ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በውቅያኖሶች ውስጥ ያሉ ዝርያዎች ብዛት
“ዓለም አቀፍ የባሕር ውስጥ ሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በየሳምንቱ ከ30 በላይ አዳዲስ ዝርያዎች እያገኙ ናቸው” ሲል ላይፕጺገር ፎልክስሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ ዘግቧል። ከ53 አገሮች የተውጣጡ 300 የሚያህሉ ሳይንቲስቶች የተካተቱበት በ2000 የተጀመረውና ለአሥር ዓመት የሚቆየው የባሕር ውስጥ ፍጥረታት ቆጠራ ፕሮጀክት በመጀመሪያው ዙር ሂደት ሪፖርቱ ላይ ይህን መግለጫ አውጥቷል። ተመራማሪዎቹ “በውቅያኖሶች ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ” ያምናሉ ሲል ጋዜጣው ዘግቧል። “በውቅያኖሶች ውስጥ ካሉት የእንስሳት ዝርያዎች መካከል ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ገና እንዳልተደረሰባቸው ይገመታል።”
ውኃ ፈጅ ግብርና
“አውስትራሊያ ካሉት አሕጉሮች መካከል በጣም በረሃማ ብትሆንም የነፍስ ወከፍ የውኃ ፍጆታችን በዓለም ላይ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል” ሲል አውስትራሊያን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በአውስትራሊያ አንድ ሰው በአማካይ 900 ሊትር ውኃ በእያንዳንዱ ቀን የሚፈጅ ሲሆን በሰሜን አሜሪካ የሚኖር ሰው ግን የሚጠቀመው 600 ሊትር ነው። ዘገባው “በአውስትራሊያ ጥቅም ላይ ከሚውለው ውኃ ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆነው የሚውለው ለመስኖ ልማት ነው” ሲል ገልጿል። አንድ ኪሎ ስንዴ ለማምረት 1010 ሊትር ውኃ ያስፈልጋል። አንድ ሊትር ወተት ለማግኘት ላሞች ለግጦሽ የሚሰማሩበት መስክ 600 ሊትር ውኃ ማግኘት ያስፈልገዋል። አንድ ኪሎ ቅቤ ለማምረት ደግሞ ከ18,000 ሊትር በላይ ውኃ የሚያስፈልግ ሲሆን አንድ ኪሎ ምርጥ ሥጋ ለማግኘት 50,000 ሊትር ውኃ ያስፈልጋል። የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪም ቢሆን ከፍተኛ የውኃ ፍጆታ ያለው ተቋም ነው። አንድ ኪሎ ጥጥ ለማምረት 5,300 ሊትር ውኃ የሚያስፈልግ ሲሆን አንድ ኪሎ ሱፍ ለማዘጋጀት ደግሞ ከ171,000 ሊትር በላይ ውኃ ያስፈልጋል። ከሱፍ የተሠራ አንድ ሙሉ ልብስ ለማምረት 685,000 ሊትር ውኃ እንደሚያስፈልግ ይገመታል።
ሞቃታማ የአየር ጠባይና የዱር ፍጥረታት
“ሬድባክ የሚባሉትን ገዳይ የሆኑ የሸረሪት ዝርያዎች ጨምሮ በአውስትራሊያ የሸረሪቶች ብዛት በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። መንስኤው በዓለም ዙሪያ የሙቀት መጠን መጨመር በዱር ፍጥረታት ላይ ቀውስ ማስከተሉ ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች ገምተዋል” ሲል ዘ ዊክኤንድ አውስትራሊያን ዘግቧል። የክዊንስላንድ ሙዚየም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሮበርት ሬቨን እንዳሉት በዓመት አንዴ ብቻ እንቁላል ይጥሉ የነበሩ ሸረሪቶች ዘንድሮ ግን ሦስት ወይም አራት ጊዜ እንደሚጥሉ ይጠበቃል። “በዚህ ወቅት እንጭጭ መሆን የነበረባቸው ሸረሪቶች ገና ካሁኑ እድገታቸውን ጨርሰዋል” ብለዋል። “ዕድሜያቸው በእጥፍ የጨመረ ሸረሪቶች ላይ ጥናት እያካሄድን ነው።” የአየሩ ጠባይ ሞቃታማ መሆኑ በአእዋፍ ሕይወትም ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ተመራማሪዎች ያምናሉ። ጋዜጣው እንዲህ ይላል:- “ወትሮ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንቁላል ይጥሉ የነበሩት ባለ ሰማያዊ ቀለም የአሳ አመቴን የመሳሰሉ የወፍ ዝርያዎች አሁን ግን በዓመት ሁለቴ መጣል ጀምረዋል።” ከዚህ በተጨማሪ ወፎች “ከጊዜያቸው በፊት እንቁላል እየጣሉና በአውሮፓ የክረምቱ ወቅት ከማለፉ በፊት አስቀድመው እየተመለሱ ነው። ይህም ለውጡ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው ያመላክታል።”
የመዛል ስሜት የልብ ሕመም ምልክት ሊሆን ይችላል
አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ከባድ ድካምና እንቅልፍ ማጣት ሴቶች በልብ ሕመም ሊጠቁ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ የመጀመሪያዎቹ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ” ሲል ዘ ማያሚ ሄራልድ በዓለም አቀፍ እትሙ ላይ ዘግቧል። በጥናቱ ከተካተቱት ሴቶች መካከል የመጀመሪያው ምልክት ደረታቸው አካባቢ የተሰማቸው ውጋት እንደሆነ የተናገሩት 30 በመቶ ብቻ ሲሆኑ 71 በመቶ የሚሆኑት ግን በልብ ሕመም ከመጠቃታቸው በፊት ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ከባድ ድካም ይሰማቸው እንደነበር ገልጸዋል። የአርካንሰስ የሕክምና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጄን መክስዊኒ እንዲህ ብለዋል:- “የድካም ስሜቱ ለመግለጽ የሚያስቸግርና ከወትሮው የተለየ ነው። . . . አንዳንድ ሴቶች በጣም ስለሚደክማቸው አልጋ አንጥፎ ለመጨረስ እንኳ በየመሃሉ ለማረፍ ይገደዳሉ። . . . የልብ በሽታ ቁጥር 1 የሴቶች ቀሳፊ በሽታ ነው።” ፕሮፌሰሯ እንዲህ ብለዋል:- “ሴቶች ምልክቶቹን አስቀድመው ማወቅ እንዲችሉ ካደረግን በሕክምና በሽታውን መከላከል ወይም ማዘግየት እንችላለን።”
ተጨማሪ ጨረቃዎች ተገኙ
ቴክኖሎጂው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በእኛ ሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቁት ጨረቃዎች ብዛት በእጥፍ ጨምሯል ሲል የሜክሲኮ ናሽናል ኦቶኖመስ ዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጀው ኮሞ ቬስ? የተባለው የሳይንስ መጽሔት ዘግቧል። በ2003 መጨረሻ ላይ ሰባት የሚያህሉትን ፕላኔቶች የሚሽከረከሩ 136 ጨረቃዎች መኖራቸው የተደረሰበት ሲሆን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ሌሎች ጨረቃዎችንም እንደሚያገኙ ተስፋ ያደርጋሉ። ጨረቃ የላቸውም የሚባሉት ሜርኩሪና ቬኑስ ብቻ ናቸው። ብዙ ጨረቃዎች ያሏት ጁፒተር ስትሆን (61) ከዚያ በመቀጠል ሳተርን (31)፣ ኡራነስ (27)፣ ኔፕትዮን (13) እና ማርስ (2) ናቸው። ፕሉቶና ምድር እያንዳንዳቸው አንድ ጨረቃ አላቸው።
ማጨስን የሚመለከቱ ዜናዎች
• “ቡና ቤት፣ ምግብ ቤትና የንግድ እንቅስቃሴ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ውስጥ ሲጋራ ማጨስ የሚከለክል ሕግ በሄሌና፣ ሞንታና፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወጥቶ ተፈጻሚነት ባገኘባቸው ስድስት ወራት ውስጥ በልብ በሽታ ምክንያት
ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር 60 በመቶ ገደማ መቀነሱን ተመራማሪዎች ደርሰውበታል” ሲል ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። በከተማው ያለ አንድ ፍርድ ቤት ይህን ሕግ ከሻረ በኋላ ግን የልብ ታማሚዎች ብዛት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመልሷል። “ይህ ሁኔታ ሲጋራ የሚያጨስ ሰው አጠገብ ሆኖ ጭሱን መማግ አደገኛ መሆኑን የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው” ሲሉ የልብ ሐኪም የሆኑት ሲድኒ ስሚዝ ተናግረዋል።• “ከዚህ ቀደም የሲጋራ ኢንዱስትሪ ቀንደኛ ጠላት የነበሩት ክልላዊ መንግሥታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቋማቸውን ቀይረዋል:- በአገሪቱ ያለውን ትልቁን ሲጋራ አምራች ኩባንያ ከኪሳራ ለማዳን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው” ሲል ጆርናል ገልጿል። ምክንያቱ ምን ይሆን? ኩባንያው ከዚህ በፊት ለተላለፈበት ብይን ያቀረበው ይግባኝ እንዲታይለት 12 ቢሊዮን ዶላር ማስያዝ እንዳለበት አንድ ዳኛ በመወሰናቸው ነው። ይህ ደግሞ ኩባንያውን ለኪሳራ የሚዳርገው ከመሆኑም ሌላ ከዚህ በፊት የተፈረደበትን ብዙ ቢሊዮን ዶላር የመክፈል አቅም ያሳጣዋል። ክልላዊ መንግሥታቱ “ከክፍያው ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያገኙ አብዛኞቹ የባጀት እጥረት እንዳያጋጥማቸው ማድረግ የሚችሉት በዚህ መንገድ ነው” ሲል ጽሑፉ አመልክቷል። ይህ ሁኔታ “መንግሥታቱ አቋማቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል።” ከሁለት ሳምንት በኋላ ዳኛው ውሳኔያቸውን በመቀየር ኩባንያው አነስተኛ ገንዘብ እንዲያስይዝ ፈቅደዋል።
አርፋጅነትን መዋጋት
በኢኳዶር የሰዓት አክባሪነት አገር አቀፍ ዘመቻ ተጀምሯል። ኢኮኖሚስት መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ ማርፈድ ከሚፈጥረው የሥራ መጓተት በተጨማሪ ኢኳዶርን በዓመት 742 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣት ተገምቷል። ይህም ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ዓመታዊ ምርት ውስጥ 4.3 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። “ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕዝባዊ ስብሰባዎችና አንዳንድ ትልልቅ ዝግጅቶች የሚጀምሩት ዘግይተው ነው” ሲል ሪፖርቱ ገልጿል። የሰዓት አክባሪነት ዘመቻው አንዳንድ መልካም ውጤቶች እያስገኘ ነው። “አርፍደው ወደ ስብሰባ የሚመጡ ሰዎች እንዳይገቡ ይከለከላሉ። . . . በአገሪቱ የሚታተም አንድ ጋዜጣ [ደግሞ] ወደ ስብሰባና ወደ ተለያዩ ትልልቅ ዝግጅቶች አርፍደው የመጡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ስም ዝርዝር በየዕለቱ ያወጣል” ሲል ዚ ኢኮኖሚስት ገልጿል።
መማር ዕድሜ ይገድበዋል?
በናይሮቢ የሚታተመው ዴይሊ ኔሽን የተባለው ጋዜጣ “[በኬንያ ስምጥ ሸለቆ ክልል በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ] በሚማሩ የስድስት ዓመት ሕፃናት መካከል የአንድ ሰው ራስና ትከሻ ከሌሎቹ ጎልቶ ይታያል” በማለት ዘግቧል። እኚህ ሰው “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲችሉ” አንደኛ ክፍል የገቡ የ84 ዓመት አዛውንት ናቸው። በብዙ ክፍል የሚበልጧቸው የልጅ ልጆች ያሏቸው ቢሆንም በክፍል ውስጥ ተቀምጠው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። “ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነገሮች እየነገሩኝ ነው። እኔ ግን የሚነግሩኝ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይኑር አይኑር አላውቅም። ስለዚህ እኔ ራሴ ቅዱሱን መጽሐፍ አንብቤ እውነቱን ማወቅ እፈልጋለሁ” በማለት አዛውንቱ ለጋዜጣው ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱን ዩኒፎርም በመልበስና ሌሎችንም የትምህርት መሣሪያዎች በማሟላት ጥብቅ የሆነውን የትምህርት ቤት ደንብ ለማክበር ይጥራሉ። ይሁን እንጂ ለእሳቸው የሚፈቀዱላቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ሌሎቹ ተማሪዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉና ሲሮጡ እሳቸው “ቀስ እያሉ ወዲያ ወዲህ በማለት ሰውነታቸውን እንዲያፍታቱ ይፈቀድላቸዋል።”