በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጣም ከባድ ጥያቄ

በጣም ከባድ ጥያቄ

በጣም ከባድ ጥያቄ

“ለምን?” ይህች አንዲት ቃል በሰዎች ልብ ውስጥ ታምቆ የሚገኘውን ከፍተኛ ሥቃይና ምሬት ልትገልጽ የምትችል መሆኗ በጣም የሚያስገርም ነው። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለምን ብለው የሚጠይቁት የተፈጥሮ አደጋ ወይም አንድ አሳዛኝ ክስተት ከደረሰ በኋላ ነው። ለምሳሌ፣ አውሎ ነፋስ አንድን አካባቢ በመምታቱ እልቂትና ጥፋት ሲደርስ፣ በምድር መንቀጥቀጥ ሳቢያ አንዲት ከተማ ወደ ፍርስራሽነት ስትለወጥ፣ በሽብርተኞች ጥቃት በአንድ ጀምበር ሰላም ጠፍቶ ፍርሃትና ሁከት ሲነግስ ወይም በአደጋ ምክንያት ሰዎች አንድ ወዳጃቸው ጉዳት ሲደርስበት አሊያም ሕይወቱ ሲጠፋ ሲመለከቱ ለምን ብለው ይጠይቃሉ።

አብዛኛውን ጊዜ የአደጋ ሰለባ ከሚሆኑት መካከል ስለ ጉዳዩ ምንም የማያውቁና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎች ይገኙበታል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያሉ በርካታ አደጋዎች ተከስተው የነበረ ሲሆን ብዙዎች “ለምን?” ብለው ወደ አምላክ እንዲጮሁ አድርገዋቸዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት:-

▪ “አምላክ ሆይ ለምን ይህን አመጣህብን? አንተን የሚያስቆጣ ምን ነገር አደረግን?” በሕንድ የሚኖሩ አንዲት አዛውንት ሱናሚ መንደራቸውን ካወደመባቸው በኋላ እንዲህ ብለው እንደጠየቁ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

▪ “አምላክ የት ነበር? ደግሞስ ሁሉን ነገር መቆጣጠር የሚችል ከሆነ እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ?” መሣሪያ የታጠቀ ሰው በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኩስ ከፍቶ በርካታ ምእመናንን ካቆሰለና ከገደለ በኋላ በቴክሳስ ዩ ኤስ ኤ የሚታተም አንድ ጋዜጣ እነዚህን ጥያቄዎች አንስቶ ነበር።

▪ “አምላክ ለምን እንድትሞት ፈቀደ?” አንዲት ሴት ይህን ጥያቄ ያነሳችው ጓደኛዋ በካንሰር ምክንያት አምስት ልጆቿን ባሏ ላይ ጥላ በሞተች ጊዜ ነበር።

ለደረሰባቸው መከራ የአምላክ እጅ ሊኖርበት እንደሚችል የሚሰማቸው ሰዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን በተመለከተ በኢንተርኔት አስተያየት ከሰጡ ሰዎች መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት እንደ አውሎ ነፋስ ያሉ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። ብዙዎች እንዲህ ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?

ሃይማኖት የሚፈጥረው ግራ መጋባት

አብዛኛውን ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች ሰዎች ለሚያነሱት ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ከመስጠት ይልቅ ለሚፈጠረው ግራ መጋባት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። እስቲ ለአደጋዎች መንስኤ ናቸው ብለው ከሚጠቅሷቸው ሐሳቦች መካከል ሦስቱን እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ ብዙ የሃይማኖት መሪዎች አምላክ አደጋዎችን የሚያመጣው ዓመጸኛ ሰዎችን ለመቅጣት ሲል ነው ብለው ይሰብካሉ። ለምሳሌ፣ በዩናይትድ ስቴትስ በሉዊዚያና ግዛት የምትገኘው ኒው ኦርሊየንስ ከተማ ካትሪና በተባለች አውሎ ነፋስ ከተመታች በኋላ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከተማዋን አምላክ እንደቀጣት አድርገው ተናግረዋል። ለዚህ ምክንያት አድርገው የጠቀሱት ደግሞ ሙስና፣ ቁማርና የሥነ ምግባር ርኩሰት እያየለ መሄዱን ነው። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ ክፉዎችን በውኃ ወይም በእሳት ያጠፋበትን አጋጣሚ በማንሳት መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ መጥቀስ ይሆናል።—“በእርግጥ የአምላክ ሥራዎች ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ሁለተኛ:- አንዳንድ ቀሳውስት አምላክ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ያመጣበት የራሱ የሆነ ምክንያት እንደሚኖረው ነገር ግን ምክንያቱ ከእኛ የመረዳት ችሎታ በላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ብዙ ሰዎች ይህ ሐሳብ አይዋጥላቸውም። ‘አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር ሊያመጣ ብሎም መጽናናት ለሚፈልጉና “ለምን” ለሚለው አንገብጋቢ ጥያቄያቸው መልስ ለማግኘት ለሚናፍቁ ሰዎች ምላሽ ሊነፍጋቸው ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ። ደግሞም እውነት አላቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ይናገራል።—1 ዮሐንስ 4:8

ሦስተኛ:- ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ‘ምናልባት አምላክ ኃይል ባይኖረውና አፍቃሪ ባይሆን ነው’ ብለው ያስባሉ። ይህም ቢሆን ከባድ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ የማይቀር ነው። እጅግ ውስብስብ የሆነውን አጽናፈ ዓለም ጨምሮ ‘ሁሉን የፈጠረ’ አምላክ በዚህች አንድ ፕላኔት ላይ ያለውን መከራ ማስቀረት ያቅተዋል? (ራእይ 4:11) የማፍቀር ችሎታ የሰጠን እንዲሁም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ የፍቅር ተምሳሌት አድርጎ የሚገልጸው አምላክ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለው ሥቃይ እንዴት ሳይሰማው ይቀራል?—ዘፍጥረት 1:27፤ 1 ዮሐንስ 4:8

እርግጥ ነው፣ ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ነጥቦች አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ ለሚለውና ለዘመናት እንቆቅልሽ ሆኖ ለኖረው ጥያቄ ሰዎች መልስ ለመስጠት የሞከሩባቸውን አንዳንድ መንገዶች የሚያሳዩ ናቸው። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ለዚህ በጣም አስፈላጊ እንዲሁም ወቅታዊ ለሆነ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ምን መልስ እንደሚሰጥ እናያለን። ወደፊት እንደምትመለከተው መጽሐፍ ቅዱስ አሳማኝና ምክንያታዊ ማብራሪያ በመስጠት የተፈጠረውን ግራ መጋባት ያስወግዳል። ከሁሉም በላይ በሕይወታቸው ውስጥ መከራ ለገጠማቸው ሰዎች ብዙ ማጽናኛ ይሰጣል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በእርግጥ የአምላክ ሥራዎች ናቸው?

በዛሬው ጊዜ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል? በፍጹም! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የምናገኛቸው የአምላክ የፍርድ እርምጃዎች ከተፈጥሮ አደጋዎች በእጅጉ የተለዩ ናቸው። አንደኛ ነገር አምላክ የሚያጠፋው በጅምላ ሳይሆን እየመረጠ ነው። የሰዎችን ልብ ማንበብ ስለሚችል እርምጃ የሚወስደው ጥፋት በሚገባቸው ሰዎች ላይ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 18:23-32) ከዚህም በላይ አምላክ ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ከጥፋቱ መዳን እንዲችሉ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ያስነግራል።

ከዚህ በተለየ መልኩ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱት የተወሰኑ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ብቻ አሳይተው አሊያም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ነው። በተጨማሪም እገሌ ከእገሌ ሳይሉ ይገድላሉ ወይም አካል ጉዳተኛ ያደርጋሉ። የሰው ልጆች አካባቢያቸውን በማበላሸት፣ ለመሬት መንቀጥቀጥና ለጎርፍ በተጋለጡ እንዲሁም መጥፎ የአየር ንብረት ባለባቸው ቦታዎች ላይ ቤቶችንና ሕንጻዎችን በመገንባት በተወሰነ መጠንም ቢሆን እነዚህ አደጋዎች የሚያስከትሉት ጥፋት የከፋ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

[ምንጭ]

SENA VIDANAGAMA/AFP/Getty Images

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሃይማኖት መሪዎች ግራ የሚያጋቡ የተለያዩ መልሶችን ይሰጣሉ