጆች ሁሉም ነገር ሲሟላላቸው እኔ ግን ከውስጥ የሚለበሱ ልብሶች ቅያሪ እንኳ አልነበረኝም።” ሱዛን ይህን የተናገረችው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ እንደምትፈልግ አክስቷ ስትሰማ ችግሩ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ለማድረግ ብላ ነው።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ያወቀችው እንዴት ነው?
ሱዛን እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ወንድም ጀንሪክ፣ ሎራ ከተባለች አንዲት የበሰለች ክርስቲያን እህት ጋር
አስተዋወቀኝ። ይህች እህት ብዙውን ጊዜ ወደ ልብስ ማጠቢያ ቤት እየመጣች ለበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቼ መልስ በመስጠት ረጅም ሰዓት ታሳልፍ ነበር።” ሱዛን እስከዚያ ጊዜ ድረስ ስለ ምንም ነገር የራሷን ውሳኔ አድርጋ እንደማታውቅ ተናግራለች። ይሁን እንጂ ከእህት ጋር ከተወያየችና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት እንደሚሉት ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ካነበበች በኋላ የራሷን ውሳኔ አደረገች።ሱዛን ቀጥላ እንዲህ ብላለች:- “ዕለቱ አርብ ነበር፤ ማታ ላይ፣ ለአክስቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እየተወያየሁ መሆኑን ነገርኳት። ከዚያም እንቅልፍ እንዳልተኛ ሌሊቱን ሙሉ ኩሽናው መሃል እንድቆም አደረገችኝ። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የቆረጥኩት በዚህ ጊዜ ነበር።”
ወንድም ጀንሪክ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሱዛን መጽሐፍ ቅዱስን እንድትረዳ የሚያስችሏትን ጽሑፎች ያመጣላት ጀመር። “የ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም። ምክንያቱም መጽሐፉ ጀርመን ውስጥ በናዚ ግዛት ሥር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ሆነ ከዚያ በፊት የደረሰባቸውን ስደት እንዴት እንደተቋቋሙ ይናገራል። . . . የመንግሥቱን መዝሙሮች መለማመድ እንድችል መዝሙሮቹን በቴፕ እንዲቀዳልኝ የጉባኤ ሽማግሌውን የጠየቅሁት በዚህ ወቅት ነበር። ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ ‘በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ’ (እንግሊዝኛ) በተባለው በ1966 በተዘጋጀው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን 119 መዝሙሮች በቅደም ተከተል መዘመር ችዬ ነበር።”
“ወንድም ጀንሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች፣ ድራማዎችና የትልልቅ ስብሰባ ፕሮግራሞች የተቀዱባቸውን የቴፕ ክሮችም ያመጣልኝ ነበር። ካሴቶቹን የሚያስቀምጥልኝ ሩት-10 በተባለ መንገድ ላይ በሚገኝ የስልክ እንጨት አጠገብ ሲሆን እኔም እዚያ ሄጄ እወስዳቸዋለሁ። . . . አሁን ግን ሁኔታዬ ያስጨንቀኝ ጀመር። ምክንያቱም ስብሰባ ላይ አንድ ጊዜ እንኳ ሳልገኝ የቻልኩትን ያህል መንፈሳዊ እድገት አድርጌያለሁ። ከዚህ በኋላ ግን በትግሉ ለመቀጠል የሚያስችል አቅም እንደማይኖረኝ ተሰማኝ።”
ሱዛን ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በጣም ከባድ እንደነበሩ ተናግራለች። ከምታውቃቸው ከሁለቱ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጣለች። ከዚያ በኋላ “ሁሉንም መዝሙሮች ማወቄ እረፍት ይነሳኝ ጀመር” ስትል ተናግራለች። ለምን? “ምክንያቱም ‘የያህ ወታደሮች አይዘናጉም’ እንደሚሉት ያሉ ስንኞች ትዝ ይሉኝ ነበር። እነዚህን ቃላት የጻፈው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስሮ የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ማወቄ ደግሞ ይበልጥ ረበሸኝ። ፈሪ እንደሆንኩ የተሰማኝ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ትቶኛል ብዬ አሰብኩ” ብላለች። *
በመጨረሻ ነፃ ወጣች
“በሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ነገር የተከሰተው በ18ኛው ዓመት የልደት ቀኔ ነበር። ቤታችን ‘የይሖዋ ምሥክሮችን እንደማይፈልጉ’ ከተናገሩት ዝርዝር ውስጥ ስለገባ የይሖዋ ምሥክሮች ለዓመታት መጥተው አያውቁም ነበር። ይሁን እንጂ ሌላ ጉባኤ የምትካፈል አንዲት ሴት ያን ቀን ቤታችን መጣች። ቤት ውስጥ ከእኔ በስተቀር ማንም ስላልነበረ አነጋገርኳት። ከዚያ በፊት ቅዳሜ ዕለት ብቻዬን የነበርኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። ይህ አጋጣሚ ይሖዋ እንዳልተወኝ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ተሰማኝ። ስለዚህ መጀመሪያ ወደተዋወቅኩት ወደ ወንድም ጀንሪክ ስልክ ደወልኩና ከቤት ለመውጣት ዝግጁ እንደሆንኩ አጫወትኩት፤ ይህን በተመለከተ የሚለግሰኝ ሐሳብ እንዳለ ጠየቅኩት። በመጨረሻም ከቤት መውጣት የሚያስችለኝን እርዳታ አገኘሁ።”
ሱዛን በሚያዝያ ወር 1977 ወደ ሌላ አካባቢ ተዛወረች። ደብዳቤዋ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “በቀጣዩ ዓመት በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎችም ይሁን በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የቻልኩ ከመሆኑም ሌላ በመስክ አገልግሎትም መካፈል ጀመርኩ። እናቴንም እንደገና አገኘኋት። በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ምን ያህል በደል ሲፈጸምብኝ እንደቆየ አታውቅም ነበር። ስለዚህ ሁኔታዎቹ በጣም አስደነገጧት። ወዲያውኑ የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ አሟላችልኝ። እማማ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ አላስካ ተዛውራ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት እንዳላት ስገነዘብ በ1978 ከእርሷ ጋር ለመኖር ወደ አላስካ ሄድኩ። እናቴ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነች ሲሆን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ ታማኝነቷን ጠብቃ ኖራለች።”
“በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርኩ በኋላ ወንድም ጀንሪክ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች
ዋና መሥሪያ ቤት በቡድን ለመጎብኘት ዝግጅት አድርጎ ስለነበር እኔም አብሬያቸው እንድሄድ ጋበዘኝ። ይህም እስከዛሬ ካገኘኋቸው ዘላቂ ጥቅም ካላቸው ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም ጉብኝቱ ለይሖዋ ድርጅት የዕድሜ ልክ አድናቆት አሳድሮብኛል። ታሪኬ ይኸው ነው። በአጭሩ የጻፍኩት ቶሎ መጨረስ ስለፈለግኩ ነው።”ከላይ የሰፈሩት ሐሳቦች ጥቅጥቅ ተደርጎ ከተጻፈ ስድስት ገጽ ተኩል ደብዳቤ ላይ ተቀንጭበው የተወሰዱ ናቸው። ሱዛን በደብዳቤዋ መጨረሻ ላይ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ባለፈው ወር በጣም አሞኝ ሆስፒታል የገባሁ ጊዜ መሞቴ እንደማይቀር ተሰምቶኝ ነበር። . . . በጥሩ ጤንነት የማሳልፋቸው ሁለት ሳምንታት ብቻ እንኳ እንዲኖሩኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ምክንያቱም አንዳንድ ነገሮችን መልክ ባስይዝ ደስ ይለኝ ነበር። . . . ከዚህ በኋላ ረጅም ጊዜ እኖራለሁ ብዬ አላስብም። ይሁንና በእውነት ውስጥ የቆየሁባቸው እነዚህ ዓመታት ማንም ሊገምተው ከሚችለው በላይ አስደሳች እንደነበሩ ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም።”
ደብዳቤው፣ የመደምደሚያ ቃላትም ሆነ የጸሐፊዋ ፊርማ የሌለው ከመሆኑም በላይ ለማንም አልተላከም። ደብዳቤውን ያገኙት ሰዎች ለማን መስጠት እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸው ነበር። ይሁንና ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በመጨረሻ ወደ ሱዛን እናት ተላከ።
የሱዛን ተጨማሪ ታሪክ
ሱዛን ሚያዝያ 14, 1979 ከተጠመቀች በኋላ እናቷ ወደ ፍሎሪዳ ተመለሰች። ሱዛን ግን ከኖርዝ ፖል ጉባኤ አባላት ጋር በጣም ተግባብታ ስለነበር አላስካ ለመቆየት ወሰነች። ብዙም ሳትቆይ አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ወደ ፍሎሪዳ የተዛወረች ሲሆን በ1991 እንደ እርሷ በአቅኚነት የሚያገለግል የጉባኤ ሽማግሌ አገባች። ባለቤቷም እርሷ ከሞተች ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሞት አንቀላፍቷል።
ሱዛንና ባለቤቷ በጣም ተወዳጅ ባልና ሚስት ነበሩ። የሱዛን በሽታ የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ እስካስገደዳቸው ጊዜ ድረስ በአቅኚነታቸው ቀጥለው ነበር። ሱዛን በጠቅላላው ከ20 ዓመት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍላለች። በፍሎሪዳ የቀረበው የቀብር ንግግር አላስካ ለሚገኘው ኖርዝ ፖል ጉባኤ በስልክ ተላልፎ ነበር።
የሱዛን ደብዳቤ፣ ግሩም የሆነው የትንሣኤ ተስፋ ያላቸው የይሖዋ አገልጋዮች በአሁኑ ጊዜ ለሚያገኟቸው መንፈሳዊ በረከቶች ያለን አድናቆት እንዲጨምር ይረዳናል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) በተጨማሪም ይህ የሕይወት ታሪክ፣ አምላክ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ ቅርብ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል!—ያዕቆብ 4:7, 8
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 ወንድም ጀንሪክ እና ባለቤቱ በ1993 በደረሰባቸው አሳዛኝ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል።
^ አን.6 የታኅሣሥ 22, 1999 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 7ን ተመልከት።
^ አን.13 ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ፣ መዝሙር ቁጥር 11 (29)፣ “እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘በእውነት ውስጥ የቆየሁባቸው እነዚህ ዓመታት ማንም ሊገምተው ከሚችለው በላይ አስደሳች ነበሩ’
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሱዛን የአሥር ዓመት ልጅ ሳለች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሱዛን ከባለቤቷ ከጄምስ ሲይሞር ጋር