ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ሰካራም እንስሳት
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት አልኮል መጠጣት ስካር እንደሚያስከትል የሚያውቁት ሰዎች ብቻ አይደሉም። በቅርቡ በአሳም፣ ሕንድ በሚገኝ አንድ መንደር ውስጥ አንድ የዝሆኖች መንጋ ቢራ አግኝቶ ከጠጣ በኋላ የሚያደርገው ጠፍቶት በርካታ ቤቶችን አፈራርሷል። በቦስንያ በተጣሉ የቢራ ቆርቆሮዎች ውስጥ ያገኘውን ጭላጭ ቢራ መጠጣት የለመደ አንድ ድብ ተጨማሪ ቢራ አጠጡኝ ብሎ ማስቸገር ጀመረ። የድቡ ረብሻ ያስቸገራቸው የመንደሩ ሰዎች አልኮል የሌለው ቢራ ለማስቀመጥ ወሰኑ። ይህም ጥሩ ዘዴ ሆነላቸው። ድቡ ቢራውን አጣጥሞ ቢጠጣም ሰክሮ ማስቸገሩ ግን ቆመላቸው። በሰሜናዊ ካሊፎርኒያ በመንገድ ዳር የበቀሉ ቁጥቋጦዎችን ፍሬ የበሉ ወፎች ሰክረው በተላላፊ መኪናዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። መፍትሔው ቁጥቋጦዎቹን መቁረጥ ነበር። የፈሉ ቀሰሞችን ሲቀስሙ የዋሉ ንቦች በመስከራቸው ወደ ቀፏቸው መመለስ አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀዋል ወይም ከዛፎች ጋር ተላትመዋል። ወደ ቀፏቸው መመለስ የቻሉትም ቢሆኑ በቀፎው ውስጥ ያሉትን ንቦች ከስካር ለመጠበቅ ዘብ የቆሙ ንቦች የሚያደርሱባቸውን ተቃውሞ ለመቋቋም ተገድደዋል።
እንደ ወንጀል አይቆጠርም
“በሜክሲኮ ከእስር ቤት ማምለጥ እንደ ወንጀል አይታይም” ይላል ዘ ኮሪያ ሄራልድ። “የሜክሲኮ ሕግ ሁሉም ሰው ነጻ ሆኖ የመኖር ፍላጎት እንዳለው እውቅና ይሰጣል። አንድ ሰው በነጻነት ለመኖር ሲል ማንኛውንም እርምጃ ቢወስድ ቅጣት አይበየንበትም።” እስረኞች የሚቀጡት በሚያመልጡበት ጊዜ በሌላ ሰው ወይም ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወይም ጉቦ በመስጠት ወይም ከሌሎች እስረኞች ጋር በማሴር ሕግ ከተላለፉ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አመለካከት ችግር ሊያስከትል ይችላል። የእስር ቤት ዘበኞች ማንም ሰው ለማምለጥ ቢሞክር ተኩሶ የመምታት ሥልጣን አላቸው። በዚህ ምክንያት በጣም የተራቀቁ የማምለጫ ዘዴዎች ተቀይሰዋል። ለምሳሌ ያህል በ1998 አንድ በነፍስ ግድያ የተፈረደበት ሰው ምግብ በመቀነስ በጣም ከስቶ 50 ኪሎ ግራም ሲመዝን ባለቤቱ የቆሸሹ ልብሶቹን ወደ ቤቷ ወስዳ ለማጠብ በያዘችው ሻንጣ ውስጥ ተሸክማ አውጥታዋለች። ከዘጠኝ ወር በኋላ ቢያዝም እንደገና ለማምለጥ ችሏል። ከዚያ ወዲህ ግን የት እንደደረሰ አይታወቅም።
የቤተሰብ ጭውውት አስፈላጊነት
የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “ቤተሰቦች ከማጉተምተም ያለፈ ጭውውት ስለማያደርጉ ልጆች በትክክል መናገርና ሐሳባቸውን መግለጽ እያስቸገራቸው መጥቷል” ሲል ዘግቧል። በብሪታንያ የትምህርት ጥራት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት ቤዚክ ስኪልስ ኤጀንሲ የተባለ መንግሥታዊ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት አለን ዌልስ የልጆች ችሎታ እያሽቆለቆለ የመጣው “ቤተሰቦች ቴሌቪዥን በመመልከትና ኮምፒውተር በመጠቀም የሚያሳልፉት ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ እንዲሁም አንድ ላይ ሆነው የሚመገቡበት ጊዜ እያነሰ በመምጣቱ ምክንያት ነው” ብለዋል። በነጠላ ወላጆች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ፣ የአያቶች አለመኖርና ለልጆቻቸው የሚያነቡ ወላጆች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ዌልስ ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በአራት ወይም በአምስት ዓመታቸው ትምህርት ቤት የሚገቡ ልጆች የቀድሞዎቹን ያህል “አንደበተ ርቱዕ ያልሆኑትና ሐሳባቸውን መግለጽ ያቃታቸው” በዚህ ምክንያት ነው። ዌልስ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዴት እንደሚጫወቱ ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።
ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አኗኗር
አውስትራሊያ ኢንስቲትዩት የተባለው ነጻ የምርምር ድርጅት ባካሄደው ጥናት “ከ30 እስከ 59 በሚገኝ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አውስትራሊያውያን መካከል 23 በመቶ የሚሆኑት ባለፉት 10 ዓመታት ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ ኑሮ ለመምራት ሲሉ ገቢያቸውን ቀንሰዋል” ሲል ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ዘግቧል። ጤንነታቸውን ለማሻሻልና ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት በቂ ጊዜ ለማግኘት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አጥኚዎቹ “ማርሽ መቀነስ” ብለው የሚጠሩትን ይህን አዝማሚያ በመከተል ላይ ናቸው። እነዚህ ሠራተኞች “ብዙ ገንዘብ የማያስገኝ ቢሆንም ብዙ የማያደክም ሥራ በመያዝ፣ የሥራ ሰዓታቸውን በመቀነስ ወይም ጨርሶ ሥራ በመተው ላይ ናቸው” ይላል ሄራልድ። የአውስትራሊያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ክሊቭ ሃሚልተን “ይህ ሕይወትን ከገንዘብ የማስቀደም ጉዳይ ነው። እነዚህ ኑሮ ፊቷን ያዞረችባቸው ሰዎች አይደሉም። ቅንጦት አንፈልግም ያሉና ይበልጥ ሚዛናዊ ሕይወት ለመምራት ሲሉ ሆን ብለው ገቢያቸውን የቀነሱ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።
በስፖርት ሜዳዎች የሚያጋጥም ድንገተኛ ሞት
በሃምሳዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሦስት ወንዶች በተለያዩ የጃፓን አካባቢዎች በአንድ ቀን ረዥም ርቀት ከሮጡ በኋላ በልብ ድካም በመሞታቸው የስፖርት ዶክተሮች ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ተገድደዋል። የኮቤ ስፖርት አካዳሚ ሊቀ መንበርና የሕክምና ዶክተር የሆኑት ዶክተር ማሳቶሺ ካኩ አሳሂ ሺምቡን በተባለው ጋዜጣ ላይ “80 በመቶ የሚሆኑት ድንገት የሚሞቱት ከልብ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች ነው። . . . በድንገት ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የጤና ችግር የለብህም የተባሉ ሰዎች ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል። ዶክተር ካኩ የኤሌክትሮካርዲዮግራም ምርመራ መደረግ የሚኖርበት ተመርማሪው ባረፈበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የስፖርት እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ጊዜም መሆን ይገባዋል ሲሉ መክረዋል። በተጨማሪም በጣም እስኪደክም ድረስ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነና በትንሹም ቢሆን ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ ወይም የማዞር ስሜት ከተሰማ ወዲያውኑ እንቅስቃሴውን ማቆም እንደሚገባ ይመክራሉ። “ጨዋታን ወይም ሩጫን አቋርጦ መውጣት ውርደት አይደለም” ይላሉ ዶክተር ካኩ። አክለውም “አትሌቶች ሩጫውን መጨረስ እንዳለባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ሆኖም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው እንደሆነ በጥንቃቄ መወሰን ይኖርባቸዋል” ብለዋል።
መጠጥ ብዙ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ነው
ዚ ኢንዲፐንደንት የተባለው የለንደን ጋዜጣ “ከባድ ጠጪዎች የሆኑ ሴቶችና ወጣቶች ቁጥር በጣም እየጨመረ በመሄዱ በብሪታንያ ከአልኮል ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል” ሲል ዘግቧል። “አለመጠን አልኮል በመጠጣት ምክንያት የተለያዩ ዓይነት የጉበት በሽታዎች ይዘዋቸው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ባለፉት 20 ዓመታት በእጥፍ ጨምሯል።” በዚህ ችግር ወጣቶችም ጭምር እየተነኩ መጥተዋል።
“ከአሥር ዓመት በፊት የሟቾቹ የዕድሜ ጣሪያ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የ70ዎቹ መጀመሪያ ነበር። ከ1998-2000 ግን የዕድሜው ጣሪያ ወደ 50ዎቹ መገባደጃ ዝቅ ብሏል” ይላል ሪፖርቱ። ይሁን እንጂ አልኮል አለአግባብ መጠጣት የሚያስከትለው መዘዝ በበሽታ ብቻ አያበቃም። በፈረንሣይ “በሥራ ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል ከ10 እስከ 20 በመቶ ለሚሆኑት ምክንያቱ የአልኮል መጠጥ” እንደሆነ ለ ሞንድ ዘግቧል። ከዚህም በላይ በፈረንሣይ በየዓመቱ አልኮል ጠጥተው በማሽከርከር ሳቢያ በሚፈጠሩ የመኪና አደጋዎች ምክንያት 2,700 ሰዎች ሲሞቱ 24,000 የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ይደርስባቸዋል። በተጨማሪም አልኮል 30 በመቶ ለሚሆን አምባጓሮ ምክንያት ሆኗል። አልኮልን አለአግባብ መጠጣት የሚያደርሰው የገንዘብ ኪሣራም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ለ ሞንድ እንደሚለው በ1996 በፈረንሣይ አገር አልኮል አለአግባብ በመጠጣት ምክንያት የደረሰው የገንዘብ ኪሣራ 17.6 ቢሊዮን ይሮ [19.2 ቢሊዮን ዶላር] ደርሷል።ውጥረትና በሽታ
በ8,000 ሠራተኞች ላይ የተደረገ አንድ የዳች ጥናት በኔዘርላንድ ሳይንሳዊ ምርምር ድርጅት ሪፖርት እንደተደረገው “በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ውጥረትና ድካም ለጉንፋን፣ ለጉንፋን መሰል በሽታዎችና ለጨጓራ ሕመም ያጋልጣል።” “ጥናቱ ብዙ ውጥረት ያለባቸውና በጣም አድካሚ የሆኑ ሥራዎች የሚሠሩ ሠራተኞች በጉንፋን የመያዝ ዕድላቸው ቀለል ያለ ሥራ ከሚሠሩት 20 በመቶ እንደሚበልጥ አረጋግጧል።” ለኢንፌክሽን እንደሚያጋልጡ የተደረሰባቸው ሌሎች ምክንያቶች የማታ ሥራና በመሥሪያ ቤቶች የመዋቅር ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ ስጋቶች ናቸው። “በፈረቃ [ምሽትና ሌሊት] የሚሠሩ ሠራተኞች ቀን ብቻ ከሚሠሩ ሠራተኞች የበለጠ በኢንፌክሽን የመያዝ ዕድል አላቸው” በማለት ሪፖርቱ ገልጿል።
ልጆችና መዝሙር
የላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ የጆሮ፣ የአፍንጫና የጉሮሮ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ሚካኤል ፉክስ ጌዙንትሃይት በተባለው የጀርመን የጤና መጽሔት ላይ መዘመር “የልጆችን የስብዕና እድገት የሚያፋጥን አስፈላጊ የስሜት መግለጫ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ይሁን እንጂ “የልጆች ድምፅ ጥራት ባለፉት 20 ዓመታት በጣም አሽቆልቁሏል። የድምፃቸው ቃናም ቢሆን ተለውጧል” በማለት ሐዘናቸውን ይገልጻሉ። ለዚህም ሁለት ምክንያት እንዳለው ፉክስ ይናገራሉ። አንደኛ “የዛሬዎቹ ልጆች በቤታቸው ብዙ አይዘምሩም። በቀድሞው ጊዜ ቤተሰቦች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በመዘመርና ሙዚቃ በመጫወት ሲሆን ዛሬ ግን ቴሌቪዥን በማየት ሙዚቃ ያዳምጣሉ።” ሁለተኛ፣ ልጆች በሚዘምሩበት ጊዜ ዘፋኞችን ለመምሰል ሲሉ ድምፃቸውን ያጎረንናሉ። “ልጆች ዘፋኞችን ለመምሰል በሚሞክሩበት ጊዜ በድምፅ ማውጫ አካሎቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ” በማለት ፉክስ ጽፈዋል። በዚህም ምክንያት የላንቃቸውና የአንገታቸው ጡንቻዎች በጣም ይወጠራሉ። ይህ ተጨማሪ ጫና ላንቃቸው ላይ ትናንሽ እባጮች እንዲወጡ ስለሚያደርግ የድምፃቸው ጥራት ይበልጥ ይበላሻል።
ከምድጃ አደጋ መጠበቅ
በባርክሌይ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሚያዘጋጀው ዌልነስ ሌተር የተባለ ጋዜጣ “በምድጃ ላይ የሚነድ እሳት ቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ብክለት ሊያስከትል እንዲሁም ለእሳት አደጋ ምንጭ ሊሆን ይችላል” ብሏል። ጋዜጣው ሰዎች ከእሳት አደጋና ከምድጃ እሳት ከሚወጡ ብክለቶች እንዲጠበቁ ለመርዳት የሚከተሉትን ምክሮች ይሰጣል:-
● “የጭስ ማውጫውን ንጽሕና ጠብቁ። . . . እንደ አስፈላጊነቱም ጠግኑት።”
● “በተለይ ቤታችሁ የተዘጋጋ ከሆነ ካርቦን ሞኖክሳይድ መኖሩን የሚጠቁም መሣሪያ መግዛት ያስፈልጋችሁ እንደሆነ አስቡ።”
● “ብዙ እንጨት አንድ ላይ ጨምራችሁ ከማጫጫስ ይልቅ ትንሽ በትንሽ አንድዱ።”
● “ቢያንስ ለስድስት ወራት ተቀምጦ የደረቀ እንጨት ተጠቀሙ። ደረቅ እንጨቶች ጥሩና ረዥም ጊዜ የሚቆይ ፍም ይፈጥራሉ።”
● “ንጹሕ አየር እንዲገባ መስኮታችሁን በትንሹ ክፈቱት።”
● “ምድጃችሁ በእሳት ሊያያዝ ከሚችል ግድግዳና ከቤት ዕቃ ቢያንስ አንድ ሜትር መራቁን አረጋግጡ። ለወለሉ የእሳት መከላከያ” አድርጉለት።
● “ማንኛውም ዓይነት ኬሚካል የተደረገበት ወይም ቀለም የተቀባ እንጨት፣ ካርቶን፣ ፋይዚት ወይም ፕላስቲክ አታንድዱ። እነዚህ መርዘኛ ጭስ ሊፈጥሩ ይችላሉ።”
● “ሁልጊዜም በምድጃችሁ አፍ ላይ የእሳት መከላከያ በር አድርጉ።”