አለሹካና ማንኪያ መብላት
አለሹካና ማንኪያ መብላት
ጋና የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ብዙ ሰዎች የሚመገቡትን ምግብ ለመጉረስ ሹካ፣ ቢላ ወይም ማንኪያ ይጠቀማሉ። በሩቅ ምሥራቅ የሚኖሩ ሌሎች ደግሞ ቾፕስቲክ የሚባሉ ሁለት ትናንሽ እንጨቶችን ለዚሁ ተግባር ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ በእጅ የሚበሉትን ያህል አይጣፍጡም የሚባሉ ምግቦችም አሉ። የተጠበሰ ጎድን፣ የዶሮ አጥንት፣ ዳቦ ወይም እንጀራን መጥቀስ እንችላለን።
ሾርባስ? በእጅ መብላት ይቻላል? ‘ኧረ በፍጹም!’ ትል ይሆናል። ‘ትኩስና እጅ ላይ የሚጣበቅ ከመሆኑም በላይ መፍሰሱ አይቀርም።’ በብዙ የአፍሪካ አገሮች እስያውያን በቾፕስቲክ እንደሚበሉ ሁሉ በእጃቸው ሾርባ የመብላት ልማድ ያላቸው ብዙ ሕዝቦች አሉ። ከአንድ የጋናውያን ጣፋጭ ምግብና አለሹካና ማንኪያ በእጅ ብቻ መብላት ከሚሰጠው ደስታ ጋር እናስተዋውቃችሁ።
ፉፉ እና የኦቾሎኒ ሾርባ
ፉፉ ከተቀቀለ ሙዝና በሐሩር መስመር ውስጥ በሚገኙ አገሮች ከሚበቅል ካሳቫ ከሚባል ሥር የሚዘጋጅ ምግብ ነው። ጥሬው ሙዝና ካሳቫው ከተላጠና ከታጠበ በኋላ እስኪበስል ድረስ ይቀቀላል። ውኃው ከተንጠፈጠፈ በኋላ እስኪልም ድረስ በሙቀጫ ይወቀጣል። ከተዋሃደና ከላመ በኋላ በትንሽ በትንሹ ይድበለበላል።
የኦቾሎኒ ሾርባ ደግሞ የሚዘጋጀው ከተቦካ የኦቾሎኒ ዱቄት፣ ከሥጋ ወይም ከዓሣ፣ ከቲማቲም፣ ከሽንኩርት፣ ከቁንዶ በርበሬና ከሌሎች ቅመሞች ነው። ሥጋው ወይም ዓሣው ከተቀቀለና ቅመማ ቅመም ከተደረገበት በኋላ የተቦካው የኦቾሎኒ ዱቄትና ውኃ ይጨመርበታል። አትክልቶቹ አንድ ላይ እንዲደባለቁ ከተደረጉ በኋላ ሾርባው ውስጥ ይጨመሩና እየተማሰሉ በደንብ
እንዲበስሉ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ ተድበልብለው በተዘጋጁት ፉፉዎች ላይ ትኩስ የኦቾሎኒ ሾርባ እየተጨመረባቸው በጎድጓዳ ሣህን ላይ ይቀርባሉ።የአበላሉ ዘዴ
ይህን የመሰለ ጣፋጭ ምግብ ከተዘጋጀልህ አሁን የሚነሣው ጥያቄ እንዲህ ያለውን ምግብ በባዶ እጅህ ወደ አፍህ ልታስገባ የምትችለው እንዴት ነው የሚለው ነው። ትክክለኛውን ዘዴ ማወቅ ይጠይቃል።
በመጀመሪያ እጅህን ጥሩ አድርገህ መታጠብ እንደሚያስፈልግህ የታወቀ ነው። ቀጥለህ የቀኝ እጅህን ጣቶች ሾርባው ውስጥ አስገባ። ግን እዚህ ላይ ተጠንቀቅ! ልምድ ከሌለህ በጣም ሊያቃጥልህ ይችላል።
በአውራ ጣትህ፣ በሌባ ጣትህ፣ በመካከለኛው ጣትህና በቀለበት ጣትህ ተጠቅመህ ጥቂት ፉፉ አውጣ። አንድ ፉፉ ሾርባው ውስጥ ታስገባና በአውራ ጣትህ ቀስ ብለህ ተጭነህ ሾርባው የሚገባበት ትንሽ ጉድጓድ እንዲፈጠር አድርግ።
ከዚያም ፉፉውን አውጣ። ካወጣህ በኋላ እጅህንና ጣቶችህን ወደ አፍህ አዙር። ጣቶችህ ግን ከእጅህ አንጓ ከፍ እንዳይሉ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። እንዲህ ካደረግህ ሾርባው ወደ ክንድህ እንዳይፈስ ማድረግ ትችላለህ።
ከአንገትህ ትንሽ ጎንበስ በልና እጅህ ከንፈሮችህ ጋር ሲደርስ በመካከለኛና በቀለበት ጣትህ ፉፉውንና ሾርባውን በቀጥታ ወደ አፍህ
ትገፋለህ። አሁን አጣጥመህ መብላት ትችላለህ። ሆኖም አሁንም ጠንቀቅ በል። የጋና ምግቦች አብዛኛውን ጊዜ ቅመም ስለሚበዛባቸው ያቃጥልህ ይሆናል።ፉፉው እስኪያልቅ ድረስ ይህንኑ ማድረግ ይኖርብሃል። በሾርባው ውስጥ የተጨመሩትን እንደ ሥጋ ያሉ ሌሎች ምግቦች ለብቻ ትበላለህ። ሾርባው ሳያልቅ ከቀረ በእጅህ ልትጨርሰው ትችላለህ።
በእጅ መብላት የሚያሳድረው ስሜት
አንዳንድ ጋናውያን በሚመገቡበት ጊዜ አምስቱንም የስሜት ሕዋሳት መጠቀም ይፈልጋሉ። ምግቡ በሚበስልበት ጊዜ ጆሮህ ይሰማል፣ አፍንጫህም ያሸታል። በምትበላበት ጊዜ ደግሞ ታየዋለህ፣ ታጣጥመዋለህ። አምስተኛው የስሜት ሕዋስህ ተካፋይ እንዲሆን ግን በጣቶችህ መንካት ይኖርብሃል።
የትውልድ አካባቢህ የትም ይሁን የት ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ‘ለሰው ሁሉ’ እንደሚያስብ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) በዚህም የተነሣ ብዙ የተለያዩ ባሕሎችና ልማዶች ሊኖሩ ችለዋል። አለማንኪያ ሾርባ መብላት አዲስ ነገር ቢሆንብህም እንኳ በዚህ መንገድ መመገብ የሚያስደስት ሆኖ ታገኘዋለህ።