የሙዚቃ ፊልሞችን ብመለከት ምን ጉዳት አለው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
የሙዚቃ ፊልሞችን ብመለከት ምን ጉዳት አለው?
“የሙዚቃ ፊልሞች በጣም ያስደስቱኛል። አንዳንዶቹ ልክ እንደ አጫጭር ፊልሞች ናቸው። ታሪክ ያዘሉ ሲሆን ዳንሱንም እወደዋለሁ።”—ኬሲ
“ከአዳዲስ ዘፈኖች ጋር ያስተዋውቁሃል። ከተለመዱት ታዋቂ ዘፈኖች በተጨማሪ ሌሎች ሙዚቃዎችን መስማት ትችላለህ። ከዚህም በላይ ጨዋታ ለመጀመር ጥሩ ርዕስ ይሆናሉ።”—ጆሽ
“የሙዚቃ ፊልሞች ዘፋኟ ማን እንደሆነች፣ ምን እንደለበሰች፣ እንዴት እንደምትደንስና የመሳሰሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ለማወቅ ስለሚያስችሉኝ እወዳቸዋለሁ። ይህ ሁሉ ተዳምሮ ለግጥሙ ትርጉም ይሰጠዋል።”—ኪምበርሊ
“የምወደው የሙዚቃ ጓድ ምን አዲስ ነገር እንዳወጣ ማየት እፈልጋለሁ። ቅንብሩን ማየት ያስደስተኛል። አንዳንድ የሙዚቃ ፊልሞች ደግሞ አስቂኝ ናቸው። ያም ሆኖ ግን ጠንቃቃ መሆን ያስፈልጋል።”—ሳም
ምናልባት አንተም የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከት ያስደስትህ ይሆናል። የሙዚቃ ፊልሞች መጀመሪያ ላይ በቴሌቪዥን መቅረብ ሲጀምሩ በአነስተኛ ወጪ የሚዘጋጁ ፕሮግራሞች ነበሩ። እያደር ግን አንድ ሰሞን ብቅ ብለው የሚያልፉ ሥራዎች እንዳልሆኑና ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኙ ሲታወቅ በሥነ ጥበብም ሆነ በቴክኒካዊ ቅንብራቸው ረገድ ይበልጥ እየተራቀቁ መጡ። ዛሬ በሙዚቃው ዓለም ትልቅ ቦታ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈዋል። በአንዳንድ አገሮች የሙዚቃ ፊልሞችን ብቻ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ!
ይሁን እንጂ እዚህ ላይ እንደተጠቀሰው እንደ ሳም ያሉ አንዳንድ ወጣቶች በምንመለከታቸው የሙዚቃ ፊልሞች ረገድ ጠንቃቆች መሆን እንዳለብን የሚናገሩት ለምንድን ነው? ምናልባት አንዳንድ የሙዚቃ ፊልሞች አስተሳሰብህንና የሥነ ምግባር አቋምህን ከዚያም አልፎ ከፈጣሪህ ጋር ያለህን ዝምድና በማበላሸት ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆን? እንደዚህ ያለው ጥያቄ በጣም የተጋነነ ይመስል ይሆናል። ሆኖም እስኪ አንድ ምሳሌ እንመልከት:- ለመዋኘት ወደ አንድ ሐይቅ ወይም ውቅያኖስ ብትሄድና በዚያ መዋኘት አደገኛ መሆኑን የሚገልጽ ጽሑፍ ብትመለከት እንደዚህ ያለውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ ማለፍ የጥበብ እርምጃ ይሆናልን? እንደማይሆን የታወቀ ነው። እንግዲያው የሙዚቃ ፊልሞችን በተመለከተም አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ልብ ማለትህ ተገቢ ይሆናል።
የአደጋ ቀጠና
የምታየውና የምትሰማው ነገር ተጽዕኖ ሊያሳድርብህ እንደሚችል አምነህ መቀበል ይኖርብሃል! የእስራኤል 1 ሳሙኤል 16:14-23) ሙዚቃ የሚያሳድረው ጎጂ ተጽዕኖስ ይኖር ይሆን? ሮክ ኤንድ ሮል-ኢትስ ሂስትሪ ኤንድ ስታይሊስቲክ ዴቨሎፕመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ሁለት ወዶ አይሆንም። የሮክ ሙዚቃ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ሁሉ (ደግሞም አለው) ጎጂ ተጽዕኖም ሊያሳድር እንደሚችል (ደግሞም አለው) ልናምን ይገባል። ‘ሙዚቃውን ብሰማም በእኔ ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም’ ብሎ የሚናገር ሰው ሞኝ አሊያም ምንም የማያውቅ ምስኪን ነው።”
የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ሳኦል ስሜቱን ለማረጋጋት ሙዚቃ ያዳምጥ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (መጽሐፍ ቅዱስ የምናየው ነገር በአስተሳሰባችንና በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በተደጋጋሚ ይናገራል። (ምሳሌ 27:20፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16) የፊልም አምራቾች ሙዚቃ በፊልም የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ በአድማጮች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያደርጋሉ። በአብዛኛው ከዘፈኑ ጋር የሚታዩት ምን ዓይነት ፊልሞች ናቸው?
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሮክ የሙዚቃ ፊልሞች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት በዓመጽ ድርጊቶች የተሞሉ ሲሆኑ 76 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከጾታ ብልግና ጋር የተያያዙ ናቸው። ሌላ በቅርቡ የተደረገ ጥናት 75 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፊልሞች የብልግና ምስሎችን እንደሚያሳዩና ከግማሽ በላይ የሆኑት ደግሞ ባብዛኛው በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የዓመጽ ድርጊቶችን እንደሚያንጸባርቁ አመልክቷል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ እንደዚህ ዓይነት ፊልሞችን መመልከት ጉዳት ያስከትልብሃልን? የሚለው ይሆናል። አንድ መጽሔት እንደገለጸው “ወጣቶች የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከታቸው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚፈጸምንና ለእርግዝናና ለበሽታ የሚያጋልጥ የጾታ ግንኙነትን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርግ እንደሚችል ጥናታዊ ሙከራዎች አሳይተዋል።” ከዚህም በላይ ሙዚቀኞች ከእነሱ በፊት ከነበሩትና አሁን ከሚፎካከሯቸው ዘፋኞች ይበልጥ ጉድ የሚያሰኝ ሙዚቃ ለማውጣት በሚያደርጉት ጥረት የሙዚቃ ፊልሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ ልቅ እየሆኑ እንደሚሄዱ አይካድም።
በማስተማሩ ሥራ የተሰማሩ አንድ ባለሞያ እንዲህ ብለዋል:- “ብዙዎች ዛሬ የሚያዳምጧቸውና በሙዚቃ ፊልሞች አማካኝነት የሚያዩአቸው ሙዚቃዎች በቀደሙት ዘመናት ከነበሩት ሙዚቃዎች የተለዩ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። . . . ሆኖም ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ አርቲስቶች ሽያጫቸውን ከፍ ለማድረግ ሲሉ በፊልሞቹ ውስጥ ጸያፍ ንግግርንና ልቅ ምግባርን ማካተታቸው ተቀባይነት ያለው ነገር ሆኗል።” ቺካጎ የተባለው መጽሔት የሙዚቃ ፊልም የሚያስተላልፍ አንድ ጣቢያ “በተመልካቾቹ ላይ በጣም ልቅ የሆኑ ወሲባዊ ስዕሎች ውርጅብኝ” እንደሚያወርድባቸው ተናግሯል።
ይኸው መጽሔት ስለ አንድ የሙዚቃ ፊልም ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ባልኮኒውን ተደግፎ የተቀመጠ አንድ ወጣት ጭንቅላቱን ወደኋላ ያዘነብላል። ከዚያም አንገቱ በድንገት ተቆረጠና ጭንቅላቱ ተቀንጥሶ ወደቀ።” በሌላ የሙዚቃ ፊልም ላይ ደግሞ አንድ ሰው ልብሱን ሲያወልቅ ከቆየ በኋላ ሥጋውንና ከዚያም ጡንቻዎቹን ጭምር ሲገፍፍ እንደታየ ተዘግቧል። ሌሎች ለመናገር በጣም የሚቀፉ ትዕይንቶችም ቀርበዋል።
አንዳንዶች እዚህ ላይ የተገለጹት ሁኔታዎች በጣም የተጋነኑ እንደሆኑና አብዛኞቹ ፊልሞች ግን ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆኑ ይናገሩ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች የሙዚቃ ፊልሞች እነርሱን እንደማይዘገንኗቸው ይናገሩ ይሆናል። ምናልባት እነዚህ ሰዎች ምንም ያልተሰማቸው እንደነዚህ ያሉ የሙዚቃ ፊልሞችን በተደጋጋሚ ከመመልከታቸው የተነሳ ስሜታቸው ስለደነዘዘ ይሆን? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኬሲ እንዲህ ብሏል:- “በምትመለከቱት ነገር ረገድ ገደብ ካላበጃችሁ መጀመሪያ ላይ በጣም ይዘገንናችሁ የነበረውን ነገር እያደር እንደ ተራ ትቆጥሩታላችሁ። ሳታውቁት ከዚያ የበለጠ ነገር ለማየት ትፈልጋላችሁ፤ በፊት ይሰቅቃችሁ የነበረውን ነገር በግድየለሽነት መመልከት ትጀምራላችሁ።”
ይህ ምን ያስከትላል? በሥነ ምግባር ረገድ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታችሁን ቀስ በቀስ ታጣላችሁ። አፍራሽ የሆኑ ነገሮች በአመለካከታችን ላይ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያደርጉብን ስለሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን እንድንጠብቅ’ ይመክረናል። (ምሳሌ 3:21፤ 5:2) ሌላው ጉዳት ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት መበላሸቱ ነው። ይህ ዝምድና ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ውድ ነገር አይደለምን? ከሆነ ከማንኛውም ዓይነት ተገቢ ያልሆነ መዝናኛ ለመራቅ እርምጃ በመውሰድ ይህንን ወዳጅነት መጠበቅ ይኖርብሃል። እንደዚህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ራስህን ከአደጋ መጠበቅ
በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚያወግዛቸውን ነገሮች የሚያቀርቡ የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከት ስህተት መሆኑን አምነህ ተቀበል። (መዝሙር 11:5፤ ገላትያ 5:19-21፤ ራእይ 21:8) አንድ የሙዚቃ ፊልም “ለቅዱሳን” የማይገቡ ነገሮችን የሚያወድስ ከሆነ መመልከትህን ማቆም ይገባሃል። (ኤፌሶን 5:3, 4) አንድ የሚያስደስት የሙዚቃ ፊልም እየታየ እያለ ጣቢያውን መቀየር ወይም እስከ ጭራሹ ቴሌቪዥኑን ማጥፋት ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። በመሆኑም “ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” ብሎ እንደጻፈው መዝሙራዊ አንተም መጸለይ ያስፈልግህ ይሆናል።—መዝሙር 119:37
ምናልባት ከላይ እንደገለጽናቸው ያሉ ዘግናኝ የሙዚቃ ፊልሞችን አትመለከት ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ፊልሞች የሚቀርቡት በረቀቀ መንገድ ነው። የጾታ ብልግና ሲፈጸም የሚታየው ለቅጽበት ያህል ብቻ ሊሆን ይችላል። ግጥሞቹና ትዕይንቶቹ መጥፎ ነገሮችን በግልጽ ባይናገሩም ወይም ባያሳዩም ከአምላካዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጩ አመለካከቶችን በስውር የሚያስተላልፉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያም ሆነ በዚህ አንድ ፊልም ከተመለከትክ በኋላ ምነው ባላየሁት ኖሮ የሚል ስሜት ከተሰማህ ፊልሙ ጤናማ ያልሆነና ለክርስቲያኖች የማይገባ ነበር ማለት ነው። ታዲያ አንድ ፊልም ተገቢ ነው ወይስ ተገቢ አይደለም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚቻለው እንዴት ነው?
እርግጥ፣ የሙዚቃ ፊልሞችን መመልከት አለብህ ወይስ የለብህም የሚለውን የምትወስኑት አንተና ልታያቸው የሚገቡህንና የማይገቡህን ፊልሞች የመወሰን ኃላፊነት የተጣለባቸው ወላጆችህ ናችሁ። (ኤፌሶን 6:1, 2) ወላጆችህ የሙዚቃ ፊልሞችን እንድታይ ከፈቀዱልህ ግን ለአንተ መልካም መስሎ የታየህን ብቻ ማድረግ የለብህም። ዕብራውያን 5:14 [NW ] ‘መልካምና ክፉውን መለየት እንድንችል የማስተዋል ችሎታችንን እንድናሠለጥን’ ያበረታታናል። የማስተዋል ችሎታችንን ለማሰልጠን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ማጥናት ያስፈልገናል፤ እነዚህ መመሪያዎች ከይሖዋ አመለካከት አንጻር መልካምና ክፉውን ለመለየት የሚያስችል መሠረት ይሆኑናል። በእነዚህ መመሪያዎች ላይ ማሰላሰልህ በግልጽ የሰፈረ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በማይኖርበት ጊዜም እንኳን ለመንፈሳዊ ጤንነትህ አደገኛ የሆኑትን ነገሮች ለመለየት ያስችልሃል።
የሙዚቃ ፊልሞችን በመመልከት ረገድ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሊሰጡህ የሚችሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? ይህ ወደፊት በሚወጣ ርዕስ ላይ ይብራራል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“‘ሙዚቃውን ብሰማውም በእኔ ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም’ ብሎ የሚናገር ሰው ሞኝ አሊያም ምንም የማያውቅ ምስኪን ነው።”
[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጤናማ ያልሆነ ነገር እየተመለከትህ ተጽዕኖ አያደርግብኝም ማለት ትችላለህ?