ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በመላው ዓለም ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ነው
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “የሕፃናት ከመጠን በላይ መወፈር መላውን ዓለም ያዳረሰ ወረርሽኝ ሲሆን ችግሩንም ከሥሩ ለማስወገድ ለዚህ ዋነኛ መንስኤ ከሆነው ከአሸር ባሸር ምግብ መነሳት ይኖርብናል” ሲል ዘግቧል። “የውፍረት መከላከል ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል ባቀረበው መረጃ መሠረት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች 10 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ከልክ በላይ ወፍራሞች ናቸው።” ማልታ (33 በመቶ)፣ ኢጣሊያ (29 በመቶ) እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ (27 በመቶ) የቀዳሚነቱን ደረጃ ይዘዋል። በቺሊ፣ በሜክሲኮና በፔሩ ከ4 እስከ 10 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ከመጠን በላይ ወፍራሞች ናቸው። በአፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ከቀጭኖቹ ይልቅ የወፍራሞቹ ልጆች ቁጥር ይበልጣል። ውፍረት ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው? “በአሜሪካ አንድ ልጅ በዓመት ውስጥ በአማካይ 10,000 የሚያክሉ የምግብ ማስታወቂያዎችን ሲመለከት ከእነዚህ ማስታወቂያዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት አሸር ባሸር ምግቦችን፣ ለስላሳ መጠጦችን፣ ከረሜላዎችንና ሌሎች ስኳር ያለባቸው ምግቦችን የሚያስተዋውቁ ናቸው። እነዚህ ምግቦች በሙሉ ብዙ ትርፍ የሚያስገኙ ይሁኑ እንጂ በምግብነት የሚሰጡት ጥቅም በጣም ዝቅተኛ ነው” በማለት ዘ ዋሽንግተን ፖስት መልሱን ይሰጣል። “የማስተዋወቂያ ዘመቻዎች አሸር ባሸር ምግቦችንና ለስላሳ መጠጦችን ከአሻንጉሊቶች፣ ከተለያዩ ጨዋታዎች፣ ከትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፣ ከፊልሞችና ዝነኛ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር አዛምደው ያቀርባሉ። . . . ታዲያ ባሁኑ ጊዜ ልጆች ከሚመገቡት ጠቅላላ ካሎሪ ውስጥ 15 በመቶውን ከአሸር ባሸር ምግቦች፣ 10 በመቶ የሚሆነውን በስኳር ከጣፈጡ ለስላሳ መጠጦች እንዲሁም ከፍራፍሬና ከአትክልት ደግሞ መመገብ ይኖርባቸዋል ከሚባለው መጠን ግማሹን ብቻ የሚያገኙ መሆናቸው ምን ያስደንቃል?”
ንቦች ዝሆኖችን ያርቃሉ
በኬንያ የዝሆኖች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጥቷል፤ ይሁን እንጂ ይህ ሌላ ችግር አስከትሏል። አካባቢውን የሚያጥለቀልቁ ዝሆኖች ዛፎችንና ሰብልን ያጠፋሉ። በተጨማሪም በአማካይ በየሁለት ሣምንቱ አንድ ሰው በዝሆን ተረግጦ ይሞታል። ይሁን እንጂ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ፍሪትስ ቮልራት ዝሆኖችን ሊያርቃቸው የሚችል አንድ ነገር አግኝተዋል። ዝሆኖች የንብ ቀፎ በሚነካኩበት ጊዜ “ንቦቹ ዝም ብለው አይመለከቷቸውም” ይላሉ። “ለበርካታ ኪሎ ሜትሮች እያሯሯጡ ያባርሯቸዋል።” ንቦቹ ዝሆኖቹን ሊያማቸው የሚችል ቦታ ማለትም በዓይናቸው ዙሪያ፣ ከጆሯቸው በስተጀርባ፣ ኩንቢያቸውና ሆዳቸው ላይ ይነድፏቸዋል። ቮልራት ንብ የገባባቸውና ያልገባባቸው የአፍሪካ ቀፎዎችን ዝሆኖቹ በሚያዘወትሩባቸው ጫካዎች ውስጥ በሚገኙ ዛፎች ላይ ሰቀሉ። እንስሶቹ ንብ ያለባቸው ቀፎዎች ከተሰቀሉባቸው ዛፎች በሙሉና ባዶ ቀፎ ከተሰቀሉባቸው ዛፎች ደግሞ አንድ ሦስተኛ ከሚሆኑት እንደራቁ ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። ቀፎ ካልተሰቀለባቸው ዛፎች ግን ከአሥሩ በዘጠኙ ላይ ጉዳት አድርሰዋል። በተጨማሪም የተቆጡ ንቦችን ድምፅ በድምፅ ማጉያ መሣሪያ ሲሰሙ እንኳ ዝሆኖቹ እንደሚሸሹ ቮልራት ተገንዝበዋል።
“የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አይፈልጉም”
በኢጣሊያ ካቶሊክ ሆኖ የተጠመቀ ሰው “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ መቆጠር ባይፈልግ” በአሁኑ ጊዜ ይህ ፍላጎቱ ሊሟላለት እንደሚችል ኢል ሶለ-24 ኦረ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ከአሁን በፊት “የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ እንደማጥፋት ይቆጠራል” በሚል ሰበብ ስሙ ከተጠማቂዎች መዝገብ ላይ እንዲፋቅለት የሚጠይቅ ሰው ጥያቄው ተቀባይነት አያገኝም ነበር። ሆኖም ከቤተ ክርስቲያን መዝገብ ስማቸው እንዲሠረዝላቸው የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች አቤቱታ በማቅረባቸው የግለሰብ መረጃዎች ጥበቃ መሥሪያ ቤት ኃላፊ በአብያተ ክርስቲያናት የጥምቀት መዝገብ ላይ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አይፈልግም” የሚል ማስታወሻ እንዲጻፍ ፈቅደዋል። እስካሁን ድረስ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የሦስት የቤተ ክርስቲያን የቀድሞ አባላትን ጥያቄ ተቀብለው ቀሳውስት ጥያቄያቸውን እንዲፈጽሙላቸው አዝዘዋል።
የሥነ ተዋልዶ ትምህርት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኗል
ከጀርመን የተገኙ ኦፊሴላዊ አኃዞች እንደሚያመለክቱት ከ1996 እስከ 2001 ባሉት ዓመታት ከ15 እስከ 17 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴት ልጆች የሚፈጽሙት ውርጃ 60 በመቶ፣ ከዚያ በሚያንሱት ደግሞ 90 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ይላል ደር ሽፒገል። የኮብለንዝ-ላንዳው ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኖርበርት ክሉገ ልጆች ለአካለ መጠን የሚደርሱበት ዓመት እየቀነሰ ከመሄዱ አንጻር ‘የሚሰጣቸው የሥነ ተዋልዶ ትምህርት በአግባብነቱም ሆነ በወቅታዊነቱ መጨመር ሲገባው እየቀነሰ መጥቷል’ ብለዋል። ልጆች ስለ ሥነ ተዋልዶ ማወቅ የሚኖርባቸው አሥር ዓመት ሳይሞላቸው ነው። ብዙ ወላጆች ግን ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ወደ ኋላ ይላሉ በማለት ክሉገ ገልጸዋል። በርሊነር ሞርገንፖስት እንደዘገበው ከሆነ በቦን የሚገኘው የወላጆች ፌዴራል ጉባኤ ወላጆች ለልጆቻቸው የሥነ ተዋልዶ ትምህርት በሚሰጡበት ጊዜ ማተኮር ያለባቸው በባዮሎጂያዊ ሂደት ላይ ሳይሆን እንደ “ፍቅርና ዝምድና” ባሉት ስሜታዊ ነገሮች ላይ መሆን ይገባዋል ሲል ወላጆችን መክሯል።
ሁለት ዓይነት የነርቭ አውታሮች?
የሰው ልጆች ፍቅርንና መውደድን የሚያጣጥሙበት የተለየ የነርቭ አውታር እንዳላቸው ቢልት ደር ቪሰንሻፍት የተባለው የጀርመንኛ ሳይንሳዊ መጽሔት ገልጿል። የስዊድን ሳይንቲስቶች ዋነኛው የመዳሰስ ስሜቷ በድን የሆነባት አንዲት ሴት በለስላሳ ብሩሽ ስትዳሰስ የደስታ ስሜት እንደሚሰማት ተገንዝበዋል። ይህ የደስታ ስሜት በቆዳዋ ውስጥ ከሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ የነርቭ አውታር የመነጨ እንደሆነ ደርሰውበታል። እነዚህ አዝጋሚ የማስተላለፍ ኃይል ያላቸው የነርቭ ጭረቶች ታክታይል ሲ ፋይበርስ ይባላሉ። ይህ የነርቮች አውታር የሚቀሰቀሰው ለስለስ ባለ ዳበሳ ሲሆን መልእክቱን ውስጣዊ ስሜቶችን ለሚከታተለው የአንጎል ክፍል ያስተላልፋል። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን የሰው ልጅ ሁለት የነርቭ ሥርዓት ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ ሐሳብ ሲሰጥ “ፈጣን የማስተላለፍ ችሎታ ያላቸው የነርቭ ጭረቶች የሚያድጉት ከልደት በኋላ ቀስ ብለው ሲሆን አዝጋሚ የማስተላለፍ ችሎታ ያላቸው ግን ሥራቸውን የሚጀምሩት ሕፃኑ ከተወለደ ጀምሮ ምናልባትም በማኅፀን ውስጥ ሳለ ጀምሮ ሳይሆን አይቀርም። አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ከወላጃቸው
ዳሰሳ በፊት ዳሰሳው የሚያስተላልፈው ፍቅር ሳይሰማቸው አይቀርም።”ለድምፃችሁ እንክብካቤ አድርጉ
የደቡብ አፍሪካው ናታል ዊትነስ ጋዜጣ “የድምፅ መታወክ በጣም የተስፋፋ ግን ብዙም ትኩረት የማይሰጠውና ሕክምና የማይደረግለት ችግር ነው” በማለት ተናግሯል። የንግግርና የማዳመጥ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ጁሊ ባርክማየር እንደሚሉት እንዲህ ያለው ሁከት የሚመጣው ከመጠን ያለፈ ድምፅ በማሰማት ምክንያት የድምፅ አውታሮች ሲቆጡ ወይም በእነዚህ አውታሮች ላይ እባጭ የመሰለ ነገር ሲፈጠር ነው። በድምፅ አውታሮች ላይ ዳት ከሚያደርሱ ነገሮች መካከል መጮህ፣ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ጎርናና ድምፅ ማሰማት፣ እንደ ሲጋራ ጭስ ወይም የፋብሪካ ጭስ የመሰለ መርዛማ ነገር በትንፋሽ ማስገባት እንደሚገኙበት አንድ የታወቀ የሕክምና መጽሐፍ ገልጿል። “የድምፅ አውታሮች ከልክ በላይ በሚርገበገቡበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ሊጋጩ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት እንደ መጅ የመሰለ ለስላሳ እባጭ ይፈጠራል” ይላል ናታል ዊትነስ። ይህም ጎርናና እና የሚቆራረጥ ድምፅ ይፈጥራል። “ለሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ የቆየ በግልጽ የሚታወቅ የድምፅ ለውጥ ከገጠማችሁ በሐኪም ብትመረመሩ ጥሩ ይሆናል” በማለት የጋዜጣው ጽሑፍ ይመክራል። “በድምፃችሁ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ . . . አትጩሁ ወይም ከልክ በላይ ጮክ ብላችሁ አትናገሩ። በጣም አትሳሉ ወይም ቶሎ ቶሎ ጉሮሯችሁን ለማጥራት አትሞክሩ። ብዙ ውኃ ጠጡ። [እንደ ቡናና ሻይ ያሉ] ካፌይን ያለባቸውን መጠጦች ቀንሱ። አታጭሱ፣ ከመናገራችሁ በፊት ደግሞ ወደ ውስጥ አየር ሳቡ። . . . በመጨረሻም ድምፃችሁ እረፍት እንዲያገኝ አድርጉ።”
አደገኛ ዕጽዋት
የሜክሲኮ ሲቲው ኤል ፊናንስየሮ ጋዜጣ “ዕጽዋት ተፈጥሯዊ በመሆናቸው በሰውነት ላይ ጉዳት አያደርሱም የሚለው የተለመደ እምነት ትክክል አይደለም” ብሏል። የሜክሲኮ ማኅበራዊ ደህንነት ተቋም ባልደረባ የሆኑት አቢጋኤል አጉዌላር ኮንትሬራስ እንዳሉት ከሆነ ዕጽዋትን በመውሰድ ራስን በራስ ማከም አደገኛ ነው። “መድኃኒትነት ያላቸው ዕጽዋት በውስጣቸው የተለያዩ ቅመሞች ስላሏቸው በሰውነት ላይ ጉዳት ሊያደርሱና ሊገድሉ ይችላሉ” ይላል ጋዜጣው። ክብደት ለመቀነስ ሲባል የሚወሰደው ዬሎ ኦልያንደር የተባለ ዕፅ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። ይህ ዕፅ ሊያስቀምጥ እንዲሁም ሊያስመልስ ከመቻሉም በላይ በልብም ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ስለዚህ ዕጽዋትን ለመድኃኒትነት ለመውሰድ ያሰበ ሰው ባለሞያ ቢያማክር ጥሩ ይሆናል።
በተለያዩ ዓመታት የተወለዱ መንትዮች
“ካሌ እና ኤሚሊ ጆንሰን በተለያዩ ዓመታት ቢወለዱም በብዙ ነገር ይመሳሰላሉ” በማለት የኒው ዮርኩ ዴይሊ ኒውስ ዘግቧል። “ካሌ የተወለደችው ከምሽቱ 5:24 ታኅሣሥ 31 ቀን ሲሆን ኤሚሊ ደግሞ ወደዚህ ዓለም የመጣችው ከሌሊቱ 6:19 ጥር 1 ቀን ነው።” በባርነጋት፣ ኒው ጀርሲ የምትኖረው እናታቸው ዶን ጆንሰን በጣም ተደስታለች። “መንትዮች ቢሆኑም የተለያየ መታወቂያ እንዲኖራቸው እፈልግ ነበር። ከመጀመሪያው አንስቶ የተለያዩ ሰዎች መሆናቸውን አስመስክረዋል” ብላለች። መንትዮቹ ይወለዳሉ ተብለው ከተጠበቁበት ከየካቲት 2 ቀን አንድ ወር ያህል ቀድመው ተወልደዋል።
ስለ ቡና የተገኘ አዲስ መረጃ
የለንደኑ ዘ ታይምስ “በጤንነት ረገድ ካፌን አልባ ቡና ከመደበኛው ቡና የሚሻልበት ምንም መንገድ የሌለ ሲሆን የመደበኛውን ቡና ያህል እንቅልፍ ሊነሣ ይችላል” ብሏል። በዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ በሚገኝ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች ሁለቱም ዓይነት ቡናዎች በልብና በደም ሥሮች ላይ እንዲሁም በነርቭ አውታሮች ላይ በሚያሳድሩት ተጽእኖ ረገድ ምንም ልዩነት ስለሌላቸው ችግሩ ከቡና ካፌን አይደለም ማለት ነው። ዶክተር ሮቤርቶ ኮንቲ የተባሉት ዋና ተመራማሪ “እስካሁን ቡና በልብና በደም ቧንቧዎች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው በካፌን ምክንያት ነው ብለን እናስብ ነበር። ይሁን እንጂ ቡና የማይጠጡ ሰዎችም ካፌን አልባ ቡና ሲሰጣቸው እነዚሁ ውጤቶች ይታዩባቸዋል። ይህ የሚያሳየው በመላው ዓለም እጅግ ተወዳጅና ተዘውታሪ ስለሆነው መጠጥ የማናውቀው ብዙ ነገር እንዳለ ነው” ብለዋል።