ጤንነትህን ለመጠበቅ የሚረዱ ስድስት መንገዶች
ጤንነትህን ለመጠበቅ የሚረዱ ስድስት መንገዶች
በታዳጊ አገሮች የሚያጋጥም ችግር
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በተለይ ንጹሕ ውኃና በቂ የቆሻሻ ማስወገጃ በማይገኝባቸው አገሮች ንጽሕናቸውን ጠብቀው መኖር ያስቸግራቸዋል። ሆኖም የተቻለውን ያህል ጥረት ተደርጎ ንጽሕናን መጠበቅ ያስፈልጋል። በሞት ከሚቀጩት ልጆች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚሞቱት በቆሻሻ እጅ ወይም በተበከለ ምግብና መጠጥ አማካኝነት ወደ አፍ በሚገቡ ጀርሞች ምክንያት እንደሆነ ይገመታል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት በሚያሳትመው ፋክትስ ፎር ላይፍ የተባለ ጽሑፍ ላይ የወጡትን የሚከተሉትን ምክሮች በመከተል ብዙ በሽታዎችን በተለይም የተቅማጥ በሽታን ማስወገድ ይቻላል።
1 ዓይነ ምድርን በተገቢ ሁኔታ አስወግድ
በዓይነ ምድር ውስጥ ብዙ ጀርሞች ይገኛሉ። በሽታ አምጪ ጀርሞች ምግብና መጠጥ ውስጥ ከገቡ ወይም ምግብ ለማዘጋጀትና ለማቅረብ በሚያገለግሉ ዕቃዎች አሊያም እጆች ላይ ካረፉ በቀላሉ ወደ አፍ ሊገቡና በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ። የእነዚህን ጀርሞች መስፋፋት ለማገድ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ማንኛውንም ዓይነ ምድር ማስወገድ ነው። ለዚህም መጸዳጃ ቤት ወይም ጉድጓድ መጠቀም ያስፈልጋል። በቤቶች አካባቢ፣ በመተላለፊያዎችና በልጆች መጫወቻ ቦታዎች የእንስሳት ዓይነ ምድር አለመኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።
መጸዳጃ ቤት ከሌለ ዓይነ ምድርን ወዲያው መቅበር ያስፈልጋል። የልጆችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነ ምድር በሽታ ሊያመጡ የሚችሉ ጀርሞች እንዳሉበት አትዘንጉ። የልጆችም ዓይነ ምድር መጸዳጃ ቤት ውስጥ መጨመር ወይም መቀበር ይኖርበታል።
መጸዳጃ ቤቶችን አዘውትራችሁ አጽዱ። የመጸዳጃ ቤቶችን አፍ ክደኑ።
2 እጅህን ታጠብ
እጅን አዘውትሮ መታጠብ ያስፈልጋል። እጅን በሳሙናና በውኃ ወይም በአመድና በውኃ መታጠብ ጀርሞችን ለማስወገድ ይረዳል። እጅን በውኃ ማለቅለቅ ብቻውን በቂ አይሆንም። ሁለቱም እጆች በሳሙና ወይም በአመድ ታሽተው መታጠብ አለባቸው።
ከተጸዳዳህ በኋላ ወይም ሕፃን ልጅ ተጸዳድቶ መቀ
መጫውን ከጠረግህ በኋላ እጅህን መታጠብ ይኖርብሃል። በተጨማሪም እንስሳትን ከነካካህ ምግብ ከመንካትህና ልጆችን ከማብላትህ በፊት እጅህን መታጠብ ያስፈልግሃል።እጅ መታጠብ ሰዎችን በሽታ ከሚያመጡ ትላትል ይጠብቃል። እነዚህ ትላትል በጣም ጥቃቅን በመሆናቸው በአጉሊ መነጽር ካልሆነ በቀር እንዲሁ ማየት አይቻልም። በዓይነ ምድርና ሽንት ውስጥ፣ በተጠራቀመ ውኃና አፈር ውስጥ እንዲሁም በጥሬ ወይም በደንብ ባልበሰለ ሥጋ ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ትላትል ወደ ሰውነት እንዳይገቡ ለመከላከል የሚቻልበት ዋነኛ መንገድ እጅን መታጠብ ነው። በተጨማሪም መጸዳጃ ቤት አካባቢ በምትሆንበት ጊዜ ጫማ ማድረግህ በአካባቢው የሚገኙ ትላትል በእግርህ በኩል ወደ ሰውነትህ እንዳይገቡ ለመከላከል ይረዳሃል።
አብዛኛውን ጊዜ ልጆች እጃቸውን አፋቸው ውስጥ ስለሚከቱ በተለይ ከተጸዳዱ በኋላና ምግብ ከመብላታቸው በፊት እጃቸውን አዘውትራችሁ እጠቧቸው። እጃቸውን እንዴት እንደሚታጠቡና በመጸዳጃ ቤቶች ወይም ሽንት በሚሸናባቸውና ዓይነ ምድር በሚጣልባቸው አካባቢዎች እንዳይጫወቱ አስተምሯቸው።
3 ፊትህን በየቀኑ ታጠብ
ዓይንህ እንዳይታመም ፊትህን በውኃና በሳሙና በየቀኑ ታጠብ። የልጆችም ፊት መታጠብ ይኖርበታል። የቆሸሸ ፊት ጀርሞችን የሚሸከሙ ዝንቦችን ይስባል። እነዚህ ጀርሞች የዓይን ሕመም አልፎ ተርፎም ዓይነ ሥውርነት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የልጆችህ ዓይኖች ጤናማ መሆናቸውን አዘውትረህ ተመልከት። ጤናማ ዓይኖች አንጸባራቂና እርጥብ ናቸው። የልጁ ዓይኖች ደረቅ፣ ቀይ ወይም የተቆጡ ከሆኑ አሊያም ፈሳሽ ካላቸው ልጁን ወደ ሐኪም መውሰድ ይገባል።
4 ንጹሕ ውኃ ብቻ ተጠቀም
በንጹሕ ውኃ የሚጠቀሙና ውኃቸው በጀርሞች እንዳይበከል ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቤተሰቦች ብዙ ጊዜ በበሽታ አይጠቁም። የምትጠቀምበት ውኃ በደንብ ከተሠራና በቂ እድሳት ከሚደረግለት ቧንቧ ወይም ካልተበከለ ጉድጓድና ምንጭ የሚገኝ ከሆነ ንጹሕ መሆኑ አይቀርም። ከኩሬ፣ ከወንዝ ወይም ክፍት ከሆነ ማጠራቀሚያ የሚቀዳ ውኃ ንጽሕናው አስተማማኝ ስለማይሆን መፍላት ይኖርበታል።
የውኃ ጉድጓዶች መከደን ይኖርባቸዋል። ውኃ ለመቅዳትና ለማስቀመጥ የሚያገለግሉ እንደ ባልዲ፣ ገመድና እንስራ የመሰሉ ዕቃዎች በየጊዜው መጽዳትና ንጹሕ ቦታ ላይ መቀመጥ ይኖርባቸዋል እንጂ መሬት ላይ መጣል አይገባቸውም። እንስሳት ወደ መጠጥ ውኃ ምንጮችና
ወደ ሰው መኖሪያ ቦታዎች መቅረብ የለባቸውም። የመጠጥ ውኃ በሚቀዳባቸው አካባቢዎች ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ወይም ኬሚካሎች መርጨት አይገባም።ውኃ ንጹሕ በሆነና በተከደነ ዕቃ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል። ውኃ የምናስቀምጥበት ዕቃ መክፈቻና መዝጊያ ያለው ቧንቧ ቢደረግለት ጥሩ ይሆናል። ቧንቧ ከሌለው ንጹሕ በሆነ ጭልፋ ወይም ጣሳ መቅዳት ይገባል። ንጹሕ ባልሆነ እጅ የመጠጥ ውኃን መንካት በፍጹም አይገባም።
5 የምትመገባቸውን ምግቦች ከጀርሞች ጠብቅ
ምግቦችን ጥሩ አድርጎ በማብሰል ጀርሞችን መግደል ይቻላል። ማንኛውም ምግብ በተለይም የከብትና የዶሮ ሥጋ በደንብ መብሰል ይኖርበታል። ጀርሞች በደንብ ባልሞቁ ምግቦች ውስጥ ፈጥነው ይራባሉ። ስለዚህ ማንኛውም ምግብ በተቻለ መጠን ከእሳት እንደወጣ መበላት ይኖርበታል። ከሁለት ሰዓት በላይ ማቆየት ካስፈለጋችሁ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ቦታ ማስቀመጥ ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ሌላ ጊዜ መመገብ የምትፈልጉትን የበሰለ ምግብ በደንብ ከድናችሁ አስቀምጡ። እንዲህ ማድረግ ምግብን ከዝንብና ከሌሎች ነፍሳት ይጠብቃል። ምግቡን ከመብላታችሁ በፊት ማሞቅ ይኖርባችኋል።
ለሕፃናት ከእናታቸው ጡት የተሻለ አስተማማኝና ጥሩ ወተት ማግኘት አይቻልም። የፈላ ወይም በፋብሪካ የታሸገ የከብት ወተት ካልፈላ ወተት ይሻላል። ሕፃኑ በጠባ ቁጥር በፈላ ውኃ የማታጥቡት ከሆነ በጡጦ አትጠቀሙ። በጡጦ ውስጥ ሕፃኑን እንዲያስቀምጠው የሚያደርጉ ጀርሞች ይኖራሉ። ሕፃናትን ጡት ማጥባት ወይም ንጹሕ በሆነ ኩባያ ማጠጣት የተሻለ ይሆናል።
ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን በንጹሕ ውኃ እጠቡ። በተለይ ጥሬያቸውን የሚበሉ ምግቦች ለሕፃናትና ለልጆች ከመሰጠታቸው በፊት በደንብ መታጠብ ይኖርባቸዋል።
6 የቤት ውስጥ ጥራጊዎችን በተገቢ ሁኔታ አስወግድ
ዝንቦች፣ በረሮዎችና አይጦች ጀርም ይሸከማሉ። እነዚህ ፍጥረታት የሚራቡት በቆሻሻ ውስጥ ነው። በምትኖሩበት አካባቢ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከሌለ ከቤት የሚወጣውን ጥራጊ ለመቅበር ወይም ለማቃጠል በሚያስችል ጉድጓድ ውስጥ አጠራቅሙ። ቤታችሁ ከጥራጊና ከቆሻሻ ውኃ የጸዳ እንዲሆን አድርጉ።
እነዚህን ምክሮች ሥራ ላይ ማዋል ስትጀምሩ ብዙም ሳይቆይ የተለመደ የዕለት ተዕለት ሥራችሁ ክፍል ይሆናሉ። አስቸጋሪ ወይም ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ አይደሉም። ከዚያ ይልቅ የራሳችሁንና የቤተሰባችሁን ጤንነት ይጠብቁላችኋል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጸዳጃ ቤት ከሌለ ዓይነ ምድርን ወዲያው መቅበር ያስፈልጋል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዘውትረህ እጅህን ታጠብ
[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፊትህን በውኃና በሳሙና በየቀኑ ታጠብ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በንጹሕ ውኃ የሚጠቀሙና ውኃቸው በጀርሞች እንዳይበከል ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቤተሰቦች በበሽታ አይጠቁም
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌላ ጊዜ መመገብ የምትፈልጉትን የበሰለ ምግብ በደንብ ከድናችሁ አስቀምጡ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤት ውስጥ ጥራጊ በየቀኑ መቀበር ወይም መቃጠል ይኖርበታል