ከመኪና ጠላፊዎች ራሳችሁን ጠብቁ!
ከመኪና ጠላፊዎች ራሳችሁን ጠብቁ!
ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
የመኪና ጠለፋ ከካራቺ እስከ ሊዝበን እንዲሁም ከናይሮቢ እስከ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ድረስ ባሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ችግር ነው። የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ቢሮ ይፋ ያደረገው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ1993 እስከ 2002 በነበሩት ዓመታት መካከል በዚያች አገር ብቻ በየዓመቱ 38,000 የመኪና ጠለፋ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
የዩናይትድ ስቴትስን አንድ ስድስተኛ የሚሆን የሕዝብ ብዛት ባላት በደቡብ አፍሪካ ከዚህ የበለጠ የመኪና ጠለፋ ወንጀል ይፈጸማል፤ በዚህች አገር በየዓመቱ ከ14,000 በላይ መኪኖች ይጠለፋሉ። ጥቂት ምሳሌዎችን ከተመለከትክ በኋላ ብዙዎች የመኪና ጠለፋን እጅግ አስፈሪ ከሆኑት ወንጀሎች መካከል የሚፈርጁት ለምን እንደሆነ ግልጽ ይሆንልሃል። ከዚህ ቀጥሎ የደቡብ አፍሪካ ትልቁ ከተማ በሆነው በጆሃንስበርግ በሚኖሩ ግለሰቦች ላይ የደረሱ እውነተኛ ተሞክሮዎች ቀርበዋል። አንተም ተሞክሯቸውን ማንበብህ መኪናህ ቢጠለፍ ምን እንደምታደርግ ወይም ከሁሉ የተሻለውን ነገር ማለትም የዚህ ወንጀል ሰለባ የመሆንን አጋጣሚ እንዴት መቀነስ እንደምትችል ለማወቅ ይረዳህ ይሆናል።
እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎች
▪ “እኔና ሱዛን የተባለችው ጓደኛዬ ለአንድ ዓመት ያህል በወንጌላዊነቱ ሥራ አብረን ስንካፈል ቆይተናል። አንድ ረቡዕ ዕለት፣ ወደሚቀጥለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ከመሄዳችን በፊት ሻይ ለመጠጣት አሰብንና በአንድ የመኖሪያ ሰፈር ውስጥ በሚገኝ ዛፍ ሥር መኪናችንን አቆምን። ከዚያም ሱዛን ዕቃውን ከመኪናው ኋላ ለማውጣት ወረደች። ሱዛን ገና ስኒውን እየሰጠችኝ እያለ ከየት መጡ ሳይባል ሁለት ሰዎች ብቅ አሉና አንደኛው በሱዛን አንገት ላይ ሽጉጥ ደገነባት። በጣም ደንግጬ ከመኪናው ለመውረድ ስሞክር ሌላው ሰውዬ ገፍትሮ ወደ ውስጥ አስገባኝ። በዚህ ዓይነት አስገድደው ካስገቡን በኋላ መኪናዋን እያሽከረከሩ ይዘውን መሄድ ጀመሩ። ሊደፍሩን ወይም ሊገድሉን እንደሆነ አልተጠራጠርኩም ነበር።”—ወጣት ባለትዳር የሆነችው አኒካ
▪ “ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ በመኪና ወደ ሥራ እየሄድኩ ነበር። ሥራ የሚፈልጉ ሰዎች በሚበዙበት አካባቢ በሚገኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆም አልኩ። አንድ ሰው በተከፈተው መስኮት በኩል ያስገባውን ሽጉጥ አንገቴ ላይ ደግኖ “ውጣ፣ አለዚያ እተኩስብሃለሁ” እስኪለኝ ድረስ በአካባቢዬ ያለውን ሁኔታ ምንም አላስተዋልኩም ነበር። በዚያችው ቅጽበት የትራፊክ ሄሊኮፕተር ከበላያችን ያንዣብብ ጀመር። መኪናዬን ሊሰርቅ ያሰበው ሰውም የፖሊስ ሄሊኮፕተር ስለመሰለው ሽጉጡን ተኩሶብኝ ሮጠ። ጥይቱ አንገቴ ላይ ስለመታኝ አከርካሪዬ ተቆረጠ። ይህም ከአንገቴ በታች ሙሉ በሙሉ ሽባ አድርጎ አስቀረኝ። በእጆቼና በእግሮቼ መጠቀም የማልችል ከመሆኑም በላይ ሰውነቴ ስለደነዘዘ ምንም አይሰማኝም።”—በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ወንድ ልጅ ያለው ባሪ
▪ “እኔና ባለቤቴ ሊንዚ ወጣ ብለን ምሳ ለመብላት ስላሰብን እስክትመጣ ድረስ መኪናዬ ውስጥ ሆኜ እየጠበቅኳት ነበር። የመኪናው በሮች ቢቆለፉም መስኮቶቹ ግን ሙቀት ስለሆነ በትንሹ ተከፍተዋል። ከተቀመጥኩበት ሆኜ ሁለት ሰዎች ከመንገዱ ዳር ታጥፈው ዘና ባለ አካሄድ ሲመጡ እያየኋቸው ነበር። ከመኪናው ፊት ስምንት እርምጃ የሚያህል ርቀት ላይ ሲደርሱ ተነጣጠሉና አንዱ ከመኪናው በስተግራ ሌላው ደግሞ በስተቀኝ በኩል መሄድ ጀመሩ። በድንገት በሁለቱም አቅጣጫ በመኪናው በሮች በኩል ቆሙና ሁለቱም ሽጉጥ ደግነውብኝ በጩኸት ትእዛዝ ይሰጡኝ ጀመር። ባዘዙኝ መሠረት መኪናውን ካስነሳሁ በኋላ ከመኪናው ወጥቼ የኋላ ወንበር ላይ እንድቀመጥ በቁጣ ነገሩኝ። አንዱ መኪናውን ሲነዳ ሌላው ደግሞ አንገቴን አቀርቅሬ እንድቀመጥ አስገደደኝ። ከዚያም ‘እንዳልገድልህ የሚያደርግ ምን ምክንያት ልትሰጠኝ ትችላለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። ‘የይሖዋ ምሥክር ነኝ’ ብዬ መለስኩለት። እየደጋገመ እንደሚገድለኝ ይናገር ነበር፤ እኔም መጸለዬን አላቋረጥኩም። ውዷ ባለቤቴ ባሏና መኪናው መሰወራቸውን ስትመለከት ምን ልታደርግ እንደምትችል አስብ ነበር።”—አባትና ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነው አላን
እነዚህ ተሞክሮዎች የመኪና ጠለፋ ምንም ሳናስበው በፍጥነት ሊፈጸም እንደሚችል ያሳያሉ። የመኪና ጠላፊዎቹ የሚጠቀሙባቸውን የተለመዱ ሁኔታዎችም ይጠቁማሉ። በብዙ ቦታዎች በመኖሪያ አካባቢዎች ባሉ መንገዶች ላይ በቆሙ መኪናዎች ውስጥ ሆኖ ሰው መጠበቅ ወይም ዘና ማለት ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ሌሎቹ አደገኛ ቦታዎች ደግሞ መስቀለኛ መንገዶችና ቤታችሁ አካባቢ የሚገኙት የሠፈር ውስጥ መንገዶች ናቸው።
አደጋው ያስከተለውን መጥፎ ስሜት መቋቋም
ደስ የሚለው ነገር ሱዛንና አኒካ ያጋጠማቸው የመኪና ጠለፋ ሙከራ መጨረሻው ያማረ ነው። ጠላፊዎቹ ሁለቱን ሴቶች በገዛ መኪናቸው እየወሰዷቸው ሳሉ ሴቶቹ ሲያከናውኑ ስለነበረው መጽሐፍ ቅዱስን የማስጠናት ሥራ ለጠላፊዎቹ ይነግሯቸው ጀመር። ይህም ሕሊናቸው እንዲወቅሳቸው ሳያደርግ አልቀረም። አኒካ “ላደረጉት ነገር ይቅርታ ጠየቁ” ትላለች። “ይሁን እንጂ የምንኖርበት ጊዜ አስቸጋሪ በመሆኑ ለመኖር ሲሉ መስረቅና መኪና መጥለፍ ግድ እንደሆነባቸው ተናገሩ። አምላክ ድህነትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ አስረዳናቸው።” ሰዎቹ ልባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ስለተነካ የወሰዱትን ገንዘብና የእጅ ሰዓት መልሰው ለመስጠት ወሰኑ። በተጨማሪም ሱዛንንና አኒካን ምንም ጉዳት እንደማያደርሱባቸው አረጋገጡላቸው። “ከዚያም አንደኛው ጠላፊ ለወደፊቱ መኪናችን እንዳይጠለፍ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይሰጠን ጀመረ” በማለት ሱዛን ትናገራለች። አኒካም በማከል “ከዚህ በኋላ ሻይ ለመጠጣት በመንገድ ዳር መኪና እንዳናቆም ቃል አስገቡን” ብላለች። ከዚያም ጠላፊዎቹ ቃል በገቡት መሠረት በእህቶች ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርሱባቸው መኪናውን አቆሙና ወረዱ፤ ሱዛንና አኒካ የሰጧቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በምስጋና ከተቀበሉ በኋላ እህቶች መኪናቸውን ይዘው በሰላም እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው።
ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነው አላንን ጠላፊዎቹ ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሲደርሱ ከመኪናው እንዲወጣ አዘዙት። 2 ቆሮንቶስ 4:1, 7
አላን ውድ ንብረቶቹን ቢያጣም አካላዊ ጉዳት ስላላደረሱበት በጣም አመስጋኝ ነው። ሁኔታውን አስታውሶ ሲናገር “ምንም ጉዳት ሳይደርስብኝ በቀላሉ ልገላገል የቻልኩት ተባባሪ ስለሆንኩላቸውና ኃይለ ቃል ስላልተናገርኩ እንዲሁም ስላልተደናገጥኩ ይመስለኛል። ሆኖም መጀመሪያ ላይ ዙሪያዬን ይበልጥ ማስተዋል እችል ነበር። ዛሬ የምንኖረው የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ይበልጡን ወደ መጨረሻው በተቃረበበት ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ንቁ ከመሆን ወደኋላ ማለት እንደሌለብን ከዚህ ገጠመኝ ተምሬያለሁ” ይላል። አላንና ሊንዚ በቀጣዩ ቀን ከተመደቡበት ጉባኤ ጋር ሆነው አገልግሎታቸውን ለመቀጠል ወደዚያው ቦታ ተመልሰው ሄደው ነበር። አላን እንዲህ ብሏል:- “ጸለይን፤ ደግሞም ቀኑን ሙሉ ዙሪያችንን በንቃት እንመለከት ነበር። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም ይሖዋ ‘እጅግ ታላቅ ኀይል’ ሰጥቶናል።”—በመኪና ጠላፊዎች የከፋ ጉዳት የደረሰበት ባሪ መንቀሳቀስ የማይችል በመሆኑ ላለፉት 11 ዓመታት በተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም ተገዷል። ደግነቱ ባሪ አዎንታዊ አመለካከቱን እንደያዘ የቀጠለ ሲሆን የደረሰበት በደል እንዲመረር አላደረገውም። ይሖዋ ቃል የገባው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የማያወላውል እምነት አለው። (2 ጴጥሮስ 3:13) ባሪ አዘውትሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን እምነቱን ለሌሎች ለማካፈል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማል። እንዲህ ይላል:- “ይሖዋን ማገልገል ምንጊዜም ቢሆን ያስደስተኛል። ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስም ሆነ ራሴን መርዳት ባልችልም ይሖዋ ባደረገልኝ ነገሮች ላይ ዘወትር ማሰላሰሌ እንድጸና ረድቶኛል። በቅርቡ ይህ ክፉ ሥርዓት ያከትማል፤ እንደገና በእግሬ መሄድ የምችልበት ቀን ሲመጣ ምንኛ እደሰት ይሆን!”—ኢሳይያስ 35:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
በደቡብ አፍሪካ ባለ ሥልጣናት የወሰዷቸው አንዳንድ እርምጃዎች የመኪና ጠለፋን ለመቀነስ ረድተዋል። ሆኖም የመኪና ጠለፋ አሁንም የቀጠለ ሲሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም የበለጠ እየጨመረ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ወንጀልና ዓመጽ የሚያስቆመውን ብቸኛ መስተዳድር ማለትም የአምላክን መንግሥት በጉጉት ይጠብቃሉ።—መዝሙር 37:9-11፤ ማቴዎስ 6:10
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሊያጋጥማችሁ የሚችልበትን አጋጣሚ ለመቀነስ የሚረዱ ሐሳቦች
▪ የመኪና ጠለፋ በደረሰበት አካባቢ የምትነዳ ከሆነ የመኪናህን በር ቆልፍ፤ መስኮቶቹንም ዝጋ።
▪ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ለማቆም ፍጥነትህን ስትቀንስ በመንገዱ ግራና ቀኝ ወዲያ ወዲህ የሚሉና የሚያጠራጥሩ ሰዎችን በንቃት ተከታተል።
▪ በአንተና ከፊትህ በቆመው መኪና መካከል መጠነኛ ርቀት እንዲኖር ማድረጉ ከአደጋ ለማምለጥ ብትፈልግ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ ያስችልሃል።
▪ አንድ መኪና ከኋላህ መጥቶ ገጨት ቢያደርግህ የደረሰውን ጉዳት ለማየት ከመኪና ለመውጣት የምታስብ ከሆነ እንዲህ ከማድረግህ በፊት ሊያጋጥምህ ስለሚችለው አደጋ አስብ። ይህ የመኪና ጠላፊዎች ዘዴ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ያጋጠመህ የመኪና ጠለፋ በተደጋጋሚ በሚደርስበት አካባቢ ከሆነ በአቅራቢው ወዳለው ፖሊስ ጣቢያ መሄዱ ያዋጣል።
▪ በቤትህ መግቢያ አካባቢ ወዲያ ወዲህ የሚዘዋወሩ እንግዳ ሰዎች ካሉ በንቃት ተከታተል። እንዲህ ያለ ሁኔታ መኖሩን ካስተዋልክ ሳትቆም እየነዳህ ማለፍና ወደ ቤትህ በኋላ መመለስ የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ አለዚያም በቅርብ ወዳለው ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ልትወስን ትችላለህ።
▪ አደገኛ በሆነ አካባቢ ወይም ብዙ ሰዎች በሌሉበት ቦታ መኪናህን አቁመህ መቆየት ካለብህ ከፊትህና ከኋላህ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በንቃት ተከታተል። አደጋ መኖሩን ከተጠራጠርክ መኪናህን አስነሳና ወደ ሌላ አካባቢ ሂድ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሪ በተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም ቢገደድም አዎንታዊ አመለካከቱን እንደያዘ ቀጥሏል