በውኃ፣ በሰማይና በነፋስ እየተመሩ የባሕር ላይ ጉዞ ማድረግ
በውኃ፣ በሰማይና በነፋስ እየተመሩ የባሕር ላይ ጉዞ ማድረግ
የምድር ጠርዝ ላይ ደርሼ ቁልቁል እወድቃለሁ ብለህ ፈርተህ ታውቃለህ? አታውቅ ይሆናል። በቀድሞዎቹ ዓመታት ግን መርከበኞች ምድር ጠርዝ ላይ እንደርስና እንወድቃለን የሚል ፍርሃት ነበረባቸው። ብዙዎቹ የሚጓዙት ከመሬት ሳይርቁ የየብሱን ዳርቻ እየተመለከቱ ነበር። ደፋር የሆኑ ባሕረኞች ግን ይህን ሁሉ ፍርሃት አሸንፈው ባሕሩን እያቋረጡ ይጓዙ ነበር።
ፊንቃውያን ባሕረኞች ከ3,000 ዓመት ገደማ በፊት ከሚኖሩበት ከምሥራቁ የሜድትራንያን ጠረፍ ተነስተው እስከ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ድረስ በመጓዝ ይነግዱ ነበር። በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ፓይትየስ የተባለ አንድ ግሪካዊ አሳሽ ብሪታንያን ዞሮ እስከ አይስላንድ ድረስ ተጉዞ ነበር። በተጨማሪም የአውሮፓውያን መርከቦች በሕንድ ውቅያኖስ ላይ መጓዝ ከመጀመራቸው ከብዙ ጊዜ በፊት አረቦችና ቻይናውያን መርከበኞች ውቅያኖሱን ያቆራርጡ ነበር። እንዲያውም ሕንድ ለመድረስ የመጀመሪያው አውሮፓዊ የሆነውና ቫስኮ ደጋማ የተባለው መርከበኛ በደህና ሊደርስ የቻለው መርከቦቹ ሕንድ ውቅያኖስን ለማቋረጥ ባደረጉት የ23 ቀን ጉዞ ኢብን መጅድ በተባለ አረብ ካፒቴን ይመሩ ስለነበረ ነው። እነዚህ የጥንት መርከበኞች ለጥ ባለው ባሕር ላይ መንገድ ሳይጠፋቸው ካሰቡበት ሊደርሱ ይችሉ የነበረው እንዴት ነው?
በሕይወት እንዲመለሱ ያስቻላቸው ግምታዊ ስሌት
የጥንቶቹ ባሕረኞች በግምታዊ ስሌት ላይ መተማመን ነበረባቸው። ይህን የመሰለ ስሌት ለማድረግ ከታች ያለው ሥዕል እንደሚያመለክተው መርከበኞቹ ሦስት ነገሮችን ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። (1) የመርከቢቱ መነሻ ነጥብ፣ (2) ፍጥነት እና (3) የጉዞ አቅጣጫ። የመነሻውን ነጥብ ማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። ሆኖም መርከቡ የሚጓዝበትን አቅጣጫ እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ክርስቶፎር ኮሎምበስ በ1492 የሚጓዝበትን አቅጣጫ እንዲያውቅ የረዳው አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መሣሪያ በአውሮፓ አገልግሎት ላይ የዋለው ከ12ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ነበር። አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ባልነበረበት ዘመን መርከበኞች ይጓዙ የነበረው በፀሐይና በከዋክብት እየተመሩ ነበር። ፀሐይና ከዋክብት በደመና በሚጋረዱበት ጊዜ ደግሞ መርከበኞች ነፋሳት በሚፈጥሩት የባሕር ሞገድ ይመራሉ። የሞገዶቹን አቅጣጫ ፀሐይና ከዋክብት ከሚወጡበትና ከሚጠልቁበት አቅጣጫ ጋር በማገናዘብ ጉዟቸውን ያደርጉ ነበር።
ፍጥነታቸውንስ የሚገምቱት እንዴት ነበር? አንደኛው መንገድ ከመርከቡ ፊት አንድ ነገር ይጥሉና መርከቡ እዚያ ቦታ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀበት በማየት ነው። ቆየት
ብሎ የተሻለ የመለኪያ ዘዴ ተፈጠረ። በእኩል ርቀት በርካታ ቋጠሮዎች ከተደረጉበት ገመድ ጋር የተያያዘ ቁራጭ እንጨት ወደ ባሕሩ ይጣላል። መርከቡ እየተጓዘ ሲሄድ የሚንሳፈፈው እንጨት ገመዱን እየጎተተ ባሕሩ ውስጥ ይከትተዋል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ገመዱን ወደ መርከቡ በመሳብ ምን ያህል ቋጠሮዎች ወደ ባሕሩ እንደገቡ ይቆጠራል። በዚህ መንገድ የመርከቡ ፍጥነት ስንት ቋጠሮ ማይል ወይም ኖቲካል ማይል በሰዓት እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። ይህ የመለኪያ ዘዴ እስከዛሬ ድረስ ይሠራበታል። መርከበኛው ፍጥነቱን ካወቀ መርከቡ በቀን ውስጥ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ማስላት ይችላል። ከዚያም በመረጠው አቅጣጫ የተጓዘበትን ርቀት በካርታ ላይ ማመልከት ይችላል።እርግጥ የባሕር ሞገዶችና ከጎን የሚመጡ ነፋሳት የመርከቡን አቅጣጫ ሊያስለውጡ ይችላሉ። ስለዚህ መርከበኛው ወዳቀናበት መስመር እንዲመለስ ምን ያህል መጠምዘዝ እንዳስፈለገው በየወቅቱ ይመዘግባል። በየቀኑ ከመነሻው ጀምሮ የተጓዘበትን ርቀትና አቅጣጫ ይለካል፣ ያሰላል፣ ይስላል። በመጨረሻ መርከቡ ከታሰበበት ደርሶ መልሕቁን ሲጥል ይህ የዕለት ተዕለት መዝገብ መርከቡ እዚያ ቦታ ሊደርስ የቻለበትን መስመር የሚያሳይ ቋሚ ሰነድ ሆኖ ያገለግላል። ኮሎምበስ ከ500 ዓመታት በፊት ከስፔይን ተነስቶ ሰሜን አሜሪካ ደርሶ ሊመለስ የቻለው ይህን የግምታዊ ስሌት ዘዴ በመጠቀም ነበር። ዘመናዊ ባሕረኞችም እርሱ በጥንቃቄ የሳለውን ካርታ በመከተል እርሱ የተጓዘበትን መስመር ተከትለው በድጋሚ መጓዝ ችለዋል።
በጠፈር አካላት እየተመሩ መጓዝ
የጥንት ባሕረኞች በጠፈር አካላት እየተመሩ የተጓዙት እንዴት ነበር? የፀሐይ መውጣትና መጥለቅ ምሥራቅና ምዕራብ በየት አቅጣጫ እንደሚገኙ ይጠቁማል። ማለዳ ላይ መርከበኞች ደብዘዝ ማለት የጀመሩት ከዋክብት ከሚገኙበት ቦታ ጋር በማነጻጸር ጀንበሯ ከነበረችበት ቦታ ምን ያህል ፈቀቅ እንዳለች ያስተውላሉ። በማታ ደግሞ ፀሐይ እንደጠለቀች በሰሜናዊ ዋልታ አናት ላይ ደምቃ በምትታየው ኮከብ አማካኝነት አቅጣጫቸውን ይቆጣጠራሉ። በስተ ደቡብ ሲሆኑ ደግሞ ሳውዘርን ክሮስ በሚባለው ኅብረ ኮከብ አማካኝነት ደቡባዊ ዋልታ የሚገኝበትን አቅጣጫ ያውቃሉ። ስለዚህ ሰማዩ የጠራ ከሆነ መርከበኞች በየትኛውም ባሕር ላይ ቢሆኑ ቢያንስ በአንድ የጠፈር አካል አማካኝነት ወዴት አቅጣጫ እያቀኑ እንዳሉ ያውቃሉ።
ይሁን እንጂ ሌሎች አቅጣጫ ጠቋሚ የጠፈር አካላትም አሉ። ለምሳሌ ያህል የፖሊኔዥያ እና ሌሎች የሰላማዊ ውቅያኖስ ባሕረኞች የሌሊቱን ሰማይ እንደ መንገድ ካርታ ማንበብ ይችሉ ነበር። ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ዘዴዎች አንዱ በሚሄዱበት አቅጣጫ የምትጠልቅ ወይም የምትወጣ ኮከብ እያዩ መጓዝ ነው። በተጨማሪም እነዚህ ባሕረኞች ከአቅጣጫቸው አለመውጣታቸውን ለማረጋገጥ የሌሎች ኮከቦችን አቀማመጥ ይከታተላሉ። አቅጣጫቸውን ከሳቱ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንዴት ሊመለሱ እንደሚችሉ የጠፈር አካላት ያሳዩዋቸዋል።
ይህ ዘዴ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? አውሮፓውያን መርከበኞች ጠፍጣፋ በሆነችው ምድር ጠርዝ ላይ ደርሰን እንወድቃለን ብለው በመፍራት የየብሱን ጥግ ጥግ እየተከተሉ በሚቀዝፉበት ዘመን የሰላማዊ ውቅያኖስ ባሕረኞች ወደ መሐል በመግባት ትናንሽ ደሴቶችን እያቋረጡ ይጓዙ ነበር። ለምሳሌ ያህል ከ1,500 ዓመታት በፊት ፖሊኔዥያውያን ከማርኬሳስ ደሴቶች ተነስተው ወደ ሰሜን በመጓዝ በጣም ሠፊ የሆነውን ሰላማዊ ውቅያኖስ አቋርጠው ነበር። በግምት 3,700 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዘው ሐዋይ ደሴት ደርሰዋል! የጥንት
ፖሊኔዥያውያን ከሐዋይ ወደ ታሂቲ ይመላለሱ እንደነበረ የሚተርኩ የጥንት አፈ ታሪኮች አሉ። አንዳንድ ታሪክ ፀሐፊዎች እነዚህ ታሪኮች እውነት እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ዘመናዊ መርከበኞች ምንም ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያ ሳይጠቀሙ በከዋክብት፣ በባሕር ሞገዶችና በሌሎች የተፈጥሮ ክስተቶች ብቻ በመመራት የጥንቶቹ ሕዝቦች ያደረጉትን ጉዞ ለመድገም ችለዋል።በነፋስ መነዳት
የመርከቦች ጉዞ ከነፋስ አቅጣጫ ጋር በጣም የተዛመደ ነው። ከበስተኋላ የሚነፍስ ነፋስ የመርከቦችን ጉዞ ሲያፋጥን ከፊት ለፊት የሚነፍስ ነፋስ ደግሞ በጣም ያዘገያቸዋል። በምድር ወገብ አካባቢ እንደሚያጋጥመው ምንም ነፋስ ካልኖረ ጉዞው በጣም አዝጋሚ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን መርከበኞች የዋና ዋና ውቅያኖስ ነፋሳትን አቅጣጫና አካባቢ በማወቃቸው መርከቦች እንደልብ ሊጓዙ የሚችሉባቸውን አውራ ጎዳናዎች ለማወቅ ችለዋል። መርከበኞች በእነዚህ ነፋሳት በጥሩ ሁኔታ ይጠቀማሉ።
እርግጥ ነው ነፋሳቱ ተስማሚ ካልሆኑ ብዙ ጭንቀት አልፎ ተርፎም ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ደጋማ በ1497 ከፖርቱጋል ብዙ ወደተወራለት የሕንዱ ማላባር የባሕር ጠረፍ ለመጓዝ ሲነሣ የገጠመው ከባድ ነፋስ ወደ ደቡባዊ አትላንቲክ ከወሰደው በኋላ ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ በመመለስ ወደ አፍሪካዋ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ አድርሶታል። ሕንድ ውቅያኖስ ሲደርስ ግን በየወቅቱ አቅጣጫቸውን ከሚቀይሩት ነፋሳት ጋር ተጋጠመ። የበጋው ነፋስ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከሕንድ ውቅያኖስ ደቡባዊ ምዕራብ ይነሳና ለበርካታ ወራት ያጋጠመውን መርከብ ሁሉ ወደ እስያ ይነዳል። በበልግ ወራት ግን የክረምቱ ነፋስ ቦታውን ይረከባል። ከሰሜናዊ ምሥራቅ እያስገመገመ ያገኘውን ሁሉ ወደ አፍሪካ ይመልሳል። ደጋማ ግን ከሕንድ የተነሣው በነሐሴ ወር ስለነበረ ወዲያው ተጻራሪ ነፋስ አጋጠመው። ወደ ምሥራቅ ለማቋረጥ የወሰደበት ጊዜ 23 ቀን ብቻ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን ሦስት ወር ያህል ፈጀበት። በዚህ ሁኔታ በመዘግየቱ ምክንያት ይዞት የነበረው ትኩስ ምግብ አልቆበት አብረውት ከነበሩት ብዙዎቹ ስከርቪ በሚባል ከቪታሚን ሲ እጥረት በሚመጣ የደም በሽታ አለቁ።
በሕንድ ውቅያኖስ የሚጓዙ ብልሕ መርከበኞች የሚጓዙበትን ወቅትና አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያቸውን ማገናዘብ እንደሚያስፈልጋቸው አወቁ። በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ አልፈው ወደ ሕንድ የሚጓዙ መርከቦች በጋ መጀመሪያ ላይ መጓዝ ካልጀመሩ ዕጣቸው የነፋሱ አቅጣጫ እስኪቀየር ድረስ ለበርካታ ወራት መቆየት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሕንድ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ የመርከብ ካፒቴኖች ከበጋው ነፋስ ጋር ፊት ለፊት ከመታገል ለመዳን በበልግ ወራት መጨረሻ ላይ ጉዞ ይጀምራሉ። በዚህ መንገድ የሕንድ ውቅያኖስ ጉዞ በየወቅቱ የሚቀያየር የአንድ አቅጣጫ ብቻ ጉዞ ሆኖ ቆይቷል።
የመርከብ ጉዞ ያደረገው እድገት
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የባሕር ጉዞ ጥበብም አዲስ አቅጣጫ መያዝ ጀመረ። ተንቀሳቃሽ መሣሪያዎች በተራ ዓይንና በግምታዊ ስሌት የመተማመንን አስፈላጊነት እየቀነሱ መጡ። የፀሐይን ወይም የአንድን ኮከብ ከአድማስ በላይ ከፍታ ለመለካት የሚያስችለው አስትሮሎብ ወይም ይበልጥ ትክክለኛ የሆነው ሴክስታንት የተባለ መሣሪያ መርከበኞች ከምድር ወገብ በታች ወይም በላይ በስንት ዲግሪ ኬክሮስ ላይ እንደሚገኙ እንዲያውቁ አስችሏል። ማሪይን ክሮኖሜትር የተባለው አስተማማኝ የባሕር ላይ ሰዓት ደግሞ የሚገኙበትን የኬክሮስ ነጥብ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። እነዚህ መሣሪያዎች ከግምታዊ ስሌት የበለጠ በጣም ትክክልና አስተማማኝ ናቸው።
ዛሬ ጋይሮኮምፓስ የተባለው መሣሪያ አለማግኔታዊ መጠቆሚያ የሰሜንን አቅጣጫ ያመለክታል። ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም የተባለው ዘዴ ጥቂት ቁልፎችን ብቻ በመጫን የሚገኙበትን ትክክለኛ ቦታ ለማወቅ ያስችላል። የወረቀት ካርታዎች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ተተክተዋል። አዎን፣ የመርከብ ጉዞ የተራቀቀ ሳይንስ ሆኗል። ይህ ሁሉ መራቀቅ ግን በውኃ፣ በሰማይና በነፋስ ብቻ እየተመሩ መርከቦቻቸውን በሰፊ ውቅያኖስ ላይ ይቀዝፉ የነበሩት ባሕረኞች ላሳዩት ድፍረትና ችሎታ ታላቅ አድናቆት እንዲኖረን የሚያደርግ ነው።
[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ግምታዊ ስሌት
ወደፊት ለሚደረግ ጉዞ እንዲያገለግሉ በግምት የተደረጉ ስሌቶች በጥንቃቄ ይመዘገባሉ
1 መነሻ ነጥብ
↓
2 ፍጥነት ቁራጭ እንጨት፣ በእኩል ርቀት ቋጠሮዎች የተደረጉበት ገመድና የጊዜ መለኪያ በመጠቀም የመርከብን ፍጥነት መለካት
↓
3 የጉዞ አቅጣጫ የባሕር ሞገዶችን፣ ከዋክብትን፣ ፀሐይንና ነፋስን በመጠቀም የጉዞ አቅጣጫን ማወቅ
[ሥዕሎች]
አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ
ሴክስታንት
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዘመናዊ መሣሪያዎች የዛሬው የባሕር ጉዞ የተራቀቀ ሳይንስ እንዲሆን አስችለዋል
[ምንጭ]
Kværner Masa-Yards