ማንን ማመን ይኖርብሃል?
ማንን ማመን ይኖርብሃል?
“እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው።”—ዕብራውያን 3:4
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከገለጸው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አትስማማም? ይህ ጥቅስ ከተጻፈ ወዲህ የሰው ልጅ ሳይንሳዊ እድገት የታየባቸው 2,000 የሚያህሉ ዓመታት አሳልፏል። ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በዚህ ዘመን ‘በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየው የረቀቀ ጥበብ አንድ ንድፍ አውጪ ወይም ፈጣሪ አለ ብለን እንድናምን ግድ ይለናል’ ብሎ የሚያምን ሰው ይኖራል?
በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች እንኳ ሳይቀር አዎ ብለው የሚመልሱ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኒውስዊክ መጽሔት በ2005 ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው 80 በመቶ የሚያህሉ ሰዎች “አምላክ ጽንፈ ዓለሙን እንደፈጠረ ያምናሉ።” እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ እምነት ሊኖራቸው የቻለው በቂ ትምህርት ሳያገኙ በመቅረታቸው ይሆን? እስቲ በአምላክ የሚያምን ሳይንቲስት ይኖር እንደሆነ እንመልከት። ኔቸር የተባለው ሳይንሳዊ መጽሔት በ1997 እንዳመለከተው በአንድ ጥናት ውስጥ ከተካተቱ የባዮሎጂ፣ የፊዚክስና የሒሣብ ሊቃውንት መካከል 40 በመቶ የሚያህሉት አምላክ መኖሩን ብቻ ሳይሆን ይህ አምላክ ጸሎት ሰምቶ መልስ እንደሚሰጥ ጭምር ያምናሉ።
ይሁን እንጂ ይህን አጥብቀው የሚቃወሙ ሌሎች ሳይንቲስቶች አሉ። የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዶክተር ኸርበርት ሃውፕትማን በቅርቡ በአንድ ሳይንሳዊ ስብሰባ ላይ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ታላቅ ኃይል፣ በተለይ ደግሞ በአምላክ ማመን ከትክክለኛ ሳይንስ ጋር ሊጣጣም እንደማይችል ተናግረዋል። አክለውም “እንዲህ ያለው እምነት የሰውን ዘር ደኅንነት በእጅጉ ይጎዳል” ብለዋል። በአምላክ የሚያምኑ ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ በዕፅዋትና በእንስሳት ላይ የሚታየው የረቀቀ ንድፍ በፈጣሪ መኖር እንድናምን ያስገድደናል ብለው ለማስተማር አይደፍሩም። ለምን? በስሚዝሶንያን ተቋም ፓሊዮባዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ዳግላስ ኧርዊን ይህ የሆነበትን አንደኛውን ምክንያት ሲያስረዱ “ከሳይንስ ሕግጋት አንዱ ተአምር በሚባል ነገር አለማመን ነው” ብለዋል።
አንተም ሌሎች በምታስበውና በምታምንበት ነገር ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብህ ልትፈቅድ አሊያም አንዳንድ መረጃዎችን ራስህ በሚገባ መርምረህ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ልትደርስ ትችላለህ። በሚቀጥሉት ገጾች ላይ የሠፈሩትን የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶች በምታነብበት ጊዜ “ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው?” እያልክ ራስህን ጠይቅ።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ማስረጃዎቹን ራስህ መርምር
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የይሖዋ ምሥክሮች ክሪኤሽኒስት ናቸው?
የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ሠፍሮ በሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ከክሪኤሽኒስቶች (የፍጥረት አማኞች) ፈጽሞ የተለዩ ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ብዙ ክሪኤሽኒስቶች ምድርንና በምድር ላይ የሚኖሩትን ሕያዋን ፍጥረታት ጨምሮ መላው ጽንፈ ዓለም የተፈጠረው የዛሬ 10,000 ዓመት ገደማ እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። * በተጨማሪም ክሪኤሽኒስቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ በሌላቸው በርካታ መሠረተ ትምህርቶች ያምናሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ግን ሙሉ በሙሉ የተመሠረቱት በአምላክ ቃል ላይ ነው።
ከዚህም በላይ በአንዳንድ አገሮች “ክሪኤሽኒስት” የሚለው ቃል በፖለቲካ ጉዳዮች በንቃት የሚካፈሉ አክራሪ ቡድኖችን ያመለክታል። እነዚህ ቡድኖች ፖለቲከኞች፣ ዳኞችና የትምህርት ባለሞያዎች ከክሪኤሽኒስቶች ሃይማኖታዊ ሕግጋት ጋር የሚስማሙ ሕጎችንና ትምህርቶችን እንዲከተሉ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ ናቸው። መንግሥት ያለውን ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም መብት ያከብራሉ። (ሮሜ 13:1-7) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ የተናገረውን ቃል አክብደው ይመለከታሉ። (ዮሐንስ 17:14-16) በሕዝባዊ አገልግሎታቸው አማካኝነት ሰዎች የአምላክን ሕግጋት አክብሮ መኖር የሚያስገኘውን ጥቅም የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግጋት እንዲከተሉ የሚያስገድድ መንግሥታዊ ሕግ እንዲወጣ ለሚጥሩ አክራሪ ቡድኖች ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን አያላሉም።—ዮሐንስ 18:36
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.11 እባክህ በዚህ እትም ገጽ 18 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት—ሳይንስ ከዘፍጥረት ዘገባ ጋር ይጋጫል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።