ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ፍሎረንስ የአርባ ዓመት ሴት ስትሆን ልጅ የመውለድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። ይሁን እንጂ ነፍሰ ጡር ሳለች አንድ ዶክተር የምትወልደው ልጅ ዘገምተኛ አእምሮ ሊኖረው እንደሚችል ነገራት። ቢሆንም ጽንሱን ለማስወረድ ፈቃደኛ አልሆነችም፤ ጤነኛ የሆነ ወንድ ልጅም ወለደች።
ስቲቨን ከተወለደ ከጥቂት ጊዜ አንስቶ ፍሎረንስ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ለልጅዋ ማንበብና እርሱን ማነጋገር ጀመረች። ልጁ በዕድሜ ከፍ ሲል አብረው ይጫወቱ፣ ሽርሽር ይሄዱ፣ መዝሙር ይዘምሩ እንዲሁም መቁጠር ታስተምረው ጀመር። “ገላውን በማጥብበት ጊዜ እንኳን አንድ ዓይነት ጨዋታ እንጫወት ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ይህ ሁሉ ጥረቷ ዋጋ አስገኝቶላታል።
ስቲቨን ገና የ14 ዓመት ልጅ እያለ ከማያሚ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ተመረቀ። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ16 ዓመቱ በሕግ ትምህርት የተመረቀ ሲሆን የሕይወት ታሪኩ እንደሚያመለክተውም በዩናይትድ ስቴትስ በዕድሜ ትንሹ የሕግ ባለሞያ ሆነ። እናቱ ዶክተር ፍሎረንስ ባከስ መምህርና የተማሪዎች አማካሪ የነበረች ሲሆን ልጆችን ከትንሽነታቸው አንስቶ ስለማስተማር በርካታ ጥናቶች አድርጋለች። ለልጅዋ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ትኩረት መስጠቷና አእምሮውን ማነቃቃቷ በሕይወቱ ላይ ለውጥ እንዳስከተለ እርግጠኛ ነች።
ተፈጥሮ ወይስ እንክብካቤ?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕፃናት ሥነ አእምሮ ሊቃውንት፣ በአንድ ሕፃን እድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣው “ተፈጥሮው” ማለትም በውርሻ ያገኘው ባሕርይ ነው ወይስ የተደረገለት “እንክብካቤ” ማለትም አስተዳደጉና የተሰጠው ሥልጠና የሚለው ጉዳይ ያወዛግባቸው ጀምሯል። አብዛኞቹ ተመራማሪዎች እነዚህ ሁለት ነገሮች በአንድ ልጅ አስተዳደግ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እርግጠኞች ናቸው።
የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ፍሬዘር መስተርድ “በአሁኑ ጊዜ በጥናት የደረስንበት ነገር አንድ ልጅ በጨቅላነት ዕድሜው ያሳለፋቸው ተሞክሮዎች በአእምሮ እድገቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ፕሮፌሰር ሱዛን ግሪንፊልድ “ለምሳሌ በቫዮሊን ተጫዋቾች አንጎል ውስጥ የግራ እጅን ጣቶች የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ዳብሮ ተገኝቷል” ብለዋል።
ምን ዓይነት ሥልጠና ይሰጥ?
ብዙ ወላጆች እንደነዚህ ያሉትን ግኝቶች በመመልከት ልጆቻቸውን በጣም ጥሩ ወደሆኑ መዋዕለ ሕፃናት ከመላክም አልፈው ሙዚቃና ሥነ ጥበብ ለማስተማር በጣም ብዙ ገንዘብ ይከሰክሳሉ። አንዳንዶች አንድ ሕፃን ሁሉንም ነገር ከተለማመደ ትልቅ ሲሆን ማንኛውንም ነገር ማድረግ አያቅተውም ብለው ያምናሉ። የተለያዩ የማሠልጠኛና የቅድመ ትምህርት መስጫ ተቋሞች እንደ አሸን እየፈሉ መጥተዋል። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ከሌሎች በልጠው እንዲገኙ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው።
እንዲህ ያለው መሥዋዕትነት እውነት ጠቃሚ ነው? እንዲህ ያለው አስተዳደግ ልጆች በጣም ሰፊ አጋጣሚና እድል እንዲያገኙ የሚያስችል ቢመስልም አብዛኛውን ጊዜ ልጆቹ በነፃነት እንደ ልብ መጫወታቸው የሚያስገኘውን ወሳኝ የሆነ የትምህርት ክፍል እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል። የትምህርት ባለሞያዎች እንደሚሉት ልጆች ደስ እንዳላቸው መጫወታቸው የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያዳብርላቸው ከመሆኑም በላይ የአንድን ሕፃን ማኅበራዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ችሎታዎች ያነቃቃል።
አንዳንድ የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያዎች በወላጆች የሚመራ ጨዋታ አዲስ ዓይነት ችግር ያለባቸው ልጆች እንደፈጠረ ያምናሉ። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ላይ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ልጆች ውጥረት፣ የስሜት አለመረጋጋት፣ የእንቅልፍ እጦትና ሕመም ያጋጥማቸዋል። ከነዚህ ልጆች አብዛኞቹ አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚደርሱበት ጊዜ ችግር የመቋቋም ችሎታ የሌላቸው፣ “በአካልና በስሜት የተዳከሙ፣ ከሰው ጋር ተግባብተው መኖር የማይችሉና ዓመጸኞች ይሆናሉ” በማለት አንድ የሥነ አእምሮ ሊቅ ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያት ብዙ ወላጆች ግራ ተጋብተዋል። ልጆቻቸው እምቅ ችሎታቸውን አዳብረው በተሟላ መልኩ እንዲጠቀሙበት ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ትናንሽ ልጆችን አላቅማቸው መገፋፋትና መጫን ስህተት መሆኑን ማስተዋል ይችላሉ። ታዲያ በሁለቱ መካከል የሆነ ሚዛናዊ አቋም መያዝ ይቻላል? ትናንሽ ልጆች እድገት የማድረግ አቅማቸው እስከምን ድረስ ነው? ይህን አቅማቸውንስ ማሳደግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወላጆች ልጆቻቸው የተሳካላቸው እንዲሆኑ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራሉ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ልጅ ገና ትንሽ ሳለ የሚያጋጥሙት ሁኔታዎች በአንጎሉ እድገት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጨዋታ የፈጠራ ችሎታን ከማነቃቃቱም በላይ የአንድን ልጅ ተፈጥሯዊ ችሎታዎች ያዳብራል