ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
የንቁ! መጽሔት አዲስ አቀራረብ የጥር 2006 ንቁ! መጽሔትን ትናንት ማታ አንብቤ ጨረስኩ። አዲሱን አቀራረብ በጣም ወድጄዋለሁ! በአሁኑ ሰዓት ንቁ! መጽሔት አንባቢው ይበልጥ እንዲያሰላስል የሚያደርግ ሆኗል። የመጽሔቱ አጠቃላይ ይዘት ይሖዋ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያስችለንን አመራር እየሰጠን መሆኑን እንድገነዘብ አስችሎኛል።
ቢ. ኤን.፣ ካናዳ
አሥራ ስድስት ዓመቴ ነው። የንቁ! መጽሔት አዳዲስ ገጽታዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረገድ ከፍተኛ እርዳታ ያበረክቱልናል። አንዳንዶቹ ርዕሶች አንባቢው ባነበበው ነገር ላይ እንዲያሰላስል የሚረዱትን ጥያቄዎች ይዘዋል። ንቁ! መጽሔትን በትምህርት ቤት የሚሰጡንን የቤት ሥራዎች ለመሥራት እጠቀምበታለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ግሩምና ጠቃሚ የሆነ መረጃ ማቅረባችሁን እንደምትቀጥሉ ተስፋ አደርጋለሁ።
ኤስ. ኤን.፣ ናሚቢያ
እምነቴ የያዘኝን ከባድ በሽታ እንድቋቋም ረድቶኛል (ጥር 2006) የጄሰን ስቱዋርትን ተሞክሮ ካነበብኩ በኋላ ያሉብኝ ችግሮች ሁሉ እዚህ ግባ የሚባሉ እንዳልሆኑ ተሰማኝ። ይሖዋ እንደየሁኔታችን የምናቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ተገንዝቤያለሁ። የጄሰን ባለቤት ያሳየችው የራስን ፍላጎት መሥዕዋት የማድረግና በይሖዋ ላይ የመታመን መንፈስ እጅግ አስደንቆኛል። ይህ ተሞክሮ ምንጊዜም ከልቤ አይጠፋም እንዲሁም ወደፊት ሊገጥሙኝ የሚችሉ ችግሮችን ለመወጣት ይረዳኛል።
ሲ. አር. ኤስ.፣ ፔሩ
የጄሰንን ታሪክ ካነበብኩ በኋላ አለቀስኩ። ያለቀስኩት በደረሰበት ችግር ልቤ ስለተነካ ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን እንዲህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ወንድም በማግኘቴ ኩራት ስለተሰማኝ ጭምር ነው። ይህ ተሞክሮ ማናችንም ብንሆን “ጊዜና አጋጣሚ” ምን እንደሚያመጣብን ማወቅ ስለማንችል ሊገጥመን ለሚችለው መከራ ከወዲሁ ራሳችንን ማዘጋጀታችን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቦኛል።—መክብብ 9:11 NW
ቲ. ኤ.፣ ሃንጋሪ
እናቴ የሞተችው በኤ ኤል ኤስ በሽታ ነው። በመሆኑም የጄሰን ተሞክሮ ልቤን ነክቶታል። የእሱ ምሳሌነት በአገልግሎት አቅሜ የፈቀደውን ያህል እንድካፈል አበረታቶኛል። ይሖዋ ለዚህ ወንድምም ሆነ ለባለቤቱ ጥንካሬ መስጠቱን እንዲቀጥል እጸልያለሁ።
ኤል. ዜድ. ጂ.፣ ፓራጓይ
ጄሰን ጤነኛ በነበረበት ወቅት ጥሩ የግል ጥናት በማድረግ በአስፈላጊ ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችለውን መንፈሳዊ ስንቅ አከማችቶ የነበረ መሆኑ እኔም በጉዳዩ ላይ እንዳስብ አድርጎኛል። ይህ እኔም የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ይበልጥ በቅንዓት ለማከናወን ያደረግኩትን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮልኛል።
ዩ. ኤም.፣ ጃፓን
የወጣቶች ጥያቄ—በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምንድን ነው? (ጥር 2006) ከአደንዛዥ ዕጽና ከአልኮል መጠጥ ችግር ጋር የምታገል ወጣት ብሆንም በጣም ከባድ የሆነብኝ ግን በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማድረሴ ጉዳይ ነው። የማያቋርጥ ትግል ማድረግ ቢኖርብኝም እንደነዚህ ያሉት ርዕሰ ትምህርቶች ብርታት ይሰጡኛል። የተሰማኝን አድናቆት ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል።
ኢ. ከ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ከአሥራዎቹ ዕድሜዬ ጀምሮ የገዛ አካልን የመጉዳት ችግር ነበረብኝ። አሁን 56 ዓመቴ ነው። ይህን ልማዴን ከአራት ዓመት በፊት ያቆምኩ ቢሆንም እንኳ አንዳንዴ ያሉብኝ ችግሮች ሲያይሉብኝ የገዛ አካሌን ለመጉዳት እፈልጋለሁ። ይህ ርዕስ ስሜቴን በጥልቅ ነክቶታል። ይህ ርዕሰ ጉዳይ እኔም ሆንኩ እንደ እኔ ያሉ ሌሎች ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚገጥሙንን ችግሮች እንድንጋፈጥ የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።
ስም አልተጠቀሰም፣ ኔዘርላንድ
የ17 ዓመት ወጣት ስሆን ይህን ርዕስ ስላወጣችሁልን ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። እኔም የገዛ አካሌን የመጉዳት ችግር አለብኝ። እንዲያውም በቅርብ ጊዜ በራሴ ላይ ጉዳት አድርሼ ነበር። ከዚያም ወደ እናቴ
ሄድኩና አብራኝ እንድትጸልይ ጠየቅኳት። ይህ ችግር ቢኖርብኝም እንኳ ይሖዋ እንደሚወደኝ ተረድቻለሁ። ያወጣችሁት ርዕሰ ጉዳይ ከፍተኛ እርዳታ አበርክቶልኛል፤ ለዚህ ሁሉ አምላክን አመሰግነዋለሁ!ኤን. ኤም.፣ ቼክ ሪፑብሊክ
“እኔ አላምንም!” ይህን ርዕሰ ትምህርት ስመለከት ያልኩት ይህን ነበር። የ18 ዓመት ወጣት ስሆን የገዛ አካልን የመጉዳት ልማድ ነበረብኝ። ሰውነቴን ስጎዳ የሚሰማኝ ሕመም የውስጥ ስሜቴ ገንፍሎ እንዳይወጣ ይረዳኛል። ብዙውን ጊዜ ራሴን እየጎዳሁ እንዳለ ሆኖ ይሰማኝ የነበረ ቢሆንም እንዲህ ለማድረግ የሚገፋፉኝን ስሜቶች ግን እንዴት መቆጣጠር እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። ይህን ርዕስ መመልከቴ በጣም አስደንቆኛል። ዓይኖቼ እንባ ያቀረሩ ሲሆን ይሖዋንም በጸሎት አመስግኜዋለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ማጽናኛ ማግኘት የሚቻለው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብቻ ነው!
ኤ. ፒ.፣ ሩሲያ
የነበረብኝን የስሜት ሥቃይ ለማስታገስ ስል የገዛ አካሌን መጉዳት የጀመርኩት ገና በ14 ዓመቴ ነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ በዚሁ ምክንያት ሆስፒታል እስከ መሄድ ደርሻለሁ። ያሳለፍኳቸውን ሁኔታዎች በግል ማስታወሻዬ ላይ ማስፈሬ ወደዚህ ችግር የሚመሩኝን ሁኔታዎች ለመቆጣጠር ረድቶኛል። ከዚህ በተጨማሪ ራሴን ለመጉዳት ስፈተን ችግሬን የሚረዳልኝ ሰው እጠራለሁ። በተለይ ደግሞ ጸሎት እጅግ ጠቅሞኛል። ለመጸለይ ብቁ እንዳልሆንኩ ሲሰማኝ ጓደኞቼ ወይም የጉባኤ ሽማግሌዎች አብረውኝ እንዲጸልዩ አደርጋለሁ። ከባድ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ እንዴት ልቋቋመው እንደምችል የተማርኩ ሲሆን የገዛ አካሌን እንዳልጎዳ የሚቀርብልኝን ማንኛውንም እርዳታ እቀበላለሁ።
ኤን. ደብሊው.፣ ጀርመን
በዚህ ርዕስ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ፀጉሯን የምትነጭ አንዲት ወጣት ትታያለች። እንዲሁም በርዕሰ ትምህርቱ ውስጥ “ሤራ” የምትባል ልጅ ራስዋን ለመገሠጽ ስትል ፀጉሯን እንደምትነጭ የሚናገር ሐሳብ ይገኛል። ሴት ልጄ ትሪኮቲሎማኒያ የሚባል ችግር አለባት፤ ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ፀጉራቸውን በኃይል ይነጫሉ። ይህ ደግሞ ኦብሰሲቭ-ኮምፐልሲቭ ከተባለ ችግር ጋር ግንኙነት አለው። እንዲህ ያለ ችግር ያለበት ሰው የገዛ አካሉን የሚጎዳው ፈልጎ ሳይሆን ከቁጥጥሩ ውጪ በሆነ ስሜት ተገፋፍቶ ነው። ፀጉር መንጨት ሆነ ተብሎ የገዛ አካልን ከመቁረጥ ችግር ጋር ግንኙነት የለውም።
ኤም. ኤች.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የንቁ! አዘጋጆች መልስ:- ትሪኮቲሎማኒያ የሚለው ስያሜ የተፈጠረው በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሲሆን አንድ ሰው ፀጉሩን ለመንጨት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርበት የሚያደርገውን የባሕርይ ችግር ያመለክታል። ፎቶ ግራፉ በጥሩ መንገድ እንደሚያሳየው የገዛ አካላቸውን የመጉዳት ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ፀጉራቸውን ይነጫሉ። ይሁን እንጂ ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ፀጉራቸውን የሚነጩ ሰዎች ሁሉ በርዕሰ ትምህርታችን ላይ እንደተጠቀሱት ሰዎች በገዛ ሰውነታቸው ላይ ሆነ ብለው ጉዳት የሚያደርሱ ናቸው ማለት አይደለም። ከላይ የተጠቀሱት አንባቢ እንደጠቆሙት ፀጉርን የመንጨት ችግር አንዳንድ ጊዜ ከአእምሮ ችግር ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል።
ያም ሆነ ይህ አንዳንድ ባለሙያዎች ከችግሩ ጋር ተስማሚ የሆነ ሕክምና ለመስጠት ለትሪኮቲሎማኒያ መነሾ የሆነውን ነገር ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች የግል ምርመራና ተከታታይ ሕክምና ለማግኘት የሕክምና ባለሙያ ጋር ቢሄዱ መልካም ነው።
መልስህ ምንድን ነው? (ጥር 2006) በዚህ አዲስ አቀራረብ በጣም ተደስቻለሁ! የልጅ ልጆቻችንን እቤታችን ውስጥ እያስተማርናቸው እንገኛለን። ይህ አቀራረብ እንደ ቤት ሥራቸው አድርገው ከሚመለከቷቸው የዕለት የመጽሐፍ ቅዱስና የንቁ! መጽሔት ንባባቸው ባሻገር ተጨማሪ መማሪያ ሆኖላቸዋል። ለወጣቶች ስለምታሳዩት ጥልቅ አሳቢነት እናመሰግናችኋለን።
ቢ. ኢ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ይህ አዲስ ገጽታ ከበድ ቢልም አንድ መልስ ባገኘሁ ቁጥር እጅግ እደሰታለሁ! ትናንት ማታ ምሽቱን በሙሉ ያሳለፍኩት ይህን ገጽ በማንበብ ነበር። በጣም አስደሳች ነው! ትልቅ ስሆን ሌሎች ስለ ይሖዋ መማር እንዲችሉ ለመርዳት ሲባል በሚዘጋጀው በዚህ መጽሔት ሥራ ላይ ለመካፈል እፈልጋለሁ!
ዲ. ኤች.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የስምንት ዓመት ልጅ ነኝ። ይህን ዓምድ በቤተሰብ ጥናታችን ላይ እንወያይበታለን። ከዚህ ዓምድ ጋር በተያያዘ የምናደርገው ምርምር ያስደስተናል። “እኔ ማን ነኝ?” የሚለው ክፍል ከበድ ያለ ቢሆንም መልሱን ለማግኘት የምናደርገው ጥረት በራሱ አስደሳች ነው። በዚሁ ግፉበት።
ኬ. ደብሊው.፣ ዩናይትድ ስቴትስ