የጭፍን ጥላቻ መንስኤ ምንድን ነው?
የጭፍን ጥላቻ መንስኤ ምንድን ነው?
ጭፍን ጥላቻ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል። ቢሆንም በበቂ መረጃ የተረጋገጡ ሁለት መንስኤዎች አሉት። እነርሱም (1) ማሳበቢያ መፈለግ እና (2) ቀደም ባሉ ዘመናት የተፈጸመ ግፍ ያስከተለው ቂም ናቸው።
በቀደመው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ሰዎች አንድ ዓይነት ጥፋት ሲደርስባቸው ማሳበቢያ ማግኘት ይፈልጋሉ። ታዋቂ ሰዎች አንድን አናሳ ቡድን በተደጋጋሚ በሚወነጅሉበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኝና ጭፍን ጥላቻ ይፈጠራል። አንድ የተለመደ ምሳሌ ብንጠቅስ በምዕራባውያን አገሮች ኢኮኖሚው ሲያሽቆለቁል ሰዎች ሥራ ያጣነው ከሌሎች አገሮች በመጡ ሰዎች ምክንያት ነው ብለው ያማርራሉ። ሆኖም የባዕድ አገር ሰዎች የሚይዙት ሥራ አብዛኛውን ጊዜ የአገሩ ሰዎች ንቀው የተዉትን ነው።
ይሁን እንጂ ሁሉም ዓይነት ጭፍን ጥላቻ ማሳበቢያ ከመፈለግ የሚመነጭ አይደለም። ቀደም ባሉ ጊዜያት በተፈጸሙ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል። ዩኔስኮ አጌንስት ሬሲዝም በሚል ርዕስ የቀረበው ሪፖርት “በጥቁሮች ላይ የባሕል ንቀትና የዘር ጥላቻ የሚሰነዘርበትን ሁኔታ ያመቻቸውና መሠረት የጣለው የባሪያ ንግድ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብሏል። የባሪያ ነጋዴዎች አስነዋሪ ሥራቸውን ሕጋዊ ለማስመሰል ሲሉ አፍሪካውያን ከነጮች ያነሱ ናቸው የሚል አስተሳሰብ አሰራጭተዋል። ይህ ቆየት ብሎ ሌሎች ቅኝ ተገዥ ሕዝቦችን ያካተተው መሠረተ ቢስ ጥላቻ እስካሁን ድረስ ርዝራዡ አልጠፋም።
በመላው ዓለም ቀደም ባሉት ዘመናት የተፈጸሙና እስከ ዘመናችን ድረስ ለዘለቀው ጭፍን ጥላቻ ምክንያት የሆኑ ተመሳሳይ የጭቆናና የግፍ ድርጊቶች አሉ። በአየርላንድ የሚታየው የካቶሊኮችና የፕሮቴስታንቶች ጠላትነት መነሻው የእንግሊዝ ገዥዎች በ16ኛው መቶ ዘመን በካቶሊኮች ላይ የፈጸሙት ስደትና ጭፍጨፋ ነው። ክርስቲያን ነን ባዮች በመስቀል ጦርነት ጊዜ የፈጸሙት የጭካኔ ድርጊት ዛሬም በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሙስሊሞችን ያስቆጣል። በባልካን አገሮች በሰርቦችና በክሮአቶች መካከል የሚታየው ጥላቻ የተካረረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ነው። እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በሁለት ሕዝቦች መካከል የኖረ የጠላትነት ታሪክ ጭፍን ጥላቻ እንዲጠናከር ምክንያት ይሆናል።
አለማወቅ ችግሩን ያጠናክረዋል
ድክ ድክ የሚል ሕፃን ልብ ለጭፍን ጥላቻ ቦታ የለውም። እንዲያውም ተመራማሪዎች እንዳስተዋሉት ብዙውን ጊዜ ሕፃን ልጅ ሌላ ዘር ካለው ሕፃን ጋር ለመጫወት ምንም አይቸገርም። ይሁን እንጂ 10 ወይም 11 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ሌላ ዘር፣ ጎሣ ወይም ሃይማኖት ካላቸው ሰዎች መራቅ ሊጀምር ይችላል። በጨቅላነት ዕድሜው በሕይወት ዘመኑ በሙሉ አብሮት የሚኖር የተሳሳተ አስተሳሰብ ሊቀረጽበት ይችላል።
እንደነዚህ ያሉትን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች የሚማረው እንዴት ነው? አንድ ልጅ በቃል ሲነገር ይስማም አይስማ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ በመጀመሪያ የሚማረው ከወላጆቹ በኋላም ከጓደኞቹ ወይም ከአስተማሪዎቹ ነው። ቆየት ሲልም ከጎረቤቶች፣ ከጋዜጦች፣ ከሬዲዮ ወይም ከቴሌቪዥን የሚቀስመው ነገር ተጨማሪ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል። ስለሚጠላቸው ሰዎች እምብዛም የሚያውቀው ነገር ባይኖርም ትልቅ ሰው በሚሆንበት ጊዜ የማይታመኑና የተናቁ ናቸው ብሎ ይደመድማል። እንዲያውም ሊጠላቸው ይችላል።
በብዙ አገሮች ንግድና ከቦታ ቦታ መዘዋወር እየጨመረ በመምጣቱ የተለያየ ባሕልና ጎሣ ባላቸው
ሰዎች መካከል የሚደረገው ግንኙነት እየጨመረ መጥቷል። ቢሆንም ከፍተኛ ጥላቻ ኖሮት የቆየ ሰው ብዙውን ጊዜ ያንኑ አመለካከቱን ይዞ ይቀጥላል። በብዙ ሺዎች አልፎ ተርፎም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሁሉም አንድ ዓይነት መጥፎ ባሕርይ አላቸው ብሎ በማሰብ በአንድ ዓይነት ጎራ ይፈርጃቸዋል። የዚያ ቡድን አባል የሆነ አንድ ሰው የፈጸመበት መጥፎ ነገር ለጠቅላላው ጎሣ ያለውን ጥላቻ ያጠናክርበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ቢደረግለት ያ ግለሰብ የተለየ ሰው ስለሆነ ያደረገለት እንደሆነ በመቁጠር ችላ ብሎ ያልፈዋል።ከጭፍን ጥላቻ መላቀቅ
አብዛኞቹ ሰዎች ጭፍን ጥላቻን በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ የሚያወግዙ ቢሆኑም ከጭፍን ጥላቻ መዳፍ የሚላቀቁ ግን ጥቂቶች ናቸው። እንዲያውም ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ብዙ ሰዎች ጥላቻ እንደሌላቸው ሊናገሩ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች ጭፍን ጥላቻቸውን ይፋ እስካላወጡ ድረስ ምንም ጉዳት የለውም ይላሉ። ይሁን እንጂ ቀደም ብለን እንዳየነው ጭፍን ጥላቻ ሰዎችን ስለሚጎዳና ስለሚከፋፍል መጥፎ ነገር ነው። ጭፍን ጥላቻ የድንቁርና ልጅ ነው ቢባል የልጅ ልጁ ደግሞ ጠላትነት ነው። ቻርልስ ካለብ ኮልተን የተባሉት ደራሲ (1780?-1832) “አንዳንድ ሰዎችን ስለማናውቃቸው እንጠላቸዋለን። ስለምንጠላቸውም ልናውቃቸው አንችልም” ብለዋል። ይሁን እንጂ ጭፍን ጥላቻን መማር እንደሚቻል ሁሉ ማስወገድም ይቻላል። ግን እንዴት?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሃይማኖት—የመቻቻል መንፈስ ያሰፍናል ወይስ ጭፍን ጥላቻ እንዲስፋፋ ያደርጋል?
ጎርደን ደብሊው አልፖርት ዘ ኔቸር ኦቭ ፕረጀዲስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በአማካይ ሲታይ የቤተ ክርስቲያን አባላት ከሌሎቹ ሰዎች የበለጠ ጥላቻ አላቸው” ብለዋል። ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ ጭፍን ጥላቻን የሚያስወግድ ሳይሆን የሚያነሳሳ መሆኑን ካስታወስን ይህ አባባላቸው አያስገርመንም። ለምሳሌ ፀረ ሴማዊ እንቅስቃሴ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲቀጣጠል እንዲኖር ያደረጉት የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በተባለው መጽሐፍ መሠረት ሂትለር በአንድ ወቅት “አይሁዳውያንን በተመለከተ እኔ ያራመድኩት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለ1500 ዓመታት ስትከተል የኖረችውን መርህ ነው” ብሏል።
በባልካን አገሮች አሰቃቂ የሆነ እልቂት በተፈጸመበት ወቅት የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ትምህርቶች የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ጎረቤታሞች ተቻችለው እንዲኖሩ አላስቻሉም።
በተመሳሳይም በሩዋንዳ የቤተ ክርስቲያን አባላት የእምነት ባልደረቦቻቸውን ጨፍጭፈዋል። ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር በዚያ የተደረገው ውጊያ “ካቶሊኮችም ጭምር በኃላፊነት የሚጠየቁበት እውነተኛና የተረጋገጠ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነበር” ብሏል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ራስዋ ያለመቻቻል መጥፎ ታሪክ እንዳላት አምናለች። የሮማው ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ2000 በሮም በብዙ ሕዝብ ፊት በተደረገ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ “በቀደሙት ዘመናት ለተፈጸሙት በደሎች” ይቅርታ ጠይቀዋል። በዚሁ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ “በአይሁዳውያን፣ በሴቶች፣ በአገር ተወላጆች፣ ከባዕዳን አገሮች በመጡ ሰዎች፣ በድሆች እንዲሁም ባልተወለዱ ሕፃናት ላይ የተፈጸሙ ግፎችና ያለመቻቻል እርምጃዎች” ተለይተው ተጠቅሰዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ:- የስደተኞች ሠፈር፣ ቦስኒያና ሄርዞጎቪና፣ ጥቅምት 20, 1995
የእርስ በርስ ጦርነቱ የሚያቆምበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ሁለት የቦስኒያ ሰርብ ስደተኞች
[ምንጭ]
Photo by Scott Peterson/Liaison
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥላቻን መማር
አንድ ሕፃን አሉታዊ አመለካከቶችን ከወላጆቹ፣ ከቴሌቪዥንና ከሌላ ምንጭ ሊቀስም ይችላል