ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የሚገኙትን ወጣቶች መርዳት (ሰኔ 2005) በዚህ ርዕስ ሥር ከወጡት ተከታታይ ትምህርቶች ጠቃሚ መረጃዎችን አግኝቻለሁ። አንዳንዴ የጉርምስና ዕድሜ ፈታኝ ነው፤ ይሁንና ይህን የመሰሉ አበረታች ርዕሰ ትምህርቶችን ማግኘት ችግሩን ትንሽ ይቀንሰዋል። በዚህ “የሚያስጨንቅ ጊዜ” ውስጥ ማግኘት የሚያስፈልገን ወቅታዊ ማጽናኛ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት ማሳሰቢያዎች ‘በዲያብሎስ የተንኰል ሥራ’ እንዳንጠመድ ይረዱናል። (ኤፌሶን 6:11) በተገቢው ጊዜ ስለምታቀርቡት መንፈሳዊ ምግብ አመሰግናችኋለሁ።
ኬ. ኤስ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ንጹሕ ቤት—እያንዳንዳችን የምናበረክተው አስተዋጽኦ (ነሐሴ 2005) ልጅ እያለሁ ወላጆቻችን ወደ ሥራ ሲሄዱ ሦስታችን ደግሞ ቤት ውስጥ ስንጫወት እንውል ነበር። በዚህ ጊዜ ቤቱን ምስቅልቅሉን እናወጣዋለን። አሁንም ቢሆን ማጽዳት ብሎ ነገር አልወድም። ይሁንና ይህን ርዕስ ሳነብ እናቴ እንዴት ማጽዳት እንዳለብኝ በደግነት እንደምታስተምረኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። አሁን ትልልቅ ልጆች አድርሻለሁ፤ እነርሱም ማጽዳት አይወዱም። ገና ብዙ ነገሮችን ማስተማር ይኖርብኛል። ይህ ርዕሰ ትምህርት አበረታቶኛል።
ዩ. ኢ.፣ ጃፓን
የወጣቶች ጥያቄ “የወጣቶች ጥያቄ . . . ነገሮች አልሆን ሲሉኝ የሚሰማኝን የዋጋ ቢስነት ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ ለወጣው ግሩም ሐሳብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። (ታኅሣሥ 2004) ልክ እንደ አና እኔም አምላክ እንዳዘነብኝና መቼም ቢሆን ይቅር እንደማይለኝ ተሰምቶኝ ነበር። ይሁንና በዚህ ርዕሰ ትምህርት ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን ይቅር ያለው ከመሆኑም በላይ ድክመቶች የነበሩበት ቢሆንም እንኳ አልተወውም። ብንወድቅም እንኳ ይሖዋ እንድንነሳ እንደሚረዳን ማወቁ ምንኛ ያጽናናል!
ጄ. ኬ.፣ ጣሊያን
ከሁሉም በላይ የረዳኝ ገላትያ 6:4 ላይ ያለው ሐሳብ ነው። በክፍሌ ውስጥ ከሚገኙት ጎበዝ ተማሪዎች ጋር ራሴን የማወዳደር ልማድ እንደነበረኝ ተረድቻለሁ። ይህ ርዕስ ራሴን እየጎዳሁ እንደሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል።
ሲ.ሲ.፣ ፈረንሳይ
በለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች እርግዝና “በለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች እርግዝና የመላው ዓለም አሳዛኝ ችግር” በሚል ርዕስ ሥር ለወጡት ተከታታይ ትምህርቶች ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። (ታኅሣሥ 2004) ገና አንብቤ ሳልጨርስ ማልቀስ ጀመርኩ። ጽሑፉ እህቴ ያለችበትን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ነው። ስሜቶቿን በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስቻለኝን ይህን ወቅታዊ ጽሑፍ እንዳገኝ ስለረዳኝ ይሖዋን እጅግ አመሰግነዋለሁ።
ኤም. ኤስ.፣ ኢንዶኔዥያ
በገጽ 10 ላይ ባለው ፎቶግራፍ ውስጥ የሚታዩት የጉባኤ ሽማግሌዎች አፍቃሪና አዛኝ እንደሆኑ በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። በእርግጥም ፎቶው ተወዳዳሪ የሌለውን የይሖዋን ፍቅርና ምሕረት አጉልቶ ያሳያል! ከባድ ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ ለገቡ ሰዎች ባለን አመለካከት ረገድ ይሖዋን እንድንመስል ስለምታስተምሩን እናመሰግናችኋለን።
ቲ. ኬ.፣ ዩክሬን
ዕጥፉን መንገድ “‘ዕጥፉን መንገድ በመሄዴ’ ተደስቻለሁ” የሚል ርዕስ ያለውን ተሞክሮ ማንበቤ አጽናንቶኛል። (ሚያዝያ 2005) ከክሌር ቨቪ ጋር በተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የምንገኝ ከመሆኑም ባሻገር በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት ያሳለፍናቸው ዓመታትም እኩል ናቸው፤ ስለሆነም የሕይወት ታሪኳ ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው። ይበልጥ ትኩረቴን የሳበው ደግሞ ተሞክሮውን የተናገረችው አንዲት ያላገባች ወጣት መሆኗ ነው። እኔም ያላገባሁ እንደመሆኔ መጠን የክሌር ቅንዓትና አዎንታዊ አመለካከት አበረታቶኛል። ተሞክሮው በተጻፈባቸው ገጾች ውስጥ ያሉት ፎቶግራፎቿ በሙሉ እውነተኛ ደስታ እንዳላት ያሳያሉ። ይህም፣ ደስታ ማግኘታችን የተመካው በማኅበረሰቡ ዘንድ ባለን ቦታ ወይም በሀብታችን ላይ ሳይሆን ለይሖዋ ባለን ፍቅርና እርሱን በማገልገላችን መሆኑን ይበልጥ አስገንዝቦኛል።
ዋይ. አር.፣ ዩናይትድ ስቴትስ