በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከበሽታ ጋር በተደረገው ትግል የተገኙ ድሎችና ያጋጠሙ ሽንፈቶች

ከበሽታ ጋር በተደረገው ትግል የተገኙ ድሎችና ያጋጠሙ ሽንፈቶች

ከበሽታ ጋር በተደረገው ትግል የተገኙ ድሎችና ያጋጠሙ ሽንፈቶች

ነሐሴ 5 ቀን 1942 ዶክተር አሌክሳንደር ፍሌሚንግ ከታካሚዎቻቸው አንዱ የሆኑት ወዳጃቸው ሊሞቱ ሲያጣጥሩ ተመለከቱ። እኚህ የ52 ዓመት ሰው የአከርካሪ ሜነንጃይተስ ይዟቸው ነበር። ፍሌሚንግ የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም ወዳጃቸው ሊሻላቸው አልቻለም። እንዲያውም ራሳቸውን እስከመሳት ደርሰዋል።

ፍሌሚንግ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት ወደ ሰማያዊ ያደላ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሻጋታዎች የሚሠሩት አንድ አስደናቂ ንጥረ ነገር አግኝተው ነበር። ይህን ንጥረ ነገር ፔኒሲሊን ብለው ሰይመውታል። ፔኒሲሊን ባክቴሪያዎችን የመግደል ኃይል እንዳለው ቢገነዘቡም የተጣራ ፔኒሲሊን አንጥረው ማውጣት አልቻሉም ነበር። ለቁስል ማጠቢያነት ብቻ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በ1938 ሃዋርድ ፍሎሪ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ይህን ንጥረ ነገር በሰዎች ላይ ለመሞከር በሚያስችል መጠን ማምረት ችለዋል። ፍሌሚንግ፣ ፍሎሪን ያላቸውን ፔኒሲሊን በሙሉ እንዲልኩላቸው ጠየቋቸው። የወዳጃቸውን ነፍስ ለማትረፍ የቀራቸው አማራጭ ይህ ብቻ ነበር።

ፔኒሲሊኑን ጡንቻቸው ላይ መውጋት በቂ ሆኖ ስላልተገኘ ፍሌሚንግ በቀጥታ ወዳጃቸው አከርካሪ ላይ ወጉት። ፔኒሲሊኑ ከአንድ ሳምንት እጅግም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ረቂቅ ተሕዋሳቱን በሙሉ ገድሎ በመጨረሱ የፍሌሚንግ ወዳጅ ሙሉ በሙሉ ድነው ከሆስፒታል ወጡ። በዚህ መንገድ የአንቲባዮቲኮች ዘመን በመጥባቱ የሰው ልጅ ከበሽታ ጋር ባደረገው ውጊያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ።

የአንቲባዮቲኮች ዘመን

አንቲባዮቲኮች ገና እንደተፈለሰፉ ተአምረኛ መድኃኒት እንደሆኑ ተደርገው ታይተው ነበር። መድኃኒት ያልነበራቸውን በባክቴሪያ፣ በፈንገስ ወይም በሌሎች ረቂቅ ተሕዋስያን ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን አክሞ ማዳን ተቻለ። አዲሶቹ መድኃኒቶች ምሥጋና ይግባቸውና በሜነንጃይተስ፣ በሳንባ ምችና በስካርሌት ፊቨር የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀነሰ። ሆስፒታል በተኙ ታካሚዎች ላይ ይከሰቱ የነበሩና ለሞት ይዳርጉ የነበሩ ኢንፌክሽኖችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ማዳን ተቻለ።

ከፍሌሚንግ ዘመን ጀምሮ ተመራማሪዎች በደርዘን የሚቆጠሩ ተጨማሪ አንቲባዮቲኮችን ለመፈልሰፍ የቻሉ ሲሆን አዳዲስ አንቲባዮቲኮችን ለማዘጋጀት የሚደረገው ጥረትም ቀጥሏል። ባለፉት 60 ዓመታት አንቲባዮቲኮች ከበሽታ ጋር በተደረገው ውጊያ አማራጭ ያልተገኘላቸው መሣሪያዎች ሆነው ቆይተዋል። ጆርጅ ዋሽንግተን ዛሬ ኖረው ቢሆን ኖሮ ዶክተሮች በአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ሊያድኗቸው እንደሚችሉ የማያጠራጥር ሲሆን ምናልባትም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይድኑ ነበር። አንቲባዮቲኮች ሁላችንንም ማለት ይቻላል፣ የኢንፌክሽን በሽታዎችን እንድናሸንፍ ረድተውናል። ይሁን እንጂ አንቲባዮቲኮች ደካማ ጎንም እንዳላቸው ውሎ አድሮ ሊታወቅ ችሏል።

አንቲባዮቲኮች እንደ ኤድስና ኢንፍሉዌንዛ ላሉት በቫይረስ ምክንያት ለሚመጡ በሽታዎች ምንም ዓይነት ፋይዳ የላቸውም። ከዚህም በላይ አንዳንድ አንቲባዮቲኮች የማይስማሟቸው ሰዎች አሉ። ብዙ ዓይነት ተሕዋስያንን የመግደል አቅም ያላቸው አንቲባዮቲኮች ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙትን ጠቃሚ ተሕዋስያን ጭምር ይገድላሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉ የከፋው የአንቲባዮቲኮች ችግር ከአግባብ ውጭ በብዛት መወሰዳቸው ወይም ከሚገባው ያነሰ መወሰዳቸው ነው።

ከሚገባው ያነሰ ተወሰደ የሚባለው በሽተኞች ሕመሙ ስለተሻላቸው ወይም የሕክምናው ጊዜ ስለሚረዝምባቸው የታዘዘላቸውን በሙሉ ሳይጨርሱ ሲያቆሙ ነው። በዚህ ምክንያት አንቲባዮቲኩ ወራሪዎቹን ባክቴሪያዎች በሙሉ ገድሎ ሳይጨርስ ስለሚቀር መድኃኒቶቹን የመቋቋም ችሎታ ያዳበሩ ባክቴሪያዎች ሊራቡ ይችላሉ። ለሳንባ ነቀርሳ በሚሰጥ ሕክምና ረገድ ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው እንዲህ ያለ ሁኔታ ነው።

ዶክተሮችና ገበሬዎች እነዚህን አዳዲስ መድኃኒቶች አላግባብ በብዛት በመጠቀም ረገድ ጥፋተኞች ናቸው። ማን ኤንድ ማይክሮብስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “አንቲባዮቲኮች በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገባው በላይ በብዛት የሚታዘዙ ሲሆን በሌሎች አገሮች ደግሞ በከፋ መጠን አላግባብ ይወሰዳሉ። ከብቶችን ከበሽታ ለማዳን ሳይሆን እድገታቸውን ለማፋጠን ተብሎ በብዛት እንዲመገቧቸው ተደርጓል። ረቂቅ ተሕዋስያን አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ችሎታ ሊያዳብሩ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ይህ ነው።” መጽሐፉ ሲያስጠነቅቅ “አዳዲስ አንቲባዮቲኮችን የማግኘት ዕድላችን ሊሟጠጥ ይችላል” ብሏል።

የአንቲባዮቲኮች የመፈወስ አቅም ከመዳከሙ በስተቀር የ20ኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ከፍተኛ የሕክምና ድል የተገኘበት ዘመን ነበር። የሕክምና ተመራማሪዎች ለማንኛውም በሽታ መድኃኒት የማግኘት ችሎታ ያላቸው መስሎ ነበር። እንዲያውም በክትባቶች አማካኝነት በሽታዎችን ሙሉ በሙሉ መከላከል እንደሚቻል ተስፋ ተጥሎ ነበር።

የሕክምና ሳይንስ ያገኛቸው ድሎች

የ1999 የዓለም ጤና ሪፖርት “በታሪክ ዘመናት በሙሉ በጤና አጠባበቅ ረገድ ከተገኙት ስኬቶች ሁሉ ትልቁ የክትባት መገኘት ነው” ብሏል። በጣም ሰፊ በሆኑ ዓለም አቀፋዊ የክትባት ዘመቻዎች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ነፍስ ማዳን ተችሏል። በዓለም አቀፋዊ የክትባት ፕሮግራም አማካኝነት በ20ኛው መቶ ዘመን በተደረጉት ጦርነቶች በሙሉ ከሞቱት ሰዎች የሚበልጥ ሕዝብ የፈጀው ፈንጣጣ ከዓለም ተወግዷል። በተጨማሪም ተመሳሳይ በሆነ የክትባት ዘመቻ ፖሊዮ ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ተቃርቧል። (“በፈንጣጣና በፖሊዮ ላይ የተገኘ ድል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሕፃናት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ በሽታዎች የሚከላከሉላቸው ክትባቶች ይሰጧቸዋል።

ሌሎች በሽታዎችን ደግሞ ቀለል ባሉ መንገዶች ማዳከም ተችሏል። እንደ ኮሌራ ያሉት ውኃ ወለድ በሽታዎች በቂ የሆነ የቆሻሻ ማስወገጃ ባለባቸውና ንጹሕ ውኃ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ምንም ያህል ችግር አይፈጥሩም። በብዙ አገሮች ሕክምና እንደልብ ማግኘት ስለሚቻል አብዛኛዎቹን በሽታዎች ተባብሰው ለሞት ከመዳረጋቸው በፊት መርምሮ ለማግኘትና አክሞ ለማዳን ተችሏል። በተጨማሪም የአመጋገብና የመኖሪያ አካባቢ መሻሻል፣ እንዲሁም የምግቦችን አዘገጃጀትና አጠባበቅ የሚወስኑ ሕጎች መውጣታቸው የሕዝቦች ጤና እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል።

ሳይንቲስቶች የተላላፊ በሽታዎች መነሻና ምንጭ ምን እንደሆነ ካወቁ የጤና ባለሙያዎች ወዲያው ወረርሽኙን ባለበት የሚገታ እርምጃ ይወስዳሉ። አንድ ምሳሌ ብቻ እንውሰድ። በ1907 በሳን ፍራንሲስኮ የተነሳው የቡቦኒክ ቸነፈር የከተማው አስተዳደር የበሽታው አስተላላፊ የሆኑት ቁንጫዎች መኖሪያ የሆኑትን አይጦች ለማጥፋት የሚያስችል እርምጃ በመውሰዱ ብዙ ሰዎች ሳይሞቱ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል። በሌላ በኩል ግን ይኸው በሽታ መንስኤው ባልታወቀበት ዘመን በሕንድ አገር ከ1896 ጀምሮ በ12 ዓመታት ውስጥ አሥር ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።

በሽታዎችን በመዋጋት ረገድ ያጋጠሙ ሽንፈቶች

ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ድሎች እንደተገኙ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ከጤና አጠባበቅ ዘዴ ጋር በተያያዘ የተገኙት አንዳንዶቹ ድሎች በባለጠጋዎቹ አገሮች ብቻ ተወስነው ቀርተዋል። መድኃኒት የተገኘላቸው በሽታዎች በቂ ገንዘብ በመታጣቱ ብቻ ዛሬም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገድላሉ። በታዳጊ አገሮች በርካታ ሰዎች ዛሬም በቂ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የጤና ክትትልና ንጹሕ ውኃ አያገኙም። በታዳጊዎቹ የዓለም ክፍሎች ከገጠር ወደ ትላልቅ ከተሞች የሚፈልሱት ሰዎች በጣም ብዙ በመሆናቸው እነዚህን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል። እንደነዚህ ባሉት ምክንያቶች የተነሣ ድሆቹ የዓለም ሕዝቦች የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው “አብዛኛውን የበሽታ ጭነት ለመሸከም ተገድደዋል።”

ለዚህ የተዛባ ሁኔታ ዋነኛው ምክንያት አርቆ ለማሰብ አለመቻልና ራስ ወዳድነት ነው። ማን ኤንድ ማይክሮብስ የተባለው መጽሐፍ “በጣም አስከፊ ከሆኑት ተዛማች በሽታዎች አንዳንዶቹ በሩቅ ያሉና እኛ ጋር ፈጽሞ ሊደርሱ የማይችሉ ይመስላሉ” ብሏል። “ከእነዚህ በሽታዎች አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው በሐሩር ክልል አካባቢ በሚገኙ ድሀ አገሮች የተወሰኑ ናቸው።” የበለጸጉ አገሮችና የመድኃኒት ኩባንያዎች ቀጥተኛ ጥቅም ስለማያገኙባቸው ለእነዚህ በሽታዎች ማሳከሚያ የሚሆን ገንዘብ ለመመደብ እጃቸው አልፈታ ይላቸዋል።

ለበሽታ መዛመት ምክንያት የሆነው ሌላው ነገር ደግሞ ኃላፊነት የጎደለው ባሕርይ ነው። ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው ከሚተላለፈው የኤድስ ቫይረስ የተሻለ ምሳሌ አይገኝም። ይህ ወረርሽኝ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መላውን ምድር አዳርሷል። (“ኤድስ—የዘመናችን መቅሰፍት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ኤፒዲሚዮሎጂስቱ ጆ ማክኮርሚክ “የሰው ልጆች ራሳቸው በራሳቸው ላይ የጠመጠሙት ችግር ነው” ብለዋል። “ይህን ያልኩት እንዲያው የሰዎችን ሥነ ምግባር ለመተቸት ሳይሆን ሐቁ ይህ ስለሆነ ነው።”

ሰዎች ሳይታወቃቸው ከኤድስ ቫይረስ ጋር ያበሩት እንዴት ነው? ዘ ካሚንግ ፕሌግ የተባለው መጽሐፍ የሚከተሉትን ምክንያቶች ይዘረዝራል:- ማህበራዊ ለውጦች፣ በተለይ ብዙ የወሲብ ጓደኞች መያዝ ለአባለዘር በሽታዎች መስፋፋት መንገድ በመጥረጉ ቫይረሱ ሥር እንዲሰድና የቫይረሱ ተሸካሚ የሆነ ሰው ሌሎች በርካታ ሰዎችን እንዲያስይዝ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ሌላ ሰው የተጠቀመባቸውን ሲሪንጆች የተከለከሉ እጾችን ለመውሰድ ወይም በታዳጊ አገሮች እንደሚታየው መድኃኒቶችን ለመውጋት መጠቀምም ተመሳሳይ ውጤት አስከትሏል። ከዚህም በላይ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰው የደም ንግድ የኤድስ ቫይረስ ከአንድ ሰው በደርዘን ወደሚቆጠሩ ሰዎች እንዲዛመት ምክንያት ሆኗል።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ከሚገባው በላይ ወይም ከሚገባው ያነሰ መውሰድ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ረቂቅ ተሕዋስያን እንዲስፋፉ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ችግር በጣም አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቷል። ቁስል እንዲያመረቅዝ የሚያደርገው ስታፊሎኮከስ የተባለ ባክቴሪያ በፔኒሲሊን ተዋጽኦዎች በቀላሉ ይወገድ ነበር። አሁን ግን እነዚህ የተለመዱ አንቲባዮቲኮች ፋይዳ ቢስ እየሆኑ ነው። ስለሆነም ዶክተሮች በታዳጊ አገሮች የሚገኙ ሆስፒታሎች ሊያገኙ በማይችሏቸው አዳዲስና ውድ አንቲባዮቲኮች ለመጠቀም እየተገደዱ ነው። በጣም አዲስ የሆኑት አንቲባዮቲኮች እንኳን አንዳንድ ረቂቅ ተሕዋስያንን መቋቋም ሊያቅታቸው ይችላል። በዚህም የተነሣ በሆስፒታል ውስጥ የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች በጣም የተለመዱና ለሞት የሚያደርሱ እየሆኑ ይመጣሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የአለርጂና የተዛማች በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር ሪቻርድ ክራውዜ ‘መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ረቂቅ ተሕዋስያን ዘመቻ በከፈቱበት ወቅት ላይ እንገኛለን’ በማለት በግልጽ ተናግረዋል።

ሁኔታው ተሻሽሏል ወይስ ተባብሷል?

በዚህ በ21ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከበሽታ ሥጋት ገና እንዳልተላቀቅን ግልጽ ነው። ምንም ዓይነት ልጓም ያልተገኘለት የኤድስ ወረርሽኝ፣ መድኃኒት ያሸነፉ ረቂቅ ተሕዋስያን መከሰትና እንደ ሳንባ ነቀርሳና ወባ ያሉት ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ገዳይ በሽታዎች ዳግመኛ ማገርሸት ከበሽታ ጋር የተደረገው ውጊያ ገና በድል እንዳልተጠናቀቀ ያረጋግጣሉ።

የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ጆሽዋ ሌደርበርግ “ዛሬ ያለው ሁኔታ ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ተሻሽሏል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ጥያቄያቸውን ሲመልሱ “በብዙ መልኩ ሲታይ አሁን ያለው ሁኔታ ጭራሽ ብሷል” ብለዋል። “ረቂቅ ተሕዋስያንን ችላ ብለን ቆይተናል። በዚህም የተነሣ በተደጋጋሚ ለመጠቃት ተገድደናል።” በዘመናችን የደረሰው ሽንፈት የሕክምና ሳይንስና የዓለም ብሔራት በሙሉ በሚያደርጉት ቁርጠኛ ጥረት ይቀለበስ ይሆን? ዋነኞቹ ተዛማች በሽታዎች እንደ ፈንጣጣ ለአንዴና ለዘላለም ይወገዱ ይሆን? የመጨረሻው ርዕሳችን እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በፈንጣጣና በፖሊዮ ላይ የተገኘ ድል

በጥቅምት 1977 መጨረሻ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት የመጨረሻውን የፈንጣጣ ታማሚ ተከታትሎ አገኘ። በሶማሊያ የሚኖረውና የሆስፒታል ወጥ ቤት ሠራተኛ የሆነው አሊ ማው ማሊን የያዘው ፈንጣጣ በጣም ከባድ ስላልነበረ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ድኖ ተነሳ። ከእርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በሙሉ ተከተቡ።

ዶክተሮች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሌላ ሕመምተኛ መገኘቱን በከፍተኛ ጉጉት ሲከታተሉ ቆዩ። “ፈንጣጣ የያዘው በሽተኛ” ላገኘ ሰው የ1,000 ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቂያ ተነገረ። ይህ ሽልማት ይገባኛል ብሎ የቀረበ አንድም ሰው ስላልተገኘ ግንቦት 8 ቀን 1980 የዓለም ጤና ድርጅት “ዓለምና በዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች በሙሉ በፈንጣጣ ላይ ድል ተቀዳጅተዋል” የሚል ማስታወቂያ በይፋ አወጣ። ይህ ከመሆኑ ከአሥር ዓመት በፊት ፈንጣጣ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ይገድል ነበር። በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋነኛ የሆነ ተላላፊ በሽታ ሊወገድ ቻለ። *

ሕፃናትን የአካል ጉዳተኛ የሚያደርገው ፖሊዮ ወይም ፖሊዮማይላይትስ የተባለው በሽታም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማስወገድ የሚመች ሆኖ ተገኝቷል። ጆናስ ሳልክ በ1955 የፖሊዮን ክትባት አገኘና ወዲያው በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች አገሮች የክትባት ዘመቻ ተጀመረ። ቆየት ብሎ ደግሞ በአፍ የሚወሰድ ክትባት ተሠራ። በ1988 የዓለም ጤና ድርጅት ፖሊዮን ለማጥፋት ዓለም አቀፍ የሆነ ፕሮግራም ሥራ ላይ አዋለ።

በወቅቱ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የነበሩት ግሮ ሃርለም ብሩንትላን “በ1988 ፖሊዮን ለማጥፋት ዘመቻ ስንጀምር በየቀኑ 1000 ሕፃናት በፖሊዮ ሳቢያ ሽባ ይሆኑ ነበር” ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል። “በ2001 ግን በመላው ዓመት በዚህ በሽታ የታመሙት ሕፃናት ቁጥር 1000 እንኳ አይሞላም።” ዛሬ ፖሊዮ ከአሥር ባነሱ አገሮች ብቻ ተወስኖ የቀረ በሽታ ሆኗል። በሽታውን ከእነዚህ አገሮች ፈጽሞ ለማስወገድ ግን ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት አስፈላጊ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 ፈንጣጣ እንደ አይጥና ትንኞች ባሉት አስቸጋሪ በሽታ ተሸካሚዎች የሚዛመት ባለመሆኑና የበሽታው ቫይረስ ከሰው ውጭ ሊኖር የማይችል በመሆኑ ዓለም አቀፋዊ በሆነ የክትባት ዘመቻ ለማስወገድ የሚመች በሽታ ነበር።

[ሥዕል]

አንድ ኢትዮጵያዊ ልጅ በአፍ የሚወሰድ የፖሊዮ ክትባት ሲሰጠው

[ምንጭ]

© WHO/P. Virot

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኤድስ—የዘመናችን መቅሰፍት

ኤድስ አዲሱ የዓለማችን አሳሳቢ ችግር ሆኗል። በሽታው በታወቀ በሃያ ዓመት ውስጥ ከ60 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። በርካታ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በሽታው ገና “ብዙ የማደግና የመስፋፋት ዕድል አለው።” የመዛመት ፍጥነቱ “ይታሰብ ከነበረው በጣም በልጦ የተገኘ” ሲሆን በበሽታው በጣም የተጠቁትን አገሮች በከፍተኛ ደረጃ አውድሟል።

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ “በመላው ዓለም ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ጋር የሚኖሩት ሰዎች የተሻለና ብዙ መሥራት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው” ይላል። በዚህ የተነሳ በርካታ የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች እስከ 2005 ድረስ ከአምራች ሕዝቦቻቸው ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑትን እንደሚያጡ ይታመናል። በተጨማሪም ሪፖርቱ “በአሁኑ ጊዜ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የሰዎች ዕድሜ በአማካይ 47 ዓመት ሆኗል። ኤድስ ባይኖር ኖሮ 62 ዓመት ይደርስ ነበር” ይላል።

እስከ ዛሬ ድረስ ክትባት ለማግኘት የተደረገው ጥረት ከንቱ ሲሆን በታዳጊ አገሮች ከሚገኙት ስድስት ሚሊዮን የሚያክሉ የኤድስ ሕሙማን መካከል የመድኃኒት ሕክምና የሚያገኙት 4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። እስካሁን ድረስ ለኤድስ መድኃኒት አልተገኘም። ቫይረሱ ያለባቸው ሁሉ ውሎ አድሮ መታመማቸው እንደማይቀር ዶክተሮች ያምናሉ።

[ሥዕል]

በኤች አይ ቪ ቫይረስ የተያዙ ቲ ሊምፎሳይት ሕዋሳት

[ምንጭ]

Godo-Foto

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የላቦራቶሪ ሠራተኛ አስቸጋሪ የሆነ ቫይረስ ሲመረምር

[ምንጭ]

CDC/Anthony Sanchez