እጅግ ውድ የሆነው ፈሳሽ ምንድን ነው?
እጅግ ውድ የሆነው ፈሳሽ ምንድን ነው?
“ለመጓጓዣ ነዳጅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለጤና እንክብካቤም ደም አስፈላጊ ነው።”—አርተር ካፕለን፣ በፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የባዮኤቲክስ ማእከል ሥራ አስኪያጅ
እጅግ ውድ የሆነው ፈሳሽ ነዳጅ ዘይት እንደሆነ ይሰማሃል? በአሁኑ ጊዜ የነዳጅ ዋጋ በጣም እየጨመረ በመሆኑ ብዙዎች እንዲህ ይሰማቸው ይሆናል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ እያንዳንዳችን ከነዳጅ በእጅጉ የሚበልጥ ዋጋ ያለው ጥቂት ሊትር ፈሳሽ ይዘናል። የሰዎችን የነዳጅ ፍላጎት ለማርካት በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ ከከርሰ ምድር ይወጣል፤ በተመሳሳይም የታመሙ ሰዎችን ለመርዳት ሲባል ወደ 90 ሚሊዮን ዩኒት የሚጠጋ ደም ከሰዎች የሚወሰድ መሆኑን ማወቁ በጣም ያስገርማል። * ይህ የሚያስደነግጥ አኃዝ በድምሩ የ8,000,000 ገደማ ሰዎች ደም ይሆናል።
ሆኖም ልክ እንደ ነዳጅ ዘይት ሁሉ የደምም እጥረት አለ። በዓለም ዙሪያ የሚገኘው የሕክምና ማኅበረሰብ የደም እጥረት እንደሚኖር ያስጠነቅቃል። (“ስጋት የወለደው የመፍትሔ እርምጃ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ደም በጣም ውድ የሆነው በምን ምክንያት ነው?
ልዩ የሆነ የአካል ክፍል
ደም በሚያስደንቅ መንገድ ውስብስብ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ በአንድ የአካል ክፍል ይመሰላል። ዶክተር ብሩስ ሌነስ “ደም ከበርካታ የአካል ክፍሎች መካከል አንዱ ሲሆን እጅግ በጣም አስደናቂና ልዩ የሆነ ነገር ነው” በማለት ለንቁ! መጽሔት ገልጸዋል። በእርግጥም ልዩ ነገር ነው! አንድ የመማሪያ መጽሐፍ ደምን “በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ብቸኛው ፈሳሽ የአካል ክፍል” ሲል ገልጾታል። ይኸው መጽሐፍ ደም “ሕያው የማጓጓዣ ዘዴ” እንደሆነ ዘግቧል። ይህ ምን ማለት ነው?
የደም ዝውውር ሥርዓት ጥሩም ሆኑ ቆሻሻ ነገሮችን ከሚያጓጉዝ ቦይ ጋር ይመሳሰላል። ደም በሰውነታችን ውስጥ 100,000 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ሲሆን በዚህ ጊዜ ደምን የሚያጣሩትንና በትክክል መሥራታቸው በደም ላይ የተመካውን ዋነኞቹን የሰውነት ክፍሎቻችንን ማለትም ልብን፣ ኩላሊትን፣ ጉበትንና ሳምባዎችን ጨምሮ በእያንዳንዱ የአካል ክፍል ውስጥ ያልፋል ለማለት ይቻላል።
ደም እንደ ኦክስጅን፣ አልሚ ምግቦችና በሽታ ተከላካዮች ያሉ ጥሩ ነገሮችን ወደ ሰውነትህ ሕዋሳት ያደርሳል። እንዲሁም ቆሻሻን ከሕዋሳት ውስጥ ያስወግዳል፤ ከእነዚህም መካከል መርዛማ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ የተጎዱ እንዲሁም የሞቱ ሕዋሳትና ሌሎች ቆሻሻዎች ይገኙባቸዋል። ደም ቆሻሻን በማስወገድ ረገድ የሚጫወተው ሚና፣ ከሰውነት ከወጣ በኋላ መነካቱ አደገኛ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ለመገንዘብ ይረዳል። እንዲሁም ለሕመምተኛ ደም ከመሰጠቱ በፊት በውስጡ የሚገኘው ቆሻሻ በሙሉ ተለይቶ ተወግዷል ብሎ ዋስትና መስጠት የሚችል ሰው የለም።
ደም ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮችን እንደሚያከናውን ምንም አያጠያይቅም። ደም ለፈሰሳቸው ሕመምተኞች ደም መስጠት በሕክምናው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውም በዚህ ምክንያት ነው። ብዙ ዶክተሮች ደምን እጅግ ዋጋማ ያደረገው በዚህ መንገድ ለሕክምና መዋሉ እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም በሕክምናው ዓለም ነገሮች እየተለዋወጡ ነው። ቀስ በቀስ አስገራሚ ለውጦች እየተካሄዱ ነው ለማለት ይቻላል። በርካታ ዶክተሮችና የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እንደበፊቱ ደም ለመስጠት አይቸኩሉም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.3 አንድ ዩኒት የሚባለው 450 ሚሊ ሊትር ደም ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ስጋት የወለደው የመፍትሔ እርምጃ
የሕክምና ባለሙያዎች በዓለም ዙሪያ ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ዩኒት ደም በየዓመቱ ሊለገስ እንደሚገባ ይገምታሉ። ሰማንያ ሁለት በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የሚኖረው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ነው፤ ሆኖም በእነዚህ አገሮች የሚለገሰው ደም በጠቅላላ ሰዎች ከሚሰጡት ደም 40 በመቶው እንኳ አይሆንም። በመሆኑም በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሆስፒታሎች ለሕመምተኞች ደም ሳይሰጡ ሕክምና ለማድረግ ወይም በጠቅላላው ሕክምናውን ለመሰረዝ ይገደዳሉ። በኬንያ የሚታተም ዘ ኔሽን የተባለ ጋዜጣ እንደዘገበው ‘ለሕመምተኞች ደም መስጠትን ከሚጠይቁ በየዕለቱ ከሚከናወኑ ሕክምናዎች መካከል ግማሽ ያህሎቹ በደም እጥረት ምክንያት ይሰረዛሉ ወይም ለሌላ ጊዜ ይተላለፋሉ።’
በበለጸጉ አገሮችም ቢሆን የደም እጥረት የተለመደ ችግር ነው። የሰዎች የዕድሜ ጣሪያ ከፍ በማለቱና የሕክምና ዘዴዎች እየተራቀቁ በመምጣታቸው ቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ሕመምተኞች ቁጥር ጨምሯል። በተጨማሪም በደም ሊተላለፉ ለሚችሉ በሽታዎች የሚያጋልጥ ሕይወት የሚመሩ እንዲሁም ለበሽታ ወይም ለጥገኛ ሕዋሳት ወደሚዳርጓቸው ቦታዎች የተጓዙ በርካታ ደም ለጋሾች ተቀባይነት እያጡ ነው።
በዚህም የተነሳ የደም ባንኮች ያለባቸው ስጋት እየጨመረ የመጣ ይመስላል። በአጠቃላይ ሲታይ ብዙም ለክፉ የማይሰጥ የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ወጣቶች ንጹሕ ደም ሊለግሱ ይችላሉ በሚል አንዳንድ ጊዜ ትኩረት ይደረግባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዚምባብዌ 70 በመቶ የሚሆነውን ደም የሚለግሱት ተማሪ የሆኑ ልጆች ናቸው። ደም ለጋሾችን የሚያስተናግዱ ማእከሎች በቀን ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ክፍት ይሆናሉ፤ እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች ያሉ ማእከሎች ለጋሾች ወደፊትም ደም እንዲለግሱ ለማግባባት ገንዘብ ወይም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸዋል። በቼክ ሪፑብሊክ በተደረገ ዘመቻ የአገሪቱ ዜጎች የተወሰነ ደም ለግሰው ቢራ እንዲጠጡ ተጋብዘዋል! በቅርቡ በህንድ አገር በሚገኝ አንድ ቦታ፣ እየተመናመነ ያለውን የደም ክምችት ለማሳደግ ፈቃደኛ የሆኑ ለጋሾችን ለማግኘት ባለ ሥልጣናት ከቤት ወደ ቤት ሄደዋል።