መኪና ስታሽከረክር ራስህን ከአደጋ ትጠብቃለህ?
መኪና ስታሽከረክር ራስህን ከአደጋ ትጠብቃለህ?
“እስከ ዛሬ ድረስ መኪና ሳሽከረክር አደጋ አጋጥሞኝ አያውቅም፤ ስለዚህ አደጋ ይደርስብኛል ብዬ አልጨነቅም።” “አደጋ የሚደርስባቸው ያልበሰሉና ንዝህላል አሽከርካሪዎች ናቸው።” ብዙ የመኪና አሽከርካሪዎች አደጋ ይደርስብናል ብለው ፈጽሞ አያስቡም። አንተም የሚሰማህ እንደዚህ ነው? አደጋ ፈጽሞ አይደርስብኝም የሚል ስሜት አለህ?
በበለጸገ አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ በሕይወት ዘመንህ ቢያንስ አንድ ጊዜ የመኪና አደጋ ሊደርስብህ እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። ብዙዎቹ አደጋዎች ሞት የሚያስከትሉ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከግማሽ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ምናልባትም ባለፈው ዓመት በመኪና አደጋ ከሞቱት ውስጥ አብዛኞቹ እንዲህ ያለ አደጋ ይደርስብኛል ብለው ፈጽሞ አስበው አያውቁ ይሆናል። የመኪና አደጋ እንዳይደርስብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ቁልፉ አስቀድሞ መጠንቀቅ ነው። እየነዱ ከማንቀላፋትና ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ የሚደርሱ አደጋዎችን እንዴት መከላከል እንደምትችል እስቲ እንመልከት።
እንቅልፍ የሚጫጫናቸው አሽከርካሪዎች
አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት እንቅልፍ ተጫጭኖት መኪና የሚያሽከረክር ሹፌር አደጋ የማድረስ አጋጣሚው ሰክሮ መኪና ከሚያሽከረክር ሹፌር ጋር እኩል ነው። ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በእንቅልፍ ሳቢያ የሚደርሱት የመኪና አደጋዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በኖርዌይ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ12 አሽከርካሪዎች ውስጥ አንዱ እንቅልፍ እያዳፋው እንደሚያሽከረክር ፍሊት ሜንቴይናንስ ኤንድ ሴፍቲይ ሪፖርት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ገልጿል። በጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪካ የሚታተመው ዘ ስታር የተባለው ጋዜጣ በዚያች አገር ውስጥ ከሚደርሱት የመኪና ግጭቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሹፌሮች ደክሟቸው መኪና በመንዳታቸው ምክንያት የሚያጋጥም እንደሆነ ገልጿል። ከሌሎች አገሮች የሚወጡ ዘገባዎችም ድካም በማንኛውም ቦታ የሚገኙ አሽከርካሪዎችን ለአደጋ እየዳረገ እንዳለ ያሳያሉ። እንቅልፍ የሚጫጫናቸው አሽከርካሪዎች የበዙት ለምንድን ነው?
የምንኖርበት ጊዜ ሩጫ የበዛበት መሆኑ ለዚህ ችግር አስተዋጽኦ አድርጓል። በቅርቡ ኒውስዊክ መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው አሜሪካኖች “በየምሽቱ በእንቅልፍ የሚያሳልፉት ሰዓት በክፍለ ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ያሳልፉት ከነበረው በአንድ ሰዓት ተኩል እንደሚያንስና ወደፊትም ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል” ዘግቧል። ለምን? መጽሔቱ በእንቅልፍ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑትን ቴሪ ያንግን ጠቅሶ እንደተናገረው “ሰዎች ራሳቸውን እንቅልፍ ቢነፍጉ ብዙም እንደማይጎዱ አድርገው ያስባሉ። በቂ እንቅልፍ ሳያገኙ መሥራት የጠንካራ ሠራተኛነትና የእድገት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።”
አንድ ሰው በየምሽቱ በአማካይ ከስድስት ሰዓት ተኩል እስከ ዘጠኝ ሰዓት ለሚያህል ጊዜ እንቅልፍ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ይነገራል። ሰዎች ይህን ለሚያክል ጊዜ በየቀኑ ካልተኙ “የእንቅልፍ ዕዳ” ይኖርባቸዋል። የአሜሪካን የተሽከርካሪዎች ማኅበር የትራፊክ ደህንነት ተቋም ያሰራጨው አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ብዙም ሥራ በማይበዛበት ሳምንት በየምሽቱ ማግኘት ካለብህ እንቅልፍ 30 ወይም 40 ደቂቃ ያነሰ እንኳ ብትተኛ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከ3 እስከ 4 ሰዓት የሚደርስ የእንቅልፍ ዕዳ ሊጠራቀምብህ የሚችል ሲሆን ይህ ደግሞ ቀን ላይ እንቅልፍ እንዲጫጫንህ ሊያደርግ ይችላል።”
አንዳንድ ጊዜ የእንቅልፍ ማጣት፣ የልጅ መታመም ወይም ሌላ ዓይነት ከባድ ችግር ጥሩ እንቅልፍ እንዳታገኝ ሊያደርግህ ይችላል። በሚቀጥለው ቀን መኪና ስትነዳ እንቅልፍ እንቅልፍ ሊልህ ይችላል። በዚህ ጊዜ ማድረግ ያለብህ ምንድን ነው?
ቡና በመጠጣት፣ የመኪናን መስኮት በመክፈት፣ ማስቲካ በማላመጥ ወይም ቅመም የበዛበት ምግብ በመመገብ የመጣብህን
እንቅልፍ ለማባረር ብትሞክርም አንዳቸውም በንቃት እንድትነዳ አይረዱህ ይሆናል። ከእነዚህ ውስጥ የትኛውም ቢሆን ለችግርህ መፍትሔ አይሆንም። የሚያስፈልግህ መተኛት ብቻ ነው። ስለዚህ መንዳትህን አቁመህ ለምን አታሸልብም? ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ ይላል:- “ሰውነትህን ለማነቃቃት ብለህ በቀኑ ክፍለ ጊዜ የምትተኛው እንቅልፍ ከ30 ደቂቃ መብለጥ የለበትም፤ ከዚያ ከበለጠ ሰውነትህ ከባድ እንቅልፍ ውስጥ ይገባና ቶሎ መንቃት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል።” ለጥቂት ደቂቃ አረፍ ብሎ ማሸለብ ጉዞህን ሊያዘገይብህ ቢችልም ሕይወትህን ሊያራዝምልህ ይችላል።የአኗኗር ዘይቤህ መኪና ስትነዳ እንቅልፍ እንቅልፍ እንዲልህ ሊያደርግህ ይችላል። ኢንተርኔት በመጠቀም ረጅም ሰዓት ታሳልፋለህ? ወይስ ቴሌቪዥን በመመልከት እስከ ሌሊት ትቆያለህ? እስከ እኩለ ሌሊት በሚቆዩ ግብዣዎች ላይ ትገኛለህ? እንዲህ ዓይነት ልማዶች የእንቅልፍ ጊዜህን እንዲሻሙብህ አትፍቀድ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በአንድ ወቅት ጥቂት ዕረፍት እንኳ ዋጋ እንዳለው አጉልቶ ተናግሯል።—መክብብ 4:6
ልምድ ያካበቱ ሆኖም በእድሜ የገፉ
አብዛኛውን ጊዜ በዕድሜ የገፉ አሽከርካሪዎች መኪና የመንዳት ልምድ አላቸው። በተጨማሪም አይዳፈሩም እንዲሁም አቅማቸውን ያውቃሉ። እንዲህ ሲባል ግን በእድሜ የገፉ አሽከርካሪዎች የመኪና አደጋ አያጋጥማቸውም ማለት አይደለም። እንዲያውም እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ለእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ይበልጥ የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ካር ኤንድ ትራቭል የተሰኘው በዩ ኤስ ኤ የሚታተም መጽሔት “እድሜያቸው ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 9 በመቶ ብቻ ቢሆኑም በመኪና አደጋ ከሚሞቱት መካከል 13 በመቶ የሚሆኑት እነርሱ ናቸው” በማለት ዘግቧል። የሚያሳዝነው በእድሜ በገፉ አሽከርካሪዎች የሚደርሰው የመኪና አደጋ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው።
የሰማንያ ዓመት አረጋዊ የሆኑት ሙርተል የሰጡትን አስተያየት ተመልከት። * መኪና መንዳት የጀመሩት የዛሬ 60 ዓመት ሲሆን አንድም ቀን አደጋ ገጥሟቸው አያውቅም። ሆኖም እንደሌሎቹ በእድሜ የገፉ አሽከርካሪዎች ሁሉ እርሳቸውም ከዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው። በቅርቡ ለንቁ! መጽሔት ሲናገሩ “እርጅና እየተጫጫነህ ሲመጣ በሕይወት ውስጥ ሁሉም ነገሮች [መኪና መንዳትን ጨምሮ] ከባድ እየሆኑብህ ይመጣሉ” ብለዋል።
የመኪና አደጋ እንዳይደርስባቸው ምን አደረጉ? “ዓመታቱ እያለፉ ሲሄዱ እርጅና ያመጣብኝን የአቅም ገደብ ለማካካስ ማስተካከያዎችን አድርጌያለሁ” በማለት ሙርተል ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል መኪና መንዳትን በተለይ ደግሞ በምሽት መኪና በመንዳት የሚያሳልፉትን ጊዜ ቀነሱ። ይህ መጠነኛ የሆነ ለውጥ መኪና መንዳታቸውን ጨርሶ ማቆም ሳያስፈልጋቸው ከአደጋ ተጠብቀው መኪና ማሽከርከራቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል።
ለመቀበል የሚከብድ ቢሆንም እንኳ እርጅና የሚያስከትለው መዘዝ ሳይነካው የሚያመልጥ ማንም ሰው የለም። (መክብብ 12:1-7) በርካታ የጤና እክሎች ያጋጥማሉ፣ ቅልጥፍናችንና የማየት ችሎታችን በእጅጉ ይቀንሳል። እነዚህ ሁሉ ችግሮች መኪና መንዳትን አስቸጋሪ ያደርጉታል። ይሁን እንጂ የእድሜ መግፋት በራሱ አንድን አሽከርካሪ መኪና መንዳቱን እንዲያቆም አያደርገውም። ዋነኛው መለኪያ የአሽከርካሪው ቅልጥፍና ነው። በአካላዊ ሁኔታችን ላይ ያሉትን ለውጦች አምኖ መቀበልና በመኪና አነዳድ ልማዳችን ላይ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ማድረግ መኪና የማሽከርከር ብቃታችንን ሊያሻሽልልን ይችላል።
ልብ አላልከው ይሆናል እንጂ የማየት ችሎታህ እየቀነሰ ሊሆን ይችላል። እድሜህ እየገፋ ሲሄድ የእይታ አድማስህ እየጠበበ የሚሄድ ሲሆን በዓይንህ ውስጠኛ ክፍል የሚገኘው ሬቲናም ብዙ ብርሃን ማግኘት ይፈልጋል። ዚ ኦልደር ኤንድ ዋይዘር ድራይቨር የተባለው ቡክሌት እንዲህ ይላል:- “ስድሳ ዓመት የሆነው አንድ መኪና አሽከርካሪ በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኝ አንድ ልጅ ለማየት ከሚያስፈልገው በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ብርሃን የሚያስፈልገው ሲሆን ከብርሃን ወደ ጨለማ ሲገባ ዓይኖቹን ለማለማመድ የሚወስድበት ጊዜ ከልጁ በሁለት እጥፍ ይበልጣል።” በዓይናችን ላይ የሚከሰቱት እነዚህ ለውጦች በምሽት መንዳትን ፈታኝ ሊያደርጉብን ይችላሉ።
ሄንሪ የ72 ዓመት አረጋዊ ሲሆኑ ለ50 ዓመታት ሲነዱ የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው አያውቅም። ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ግን ምሽት ላይ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎች የሚያበሩት መብራት ዓይናቸውን እያጥበረበረው መኪና
መንዳትን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው አስተዋሉ። የዓይን ምርመራ ካደረጉ በኋላ ይህንን ብርሃን እንዲቀንስ ተደርጎ የተሠራ አዲስ ዓይነት መነጽር ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። ሄንሪ “አሁን አለ ችግር በምሽት መንዳት እችላለሁ” በማለት ይናገራሉ። ይህን ትንሽ ማስተካከያ ማድረጋቸው ያለ ችግር መኪና መንዳት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። እንደ ሙርተል ላሉት ሌሎች አሽከርካሪዎች ግን መፍትሔው በምሽት መኪና መንዳትን ፈጽሞ መተው ሊሆን ይችላል።በተጨማሪም የዕድሜ መግፋት ፈጠን ብሎ እርምጃ ለመውሰድ እንቅፋት ይሆናል። አረጋውያን ከወጣቶች ይልቅ ብልህና አስተዋይ ሊሆኑ ይችላሉ። ቢሆንም አንድ ሰው ዕድሜው እየገፋ በሄደ መጠን በተመለከተው ወይም በሰማው ነገር ላይ አውጥቶ አውርዶ እርምጃ ለመውሰድ ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ ይወስድበታል። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚለዋወጡት የትራፊክና የመንገድ ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ መኪና መንዳትን ለአረጋውያን ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል። አስፈላጊውን እርምጃ በወቅቱ ለመውሰድ እንዲቻል እነዚህን ለውጦች ወዲያውኑ ማገናዘብ ያስፈልጋል።
“በዕድሜ የገፉ አሽከርካሪዎች ከባድ አደጋ የሚደርስባቸው በአብዛኛው የትራፊክ ምልክቶችን ልብ ሳይሉ በመቅረታቸው ነው” በማለት ካር ኤንድ ትራቭል የተባለው መጽሔት ሪፖርት አድርጓል። ለምን? ይሄው ሪፖርት ሲቀጥል እንዲህ ይላል:- “ችግሩ . . . በዕድሜ የገፋው አሽከርካሪ ወደ መስቀለኛ መንገድ ከመግባቱ በፊት ከግራና ከቀኝ የሚመለከተውን ነገር በፍጥነት አገናዝቦ እርምጃ ከመውሰዱ ጋር የተያያዘ ይመስላል።”
ይህን ችግር ለማስወገድ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ወደ መስቀለኛ መንገዶች ስትቃረብ ጥንቃቄ አድርግ። መንገዱን ማቋረጥ ከመጀመርህ በፊት ግራና ቀኝህን ደጋግመህ የመመልከት ልማድ ይኑርህ። በተለይ ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ በምትታጠፍበት ጊዜ ጥንቃቄ አድርግ። በመስቀለኛ መንገድ ላይ መታጠፍ በተለይ ደግሞ ከፊት ለፊት የሚመጡ መኪናዎች የሚያልፉበትን መንገድ ማቋረጥ የሚኖርብህ ከሆነ አደገኛ ሊሆን ይችላል።
በዩናይትድ ስቴትስ እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ አሽከርካሪዎች በመስቀለኛ መንገድ ላይ ከሚደርስባቸው ከባድ አደጋዎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪው ወደ ግራ ለመታጠፍ በሚሞክርበት ጊዜ የሚከሰቱ ናቸው። የአሜሪካን የተሽከርካሪዎች ማኅበር የትራፊክ ደህንነት ተቋም በዚያ አገር ለሚገኙ አሽከርካሪዎች “አንዳንድ ጊዜ ወደ ግራ መታጠፍን ለማስቀረት ሦስት ጊዜ ወደ ቀኝ ታጥፈህ ወደምትፈልግበት ቦታ መሄድ ይሻላል” በማለት ሐሳብ ያቀርባል። አንተም የምትኖርበትን አካባቢ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህን ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ። አስቀድመህ ካሰብክበት አደገኛና አስቸጋሪ የሆኑ መስቀለኛ መንገዶችን ከማቋረጥ ልትድን ትችላለህ።
ልታስብበት የሚገባ ውሳኔ
መኪና የመንዳት ችሎታህን ለመመዘን ምን ልታደርግ ትችላለህ? የምትቀርበው ጓደኛህ ወይም የቤተሰብህ አባል አብሮህ እንዲጓዝ በማድረግ የመንዳት ችሎታህን እንዲገመግም ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም የሚሰጥህን ሐሳብ በጥንቃቄ አዳምጥ። እንዲሁም መኪና የመንዳት ችሎታን ለማሻሻል የሚሰጡ ትምህርቶችን መውሰድ ትችላለህ። በአንዳንድ አገሮች የሚገኙ የአሽከርካሪዎች ማኅበራት በዕድሜ ለገፉ አሽከርካሪዎች ልዩ ሥልጠና ይሰጣሉ። አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ለጥቂት ከአደጋ ከተረፍክ የመንዳት ችሎታህ እንደድሮው እንዳልሆነ የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምልክት ሊሆን ይችላል።
እድሜህ እየገፋ ሲሄድ መኪና መንዳት ማቆም እንዳለብህ መወሰንህ አይቀርም። እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማድረጉ ከባድ ሊሆን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሙርተል አንድ ቀን መኪና ማሽከርከር እንደሚያቆሙ ያውቃሉ። እስከዚያው ግን ሌሎች በሚነዱት መኪና መጓዝን ማዘውተር ጀምረዋል። ሌላ ሰው እንዲነዳላቸው በማድረጋቸው ምን ይሰማቸዋል? “መኪና መንዳት የሚያስከትለው ውጥረት ሳይሰማህ መጓዝ ደስ የሚል ነው” በማለት ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ በጥንቃቄ ካሰብክበት በኋላ አንተም እንዲህ ማድረግ እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል። ከጓደኛህ ጋር ሆነህ ገበያ መውጣት፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ማስፈጸምና ወደ ቀጠሮ ወይም ወደ ስብሰባ ቦታ መሄድ ይበልጥ አስደሳች ሊሆንልህ ይችላል። ምናልባትም ጓደኛህ መኪናህን እየነዳልህ አብረኸው ልትሄድ ትችላላችሁ። ብቻህን ከመንዳት ይልቅ ከሰው ጋር መሆኑ ይበልጥ አስተማማኝና አስደሳች ሊሆን ይችላል። በሕዝብ መጓጓዣ መጠቀምም ሌላው አማራጭ ነው። ማንነትህ የሚለካው መኪና በመንዳት ችሎታህ እንዳልሆነ አስታውስ። በቤተሰብህ፣ በጓደኞችህ እንዲሁም በአምላክ ፊት ዋጋ እንዲኖርህ የሚያደርጉት መልካም ባሕርያትህ ናቸው።—ምሳሌ 12:2፤ ሮሜ 14:18
ወጣትም ሆንክ በእድሜ የገፋህ፣ ልምድ ያካበትክ አሽከርካሪም ሆንክ ገና ለማጅ የመኪና አደጋ እንደማይደርስብህ አድርገህ ፈጽሞ ማሰብ አይኖርብህም። መኪና ማሽከርከር ከባድ ኃላፊነት እንደሆነ አስታውስ። ሊያጋጥምህ የሚችለውን የመኪና ግጭት ለመቀነስ ጥንቃቄ አድርግ። እንዲህ በማድረግ ወደፊት በምታደርጋቸው ጉዞዎች ላይ የአንተንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት መጠበቅ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.13 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌሊት ሰውነትህ በቂ እንቅልፍ እንዲያገኝ አድርግ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥቂት አረፍ ብሎ ማሸለብ ከጉዞህ በመጠኑ ቢያዘገይህም ሕይወትህን ግን ሊያድንልህ ይችላል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዕድሜ የገፉ አሽከርካሪዎች ልምድ ያካበቱ ቢሆኑም የራሳቸው ፈተናዎች አሉባቸው
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሰው ጋር ሆኖ መጓዝ ጥቅሞች አሉት