“እስረኞች ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ይቻላልን?”
“እስረኞች ለውጥ እንዲያደርጉ መርዳት ይቻላልን?”
ይህ ጥያቄ የግንቦት 2001 “ንቁ!” መጽሔት የሽፋን ርዕስ ነበር። መጽሔቱ የይሖዋ ምሥክሮች በአትላንታ፣ ጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ የፌደራል ወኅኒ ቤት ውስጥ ስለሚሰጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚገልጽ ሪፖርት ይዟል። በዚህ ርዕስ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች ያነበቡ በርካታ ሰዎች የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ቀጥሎ የቀረቡት አስተያየቶች ከደረሱን በርካታ ደብዳቤዎች ውስጥ የተወሰዱ ናቸው።
▪ “ላለፉት ስምንት ዓመታት በእስር የቆየሁ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤቶች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማራቸው እጅግ ውጤታማ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። አትላንታ በሚገኘው ወኅኒ ቤት በነበርኩባቸው ጊዜያት በመጽሔታችሁ ላይ ከተጠቀሱት አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የመሥራት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ለለገሱኝ ፍቅርና ላደረጉልኝ እርዳታ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንደ እኔ ለተሳሳቱ ሆኖም ይህን ስህተታቸውን ለማረምና የተሻሉ ዜጎች ለመሆን ለሚጥሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን ባሕርይ በማሳየታቸው እነዚህን ወንድሞች እጅግ በጣም አመሰግናቸዋለሁ።”—አር ጄ
▪ “በአሁኑ ጊዜ የምኖረው ማረሚያ ቤት ውስጥ ሲሆን በአቅራቢያው ባለ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚሰበሰቡ ወንድሞች እኛን ለመርዳት ግሩም የሆነ የትምህርት ፕሮግራም አዘጋጅተዋል። ከዚህም የተነሳ አንድ የእስር ቤት ጓደኛዬ የተጠመቀ ሲሆን እኔም ከዚህ በፊት ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግጄ የነበርኩ ብሆንም አሁን ውገዳው ተነስቶልኛል። ሌሎች በርካታ ታራሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ናቸው። በዓለም አቀፉ የማስተማር ሥራ ውስጥ የታቀፍን መሆኑን ማወቃችን ያበረታታናል። በየትም ቦታ እንኑር ይሖዋን ማገልገል መቻል እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው!”—ጄ ኤም
▪ “በ1970 ባልፈጸምኩት ወንጀል ተከስሼ ወደ ወኅኒ ወረድኩ፤ በዚያም ለ14 ዓመታት ቆየሁ። እስር ቤት እያለሁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ታማኝነታቸውና አሳቢነታቸው በጣም አስደነቀኝ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጥዬ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ተጠመቅሁ። አሁንም ቢሆን በደረሰብኝ በደል የምበሳጭበትና የምናደድበት ጊዜ አለ። ሆኖም ይሖዋ የፍትሕ መጓደልንም ይሁን ሥቃይን በቅርቡ እንደሚያስወግድ ትዝ ይለኛል። በእስር ያሉ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን መመሪያዎች ቢታዘዙ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ። እንዲሁም ልክ እንደ እኔ፣ ወንድሞች ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ ለሚሰጡት እንዲህ ዓይነቱ እርዳታና ለሚያሳዩት ትጋት አመስጋኞች መሆን ይችላሉ።”—አር ኤስ
▪ “ወደ እስር ቤት በገባሁበት ወቅት ሲጋራ አጨስ፣ አደገኛ ዕፅ እወስድ፣ አስጸያፊ ቃላት እናገር የነበረ ከመሆኑም ሌላ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች ፈጽሞ አክብሮት አልነበረኝም። በተጨማሪም የወንጀለኞች ቡድን አባል ነበርኩ። ከዚህም በላይ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግጄ ነበር። አሁን ግን ውገዳው ተነስቶልኝ ጥሩ ለውጥ በማድረግ ላይ እገኛለሁ። እውነት ምስጋና ይግባውና ፍጹም ነፃነት እንዳገኘሁ ይሰማኛል።”—አይ ጂ