ኮብላይ ልጅ ነበርኩ
ኮብላይ ልጅ ነበርኩ
ሜሮስ ዊልያም ሰንዴይ እንደተናገረው
ከሕፃንነቴ ጀምሮ ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርብኝ የሚያደርግ ትምህርት የቀሰምኩ ቢሆንም 18 ዓመት ሲሞላኝ ዓመጸኛ ልጅ ሆኜ ከቤት ወጣሁ። ለ13 ዓመታት ኢየሱስ በአንድ ምሳሌው ላይ ከጠቀሰው ኮብላይ ልጅ ጋር የሚመሳሰል ሕይወት መርቻለሁ። (ሉቃስ 15:11-24) የአደገኛ ዕፅ ነጋዴ ከመሆኔም በላይ ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ የተበላሸ ነበር ማለት ይቻላል። እስቲ አኗኗሬን እንድለውጥና እንድመለስ ያደረገኝን ነገር ልንገራችሁ።
የተወለድኩት በ1956 ሲሆን ክርስቲያን ወላጆቼ ካፈሯቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል ሁለተኛ ነኝ። ቤተሰባችን በደቡባዊ ምዕራብ ናይጄሪያ በምትገኝ ኢሌሻ በምትባል ከተማ ይኖር ነበር። አባቴ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ሆኖ ያደገ ቢሆንም በ1945 አጎቱ ዘ ሃርፕ ኦፍ ጎድ * (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠው። መጽሐፉን አንብቦ ከጨረሰ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን አፈላልጎ አገኘና ከእነርሱ ጋር መሰብሰብ ጀመረ። እርሱ በ1946 ሲጠመቅ እናቴ ደግሞ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች።
በልጅነቴ ይሖዋ ለእኔ ምን ያህል እውን እንደነበረ እንዲሁም ከወላጆቼ ጋር በስብከቱ ሥራ እንዴት በቅንዓት እካፈል እንደነበር አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። አባቴ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ነበር። በእኛ አካባቢ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል የነበረው ወንድም ባለቤት የሆነችው አሊስ ኦባራም አልፎ አልፎ ታስጠናኝ ነበር። የወላጆቼ ምኞት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንድሆን ነበር። ይሁን እንጂ እማማ በመጀመሪያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ባጠናቅቅ የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ አቀረበች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጀመርኩ ማለትም የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አክብሮት ከሌላቸው ልጆች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። ይህ እንዴት ያለ የሞኝነት ድርጊት ነበር! ብዙም ሳይቆይ ማጨስ እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸም ጀመርኩ። ይህ አኗኗሬ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከተማርኩት ነገር ጋር የማይስማማ መሆኑን በመገንዘቤ በስብሰባዎች ላይ መገኘትም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል አቆምኩ። በዚህ ወቅት ወላጆቼ በሁኔታው በጣም አዝነው ነበር፤ ይሁን እንጂ እኔ ለሌሎች ስሜት ደንታ አልነበረኝም።
ከቤት ወጣሁ
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ዓመት ብቻ ከተማርኩ በኋላ የወላጆቼን ቤት ለቅቄ በመውጣት ከሠፈር ልጆች ጋር መኖር ጀመርኩ። አንዳንዴ ማንም እንዳያየኝ ተጠንቅቄ ወደ ቤት እገባና ያገኘሁትን ምግብ ይዤ ቶሎ ከአካባቢው እሰወራለሁ። አባቴ በጣም ከመጨነቁ የተነሳ ምናልባት ይለወጥ ይሆናል ብሎ በማሰብ ለትምህርት ቤት መክፈሉን አቆመ።
ይሁን እንጂ በዚሁ ወቅት አካባቢ ነጻ የትምህርት እድል አገኘሁ። ወጪዎቼን የሚሸፍንልኝ ግለሰብ የትምህርት ቤት ክፍያዬን ይሸፍንልኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ጊዜ ገንዘብና የተለያዩ ስጦታዎች ከስኮትላንድ ይልክልኝ ነበር። በዚህን ወቅት ሁለት ወንድሞቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰባቸውን አቆሙ፤ ይህ ሁሉ ለወላጆቻችን ከባድ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። እናቴ እያለቀሰች ብዙ ጊዜ ትማጸነኝ ነበር። ምንም እንኳ በወቅቱ ሁኔታው የሚሰማኝ ቢሆንም አኗኗሬን ግን አልለወጥኩም።
በትልልቅ ከተሞች ውስጥ
በ1977 ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ሌጎስ በመሄድ ሥራ ያዝኩ። ብዙም ሳይቆይ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ አገኘሁና
ታክሲ ገዛሁ። ይህም ብዙ ገንዘብ እንዲኖረኝ ስላስቻለኝ አደገኛ ዕፆችን መውሰድ እንዲሁም አብዛኛውን ጊዜዬን በምሽት የጭፈራ ቤቶችና በሴተኛ አዳሪ ቤቶች ማሳለፍ ጀመርኩ። ሌጎስ መኖር አሰልቺ ስለሆነብኝ በ1981 ወደ ለንደን ሄድኩ። ቀጥሎም ወደ ቤልጅየም ያቀናሁ ሲሆን እዚያም በቀን ለተወሰነ ሰዓት በምግብ ቤት ውስጥ እየሠራሁ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማርኩ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው መኪናዎችንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ወደ ናይጄሪያ በመላክ ነበር።አባቴ የይሖዋ ምሥክሮች ፈልገው እንዲያገኙኝና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያስጀምሩኝ በቤልጅየም ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። እኔ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ ሲመጡ እነርሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበርኩም። እንዲያውም ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ፤ በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ካበቃ በኋላ እንበላ፣ እንጠጣና የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች እንጫወት ነበር።
አደገኛ ዕፅ በመነገድ ያሳለፍኩት ሕይወት
በ1982 በጣም ውድ የሆነች የቅንጦት መኪና ወደ ናይጄሪያ ላክሁና የጉምሩክ ፎርማሊቲውን አሟልቼ መኪናዋን ለማውጣት ወደብ ድረስ ሄድኩ። የናይጄሪያ ጉምሩክ፣ የያዝኩት ሰነድ በሙሉ የሐሰት መሆኑን ስለደረሰበት ተይዤ ለ40 ቀናት ያህል በእስር ቤት ውስጥ ቆየሁ። ይሁን እንጂ አባቴ ገንዘብ አስይዞ አስፈታኝ። የፍርድ ቤቱን ጉዳይ ለመጨረስ ገንዘብ ያስፈልገኝ ስለነበር ብዙ ኪሎ ግራም የሚመዝን ማሪዋና እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ይዤ ወደ ቤልጅየም ተመለስኩ። በሐሰት ሰነዱ ምክንያት ከነበረብኝ ክስ ነጻ ከሆንኩ በኋላ የአደገኛ ዕፅ ንግድ ጀመርኩ።
በአንድ ወቅት ለንግድ ስንቀሳቀስ ኔዘርላንድ ውስጥ ተያዝኩ። ከዚያም የኢሚግሬሽን ባለ ሥልጣናት ወደ ናይጄሪያ በሚሄድ አውሮፕላን አሳፍረው ከአገር አስወጡኝ። በጉዞ ላይ እያለሁ ከሌሎች የአደገኛ ዕፅ ነጋዴዎች ጋር ተገናኘሁና አንድ ላይ ለመስራት ተስማማን። ጥር 1984 ወደ አንድ ሌላ የአፍሪካ አገር አመራሁ። አብዛኛው የአገሪቱ ነዋሪ የሚናገረውን የፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገር ስለምችል ከፖሊሶች፣ ከወታደሮች እንዲሁም ከኢሚግሬሽን ባለ ሥልጣናት ጋር በጥቂት ጊዜ ውስጥ መግባባት ቻልኩ። ከዚያም በሺህ ኪሎ ግራም የሚገመት ማሪዋና ወደዚያች አገር ማስገባት ቻልን።
ተይዤ ታሰርኩ
አሁንም እንደገና ችግር ውስጥ ገባሁ። ሸቀጦቼን እንዲያሳልፍልኝ ተነጋግረን የነበረ አንድ ወታደራዊ ባለ ሥልጣን ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ዘግይቶ በመድረሱ ተይዤ ታሰርኩ። ፖሊሶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ክፉኛ ስለደበደቡኝና ስለገረፉኝ ራሴን ሳትኩ። በኋላም ሆስፒታል የወሰዱኝ ቢሆንም ይሞታል ብለው አስበው ስለነበር ትተውኝ ሄዱ። ምንም እንኳ ከሞት ብተርፍም ከሆስፒታል እንደወጣሁ ክስ ተመሠረተብኝና ጥፋተኛ ሆኜ በመገኘቴ ወደ ወኅኒ ወረድሁ።
ከጊዜ በኋላ ከእስር ቤት ስለቀቅ ቤቴን እንዲጠብቅልኝ አደራ ሰጥቼው የነበረ አንድ ጓደኛዬ ንብረቶቼን ሁሉ ሸጦ ተሰውሮ ነበር። ኑሮዬን ለማሸነፍ ስል ወዲያውኑ ማሪዋና መሸጥ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ከአሥር ቀን በኋላ እንደገና ተይዤ ለሦስት ወር ተፈረደብኝና ወኅኒ ወረድኩ። ከዚያ ስፈታ በጣም ከመታመሜ የተነሳ ሞት አፋፍ ላይ ደርሼ ነበር። ይሁን እንጂ እንደምንም ወደ ሌጎስ መመለስ ቻልኩ።
ወደ “ሥራ” ተመለስኩ
ሌጎስ እንደደረስኩ አብረውኝ ይሠሩ ከነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጋር ተገናኘሁና ተያይዘን ወደ ሕንድ ሄድን። ከዚያም 600,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ሄሮይን ገዝተን ከቦምቤይ (አሁን ሙምባይ ትባላለች) ወደ ስዊዘርላንድ ቀጥሎም ወደ ፖርቹጋል በመጨረሻም ወደ ስፔን ሄድን። ሁላችንም ከሽያጩ ጠቀም ያለ ትርፍ አግኝተን ወደ ሌጎስ በተለያየ አቅጣጫ ተመለስን። በ1984 መጨረሻ አካባቢ ብዛት ያለው ዕፅ ሸጥኩ። ግብ አድርጌ የነበረው አንድ ሚሊዮን ዶላር ካገኘሁ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ተረጋግቼ ለመኖር ነበር።
በ1986 ያለኝን ገንዘብ በሙሉ ሰብስቤ ከሌጎስ ምንም ነገር ያልተቀላቀለበት ንጹሕ ሄሮይን ገዛሁ። ይህንንም ለመሸጥ ወደ ሌላ አገር ተጓዝኩ፤ ይሁን እንጂ ሄሮይኑ አንድ ስግብግብ የሆነ የአደገኛ ዕፅ ነጋዴ እጅ ገባ። ይህ ሰው ምንም ሳይከፍለኝ ቀረ። እኔም ለሕይወቴ በመፍራት አንዳች ነገር ሳልተነፍስ ወደ ሌጎስ ተመለስኩ። ሁኔታው የገንዘብም ሆነ የስሜት ቀውስ አስከተለብኝ። በዚህ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ቁጭ ብዬ አሰብኩ። ‘ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ ማየት ያስፈለገኝ ለምንድን ነው?’ በማለት ራሴን ጠየቅሁ።
ወደ አምላክ ተመለስኩ
ይህ ከደረሰብኝ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ቀን ምሽት ላይ ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት አንድ አረጋዊ ሰውና ባለቤታቸው የቤቴን በር አንኳኩ። እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በእርጋታ ካዳመጥኳቸው በኋላ መጽሔት ወሰድኩ። ከዚያም “ቤተሰቦቼ
የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ እንዲያውም አሊስ ኦባራ መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ ነበር” ብዬ ነገርኳቸው።ኦግባኔፌ የሚባሉት አረጋዊው ሰው “ወንድም ኦባራንና ባለቤቱን እናውቃቸዋለን፤ እንዲያውም አሁን ሌጎስ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በማገልገል ላይ ናቸው” አሉኝ። በመቀጠልም ኦባራንና ባለቤቱን እንዳገኛቸው አበረታቱኝ። ኦባራና ሚስቱን ካገኘኋቸው በኋላ ከእነርሱ ጋር ያደረግሁት ውይይት ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ወንድም ኦግባኔፌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ካስጀመሩኝ በኋላ በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ሆኖም ለረጅም ጊዜ አደገኛ ዕፅ ስወስድ ስለቆየሁ እንዲህ ማድረጉ ቀላል አልነበረም። ሆኖም አኗኗሬን ለመለወጥና ንጹሕ ሕይወት ለመምራት ቆርጬ ነበር።
ይሁን እንጂ በርካታ የሚያጓጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙኝ እንዲሁም ግፊት ይደረግብኝ ነበር! ጓደኞቼ የነበሩ ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ቤቴ ድረስ በመምጣት ፈታኝ የሆኑ ግብዣዎች ያቀርቡልኝ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት የማጨስ እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና የመፈጸም ችግሬ አገርሽቶብኝ ነበር፤ በዚህ ጊዜ የልቤን ግልጥልጥ አድርጌ ወደ አምላክ ጸለይኩ። መጀመሪያውንም ቢሆን ለዚህ ያበቁኝ የዓለም ወዳጆች በመሆናቸው አሁንም ሊረዱኝ እንደማይችሉ ተገነዘብኩ። በመንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የግድ ሌጎስን መልቀቅ እንደሚኖርብኝ ተረዳሁ። ይሁን እንጂ ኢሌሻ ወደሚገኘው ቤታችን መመለስ አሳፈረኝ። በመጨረሻም ለአባቴ እንዲሁም ለታላቅ ወንድሜ ወደ ቤት መምጣት እንደምፈልግ ገልጬ ደብዳቤ ጻፍኩላቸው።
አባቴ ወደ ቤት ብመለስ ደስ እንደሚለው ሲነግረኝ ታላቅ ወንድሜ ደግሞ በገንዘብ እንደሚረዳኝ ቃል ገባልኝ። ስለዚህ ከቤተሰቤ ተለይቼ ከወጣሁ ከአሥር ዓመት በኋላ ወደ ቤት ተመለስኩ። እነርሱም በደስታ ተቀበሉኝ። እናቴ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ “ይሖዋ አመስግንሃለሁ!” በማለት ተናገረች። አባቴ ያን ቀን ማታ ወደ ቤት ሲመለስ “ይሖዋ ይረዳሃል” በማለት አበረታታኝ። ከዚያም አባቴ መላውን ቤተሰብ ሰብስቦ ባቀረበው ጸሎት ላይ ይሖዋን የእርሱን ፈቃድ ማድረግ እንድችል እንዲረዳኝ ለመነው።
የባከነውን ጊዜ ማካካስ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን የቀጠልኩ ከመሆኑም በላይ ፈጣን እድገት አድርጌ ሚያዝያ 24, 1988 ተጠመቅሁ። ወዲያውኑ በአገልግሎት በትጋት መካፈል ጀመርኩ። ኅዳር 1, 1989 አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆንኩ። በ1995 ናይጄሪያ ውስጥ በሚደረገው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት አሥረኛ ክፍል እንድካፈል ተጋበዝኩ። ከዚያም ሐምሌ 1998 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች እንድጎበኝ ተመደብኩ። ከዓመት በኋላ የትዳርም ሆነ የጉዞ አጋር የሆነችኝን ሩትን በማግኘቴ ተባርኬአለሁ።
ሌሎቹ የቤተሰቦቼ አባላትም ቢሆኑ በመንፈሳዊ እድገት አድርገዋል። ይሖዋን ማገልገሉን አቁሞ የነበረው አንደኛው ወንድሜ ወደ እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ በመጨረሻ ተጠምቋል። አባባ ወደ እውነት ተመልሰን ለማየት መብቃቱ በጣም ያስደስተኛል። በ1993፣ በ75 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በደስታ ያገለግል ነበር። እናቴ በኢሌሻ አሁንም ይሖዋን በቅንዓት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
ሀብት ለማግኘት ስል በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ ወደሚገኙ በጠቅላላው 16 ወደሚያህሉ አገሮች ሄጃለሁ። በዚህም ምክንያት ራሴን በብዙ ሥቃይ ወግቻለሁ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) አደገኛ ዕፅ በመውሰድና በብልግና ኑሮ ያሳለፍኩትን የወጣትነት ዕድሜዬን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በጣም እቆጫለሁ። ይሖዋንም ሆነ ቤተሰቤን ማሳዘኔ በጣም ይሰማኛል። ያም ሆኖ ግን እስካሁን በሕይወት ቆይቼ ወደ አእምሮዬ መመለስ በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ ለመኖር እንዲሁም እርሱን ለዘላለም ለማገልገል ቆርጫለሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓመጸኛ ወጣት በነበርኩበት ወቅት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በተጠመቅሁበት ዕለት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሩት ጋር