በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ ስም ላይ የተካሄደ ጦርነት

በአምላክ ስም ላይ የተካሄደ ጦርነት

በአምላክ ስም ላይ የተካሄደ ጦርነት

ሐናንያ ቤን ተራድዮን ይባላል። የሁለተኛው መቶ ዘመን አይሁዳዊ ምሁር ሲሆን ሕዝብ በአደባባይ ሰብስቦ ሰፈር ቶራህ ተብሎ ከሚጠራው ጥቅልል በማስተማር ይታወቃል። በተጨማሪም ቤን ተራድዮን በአምላክ የግል ስም በመጠቀሙና ይህንንም ስም ለሰዎች በማስተማር ይታወቃል። በመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ የአምላክ ስም ከ1,800 ጊዜ በላይ መጠቀሱን ስንመለከት ይህ ሰው ስለ አምላክ ስም ሳያስተምር ቶራን እንዴት አድርጎ ለሕዝብ ማስተማር ይችል ነበር?

ይሁን እንጂ የቤን ተራድዮን ዘመን ለአይሁዳውያን ምሁራን በጣም አደገኛ ጊዜ ነበር። አይሁዳውያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ከሆነ የሮማ ንጉሠ ነገሥት የአይሁድ እምነትን ማስተማርም ሆነ መከተል በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን ደንግጎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሮማውያን ቤን ተራድዮንን ይዘው አሠሩት። በተያዘበት ጊዜ የቶራን ቅጂ ይዞ ነበር። ለቀረበበት ክስ መልስ ሲሰጥ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማረው የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም ሲል እንደሆነ አምኗል። ሆኖም ከሞት ፍርድ አላመለጠም።

ቤን ተራድዮን በተያዘበት ዕለት በእጁ ላይ በተገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልል ከተጠቀለለ በኋላ እንጨት ላይ ታስሮ ተቃጠለ። “ቶሎ እንዳይሞትና ሥቃዩ እንዲራዘም ተብሎ ውኃ የተነከረ የሱፍ ጨርቅ ልቡ ላይ ተደርጎ ነበር” ይላል ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ። ተጨማሪ ቅጣት እንዲሆነው ሚስቱ ስትገደል ሴት ልጁ ደግሞ በዝሙት ቤት እንድታገለግል ለባርነት ተሸጣለች።

እንደዚህ ላለው የቤን ተራድዮን አሰቃቂ ግድያ ኃላፊዎቹ ሮማውያን ይሁኑ እንጂ “የመቃጠል ቅጣት የተፈጸመበት የአምላክን ስም ሙሉ ሆሄያት በመጥራቱ ነው” ይላል ታልሙድ *። አዎ፣ ለአይሁዳውያን የአምላክን የግል ስም መጥራት በጣም ከባድ ወንጀል ነበር።

ሦስተኛው ትእዛዝ

በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአይሁዳውያን መካከል የአምላክን ስም በመጠቀም ረገድ አንድ አጉል እምነት ተስፋፍቶ ነበር። ሚሽና (ለታልሙድ መሠረት የሆነው የረቢዎች ትንታኔ ጥንቅር) “መለኮታዊውን ስም እንደተጻፈ የሚጠራ ሁሉ” አምላክ ቃል በገባው የወደፊት ምድራዊ ገነት ውስጥ ዕጣ ፈንታ እንደማይኖረው ይናገራል።

በአምላክ ስም ላይ እንዲህ ያለ እገዳ የተጣለበት ምክንያት ምንድን ነው? አንዳንዶች እንደሚሉት አይሁዳውያን የአምላክ ስም በጣም ቅዱስ በመሆኑ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሊጠሩት እንደማይገባ ያምኑ ነበር። ውሎ አድሮ ደግሞ ስሙን ለመጻፍ እንኳን ማመንታት ጀመሩ። አንድ ጽሑፍ እንደሚለው እንዲህ ያለው ፍርሃት የመነጨው ስሙ የተጻፈበት ወረቀት ቆሻሻ ውስጥ ይወድቅና መለኮታዊው ስም ይረክሳል ከሚል ሥጋት ነው።

ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ “የሐወሐ የሚለውን ስም መጥራት የቀረው . . . ሦስተኛውን ትእዛዝ በትክክል ባለመረዳት ነው” ይላል። አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው አሥር ትእዛዛት ሦስተኛው “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የአምላክህን ስም ያለ አግባብ አታንሣ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስሙን ያለ አግባብ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና” ይላል። (ዘፀአት 20:7) ስለዚህም አምላክ ስሙ አለአግባብ እንዳይጠራ የሰጠው ትእዛዝ መልኩን ለውጦ አጉል እምነት ሆነ።

ዛሬ፣ አምላክ ስሙን የጠራ ሰው እንጨት ላይ ታስሮ እንዲቃጠል ይፈልጋል ብሎ የሚከራከር ሰው እንደማይኖር የታወቀ ነው! ቢሆንም የአምላክን የግል ስም በመጥራት ረገድ አይሁዳውያን የነበራቸው አጉል እምነት አሁንም አልጠፋም። በዚህ ዘመን ቴትራግራማተን “የአምላክ ሕቡዕ ስም”፣ “መጠራት የሌለበት ስም” ነው የሚሉ ሰዎች አሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ይህን ወግ ላለመተላለፍ ሲባል የአምላክን ስም የሚጠቅሱ ቃላት አነባበብ ሆን ተብሎ እንዲዛባ ተደርጓል። ለምሳሌ የአምላክ የግል ስም አሕጽሮት የሆነው ጃህ ወይም ያህ የሚለው ቃል ካህ ተብሎ ይነበባል። ሃሌ ሉያ የሚለው ቃል ደግሞ ሃሌሉካ ተብሎ ይነበባል። እንዲያውም አንዳንዶች “አምላክ” የሚለውን ቃል በሙሉ ላለመጻፍ ሲሉ በመካከል ያሉትን ሆሄያት ሳይጽፉ የጎደለ ሆሄ መኖሩን ለማመልከት ሰረዝ ብቻ ያደርጋሉ።

የአምላክን ስም ለመሰወር የተደረገ ተጨማሪ ጥረት

የአምላክን ስም የማይጠቀም ሃይማኖት የአይሁድ እምነት ብቻ አይደለም። የካቶሊክ ቄስና የአቡነ ዳማሰስ ቀዳማዊ ጸሐፊ የነበረውን ጀሮምን እንውሰድ። ጀሮም በ405 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ላቲን ቩልጌት የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ወደ ላቲን ተርጉሞ ጨረሰ። ጀሮም በዚህ ትርጉሙ ውስጥ የአምላክን ስም አላስገባም። ከዚህ ይልቅ በዘመኑ ተስፋፍቶ የሚገኘውን ልማድ በመከተል መለኮታዊውን ስም “ጌታ” እና “አምላክ” በሚሉት ቃላት ተካ። ላቲን ቩልጌት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እውቅና ያገኘ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲሆን በሌሎች የተለያዩ ቋንቋዎች ለተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መነሻ ሆኖ አገልግሏል።

ለምሳሌ ዱዌይ ቨርሽን የተባለው በ1610 የታተመው የካቶሊክ ትርጉም ከላቲን ቩልጌት ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ ነበር። በመሆኑም በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ የአምላክ የግል ስም ፈጽሞ የማይገኝ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። ይሁን እንጂ ዱዌይ ቨርሽን እንደማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የሚታይ ተራ ትርጉም አልነበረም። እስከ 1940ዎቹ ዓመታት ድረስ እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ ካቶሊኮች ዘንድ እውቅና ያገኘ ብቸኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነበር። አዎ፣ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት የአምላክ ስም በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ካቶሊኮች ተደብቆ ቆይቷል።

በተጨማሪም ኪንግ ጀምስ ቨርሽንን እንመልከት። በ1604 የእንግሊዝ ንጉሥ የነበረው ቀዳማዊ ጀምስ፣ አንድ የምሁራን ቡድን የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲያዘጋጅ አዘዘ። ከሰባት ዓመት ያህል በኋላ ኪንግ ጀምስ ቨርሽን የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አወጡ። ይህ ትርጉም ኦቶራይዝድ ቨርሽን ተብሎም ይጠራል።

በዚህ ጊዜም ተርጓሚዎቹ መለኮታዊውን ስም በጥቂት ቁጥሮች ላይ ከመጠቀማቸው በቀር በአብዛኛው አስወግደውታል። አብዛኛውን ጊዜ የአምላክ ስም “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉት ቃላት እንዲተካ ተደርጓል። ይህ ትርጉም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ዋነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሆኖ ቆይቷል። ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚለው “ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ከወጣ በኋላ ለ200 ዓመታት የወጣ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አልነበረም። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉ በእንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም በዋነኝነት ይሠራበት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ነበር።”

ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ባለፉት መቶ ዘመናት የአምላክን ስም ካስወጡት ወይም ጎላ ብሎ እንዳይታወቅ ካደረጉት ትርጉሞች ውስጥ ሦስቱ ብቻ ናቸው። በዘመናችን አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን ባዮች መለኮታዊውን ስም አለማወቃቸው ወይም ቢያውቁትም ለመጥራት ወደኋላ ማለታቸው አያስደንቅም። ባለፉት ዓመታት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአምላክን የግል ስም በትርጉሞቻቸው ውስጥ ማስገባታቸው አይካድም። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የታተሙት በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከመሆኑም በላይ ሰዎች ለአምላክ ስም ባላቸው አመለካከት ላይ ያመጡት ለውጥ የለም።

የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ድርጊት

የአምላክን ስም ያለመጥራት ልማድ መሠረቱ ሙሉ በሙሉ የሰዎች ወግ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። “አንድ ሰው የአምላክን ስም እንዳይጠራ የሚከለክል አንድም ትእዛዝ በቶራ ውስጥ አይገኝም። እንዲያውም የአምላክ ስም ተዘውትሮ ይጠራ እንደነበረ ከቅዱሳን ጽሑፎች መረዳት ይቻላል” በማለት ተመራማሪና ጁዳይዝም 101 የተባለው የዌብ ገጽ አዘጋጅ የሆኑት አይሁዳዊው ትሬሲ አር ሪች ይገልጻሉ። አዎ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት የአምላክ አገልጋዮች በስሙ ይጠቀሙ ነበር።

የአምላክን ስም ብናውቅና ብንጠራው አምላክ ወደሚቀበለው አምልኮ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይመለክበት ወደነበረው አምልኮ ይበልጥ መቅረብ እንደምንችል ግልጽ ነው። ይህም ከእርሱ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችለን የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆንልን ይችላል። ይህ ደግሞ የአምላክን ስም ብቻ ከማወቅ በጣም የተሻለ ይሆናል። እንዲያውም ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን ዝምድና እንድንመሠርት ይጋብዘናል። “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚለው ሞቅ ያለ ግብዣ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲጻፍ አድርጓል። (ያዕቆብ 4:8) ይሁን እንጂ ‘ሟች የሆነ ሰው እንዴት ሁሉን ከሚችለው አምላክ ጋር ሊዛመድ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ ከይሖዋ ጋር እንዴት ልትዛመድ እንደምትችል ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ታልሙድ የአይሁዳውያን ጥንታዊ ወግ ጥንቅር ሲሆን እጅግ ቅዱስ ተደርገው ከሚታዩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች አንዱ ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሃሌ ሉያ

“ሃሌ ሉያ” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ምናልባት “መሲሕ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውና ሐንደል በተባለው ጀርመናዊ የሙዚቃ ሊቅ የተቀናበረው የ1700 ድንቅ ዝማሬ ይሆናል። አለዚያም “ግሎሪ ሃሌ ሉጃ” በመባል የሚታወቀው “ዘ ባትል ሂም ኦቭ ዘ ሪፐብሊክ” የተባለው ዝነኛ የአሜሪካ የአገር ፍቅር መዝሙር ይሆናል። ያም ሆነ ይህ “ሃሌ ሉያ” የሚለውን ቃል ሳትሰማ አልቀረህም። ምናልባትም አዘውትረህ የምትጠቀምበት ቃል ሊሆን ይችላል። ግን ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?

ሃሌ ሉያ:- ሃሌሉያህ ከተባለው የዕብራይስጥ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ሲሆን “ያህን አመስግኑ” ማለት ነው።

ያህ:- የአምላክ ስም የሆነው የይሖዋ አሕጽሮት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ50 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ “ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል ክፍል ሆኖ ተጠቅሷል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በአንተስ ስም ውስጥ የአምላክ ስም ይኖር ይሆን?

ዛሬም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ስሞች የሚጠሩ ሰዎች ብዙ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ስሞች የዕብራይስጥ ትርጉም ውስጥ የአምላክ ስም ይገኛል። እንደነዚህ ላሉት ስሞች ምሳሌ የሚሆኑ ስሞችና ትርጉማቸው ቀጥሎ ቀርበዋል። የአንተም ስም ከእነዚህ ስሞች አንዱ ሊሆን ይችላል።

ዮሐና:- “ይሖዋ ደግ ሆኖልናል”

ኢዩኤል:- “ይሖዋ አምላክ ነው”

ዮሐንስ:- “ይሖዋ ሞገሱን አሳይቷል”

ዮናታን:- “ይሖዋ ሰጥቷል”

ዮሴፍ:- “ያህ ይጨምር” *

ኢያሱ:- “ይሖዋ ማዳን ነው”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.34 “ያህ” “የይሖዋ” አሕጽሮተ ቃል ነው።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለአምላክ የተሰጡ ሌሎች የማዕረግ ስሞች

የጥንቶቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ለአምላክ ሁሉን ቻይ፣ ፈጣሪ፣ አባትና ጌታ እንደሚሉት ያሉ በርካታ የማዕረግ ስሞች ይሰጣሉ። ሆኖም በግል ስሙ የተጠራባቸው ጊዜያት ከእነዚህ የማዕረግ ስሞች በሙሉ እጅግ በጣም ይበልጣል። አምላክ በስሙ እንድንጠቀም ፈቃዱ እንደሆነ ግልጽ ነው። የሚከተሉት ስሞች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚገኙ እንመልከት። *

ይሖዋ:- 6,973 ጊዜ

አምላክ:- 2,605 ጊዜ

ሁሉን ቻይ:- 48 ጊዜ

ጌታ:- 40 ጊዜ

ሠሪ:- 25 ጊዜ

ፈጣሪ:- 7 ጊዜ

አባት:- 7 ጊዜ

በዘመናት የሸመገለ:- 3 ጊዜ

ታላቅ አስተማሪ:- 2 ጊዜ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.40 ይህ አሃዝ የተቀመጠው በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሠረት ነው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ነገሮች እንዲሆኑ የሚያደርግ አምላክ

ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ትርጉም በተመለከተ በምሁራን መካከል አንዳንድ ልዩነት አለ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በጉዳዩ ላይ በርካታ ጥናትና ምርምር ካደረጉ በኋላ ስሙ ሐዋ የተባለው የዕብራይስጥ ግሥ እርባታ እንደሆነና “ይሆናል” የሚል ትርጉም እንዳለው አምነዋል።

ስለሆነም ሙሴ የአምላክን ስም የጠየቀበት ዘፀአት 3:14 በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም * ላይ “በዚህ ጊዜ አምላክ ሙሴን ‘የምሆነውን እሆናለሁ።’ ቀጥሎም ‘ለእስራኤል ልጆች “እሆናለሁ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው’ አለው” ተብሎ ተተርጉሟል።

አምላክ መሆን ያስፈለገውን ሁሉ መሆን ስለሚችል ይህ አተረጓጎም ትክክል ነው። ፈቃዱን ለመፈጸም ሲል መሆን የሚፈልገውን ሁሉ ከመሆን የሚያግደው አንዳች ነገር የለም። ዓላማዎቹና ተስፋዎቹ ሁሉ ምንጊዜም እውን ይሆናሉ። አምላክ ሁሉን የማድረግ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መሆኑን በማያሻማ መንገድ አስመስክሯል። ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና እንዲመጣ አድርጓል። በተጨማሪም እልፍ አእላፋት መንፈሳዊ ፍጡራንን ፈጥሯል። በእርግጥም እርሱ ነገሮች እንዲሆኑ የሚያደርግ አምላክ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.55 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐናንያ ቤን ተራድዮንን አገዳደል የሚያሳይ ቅርጽ

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ስም በጉልህ ተጽፎ የሚታይባቸው ቦታዎች

1. በሎምቦር፣ ዴንማርክ የሚገኝ የ17ኛው መቶ ዘመን ቤተ ክርስቲያን

2. በበርን፣ ስዊዘርላንድ የሚገኝ ካቴድራል ባለቀለም መስታወት

3. የሙት ባሕር ጥቅልል፣ በጥንቱ የዕብራይስጥ አጻጻፍ፣ እስራኤል፣ ከ30-50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ

[ምንጭ]

Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem

4. የስዊድን ሳንቲም 1600

[ምንጭ]

Kungl. Myntkabinettet, Sveriges Ekonomiska Museum

5. የጀርመንኛ የጸሎት መጽሐፍ 1770

[ምንጭ]

From the book Die Lust der Heiligen an Jehova. Oder: Gebaet-Buch, 1770

6. የድንጋይ ቅርጽ፣ ባቫርያ፣ ጀርመን

7. የሞዓባውያን ድንጋይ፣ ፓሪስ፣ ፈረንሳይ 830 ከክርስቶስ ልደት በፊት

[ምንጭ]

Musée du Louvre, Paris

8. የቤተ ክርስቲያን ጉልላት የቀለም ቅብ ሥዕል፣ ስዊዘርላንድ