የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው የአእምሮ ሕመም ቢኖርበትስ?
የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው የአእምሮ ሕመም ቢኖርበትስ?
ጊዜው ማለዳ ሲሆን ዕለቱ ለፍራንክ ቤተሰብ ከሌላው የሥራ ቀን የተለየ አልነበረም። * እናትና አባት እንዲሁም ሁለቱ ልጆቻቸው ከመኝታቸው ተነስተው ልብሳቸውን በመለባበስ የዕለቱን ተግባራቸውን ለማከናወን ተዘጋጅተዋል። ጌይል የ14 ዓመት ልጅዋ ማት ሰዓት እንደረፈደበትና የትምህርት ቤቱ አውቶቡስ ሊያመልጠው እንደሚችል ነገረችው። ከዚያ በኋላ የተፈጸመው ነገር ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነበር። ማት በግማሽ ሰዓት ጊዜ ውስጥ የአንድን መኝታ ቤት ግድግዳ በቀለም ከመለቅለቁና የቤታቸውን ጋራዥ በእሳት ለማያያዝ ከመሞከሩም በላይ በሕንፃው ጣሪያ ሥር ባለ ክፍል ውስጥ ራሱን ሰቅሎ ለመግደል ሙከራ አደረገ።
ጌይልና ባሏ ፍራንክ በሆነው ነገር ግራ እንደተጋቡ ማትን የያዘውን አምቡላንስ ተከትለው ሄዱ። የሚያሳዝነው ይህ ክስተት የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አልነበረም። ማት በአእምሮ ሕመም መያዙን የሚጠቁሙ በርካታ ክስተቶች ተፈጸሙ። በሥቃይ ባሳለፋቸው አምስት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ራሱን ለመግደል ከመሞከሩም በላይ ሁለት ጊዜ ታስሯል፣ በሰባት የሥነ አእምሮ ሕክምና ተቋማት እንዲቆይ ተደርጓል እንዲሁም ከአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ጋር ብዙ ጊዜ እየተገናኘ ሕክምና ተደርጎለታል። በሁኔታው ግራ የተጋቡት ወዳጆችና ዘመዶች ብዙውን ጊዜ ምን መናገር ወይም ማድረግ እንዳለባቸው ይጨንቃቸው ነበር።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ በሕይወት ዘመኑ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ በአእምሮ በሽታ እንደሚጠቃ ይገመታል። ከዚህ አስደንጋጭ አኃዝ አንጻር ሲታይ ከወላጅህ፣ ከልጅህ፣ ከወንድምህ፣ ከእህትህ ወይም ከጓደኛህ መካከል አንዱ በአንጎል በሽታ የመጠቃት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። * የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው እንዲህ ያለ ሕመም ቢኖርበት ምን ልታደርግ ትችላለህ?
● የበሽታውን ምልክቶች ለይተህ እወቅ። የአእምሮ ሕመም ወዲያውኑ ተለይቶ ላይታወቅ ይችላል። ወዳጆችና የቤተሰብ አባላት የሕመሙን ምልክቶች በሆርሞን ላይ ከሚከሰት ለውጥ፣ ከአካላዊ በሽታ፣ ከባሕርይ ችግር ወይም ከአንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ሊያያይዟቸው ይችላሉ። የማት እናት ቀደም ሲል በልጅዋ ላይ አንዳንድ ለውጦች አይታ ነበር፤ ሆኖም ወላጆቹ በጠባዩ ላይ ያዩትን ለውጥ ያያያዙት ከጉርምስና ዕድሜው ጋር ነበር። በመሆኑም ችግሩ ጊዜያዊና ከዕድሜው ጋር የሚስተካከል ነገር እንደሆነ አድርገው አስበው ነበር። ይሁን እንጂ በእንቅልፍ፣ በአመጋገብና በጠባይ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ከታየ ከበድ ያለ ችግር እንዳለ ሊጠቁም ይችላል። ግለሰቡ የሕክምና ባለሙያ ጋር ሄዶ መመርመሩ ጥሩ ሕክምና እንዲያገኝና የተሻለ ሕይወት እንዲኖር ሊረዳው ይችላል።
● ስለ በሽታው ባሕርይ ለማወቅ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ስለ በሽታቸው ምርምርና ጥናት ለማድረግ ያላቸው አቅም ውስን ነው። በመሆኑም አስተማማኝ ከሆኑ አዳዲስ የመረጃ ምንጮች በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ጥረት ማድረግህ በአእምሮ ሕመም የተጠቃው የቤተሰብህ አባልም ሆነ በቅርብ የምታውቀው ሰው ምን ችግር እንዳለበት በሚገባ እንድታስተውል ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም ከሌሎች ጋር በእውቀት ላይ የተመሠረተ ግልጽ ውይይት ማድረግ እንድትችል ይረዳሃል። ለምሳሌ ያህል የማት እናት የሆነችው ጌይል ለማት አያቶች የሕክምና በራሪ ወረቀቶች የሰጠቻቸው ሲሆን ይህም ስለ በሽታው የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኙና የበኩላቸውን እርዳታ ማድረግ እንደሚችሉ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል።
● ሕክምና እንዲያገኝ አድርግ። አንዳንድ የአእምሮ በሽታዎች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ቢሆኑም እንኳ ብዙዎቹ ሕሙማን ተገቢውን የሕክምና ክትትል በማድረግ የተረጋጋና ሰላማዊ የሆነ ጥሩ ኑሮ መኖር ይችላሉ። የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ ለበርካታ ዓመታት ምንም ዓይነት እርዳታ ሳያገኙ የሚኖሩ መሆኑ ነው። ከባድ የልብ በሽታን የልብ ስፔሻሊስት ጋር ሄዶ መታከም እንደሚያስፈልግ ሁሉ የአእምሮ ሕመምንም እንዲህ ያለውን በሽታ እንዴት ማከም እንደሚቻል የሚያውቁ ባለሙያዎች ጋር ሄዶ መታከም ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል የሥነ አእምሮ ሐኪሞች አዘውትሮ ሲወሰድ የጠባይ መለዋወጥን ለመቆጣጠር፣ ጭንቀትን ለማቅለልና የተዛባ አስተሳሰብን ለማስተካከል ሊረዳ የሚችል መድኃኒት ሊያዙ ይችላሉ። *
● ሕመምተኛው እርዳታ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርግ አበረታታው። የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ላይገነዘቡ ይችላሉ። ሕመምተኛው አንድን ሐኪም ሄዶ እንዲያማክር፣ አንዳንድ ጠቃሚ የሆኑ ጽሑፎችን እንዲያነብ ወይም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት በሽታውን መቋቋም የቻለን ሰው እንዲያነጋግር ሐሳብ ልታቀርብለት ትችላለህ። ግለሰቡ ምክርህን ላይቀበል ይችላል። ይሁን እንጂ በአንተ እንክብካቤና ጥበቃ ሥር ያለ ሰው ራሱንም ሆነ ሌሎችን ሊጎዳ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ካለ አንድ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ማመንታት የለብህም።
● ግለሰቡን ጥፋተኛ አድርገህ ከመውቀስ ተቆጠብ። ሳይንቲስቶች በአንጎል ሥራ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩት ጀነቲካዊ፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች መካከል ያለውን ውስብስብ የሆነ ዝምድና አሁንም ድረስ ግልጽ በሆነ መንገድ ለይተው ማስቀመጥ አልቻሉም። በአንጎል ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ፣ ውጥረት የሚፈጥሩ አካባቢያዊ ሁኔታዎች፣ በሰውነት ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች መጠን መዛባትና ለበሽታው የሚያጋልጥ የዘር ውርስ አንድ ላይ ተዳምረው ለአእምሮ ሕመም አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። በአእምሮ ሕመም የተያዙ ሰዎችን ለደረሰባቸው ነገር ተጠያቂዎቹ ራሳቸው እንደሆኑ አድርጎ መውቀስ የሚያስገኘው ጥቅም የለም። ከዚህ ይልቅ እነርሱን ለመርዳትና ለማበረታታት ብትጥር የተሻለ ውጤት ይኖረዋል።
● ከሕመምተኛው የምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ይሁን። ሕመምተኛው ሊያደርገው የማይችለውን ነገር እንዲያደርግ የምትጠብቅበት ከሆነ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ያለበትን የአቅም ገደብ ከልክ በላይ የምታጋንን ከሆነ ራሱን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት ሊያደርገው ይችላል። ስለዚህ ከሕመምተኛው የምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን ይኖርበታል። እርግጥ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግ ዝም ብሎ መመልከት አይገባም። ልክ እንደማንኛውም ሰው የአእምሮ ሕመምተኞችም የፈጸሙት ድርጊት ከሚያስከትለው መዘዝ መማር ይችላሉ። ግለሰቡ ኃይል ለመጠቀምና ጥቃት ለመፈጸም የሚሞክር ከሆነ ለእሱም ሆነ ለሌሎች ደኅንነት ሲባል ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ወይም ደግሞ ከሌሎች ጋር ባለው
ማኅበራዊ ግንኙነት ረገድ አንዳንድ ገደቦችን መጣል ሊያስፈልግ ይችላል።● ጥሩ ግንኙነት ይኑርህ። አንዳንድ ጊዜ የምትናገራቸው ነገሮች የተሳሳተ ትርጉም ሊሰጣቸው ቢችልም እንኳ ከሕመምተኛው ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው አንዳንድ ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ ያልተጠበቀ ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም በወቅቱ ካለው ሁኔታ ጋር የማይሄድ ስሜት ሊያንጸባርቅ ይችላል። ሆኖም ሕመምተኛው የሚሰጠውን አስተያየት መተቸት በመንፈስ ጭንቀቱ ላይ ተጨማሪ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማው ከማድረግ በስተቀር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። የምትናገረው ነገር ምንም ውጤት እንደማያመጣ ሆኖ ሲሰማህ ቁጭ ብለህ አዳምጠው። ወቀሳ ከመሰንዘር በመቆጠብ ስሜቱንና ሐሳቡን ተረዳለት። ለመረጋጋትና ስሜትህን ለመቆጣጠር ጥረት አድርግ። ዘወትር እንደምታስብለት እንዲሰማው ማድረግ ከቻልክ ሁለታችሁም ትጠቀማላችሁ። በማት ላይ የታየው ሁኔታ ይህ ነው። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ “እርዳታ ሳልፈልግ እርዳታ ያደረጉልኝ” ሲል የገለጻቸውን ሰዎች ሁሉ አመስግኗል።
● የሌሎቹን የቤተሰብ አባላት ፍላጎት ቸል አትበል። መላው ቤተሰቡ የታመመውን ሰው ለመርዳት ሲረባረብ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ችላ ሊባሉ ይችላሉ። የማት እህት ኤሚ ለተወሰነ ጊዜ “የወንድሟ ሕመም የወላጆቿን ትኩረት እንደነፈጋት” ሆኖ ተሰምቷት ነበር። ወደ ራሷ ትኩረት ላለመሳብ ስትል በተቻለ መጠን የምታከናውናቸውን ነገሮች በመቀነስ ራሷን ለመደበቅ ሞከረች። ወላጆቿ ግን የወንድሟን ድክመት ማካካስ እንዳለባት በሚያስመስል ሁኔታ ብዙ እንድትሠራና የተሻለ ነገር እንድታከናውን ይጠብቁባት ነበር። በወንድማቸው ወይም በእህታቸው ሕመም ሳቢያ ችላ የተባሉ አንዳንድ ልጆች ችግር በመፍጠር የወላጆቻቸውን ትኩረት ለማግኘት ሲሞክሩ ይታያል። እንዲህ ያለ ችግር የገጠማቸው ቤተሰቦች ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት የሌሎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የፍራንክ ቤተሰብ ማት በገጠመው ችግር ሳቢያ ትኩረታቸውን ሁሉ እሱ ላይ አድርገው በነበረበት ወቅት በአካባቢው በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወዳጆቻቸው ለኤሚ ተጨማሪ ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን እርዳታ አድርገዋል።
● ለአእምሮ ጤንነት የሚበጁ ልማዶች እንዲዘወተሩ ጥረት አድርግ። የአእምሮን ጤንነት ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ለአመጋገብ፣ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ለእንቅልፍና ለማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ለየት ያለ ትኩረት መስጠትን የሚጨምር መሆን ይኖርበታል። አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ወዳጆች ጋር አንድ ላይ ተሰባስቦ ቀለል ያሉ ነገሮችን ማከናወን ብዙውን ጊዜ በሕመምተኛው ላይ ፍርሃትና ጭንቀት አያስከትልም። በተጨማሪም የአልኮል መጠጦች የሕመሙን ምልክቶች ሊያባብሱና ሕመምተኛው የሚወስዳቸውን መድኃኒቶች ሊጻረሩ እንደሚችሉ ማስታወስ ያስፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ የፍራንክ ቤተሰብ ለሁሉም በተለይ ደግሞ ለወንድ ልጃቸው የአእምሮ ጤንነት የሚጠቅም ጥሩ ልማድ ለመከተል እየጣረ ነው።
● የራስህን ጤንነት ጠብቅ። የአእምሮ ሕመምተኛ የሆነን ሰው ለማስታመም የምታደርገው ጥረት የሚያስከትልብህ ውጥረት የአንተንም ጤንነት ሊጎዳው ይችላል። ስለሆነም ለአካላዊ፣ ለስሜታዊና ለመንፈሳዊ ፍላጎቶችህ ትኩረት መስጠትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ፍራንክና ቤተሰቡ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ጌይል እምነቷ ቤተሰቧ የገጠመውን ችግር መቋቋም እንድትችል በእጅጉ እንደረዳት ይሰማታል። “ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ውጥረትን ለማቅለል ይረዳሉ” ትላለች፤ “የሚያስጨንቁንን ነገሮች ወደ ጎን ትተን ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮችና በወደፊት ተስፋችን ላይ እንድናተኩር ያደርጉናል። እፎይታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጸልያለሁ፤ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ሥቃዬን የሚያስታግስ አንድ ነገር ይፈጠራል። በይሖዋ አምላክ እርዳታ በእኛ ሁኔታ ይሆናል ብሎ ለመገመት የሚያዳግት የአእምሮ ሰላም አገኝ ነበር።”
ማት በአሁኑ ጊዜ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወጣት ሲሆን ሕይወትን በአዲስ መልክ መመልከት ጀምሯል። “የደረሰብኝ ሁኔታ የተሻልኩ ሰው እንድሆን የረዳኝ ይመስለኛል” ሲል ተናግሯል። የማት እህት ኤሚ የገጠማቸው ሁኔታ እሷንም እንደጠቀማት ትናገራለች። “ሌሎችን ለመተቸት አልቸኩልም” ትላለች። “አንድ ሰው ከበስተኋላ ምን ችግር ሊኖርበት እንደሚችል አናውቅም። ይህን የሚያውቀው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው።”
የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው የአእምሮ ሕመም ካለበት መጥፎ አመለካከት ሳትይዝ ይህን ሰው ለመስማትና ለመርዳት ፈቃደኛ መሆንህ ግለሰቡ ሕይወቱ እንዲተርፍ ብሎም ጥሩ ኑሮ እንዲኖር አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ምንጊዜም አትዘንጋ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.4 አንዳንዶች “የአንጎል በሽታ” የሚለው ስያሜ ብዙም ኅፍረት የማያስከትል በመሆኑና በሽታው ከነርቭ ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን በግልጽ ስለሚጠቁም ይህን ስም መጠቀም ይመርጣሉ።
^ አን.7 ሊገኙ የሚችሉት ጥቅሞች ሕክምናው ሊያስከትላቸው ከሚችላቸው ጉዳቶች ጋር ጎን ለጎን መታየት ይኖርባቸዋል። ንቁ! መጽሔት የትኛውንም ዓይነት ሕክምና ደግፎ አይናገርም። ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአእምሮ ሕመም መኖሩን የሚጠቁሙ አንዳንድ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች
የቤተሰብህ አባል ወይም በቅርብ የምታውቀው ሰው የሚከተሉት ምልክቶች የሚታዩበት ከሆነ ሐኪም ወይም የአእምሮ ጤና ባለሙያ ማማከር ሊያስፈልገው ይችላል:-
• ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ሐዘን ወይም ብስጭት
• ራስን ከሌሎች ማግለል
• ጎልቶ የሚታይ የስሜት መለዋወጥ
• ከልክ ያለፈ ቁጣ
• ግልፍተኛ መሆን
• ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን አላግባብ መጠቀም
• ከልክ ያለፈ ፍርሃትና ጭንቀት
• ክብደት እጨምራለሁ የሚል ከፍተኛ ስጋት
• በአመጋገብ ወይም በእንቅልፍ ልማድ ላይ የሚታይ ከፍተኛ ለውጥ
• ተደጋጋሚ የሆነ ቅዠት
• አጥርቶ ማሰብ አለመቻል
• ከእውነታው የራቀ አስተሳሰብ ወይም የቁም ቅዠት
• ስለሞት ወይም የራስን ሕይወት ስለማጥፋት ማሰብ
• ችግሮችን መቋቋምና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን በሚገባ ማከናወን አለመቻል
• በግልጽ የሚታዩ ችግሮችን አምኖ አለመቀበል
• መንስኤያቸው የማይታወቅ በርካታ አካላዊ ሕመሞች
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትናገረው ነገር ምንም ውጤት እንደማያመጣ ሆኖ ሲሰማህ ዝም ብለህ ሕመምተኛውን አዳምጠው