በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅነት ሳይጠግቡ የልጅ እናት መሆን

ልጅነት ሳይጠግቡ የልጅ እናት መሆን

ልጅነት ሳይጠግቡ የልጅ እናት መሆን

“የወንድ ጓደኛዬ መልከ ቀና ልጅ ነበር። ገንዘብ ያለው በመሆኑ ወደፈለግነው ቦታ እየሄድን መዝናናት እንችል ነበር። የወር አበባዬ በቀረ ጊዜ ግን አንድ ችግር ውስጥ እንደገባሁ ታወቀኝ። ለእናቴ ምን ብዬ ልናገር? እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሊደርስብኝ ይችላል? ገና የ16 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ምን እንደማደርግ ግራ ገባኝ።”—ኒኮል

ሬኒኮል * በራስዋ የምትተማመንና ብርቱ የሆነች በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ የምትገኝ የሦስት ልጆች እናት ነች። ትልቋ ልጅዋ 20 ዓመት ሆኗታል። አዎ፣ ከበርካታ ዓመታት በፊት ልጅነታቸውን ሳይጠግቡ ከጋብቻ ውጭ ከሚጸንሱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴት ልጆች መካከል አንዷ ነበረች። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ከጋብቻ ውጭ እንደሚያረግዙት እንደሌሎቹ ሴቶች ኒኮልም የወደፊት ዕጣዋ የጨለመባትና ግራ የተጋባች ልጅ ሆና ነበር።

ኒኮል እኩዮችዋ ከሚለብሱት ልብስና ከትምህርት ውጤታቸው ሌላ አንዳች የሚያሳስባቸው ነገር ባልነበረበት ለጋ ዕድሜ ስላጋጠማት ፍርሐት፣ ብስጭት፣ ተስፋ መቁረጥና ድንጋጤ ብዙ ጊዜ አታወራም። ይሁን እንጂ የኒኮል ሁኔታ ተስፋ ቢስ ሆኖ አልቀረም። ከፍተኛ የሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እንድታከብርና እንድትከተል የሚጣጣሩ ወላጆች ነበሯት። እነዚህን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ለጥቂት ጊዜ ችላ ለማለት የመረጠችና ይህም ያስከተለባትን መራራ ውጤት የቀመሰች ቢሆንም እነዚሁ የሥነ ምግባር እሴቶች ስኬታማና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድትመራ አስችለዋታል። “ተስፋዬ ሁሉ ሊጨልም አይችልም” የሚል አቋም ነበራት።

የሚያሳዝነው ግን ከጋብቻ ውጭ የልጅ እናት የሚሆኑ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ሁሉ እንደ ኒኮል ያሉ ጥሩ ድጋፍ የሚሰጡ ቤተሰቦችም ሆነ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው አይደሉም። ብዙዎቹ በጥቂት ጊዜ ውስጥ መውጫ የሌለው በሚመስል የድህነት ኑሮ ውስጥ ይወድቃሉ። አንዳንዶቹ ተገድዶ መደፈርና ድብደባ ያስከተለባቸውን የስሜት ቁስል ተሸክመው ለመኖር ይገደዳሉ።

ይህ ሁሉ ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ የልጅ እናት በሚሆኑት እናቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሚወልዷቸው ልጆች ላይ የሚያስከትለው ችግር ቀላል አይደለም። ቲን ማምስ—ዘ ፔይን ኤንድ ዘ ፕሮሚስ የተባለው መጽሐፍ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ከሚገኙ እናቶች የሚወለዱ ልጆች “ሲወለዱ የሚኖራቸው ክብደት ዝቅተኛ የመሆን፣ በሕፃናት በሽታዎች የመጠቃት፣ በጨቅላነታቸው የመሞት፣ በቂ የሕክምና እንክብካቤ ያለማግኘት፣ በረሐብና የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት የመጠቃት፣ ለጠብና አምባጓሮ የመጋለጥ እንዲሁም በዕድሜ ከፍ ካሉ እናቶች ከሚወለዱ ሕፃናት ያዘገመ እድገት የማሳየት እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል” ይላል። እንዲያውም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ እናቶች የሚወለዱ ሴት ልጆች ራሳቸው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የልጅ እናት የመሆናቸው አጋጣሚ በዕድሜ ከፍ ካሉ እናቶች ከሚወለዱ ሴት ልጆች የበለጠ ነው።

በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና ምን ያህል የተስፋፋ ነው? ይህ ሁኔታ የገጠማቸው ወጣቶችስ ችግሩን መጋፈጥና መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? ወጣቶች እንዲህ ባለው አዘቅት ውስጥ እንዳይገቡ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? ቀጣዮቹ ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት ግለሰቦች ስሞች ተለውጠዋል