ሐቀኝነት አምላክን ያስከብራል
ሐቀኝነት አምላክን ያስከብራል
ዩክሬን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑትና በዩክሬን የሚኖሩት ቺቢሶፍና ቤተሰቡ ከአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ወደ ቤት ሲመለሱ ክሬዲት ካርዶች፣ 500 የአሜሪካ ዶላር የሚሆን ገንዘብና መንጃ ፈቃድ ጨምሮ ሌሎች ውድ ዕቃዎችን የያዘ ቦርሳ አገኙ። የቤተሰቡ አባላት አምስት ሲሆኑ ከእነርሱ ውስጥ ሥራ ያለው ባልየው ብቻ ነበር። እርሱም በወር የሚያገኘው 70 የአሜሪካ ዶላር ያህል ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ገንዘብ በጣም ሊጠቅማቸው ይችል ነበር። ታዲያ ምን አድርገው ይሆን?
እናትየዋ እንዲህ ትላለች:- “ሴቶች ልጆቻችን ቦርሳውን ለባለንብረቷ እንዴት መመለስ እንደሚችሉ ወዲያውኑ መነጋገር ጀመሩ። እኔና ባለቤቴ ልጆቻችን የሠለጠነ ሕሊናቸውን እንዴት እንደተጠቀሙበት ስንመለከት በጣም ተደሰትን። በሚቀጥለው ቀን ቦርሳዋ የጠፋባት ሴት ጋር ስልክ ደወልኩ። ኦላ የመጣችው የደስታ ዕንባ እያነባች ነበር፤ እሷ እና ባለቤቷ በምንኖርበት አካባቢ ትንንሽ ሱቆች እንዳሏቸው ነገረችን። በቦርሳዋ የያዘችው ገንዘብ ለሠራተኞቻቸው የሚከፈል ደሞዝ ነበር። በተጨማሪም በቦርሳዋ ውስጥ ከነበሩት ሰነዶች አንዱ ከሥራዋ ጋር በተያያዘ በጣም ያስፈልጋት ነበር።
“ኦላ ቦርሳውን የት እንዳገኘነው ጠየቀችን። የት እንዳገኘነው ከነገርናት በኋላ እዚያ ቦታ ልንገኝ የቻልነው ከክርስቲያናዊ ስብሰባችን ስንመለስ እንደሆነ አስረዳናት። አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስንሰጣት በአክብሮት ተቀበለችን።
“ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በጉባኤያችን ያለች እህት፣ አንዲትን ሴት በመንገድ አስቁማ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ስትሰጣት ሴትየዋ ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮችን ፈጽሞ አዳምጣቸው እንደማታውቅ ነገረቻት። አሁን ግን የሚናገሩትን ለማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ጽሑፍም ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ገለጸችላት። ይህን ያህል ለውጥ ልታደርግ የቻለችው የይሖዋ ምሥክሮች የልጅዋን ቦርሳ አግኝተው በመመለሳቸው ምክንያት እንደሆነ ተናገረች።”
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቺቢሶፍ ቤተሰብ