ስለ መልክ ከልክ በላይ መጨነቅ
ስለ መልክ ከልክ በላይ መጨነቅ
አብዛኞቻችን መልካችንን በመስታወት ስንመለከት ሊስተካከሉ የሚችሉ አንዳንድ እንከኖች እናያለን። ስለዚህ ልብሳችንን ወይም ፀጉራችንን በማስተካከል ወይም ትንሽ መኳኳያዎችን በማከልና ራሳችንን በማሰማመር ወደ ዕለት ተዕለት ተግባራችን እንሰማራለን። በዚህ መልኩ ስለ መልካችን ማሰባችን ተፈጥሯዊና ተገቢም ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን ስለ መልካቸው ከልክ በላይ ይጨነቃሉ። ሐኪሞች ይህ ዓይነቱ ከልክ ያለፈ ጭንቀት ራሱን የቻለ በሽታ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
ዘ መርክ (የዓለም ትልቁ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ) ማኑዋል ኦቭ ዲያግኖሲስ ኤንድ ቴራፒ የተሰኘው ጽሑፍ ይህን የአእምሮ ሕመም ፍቺ ሲሰጠው “ትልቅ ጭንቀት እስከማስከተል ወይም በማኅበራዊ ሕይወት፣ በሥራ ወይም በሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ችግር እስከመፍጠር የሚያደርስ ሕመም” እንደሆነ ይገልጻል። * በዚህ ሕመም የተለከፉ ሰዎች በእውን ባይኖርም እንኳን በመልካቸው ላይ አንድ ዓይነት እንከን እንዳለ ስለሚያስቡ ወይም ያለባቸውን ትንሽ እንከን አጋንነው ስለሚመለከቱ ራሳቸውን አስቀያሚ አድርገው ያስባሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ የደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጄ ኬቨን ቶምፕሰን ይህ ችግር “ከጠቅላላው ሕዝብ ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ የሚሆኑትንና በተመላላሽነት ከሚታከሙ የአእምሮ ሕሙማን ደግሞ ከ10-15 በመቶ የሚሆኑትን የሚያጠቃ” አዲስና እምብዛም የማያጋጥም የጤና ቀውስ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አክለው ሲናገሩ “ይህን ሕመም ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ዘዴዎች እየተሻሻሉ በሄዱ መጠንና ኅብረተሰቡም እያደር ስለ መልክ የሚጨነቅ እየሆነ በመጣ መጠን አንዳንድ ተመራማሪዎች የዚህ ችግር ሥርጭት እየጨመረ መምጣቱን ያምናሉ” ብለዋል። ምንም እንኳ ይህ ችግር በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ነው። ዐዋቂ ሰዎችን በተመለከተ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በእኩል ደረጃ የሚያጠቃ ይመስላል። ይህም በአመዛኙ በሴቶች ላይ አይሎ ከሚታየው የምግብ ፍላጎት መዛባት ችግር የተለየ ያደርገዋል።
ስለ መልካቸው ከልክ በላይ የመጨነቅ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሁንም አሁንም *
መስታወት የማየትና አንዳንድ ጊዜም ከሰው የመገለል ባሕርይ ይታይባቸዋል። ይባስ ብሎ ደግሞ “ከችግሩ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጭንቀትና የአእምሮ መቃወስ አንድን ሰው የሆስፒታል ቁራኛ ከማድረጉም በላይ ራስን የመግደል ፍላጎት እንዲያድርበት ሊያደርግ ይችላል” በማለት ከላይ የተጠቀሰው ዘ መርክ ማኑዋል ይናገራል። እንግዲያውስ አንዳንዶቹ የዚህ ሕመም ሰለባዎች መልክን ለማሻሻል የሚረዳ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ መፈለጋቸው አያስደንቅም። በዚህ ሕመም ላይ ያተኮረ መጽሐፍ የጻፉት ዶክተር ካትሪን ፊሊፕስ ሲናገሩ “አብዛኛውን ጊዜ መልክን ለማሻሻል ተብሎ የሚደረገውን ቀዶ ሕክምና እቃወማለሁ። ቀዶ ሕክምና ሊቀለበስ የማይችል ነው። ይህ ችግር ያለባቸው ብዙዎቹ ሰዎች ደግሞ ቀዶ ሕክምና ካደረጉ በኋላ ቀዶ ሕክምናው ምንም እንዳልጠቀማቸው ይሰማቸዋል” ብለዋል።ይህ ሕመም አልፎ አልፎ ገና በለጋ ዕድሜ ላይ ባሉ ልጆች ላይም ይከሰታል። ዘ ጆርጅ ስትሪት ጆርናል * ላይ የወጣ ዘገባ አንድ የስድስት ዓመት ልጅ “ጥርሶቹ ቢጫ እንደሆኑ፣ ቦርጫም እንደሆነና ፀጉሩም እንደማያምር ይሰማዋል። እነዚህ ‘እንከኖች’ ለሌሎች አይታዩም፤ ልጁ ግን ሁልጊዜ ጧት ጧት ፀጉሩን በማበጠር አንድ ሰዓት ያህል ያባክናል። ያልተስተካከለ መስሎ ከታየው ፀጉሩን በውኃ አርሶ እንደገና ማበጠር ይጀምራል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ቤት የሚደርሰው አርፍዶ ነው” ሲል ይገልጻል። ይህ ልጅ አንድ ቀን ሐኪሙ ቢሮ ሲደርስ በሚያብረቀርቅ ወንበር መልኩን ለማየት ቁጢጥ እስከማለት ደርሷል።
ዓለም በአስተሳሰብህ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር አትፍቀድ
ሰዎች ድንቅ የሚባለውን መልክና ቁመና በሚያስተዋውቁ የፋሽን መጽሔቶች፣ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎች ተጥለቅልቀዋል። የማስታወቂያው ዓለም ዓላማ ግልጽ ነው። እሱም ተገቢ ነው ስለሚባለው ነገር አንድ ዓይነት ምስል ካቀረበ በኋላ ሰዎች ያንን መልክ ለማግኘት ሲሉ የለፉበትን ገንዘብ ሁሉ እንዲያፈሱ ማድረግ ነው። ከማስታወቂያውም በተጨማሪ የእኩዮች ተጽዕኖ፣ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች አካባቢ የሚሰነዘር አሳቢነት የጎደለው አስተያየት ሲታከልበት ሰዎች ከመጠን በላይ ስለ መልካቸው እንዲጨነቁ ሊያደርጋቸው ይችላል። * እርግጥ ይህ ዓይነቱ ጭንቀት በአእምሮ ሕመም ሳቢያ ከሚመጣው ስለ መልክ ከልክ በላይ የመጨነቅ ዝንባሌ የተለየ ነው።
ቆንጆ ወይም መልከ ቀና ካልሆንኩ ሌሎች ምንም ትኩረት አይሰጡኝም ብሎ ማሰብ የተሳሳተና እውነትነት የሌለው ነገር ነው። ሰዎች ጓደኛ የሚመርጡት በአብዛኛው በመልክ ላይ ተመሥርተው አይደለም። እውነት ነው፣ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳሳብ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የጓደኝነት ማጣበቂያ እውነተኛ ሙጫ ባሕርይና የሥነ ምግባር አቋም ነው። እያንዳንዳችን ስንታይ በተወሰነ መልኩ ከመጽሐፍ ጋር እንመሳሰላለን። መጽሐፉ የሚያምር ሽፋን ይኖረው ይሆናል። ነገር ግን በውስጡ የያዛቸው ነገሮች ስሜት የማይኮረኩሩ ከሆኑ አንባቢዎቹ ወዲያውኑ ማንበባቸውን ያቆማሉ። ይሁን እንጂ ሽፋኑ ምንም ይሁን ምን፣ ሲያነቡት የሚጥም ከሆነ ሰዎች ማንበባቸውን ይቀጥላሉ። ስለዚህ ሰው በመሆንህ ልታዳብራቸው በሚገቡህ ባሕርያት ላይ ለምን አታተኩርም? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስም የሚያበረታታን ይህንኑ እንድናደርግ ነው።—ምሳሌ 11:22፤ ቆላስይስ 3:8፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4
ደግሞ እውነቱን ለመናገር ዕድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ መልካችንም እየተለወጠ ይሄዳል። ሕይወት፣ ጓደኝነትና ደስታ በወጣትነት ዕድሜ በሚኖር ውበት ላይ የተመካ ከሆነ ወደፊት ይህ ውበት ሲጠፋ ምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ይጠብቀን ይሆን! ሆኖም የእኛ ሁኔታ ከዚህ የተለየ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
ዘላቂ የሆነው ውበት
ምሳሌ 16:31 [NW] “የሸበተ ፀጉር በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የክብር ዘውድ ነው” በማለት ይናገራል። በይሖዋ አምላክና የእሱን አስተሳሰብ በሚጋሩ ሁሉ ዘንድ፣ ይሖዋን በማገልገል ያረጁ ሰዎች መልክ እየጠፋ አይሄድም። እንዲያውም ባስመዘገቡት የቅንዓትና ለአምላክ የማደር ታሪካቸው ምክንያት የክብር ዘውድ የሚጎናጸፉት በስተ እርጅናቸው ነው። እንዲህ ያሉት ውድ ግለሰቦች ፍቅራችንና ጥልቅ አክብሮታችን ሊቸራቸው ይገባል።—ዘሌዋውያን 19:32
ከዚህም በላይ ይሖዋ አመጣለሁ ብሎ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ አረጋዊ ወጣት ሳይል ለታማኝ አገልጋዮቹ ሁሉ በአለፍጽምና ሳቢያ የደረሰውን መጥፎ ውጤት ያስወግዳል። እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ወደ ፍጽምና ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ አካላቸው እየታደሰ ሲሄድ ያያሉ። (ኢዮብ 33:25፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ምንኛ አስደሳች ተስፋ ነው! ከእነዚያ ሰዎች መካከል መገኘት ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ አስፈላጊ በሆነው የውበት ዓይነት ላይ ለማተኮር ተጣጣር እንጂ አርቴፊሻል በሆነውና ርኅራኄ በጎደለው የዓለም አስተሳሰብ አትመራ። እውነተኛውን ውስጣዊ ውበት ለማዳበር ከጣርክ በጣም ደስተኛና የምታምር ሰው ትሆናለህ።—ምሳሌ 31:30
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 “ከልክ በላይ ስለ መልክ መጨነቅ የብዙዎቹ የአእምሮ ሕመሞች የጋራ ምልክት ነው” በማለት ዘ ሜዲካል ጆርናል ኦቭ አውስትራሊያ ይናገራል። እነዚህ የአእምሮ ሕመሞች የመንፈስ ጭንቀትን፣ ስለ አንድ ነገር ከልክ በላይ መጨነቅንና የምግብ ፍላጎት መዛባት ችግርን ይጨምራሉ። በመሆኑም ከልክ በላይ ስለ መልክ የመጨነቅ ችግር ከምን እንደሚመጣ ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።
^ አን.5 “የወጣቶች ጥያቄ . . . መልክና ቁመናዬን ለማሳመር ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይኖርብኛልን?” የሚለውን የዚህ መጽሔት የመስከረም 2002 እትም ተመልከት። እርግጥ ከዚህ ጋር የተያያዘ ከባድ የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው የሥነ አእምሮ ሐኪም እርዳታ ሊያስፈልገው ይችላል።
^ አን.6 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሮዴ ደሴት በሚገኘው ብራውን ዩኒቨርሲቲ የሚታተም።
^ አን.8 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተሰኘው መጽሐፍ ላይ “መልክ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?” የሚለውን ምዕራፍ ተመልከት።