በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባድ የሆኑ የእንቅልፍ በሽታዎችን መለየት

ከባድ የሆኑ የእንቅልፍ በሽታዎችን መለየት

ከባድ የሆኑ የእንቅልፍ በሽታዎችን መለየት

አንዳንድ የእንቅልፍ ችግሮች የከባድ በሽታ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ከአንድ ወር በላይ የቆየ የእንቅልፍ ማጣት ችግር ከመንፈስ ጭንቀትና ከሌሎች ከባድ ችግሮች ጋር ተዛማጅነት ሊኖረው ይችላል። በተጨማሪም ሥር የሰደደ የእንቅልፍ ማጣት ችግር ከበድ ያለ የአካል መታወክ ምልክት ሊሆን ይችላል።

በእንቅልፍ ጊዜ የሚያጋጥም የትንፋሽ መቋረጥ ችግር (ስሊፕ አፕኒያ)

ማሪዮ ቀን ላይ እንቅልፍ እየጣለው በጣም ይቸገራል። ከቤተሰቡ ጋር መኪና እየነዳ በሚጓዝበት ጊዜ ሳይታወቀው ድንገት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ስለሚወስደው ሚስቱ በጥንቃቄ ትጠብቀዋለች። ማታ ሲተኛ በጣም ከማንኮራፋቱም በላይ አንዳንድ ጊዜ ትንፋሹ ቁርጥ ስለሚል ብንን ይላል። *

ማሪዮ ያጋጠመው በእንቅልፍ ጊዜ የሚከሰት የትንፋሽ መቋረጥ ችግር ወይም ስሊፕ አፕኒያ ነው። አፕኒያ ቃል በቃል ሲተረጎም “ትንፋሽ አልባ” ማለት ነው። ስሊፕ አፕኒያ በግለሰቡ ላይ የሚፈጥረው ችግር ከአሥር ሴኮንድ እስከ ሁለት ወይም ሦስት ደቂቃ ሊቆይ ይችላል። ታማሚው ትንፋሽ አጥቶ ከተወራጨ በኋላ ተመልሶ ይተኛና ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ ትንፋሹ ይዘጋበታል። በአንድ ሌሊት ውስጥ በመቶዎች ለሚቆጠር ጊዜ ይረበሻል። አፕኒያ በሦስት ይከፈላል።

ሴንትራል አፕኒያ የሚባለው ችግር የሚፈጠረው አተነፋፈስን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል የተስተካከለ የአተነፋፈስ ትእዛዝ ማስተላለፍ ሲሳነው ነው። ኦብስትራክቲቭ ስሊፕ አፕኒያ የሚባለው ደግሞ ከጉሮሮ በስተጀርባ ያለው የአየር መተላለፊያ የላይኛው ክፍል ተዘግቶ ትንፋሽ አላስገባ ሲል የሚያጋጥም ችግር ነው። ሚክስድ አፕኒያ የሚባለው ደግሞ የሁለቱ ድብልቅ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመውም ይኼኛው ዓይነት ነው። ዓይነቱ ምንም ይሁን ምን በእንቅልፍ ጊዜ የትንፋሽ መቋረጥ ችግር ያለበት ሰው የሚኖርበት ሁኔታ በየቀኑ እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር የሚያድር ሰው ከሚያጋጥመው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ስሊፕ አፕኒያ ያለባቸው ሰዎች ሥራቸው ላይ እንዳሉ ወይም መኪና እያሽከረከሩ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ሊወስዳቸው ስለሚችል ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ ነው። በተጨማሪም የደም ግፊት መጨመር፣ የልብ መስፋትና የልብ ድካም ሊያጋጥማቸው ወይም በአንጎላቸው ውስጥ ደም ሊፈስና ለከፋ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ። የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዊልያም ደሜንት በስሊፕ አፕኒያ ምክንያት በሚመጡ የልብና የደም ዝውውር ችግሮች ምክንያት በየዓመቱ 38,000 አሜሪካውያን እንደሚሞቱ ገምተዋል።

ስሊፕ አፕኒያ በብዛት የሚታየው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ በጣም ወፍራም የሆኑ ወንዶች ላይ ቢሆንም በማንኛውም ዕድሜ፣ በትናንሽ ልጆች ላይ እንኳ ሳይቀር ሊከሰት ይችላል። ለዚህ በሽታ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ የሕክምና ዓይነቶች አሉ። ይሁንና ሁሉም ዓይነት ሕክምናዎች በባለሙያ ክትትል የሚሰጡ መሆን አለባቸው። በትንፋሽ ቱቦ መዘጋት ምክንያት ለሚያጋጥም የእንቅልፍ ችግር ቀዶ ሕክምና ከማድረግ ሌላ በጣም የተሻለ ሆኖ የተገኘው ሕክምና በትንፋሽ መተላለፊያው ላይ ቋሚ የሆነ ግፊት የሚያደርግ መሣሪያ መጠቀም ነው። ሕመምተኛው ማታ ማታ የአየር ግፊቱን ለመመጠን የሚያስችል ማስተካከያ (በሐኪም የተስተካከለ) ያለውና የትንፋሽ መዘጋት እንዳይኖር የሚያስፈልገውን የአየር መጠን ለክቶ የሚያስተላልፍ ጭንብል አፍንጫው ላይ ያደርጋል። ይህ ችግሩን ለማስወገድ ካልቻለ በሌዘር ወይም በሌላ ዓይነት ጨረር አማካኝነት የሚደረገውን ሕክምና ጨምሮ ከጉሮሮ ላይ ትርፍ ሥጋ ለማስወገድ የሚያስችል ቀዶ ሕክምና ማድረግ ይቻላል።

ናርኮሌፕሲ

ሌላው የሕክምና ክትትል የሚያስፈልገው ከእንቅልፍ ጋር የተያያዘ ችግር ናርኮሌፕሲ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን ቀን ቀን ከመጠን ያለፈ እንቅልፍ የሚያመጣ የነርቭ ችግር ነው። ለምሳሌ፣ በክ ሁልጊዜ እንቅልፍ እንቅልፍ ይለዋል። በጣም አስፈላጊ የሆነ ስብሰባ ላይ እያለ እንኳን ድንገት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ይወስደዋል። እንቅልፍ በሚወስደው ጊዜ ከእጁ ወድቆ የሚያሰማው ድምፅ ከእንቅልፉ እንዲያባንነው ሲል ቁልፍ በእጁ ይይዝ ነበር። ከጊዜ በኋላ በጣም በሚደሰትበት ጊዜም ሆነ ስሜቱ በሚሸበርበት ወቅት ጉልበቶቹ ርደው እንዲወድቅ የሚያደርግ ካታፕሌክሲ የሚባል አካላዊ ችግር አጋጠመው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ እንቅልፍ ሊወስደው ሲል ሁለመናውን ሽባ የሚያደርግና አልፎ አልፎ የሚያቃዥ ስሊፕ ፓራላይስስ የሚባል አካላዊ እክል ደረሰበት።

ናርኮሌፕሲ አብዛኛውን ጊዜ የሚጀምረው በ10 እና 30 ዓመት ዕድሜ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የዚህ በሽታ ታማሚዎች ምንም ዓይነት እንግዳ ባሕርይ ሳያሳዩ ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ያደረጉትን ነገር ፈጽሞ ማስታወስ ያቅታቸዋል። የዚህ በሽታ አሳዛኝ ገጽታ ታማሚው በጣም ሰነፍ፣ ዘገምተኛ አእምሮ ያለው ወይም ከሰው የማይገጥም እየተባለ በሽታው ሳይታወቅለት ለብዙ ዓመታት ሊቆይ መቻሉ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ እንደታየው ይህ በሽታ ሊድን የማይችል ቢሆንም የሕመሙን ምልክቶች ሊቆጣጠር የሚችል መድኃኒት በመውሰድና የአኗኗር ለውጥ በማድረግ መጠነኛ ውጤት ሊያገኙ የቻሉ ሰዎች አሉ። *

ሌሎች የእንቅልፍ ችግሮች

አንዳንድ ጊዜ ተቀናጅተው የሚገኙትና እንቅልፍን የሚያውኩት ሌሎቹ ሁለት ችግሮች ደግሞ እጆችንና እግሮችን በቀጥታ የሚነኩና በዚህም ምክንያት እንቅልፍ የሚያሳጡ ናቸው። አንደኛው በእንቅልፍ ወቅት በተወሰነ የጊዜ ርዝመት እግሮችና አንዳንዴም እጆች እንዲወራጩ የሚያደርግ ችግር ነው። ማይክልን እንውሰድ። በእንቅልፉ ላይ የተደረገ ክትትል እንዳመለከተው በእግሮቹ መወራጨት ምክንያት በአንድ ሌሊት ውስጥ 350 ጊዜ ያህል ባንኗል።

ከዚህ ለየት የሚለው ሁለተኛው ችግር ደግሞ ሕመምተኛው በእግር ጡንቻዎቹና በጉልበቶቹ ውስጥ በሚሰማው ሕመም ምክንያት እግሮቹን እንዲያንቀሳቅስ የሚያስገድደው በመሆኑ እንቅልፍ እንዳይወስደው እንቅፋት ይፈጥርበታል። * ይህ ዓይነቱ ችግር በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግና ከደም ዝውውር ችግር ጋር የሚዛመድበት ጊዜ ቢኖርም ካፌይን መጠጦችን ከመጠጣት ጋር የሚያያዝበት ጊዜም አለ። በተጨማሪም አልኮል መጠጣት አንዳንድ ጊዜ ችግሩን ሊያባብስ እንደሚችል ታውቋል።

ብሩክሲዝም የሚባለው ደግሞ ጥርስ በማፋጨት ወይም ጥርስን በመንከስ ተለይቶ የሚታወቅ የእንቅልፍ ችግር ነው። ሁልጊዜ የሚያጋጥም ከሆነ የጥርስ መጎዳትና የመንጋጋ ሕመም ስለሚያስከትል እንቅልፍ ሊነሳ ይችላል። እንደ ችግሩ ዓይነትና ደረጃ የሚሰጠውም ሕክምና ከቀዶ ሕክምና አንስቶ ጥርስ ላይ የሚጠለቅ መከላከያ እስከ ማድረግ የተለያየ ሊሆን ይችላል።

ይህ በጥቂት የእንቅልፍ ችግሮች ላይ ያደረግነው መጠነኛ ቅኝት የእንቅልፍ ችግሮችን ችላ ማለት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል። የሚሰጠው ሕክምና ቀላል ወይም የተወሳሰበ ሊሆን ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የግድ አስፈላጊ ነው። አንተም ሆንክ የቤተሰብህ አባል ለረዥም ጊዜ በቆየ እንቅልፍ የማጣት ችግር የምትሰቃዩ ወይም ማንኛውም ዓይነት የእንቅልፍ ችግር የሚታይባችሁ ከሆነ ውላችሁ ሳታድሩ የባለሙያ እርዳታ ብታገኙ ጥሩ ይሆናል። ችግሩ ሙሉ በሙሉ በሕክምና ሊወገድ ባይችልም እንኳ ሊደርስባችሁ የሚችለውን አደጋ በእጅጉ ሊቀንስላችሁና ችግራችሁን ሊያቀልላችሁ ይችላል። ወደፊት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ መሠረት “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” አምላክ ‘ሁሉን አዲስ በሚያደርግበት ጊዜ’ ማንኛውም በሽታ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል።—ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3-5

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ድንገተኛ የሆነ ትንፋሽ የሚያቋርጥ ኩርፊያ ብዙ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው አንድ ወጥ ሥርዓት ያለው ኩርፊያ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ መታየት የለበትም። እንዲህ ያለው የተለመደ ዓይነት የማንኮራፋት ልማድ በአንድ ክፍል ውስጥ የተኙ ሌሎች ሰዎችን እንቅልፍ ከማሳጣት ያለፈ ችግር አይኖረውም።

^ አን.11 ስለ ናርኮሌፕሲ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚያዝያ 8, 1991 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 19-21 ተመልከት።

^ አን.14 ስለዚህ ችግር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የኅዳር 22, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 19-20 ተመልከት።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለእንቅልፍ ችግር የሚወሰድ ማንኛውም ሕክምና የሐኪም ክትትል ያስፈልገዋል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማንኮራፋት የስሊፕ አፕኒያ ምልክት ሊሆን ይችላል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናርኮሌፕሲ አብዛኛውን ጊዜ በስህተት እንደ ስንፍና ተደርጎ ይታያል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአየር መተላለፊያ ቧንቧ ላይ የተመጠነ የአየር ግፊት የሚያደርጉ መሣሪያዎች የስሊፕ አፕኒያ ችግሮችን ለማቃለል ሊረዱ ይችላሉ