በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጦረኛ የነበሩ ሰዎች ሰላም ፈጣሪ ሲሆኑ

ጦረኛ የነበሩ ሰዎች ሰላም ፈጣሪ ሲሆኑ

ጦረኛ የነበሩ ሰዎች ሰላም ፈጣሪ ሲሆኑ

በታኅሣሥ 2002 የንቁ! እትም ላይ ቶሺያኪ ኒዋ የሚባል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለካሚካዚ የአጥፍቶ መጥፋት ተልእኮ የሠለጠነ የቀድሞ የጃፓን የጦር አውሮፕላን አብራሪ ታሪክ ወጥቶ ነበር። በታሪኩ ውስጥ ኒዋ በነሐሴ ወር 1945 በኪዮቶ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ሠፈር ውስጥ ሆኖ በዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከቦች ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ለመሰንዘር የበላይ ትእዛዝ ይጠባበቅ እንደነበር ተናግሮ ነበር። ሆኖም ከጥቂት ቀናት በኋላ ጦርነቱ በማብቃቱ እንዲህ ያለ ትእዛዝ ሳይሰጠው ቀረ። ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ ኒዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረና አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች በጦርነት እንደማይካፈሉ ተማረ። እንዲሁም በየትኛውም ቦታ ይኑሩ ወይም የየትኛውም አገር ተወላጅ ይሁኑ ሌሎች ሰዎችን ከልብ እንደሚያከብሩ ተገነዘበ። (1 ጴጥሮስ 2:17) ቀድሞ ጦረኛ የነበረው ኒዋ አሁን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሰዎችን አንድ የሚያደርግ መልእክት ለሌሎች የሚናገር ሰላም ፈጣሪ ሆኗል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ራስል ወርትስ በዚሁ ጦርነት ላይ በተቃራኒው ወገን ሆኖ ይዋጋ የነበረ በመሆኑ የኒዋን ታሪክ ሲያነብብ ስሜቱ ተነክቶ ነበር። ወርትስ ለኒዋ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በነሐሴ ወር 1945 በኪዮቶ አቅራቢያ ሆነህ በአካባቢው ሊካሄድ የታቀደውን ወረራ ለመመከት ስትጠባበቅ እንደነበር ገልጸሃል። እኔ ደግሞ በዚያ ወቅት በወረራው ለመካፈል የሚያስችለኝን ሥልጠና እያጠናቀቅኩ ነበር። ጦርነቱ በዚያ ወቅት ባያበቃ ኖሮ ምናልባት ሁለታችንም በዚያ ውጊያ በተለያዩ ጎራዎች ሆነን ስንፋለም እንሞት ነበር። እንደ አንተና እንደ ቤተሰብህ እኔና ባለቤቴም ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነናል። በአንድ ወቅት አንዳችን ሌላውን ከመግደል የማንመለስ ጠላቶች የነበርን ሰዎች አሁን ግን ወዳጆች ብቻ ሳይሆን ወንድማማቾች እንደሆንን ማወቁ በጣም የሚያስደስት ነው!”

እንደ ቶሺያኪ ኒዋ እና ራስል ወርትስ ሁሉ ሌሎች በርካታ ሰዎችም በአንድ ወቅት በነፍስ የሚፈላለጉ ጠላቶች የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸውና የተማሩትን በሥራ ላይ በማዋላቸው በሰላምና በአንድነት እየኖሩ ነው። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን በተግባር የሚያሳዩ አይሁዶችና አረቦች፣ አርመናውያንና ቱርኮች፣ ጀርመኖችና የሩሲያ ተወላጆች እንዲሁም ሁቱዎችና ቱትሲዎች ይገኛሉ። ይህ ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 13:35

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶሺያኪ ኒዋ እና ራስል ወርትስ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት