ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
ሥራ ለማግኘት ብሎ መዋሸት
የለንደኑ ፋይናንሽያል ታይምስ “ከአራት ሰዎች አንዱ የሥራ ማመልከቻ ሲያስገባ ይዋሻል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ኮንትሮል ሪስክስ ግሩፕ የተባለ አንድ የደህንነት ጥበቃ ኩባንያ በገንዘብ ነክ አገልግሎቶችና በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የሥራ መስክ በተሰማሩ 10, 435 አመልካቾች ላይ ለ12 ወራት ምርመራ ካካሄደ በኋላ “በየትኛውም ደረጃ ያሉ ሥራ ፈላጊዎች የውሸት መረጃ እንደሰጡ” ማረጋገጡን ጋዜጣው ዘግቧል። “ከአመልካቾቹ መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት ትክክል ያልሆኑ የሥራ ልምድ መረጃዎችን ያሰፈሩ ሲሆን 32 በመቶ የሚሆኑት የተጋነነ ወይም ትክክል ያልሆነ የትምህርት መረጃ አቅርበዋል። ከዚህም ሌላ 19 በመቶ የሚሆኑት የገንዘብ ኪሣራ ደርሶባቸው እንደነበረ ወይም ብድር ወስደው ሳይከፍሉ እንደቀሩ የሸሸጉ ሲሆን 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ማንነታቸውን የሚጠቁሙ አንዳንድ መረጃዎችን ደብቀዋል።” በተለይ ውጭ አገር ሲኖሩ ቆይተው የተመለሱ ሰዎች እንደማይደረስባቸው አድርገው ስለሚያስቡ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ይዋሻሉ። ወንዶች “ከሴቶች የበለጠ የመዋሸት አዝማሚያ ይታይባቸዋል።” የምልመላና የቅጥር ኮንፌዴረሽን ባልደረባ የሆኑት ቲም ኒከልሰን ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ውጤት ትክክል መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ “የምልመላ ሠራተኞች በወረቀት ላይ ሠፍሮ ያገኙት መረጃ ሁሉ ትክክል እንደሆነ አድርገው ከተቀበሉ ሥራቸውን በትክክል አከናውነዋል ማለት አይቻልም” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
ለሰው አለርጂክ ናቸው
ላይፕሲገር ፎልክሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ጋዜጣ “ብዙ እንስሳት ለሰው አለርጂክ ናቸው” ይላል። ይኸው ጋዜጣ እንደዘገበው የጀርመን የአለርጂና የአስም ማህበር በቅርቡ “ከ20 የቤት እንስሳት መካከል አንዱ ሰው አጠገብ በሚሆንበት ጊዜ እንደ ቆዳ ማሳከክና እንደ ማስነጠስ የመሰለ የአለርጂ ምልክት እንደሚታይበት” አስታውቋል። አብዛኛውን ጊዜ ለዚህ ምክንያት የሚሆነው የሰዎች ቆዳ ቅርፊቶችና በእነዚህ የቆዳ ቅርፊቶች ላይ የሚኖሩ ትናንሽ ነፍሳት የሚጥሉት ኩስ ነው። አንድ የቤት እንስሳ ቁንጫ ሳይኖርበት ሳያቋርጥ ራሱን የሚልስ ወይም ፀጉሩን የሚያክ ከሆነ እንስሳው ለሰው አለርጂክ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። አካባቢው ሲለወጥለት ወይም ከባለቤቱ በሚርቅበት ጊዜ የሚተወው ከሆነ አለርጂክ መሆኑን በይበልጥ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። በተጨማሪም ምግብና የአበባ ብናኝ ለእንስሳት አለርጂ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል። የጀርመን የአለርጂና የአስም ማህበር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የማስነጠስ ሕመም የያዛቸው ፈረሶች ቁጥር በጣም መጨመሩን አስታውቋል።
ወፎች የጦር ቅርጽ ሠርተው አንድ ላይ የሚበሩት ለምንድን ነው?
ባሁኑ ጊዜ ተመራማሪዎች እንደ ቆልማሚት (pelican) ያሉ ወፎች “የጦር ቅርጽ ሠርተው ባንድ ላይ የሚበሩት ረዥም ጉዞ በሚጓዙበት ጊዜ ከፊታቸው ያለው አየር ፍጥነታቸውን እንዳይቀንስባቸውና በዚህም ምክንያት የሚደርስባቸውን ድካም ለመቀነስ” እንደሆነ ተመራማሪዎች ተጨባጭ ማስረጃ አግኝተዋል ይላል የለንደኑ ዘ ደይሊ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ኔቸር መጽሔት ስላቀረበው ሪፖርት ሲያትት። በፈረንሳይ አገር በቪልዬ ኦን ቧ ከተማ በብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል የሚሠሩ ተመራማሪዎች የጦር ቅርጽ ሠርተው በመብረር ላይ ያሉ ስምንት ፔሊካኖችን የልብ ምት ከለኩ በኋላ እነዚህን ቁጥሮች “ከክንፋቸው እርግብግቢት ፍጥነትና ከአበራራቸው” ጋር አወዳድረዋል። ተመራማሪዎቹ ፍጥነታቸው አንድ ዓይነት ቢሆንም አንድ ላይ ሆነው በሚበሩበት ጊዜ ያላቸው የልብ ምትና የክንፋቸው መርገብገብ ለየብቻ ሲበሩ ከሚኖራቸው ያነሰ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ወፎቹ አንድ ላይ ሆነው በቡድን በሚበሩበት ጊዜ አንደኛው ወፍ በክንፉ የሚቀዝፈው አየር ሌላውን በማንሳፈፍ በቀላሉ እንዲበርር ይረዳዋል። ነጭ ፔሊካኖች በዚህ ዘዴ በመጠቀም ብቻቸውን በሚበርሩበት ጊዜ ከሚፈጁት 20 በመቶ ያነሰ ጉልበት ይፈጃሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በፈረንሳይ
ጥናት ከተደረገባቸው ፈረንሳውያን መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ቢሆኑም በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን ያሉት ከ2 በመቶ እንደማይበልጡ ላ ክሩዋ በተባለው የካቶሊክ ጋዜጣ ላይ የወጣው የጥናት ውጤት ያመለክታል። ሰባ ሁለት በመቶ የሚሆኑት “መጽሐፍ ቅዱስን ፈጽሞ አንብበን አናውቅም” ብለዋል። ጥናት ከተደረገባቸው መካከል 54 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስ “ዘመኑ ያለፈበትና ከዘመናዊው ዓለም ጋር የማይጣጣም” ነው ብለው ያስባሉ። “ፈረንሳውያን መጽሐፍ ቅዱስን ከባሕላዊ ጠቀሜታው አንጻር ብቻ የሚመለከቱት ሲሆን የሚያነቡትም ስለ አይሁድና ስለ ክርስትና አመጣጥ ለማወቅ ሲፈልጉ ብቻ ነው” በማለት ሪፖርቱ ያብራራል። “በየዓመቱ በፈረንሳይ አገር 250, 000 መጽሐፍ ቅዱሶችና 30, 000 አዲስ ኪዳኖች ይሸጣሉ” ይላል ላ ክሩዋ።
ጽዳት ለኤቨረስት ተራራ
በከፍታው ከዓለም አንደኛ ስለሆነው የኤቨረስት ተራራ (8, 882 ሜትር) ሲነሣ ወደ አእምሮ የሚመጣው ያልተበከለና ግርማ ሞገስ የተላበሰ ታላቅ ተራራ ነው። ዳውን ቱ ኧርዝ የተባለ የኒው ዴልሂ መጽሔት ባወጣው ሪፖርት መሠረት ግን የኤቨረስት ተራራ በጣም ትልቅ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኗል። ባለፉት አሥር ዓመታት የኤቨረስትን ተራራ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ተራራ ወጪዎች “ባዶ የኦክሲጅን መያዣዎችን፣ አሮጌ መሰላሎችንና ምሰሶዎችን፣ የፕላስቲክ ምርኩዞችን” ጨምሮ በብዙ ቶን የሚመዝኑ ቆሻሻዎችን ጥለው ወርደዋል። ሪፖርቱ ከሁሉ የሚቆሽሸው “አብዛኞቹ ተራራ ወጪዎች ወደ ተራራው አናት የሚያደርጉትን ጉዞ የሚጀምሩበት የሳውዝ ኮል ሠፈር ነው” ይላል። የኔፓል ተራራ ወጪዎች ማኅበር ባለ ሥልጣን የሆኑት ቡሚ ላል ላማ “ሼርፓዎች ለሚሰበስቡት ለእያንዳንዱ ኪሎ ግራም ቆሻሻ 100 ብር ያህል ለመክፈል እያሰብን ነው” ብለዋል። ሼርፓ የሚባሉት “ለተራራ ወጪዎች መንገድ የሚያሳዩና ጓዛቸውን የሚሸከሙላቸው ሰዎች ናቸው” ይላል ሪፖርቱ።
“አስማት” ጉዳት አደረሰ
“አንድ የጋና ተወላጅ በመንደሩ የሚኖር ጠንቋይ ያደረገለትን የጥይት መከላከያ ሲሞክር” እንደተገደለ የሮይተር ዜና አገልግሎት ሪፖርት አድርጓል። በሰሜናዊ ምዕራብ ጋና የሚኖሩ የአንድ መንደር ሰዎች ለጥይት የማይበገሩ መሆን ይችሉ ዘንድ አስማት እንዲያደርግላቸው ይጠይቃሉ። “ሟቹ ለሁለት ሳምንት በየቀኑ በርካታ ቅጠላ ቅጠሎች ሲቀባ ከቆየ በኋላ አስማቱ መሥራት አለመሥራቱ በራሱ ላይ እንዲሞከር ፈቃደኛ ሆነ”
ይላል ሪፖርቱ። ሰውዬው በተተኮሰበት አንድ ጥይት ወዲያው ሞተ። ከዚያ በኋላ በነገሩ የተቆጡ ጎረቤቶቹ ጥንቆላው ስላልሰራ ጠንቋዩን አንቀው ክፉኛ ደበደቡት። በጋና ሰሜናዊ ጫፍ የሚኖሩ ሰዎች ከሌሎች ጎሣዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው የጠንቋዮችን እርዳታ ይፈልጋሉ።መኪና መንዳትና ድካም
“ድካም የተጫጫነው አሽከርካሪ በተለይ አልኮል ጠጥቶ ከሆነ ሞት ወይም ከባድ ጉዳት ለሚያደርስ ግጭት ሊጋለጥ ይችላል” በማለት ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል ዘግቧል። በፈረንሳይ አገር በቦርዶ ከተማ የሚገኙ ተመራማሪዎች በአውራ ጎዳና ላይ ከሚከሰቱ አደጋዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት አሽከርካሪዎች ድካም ሲጫጫናቸው የሚከሰቱ እንደሆነ ደርሰውበታል። ለተሽከርካሪዎች የተመቸ ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ እንኳን በአንድ ተሽከርካሪ ላይ ከሚደርሱ ከባድ ግጭቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት የሚከሰቱት ከድካም ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች የተነሣ ነው። በእንግሊዝ አገር በላፍበሮ ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ምርምር ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጂም ሆርን እንዳሉት ከሆነ ለአሽከርካሪዎች በጣም አደገኛ ከሆኑት ጊዜያት አንዱ ከሰዓት በኋላ ያለው ጊዜ ነው። “ሰዎች በተፈጥሮአችን ሁለት የእንቅልፍ ጊዜያት አሉን። አንደኛው ማታ ሲሆን ሁለተኛው ከሰዓት በኋላ ከ8 እስከ 10 ሰዓት ያለው ጊዜ ነው።” ታዲያ አንድ አሽከርካሪ እንቅልፍ፣ እንቅልፍ ሲለው ምን ማድረግ ይኖርበታል? ወዲያው ዕረፍት ማድረግ ይኖርበታል። “መስኮት ወይም ራዲዮ መክፈት መፍትሔ የሚሆነው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው” ይላሉ ሆርን። “ከሁሉ የሚሻለው ማቆሚያ ቦታ ፈልጎ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ ማሸለብ ነው።” ችግሩ ብዙ አሽከርካሪዎች እንቅልፍ፣ እንቅልፍ እንዳላቸው እያወቁ መንዳት ይቀጥላሉ። የለንደኑ ዘ ሰንዴይ ታይምስ እንዲህ ይላል:- “ማዛጋት ከጀመረህ፣ ዓይንህን መግለጥ ከከበደህ፣ ወይም በአንድ ነገር ላይ ማተኮር ካቃተህ ይህ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ምልክት መሆኑን አስታውስ። ችላ ብትል ሕይወትህ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።”
በዩናይትድ ስቴትስ የጠመንጃ ገበያ ደርቷል
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዳለው “ከመስከረም 11 ወዲህ ብዙ አሜሪካውያን ራሳቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው በማመን መሣሪያ መታጠቅ በመጀመራቸው በመላ አገሪቱ የጠመንጃዎችና የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ በጣም ከፍ ብሏል። አዳዲስ የመሣሪያ ደንበኞች በመጉረፍ ላይ ናቸው።” አንዳንድ የጠመንጃ አምራቾች አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብ ብሔራዊ ስሜት የሚቀሰቅሱ መፈክሮችንና ሥዕሎችን በመጠቀም የተፈጠረውን ችግር ለትርፍ ማጋበሻነት ተጠቅመውበታል። ይሁን እንጂ የጦር መሣሪያዎች በብዛት መሠራጨት ብዙ ባለሥልጣኖችን በጣም አሳስቧቸዋል። የሰሜን ማያሚ ቢች ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዊልያም ቢ በርገር “ይህን የሚያክል ብዙ ቁጥር ያለው ጠመንጃ ሰዎች እጅ መግባቱ ሕግ ማስከበር አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል ብለን እንሰጋለን” ብለዋል። ሕግ አክባሪ የሆኑ ሰዎች የገዟቸው የጦር መሣሪያዎች ውሎ አድሮ ወንጀለኞች እጅ እንደሚገቡ የሚያረጋግጡ አኃዛዊ መረጃዎች አሉ። በጦር መሣሪያዎች ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚከራከሩ ድርጅቶች ሰዎች የጦር መሣሪያ ከመግዛታቸው በፊት ቆም ብለው በጥሞና እንዲያስቡ አጥብቀው ይመክራሉ።
የአእምሮ ሕመም የሚያስከትለው ከባድ ኪሣራ
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ግሮ ሐርለም ብሩንትላን “የአእምሮ ሕመምና የነርቭ ቀውስ በመላው ዓለም ላይ የሚያደርሰው ኪሣራ በጣም ከፍተኛ ነው” ብለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው አንድ ሪፖርት “በመላው ዓለም ለጤና መታወክና ለአካል እክል ዋነኛ መንስዔዎች ከሆኑት መካከል አንዱ” የአእምሮ ሕመም እንደሆነ ያመለክታል። ባሁኑ ጊዜ በዓለም በአእምሮ ወይም በነርቭ መቃወስ ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር 450 ሚልዮን የደረሰ መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል። አብዛኞቹ ነርቭ ነክ በሽታዎች ሕክምና ያላቸው ቢሆንም ተለይቶ የታወቀ የአእምሮ ሕመም ካለባቸው ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት የሚደርስባቸውን መድልዎ ወይም ውርደት በመፍራት አሊያም ገንዘብ ወይም የሚያክማቸው በማጣት ምክንያት ሳይታከሙ ይቀራሉ።