በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተራሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል

ተራሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል

ተራሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል

“ሁሉም ሰው መጪዎቹ ብዙ ትውልዶች ከዓለም ተራራማ አካባቢዎች ከሚመነጨው ሀብት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ የማስቻል ኃላፊነት አለበት።”—ኮፊ አናን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ

ስለ ተራሮች ሲነሳ የሚታሰበው ግርማ ሞገሳቸው፣ የማይነቃነቁ መሆናቸውና ጥንካሬያቸው ነው። እነዚህን ግዙፍ ፍጥረታት ሊደፍር የሚችል ምን ነገር ይኖራል? የምድር ተራሮች አደጋ ተደቅኖባቸዋል የሚለው አባባል ለብዙዎች እንግዳ ሊሆንባቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ተራሮቻችን አደጋ ላይ ናቸው። የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች የተራሮችን ሥነ ምሕዳራዊ መዋቅር ቀስ በቀስ የሚሸረሽሩ በርካታ ችግሮችን ይጠቅሳሉ። እነዚህ ችግሮች በሙሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሱ ከመሆናቸውም በላይ እየተባባሱ የመሄድ እንጂ የመሻሻል አዝማሚያ አይታይባቸውም። ተራሮችን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ችግሮች አንዳንዶቹን እንመልከት።

የልማት ፕሮጀክቶች። ከዓለም ተራራማ አካባቢዎች 25 በመቶ የሚሆኑት በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ይከናወናሉ ተብለው በታቀዱ የመንገድ ሥራ፣ የማዕድን ቁፋሮ፣ የቧንቧ መስመር መዘርጋትና የግድብ ሥራ ፕሮጀክቶች ምክንያት ለአደጋ ተጋልጠዋል። የመንገዶች መሠራት በከፍተኛ ቁልቁለቶች ላይ የአፈር መሸርሸር ከማስከተሉም በላይ ከዚህ የበለጠ ጉዳት ለሚያደርሱ ደን ጨፍጫፊዎች መግቢያ በር ይከፍታል። ማዕድን በሚወጣበት ጊዜ በየዓመቱ አሥር ሺ ሚሊዮን ቶን አፈር ከነማዕድኑ ተዝቆ የሚወሰድ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሚዛቀው ከተራሮች ነው። *

የምድር ሙቀት መጨመር። ወርልድ ዋች ኢንስቲትዩት “በጣም ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበባቸው ዘጠኝ ዓመታት ከ1990 ወዲህ ያሉ ናቸው” ይላል። በተለይ በዚህ የሚጎዱት ተራራማ አካባቢዎች ናቸው። ግግር በረዶዎች በመቅለጥና በረዷማ የተራራ አናቶች በመሸሽ ላይ ናቸው። አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ይህ ሂደት በውኃ ክምችቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትል የመሬት መደርባት አደጋ ያመጣል። ባሁኑ ጊዜ በሂማሊያ ሰንሰለታማ ተራሮች የሚገኙ በርካታ ሐይቆች የተፈጥሮ ገደባቸውን ጥሰው በመውጣት አደገኛ ጎርፍ ያስከትላሉ የሚል ስጋት አለ። ደግሞም ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ይህ ነገር በተደጋጋሚ ተከስቷል።

ከእጅ ወደ አፍ ግብርና። የሕዝብ ብዛት መጨመር በሚያሳድረው ጫና ምክንያት ሕዝቦች ለምነታቸው የተሟጠጡ አካባቢዎችን ለማረስ ተገድደዋል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ባሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ ተራራማ አካባቢዎች ግማሽ ያህል የሚሆነው ለእርሻ ወይም ለከብት ማዋያነት ያገለግላል። ይህም ማለት 10 በመቶ ለእርሻ 34 በመቶ ደግሞ ለግጦሽ ይውላል። እነዚህ ደጋማ አካባቢዎች ለእርሻ ሥራ የሚያመቹ ባለመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ ከማሳዎቹ የሚገኘው ምርት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። * ለከብት ግጦሽ በሚውሉበት ጊዜ ደግሞ ቀድሞውኑ አቅመ ቢስ የነበሩት እጽዋት ይወድማሉ። አንድ በቅርቡ የተደረገ ጥናት ከጠቅላላው ተራራማ መሬት ቀጣይ የሆነ የግብርና ሥራ ለማካሄድ የሚያስችለው መሬት ከ3 በመቶ እንደማይበልጥ አረጋግጧል።

ጦርነት። የእርስ በርስ ጦርነቶች መፈንዳት በበርካታ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። አማጺያን የእንቅስቃሴያቸው ማዕከል የሚያደርጉት ተራራማ አካባቢዎችን ነው። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከአፍሪካ ተራሮች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት “በሕዝቦች መካከል በሚደረግ ግጭት ምክንያት” ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ደጋማ አካባቢዎች የአደገኛ ዕፆች የማምረቻ ማዕከላት ሆነዋል። ይህ ደግሞ ለግጭትና ለአካባቢ ጉስቁልና ምክንያት ይሆናል።

ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው?

የሰው ልጅ በተራሮች ላይ ያደረሰው ጉስቁልና ያስከተለውን ውጤት አሁንም እንኳን ማየት ጀምረናል። ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የውኃ እጥረት አዝማሚያው የሚያወላዳ እንዳልሆነ ከሚጠቁሙት ምልክቶች አንዳንዶቹ ናቸው። መንግሥታት ይህንን አዝማሚያ መገንዘብ ጀምረዋል። ደኖች መተከል ከመጀመራቸውም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ዛፎችን መቁረጥ በሕግ ተከልክሏል። በጣም ውብ የሆኑ አካባቢዎችንና ከነጭራሹ ይጠፋሉ ተብለው የሚሰጋላቸው እንስሳት የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ለመጠበቅ ሲባል ብሔራዊ ፓርኮች ተቋቁመዋል።

ይሁን እንጂ ጥብቅ ክልሎች ሳይቀሩ የአካባቢ መመናመን ከሚያስከትለው ጫና ነፃ ሊሆኑ አልቻሉም። (“ለእንስሳትና ለእጽዋት መሸሸጊያ የሆኑ አንዳንድ ክልሎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የእንስሳትና የእጽዋት ዝርያዎች የሚጠፉበት ፍጥነት ለእንስሳትና ለእጽዋት መሸሸጊያ ይሆናሉ የሚባሉትን ተራራማ አካባቢዎች ከጥፋት ለማዳን የሚደረገው ትግል የአሸናፊነት አዝማሚያ እንደማይታይበት ያመለክታል። የመስኩ ባለሞያዎች የችግሩን ባሕርይና መጠን ቢያውቁም ሰው ያልደረሰባቸውን ጠፍ አካባቢዎች ከጥፋት ለማዳን የሚያስፈልገው መጠነ ሰፊ እርምጃ አልተወሰደም። እውቅ ባዮሎጂስት የሆኑት ኤድዋርድ ዊልሰን “ያገኘነው የሳይንስ እውቀት በጣም አበረታች ቢሆንም ዋነኞቹ የብዝሐ ሕይወት መከማቻዎች እየጠፉ መምጣታቸው ተስፋ ያስቆርጠኛል” ብለዋል።

የብዝሐ ሕይወት መጥፋት በእርግጥ ይህን ያህል የሚያሳስብ ነገር ነው? ብዙ ባዮሎጂስቶች እንደሚሉት የሰው ልጆች ከምድር ብዝሐ ሕይወት መጠበቅ በርካታ ጥቅም ያገኛሉ። ለዚህም የበለጸገ ብዝሐ ሕይወት ከሚገኝበት የማዳጋስካር ተራራማ አካባቢዎች የተገኘውን ሮዚ ፔሪዊንክል የተባለ ዕፅ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ከዚህ ዕፅ ሉኪሚያ ለተባለው በሽታ በጣም ጠቃሚ መድኃኒት ተገኝቷል። በተጨማሪም ከአንዲስ ተራሮች የተገኘው ሲንቾና የተባለ ዛፍ የወባ መድኃኒት ለሆነው ኪኒንና ሌሎች መድኃኒቶች መገኛ በመሆን ለብዙ አሥርተ ዓመታት አገልግሏል። በተራራማ አካባቢዎች የሚያድጉ ሌሎች ብዙ ተክሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ታድገዋል። እርግጥ፣ ከተራራማ አካባቢዎች ከተገኙት ከእነዚህ ዕፆች መካከል ብዙዎቹን ተራራማ ባልሆኑ ሌሎች አካባቢዎች መትከልና ማልማት እንደተቻለ አይካድም። ይሁን እንጂ የሚያሳስበው ነገር በተራራማ አካባቢዎች በሚደርሰው መጠነ ሰፊ ውድመት ምክንያት በመድኃኒትነትና በምግብነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ገና ያልታወቁ ዕፆች ሊጠፉ የሚችሉ መሆናቸው ነው።

ታዲያ እንዲህ ያለውን የማውደም ግስጋሴ ማቆም ይቻላል? የደረሰውንስ ጉዳት መመለስ ይቻላል? ተራሮች የውበትና የብዝሐ ሕይወት ማዕከላት በመሆን ይቀጥላሉ?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በአማካይ ለአንድ የወርቅ ቀለበት የሚበቃ ማዕድን ለማግኘት 30 ኩንታል አፈር አብሮ ይዛቃል።

^ አን.6 በሌላ በኩል ደግሞ የተራራማ አካባቢ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ለብዙ መቶ ዘመናት የግብርና ሥራቸውን ሲያካሂዱ ኖረዋል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የተራራማ አካባቢ የእንስሳት ዝርያዎች

የተራራ አንበሳ ወይም ፑማ ተብሎ የሚታወቀው እንስሳ በአብዛኛው የሚገኘው በሮኪ እና በአንዲስ ተራሮች ነው። እንደ ብዙዎቹ ትላልቅ አዳኝ አራዊት ሰዎች ከሚያደርሱበት ጥቃት ለመሸሽ ሲል ሰው በማይደርስባቸው አካባቢዎች ይኖራል።

ቀይ ፓንዳ በሂማሊያ የተራራ ሰንሰለቶች ሌላው ቀርቶ ዝቅ ባሉት የኤቨረስት ተራራ አቀበቶች ጭምር ይኖራል። ይሁን እንጂ መኖሪያው ከሰው የራቀ ቢሆንም የሚመገበው የቀርከሃ ደን እየተመናመነ በመምጣቱ ኑሮ ሊመቸው አልቻለም።

[ምንጭ]

Cortesía del Zoo de la Casa de Campo, Madrid

ቡናማ ድብ በአንድ ወቅት በአብዛኛው የአውሮፓ፣ የእስያና የሰሜን አሜሪካ አካባቢዎች ይታይ ነበር። ምንም እንኳ በካናዳ ሮኪ ተራሮች፣ በአላስካና በሳይቤሪያ በብዛት ቢገኝም በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኘው ራቅ ብለው በሚገኙ ጥቂት ተራራማ አካባቢዎች ብቻ ነው። ባለፈው መቶ ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ ቁጥሩ 99 በመቶ ቀንሷል።

ወርቃማው ንስር በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙ የተራራማ አካባቢዎች ሰማይ ንጉሥ ነው። የሚያሳዝነው ግን ‘የተጠላ አሞራ’ ሆኖ ስለቆየ ባሁኑ ጊዜ በአውሮፓ የሚኖሩ የወርቃማው ንስር ጥንዶች ቁጥር ከ5,000 ያነሰ ነው።

የግዙፎቹ ፓንዳዎች ሕልውና ቻይናዊው የተፈጥሮ እንክብካቤ ባለሞያ ታንግ ሲያንግ እንደሚሉት “በሦስት አስፈላጊ ነገሮች ላይ የተመካ ነው።” እነርሱም “ረዣዥም ተራሮችና ጥልቅ ሸለቆዎች፣ ጥቅጥቅ ያሉ የቀርከሃ ደኖች እንዲሁም ኩልል ብለው የሚፈስሱ ጅረቶች ናቸው።” አንድ ግምት እንዳመለከተው ከሆነ በዱር የሚኖሩ ፓንዳዎች ቁጥር ከ1,600 አይበልጥም።

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ለእንስሳትና ለእጽዋት መሸሸጊያ የሆኑ አንዳንድ ክልሎች

ዮሴማይት ብሔራዊ ፓርክ (ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ) ጆን ሚውር የተባሉት የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በ1890 ተቋቋመ። የዚህን ብሔራዊ ፓርክ አስደናቂ ውበት ለማየት በየዓመቱ አራት ሚሊዮን ጎብኚዎች ይመጣሉ። ይሁን እንጂ የፓርኩ ባለ ሥልጣናት የአካባቢው ጠፍነት ሳይጠፋ ለጎብኚዎች የሚያስፈልገውን ማረፊያና መዝናኛ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

ፖዶካርፐስ ብሔራዊ ፓርክ (ኢኳዶር) በጣም ብዙ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ ማለትም 600 የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎችና 4000 ገደማ የሚደርሱ የእጽዋት ዝርያዎች በሚገኙበት በደን የተሸፈኑ የአንዲስ ተራሮች ይገኛል። ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት የታደገው የወባ በሽታ ኪኒን የተገኘው ከዚህ አካባቢ ነው። ይህም ፓርክ እንደ ሌሎቹ በርካታ ፓርኮች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የደን ጭፍጨፋና አደን ጉዳት ደርሶበታል።

የኪሊማንጃሮ ተራራ (ታንዛኒያ) በአፍሪካ በከፍታው አንደኛ የሆነ ተራራ ሲሆን በዓለም ታላላቅ ከሆኑት እሳተ ገሞራዎች አንዱ ይገኝበታል። በአካባቢው ረባዳ ክፍል ዝሆኖች ሲግጡ ከፍ ባለው ደጋማ አካባቢ እንደ ጅብራና አስታ የመሰሉ ብዙ ቦታ የማይበቅሉ እጽዋት ይገኛሉ። ለዚህ ፓርክ ስጋት የፈጠሩት ሕገወጥ አደን፣ የደን መመናመንና የቤት እንስሳት ለግጦሽ መሰማራት ናቸው።

ቴተ ብሔራዊ ፓርክ (ካነሪ ደሴቶች) እሳተ ገሞራማ አካባቢዎችን ያስጌጡ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ እጽዋት ይጠበቁበታል። ተራራማ የሆኑ እሳተ ገሞራማ ደሴቶች ሁልጊዜም አቅመ ደካማ የሆነ ሥነ ምሕዳር ያላቸው በመሆኑ ከሌሎች አካባቢዎች በመጡ ዝርያዎች ይጠቃሉ።

የፒሬና እና የኦሮዴሳ ብሔራዊ ፓርክ (ፈረንሳይና ስፔይን) በጣም ውብ የሆነው የአልፕስ ተራራ አካባቢና በዚያ የሚኖሩት የእንስሳትና የእጽዋት ዝርያዎች ይጠበቁበታል። የፒሬና ተራሮች እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ የተራራ ሰንሰለቶች ሁሉ በበረዶ መንሸራተቻዎችና በሌሎች የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋሞች በእጅጉ ተጣበዋል። በተጨማሪም ባሕላዊው የግብርና ሥራ እየቀረ መምጣቱ በአካባቢው ላይ ጫና አሳድሯል።

ሶራክሳን ብሔራዊ ፓርክ በኮሪያ ሪፑብሊክ የሚገኝ በጣም ተወዳጅ ፓርክ ነው። አለታማዎቹ የተራራ ጫፎችና በደን የተሸፈኑት ሸለቆዎች በተለይ በበልግ ወራት ልዩ ውበት ይላበሳሉ። ይሁን እንጂ በጣም ተወዳጅ በመሆኑ ምክንያት በሳምንቱ የእረፍት ቀናት አንዳንዶቹ ቀጫጭን መንገዶች ከመሐል ከተማ መንገዶች ባልተናነሰ ሁኔታ ይጨናነቃሉ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የተራራ አካባቢ እጽዋት

ታወር ኦፍ ጁውልስ። ይህ አስደናቂ አበባ በጥቂት የፀደይ ሳምንታት ውስጥ የሰው ቁመት ያህል ያድጋል። የሚገኘው 1,800 ሜትር ከፍታ ባላቸው በካነሪ ደሴቶች በሚገኙ ሁለት የእሳተ ገሞራ ጫፎች ላይ ብቻ ነው። ብዙዎቹ የተራራ ዝርያዎች የሚገኙት በጣም ውስን በሆኑ ተመሳሳይ አካባቢዎች ነው።

ካርላይን ቲስልስ። የሚበቅሉት በአልፕስና በፒሬና ተራሮች ነው። በበጋ ወራት መገባደጃ ላይ እንደ ፀሐይ ጀምበር ፈክተው መታየታቸው ለመስኮቹ ድምቀት ሲሰጡ ለበራሪ ነፍሳት የቀለብ ምንጭ ይሆናሉ።

ኢንግሊሽ አይሪስ። የዚህ የዱር አበባ ዝርያዎች በቤት አካባቢዎች ይተከላሉ። በርካታ የጓሮ አበቦች የተገኙት ከአልፕስ ተራራ አካባቢ ነው።

ማውንቴን ሀውስሊክ። በድንጋይ ስንጣቂዎች ውስጥ ተንጠላጥለው ከሚያድጉት የአልፕስ ተራራ አካባቢ እጽዋት አንዱ ነው። በደቡባዊ አውሮፓ ተራሮች የሚገኝ ዝርያ ሲሆን ባለው ጥንካሬና አይበገሬነት የተነሳ ዘላለም ኗሪ የሚል የቅጽል ስም ተሰጥቶታል።

ብሮሚሊያድስ። በሐሩር መስመር አገሮች በሚገኙ በደን የተሸፈኑ ተራሮች ብዙ ዓይነት የብሮሚሊያድስና የኦርኪድስ ዝርያዎች ይበቅላሉ። እነዚህ እጽዋት እስከ 4,500 ሜትር በሚደርስ ከፍታ ላይ ይበቅላሉ።

የአልጄሪያ አይሪስ። የሚበቅለው በሰሜን አፍሪካ በአትላስና በኤር ሪፍ ተራሮች ነው። ይህ አካባቢ የሜዲትራንያን አካባቢ የበርካታ ለአደጋ የተጋለጡ እጽዋት ዝርያዎች ማዕከል ተብሎ ተሰይሟል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢንዶኔዥያ በማኦኬ ተራሮች አካባቢ የመዳብና የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ

[ምንጭ]

© Rob Huibers/Panos Pictures

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮዚ ፔሪዊንክል