አምላክ የዓመፅ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከታል?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ የዓመፅ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከታል?
ዓመፅ በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል። በጦርነት ከሚፈጸመው ዓመፅ ሌላ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በስፖርቱና በመዝናኛው ዓለም ዓመፅ ሲፈጸም ይታያል፤ ዱርዬዎችና አደገኛ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎችም እንዲሁ የዓመፅ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ሌላው ቀርቶ በቤት ውስጥ የሚፈጸመው የኃይል ድርጊት እንኳን በብዙ ቤተሰቦች ዘንድ የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በካናዳ 1.2 ሚልዮን ወንዶችና ሴቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ በትዳር ጓደኛቸው ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። ሌላ ጥናት ደግሞ ሚስቶቻቸውን ከሚደበድቡ ወንዶች መካከል 50 በመቶ የሚያህሉት በልጆቻቸውም ላይ አካላዊ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አመልክቷል።
እነዚህ የዓመፅ ድርጊቶች እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ አንተንም እንደሚያሳዝኑህ የታወቀ ነው። ያም ሆኖ በዛሬ ጊዜ የሚቀርቡት አብዛኞቹ መዝናኛዎች በዓመፅ ድርጊቶች የተሞሉ ናቸው። በፊልሞች ላይ በማስመሰል ከሚቀርቡት የዓመፅ ድርጊቶች በተጨማሪ በእውነት የሚፈጸሙ የዓመፅ ድርጊቶች በቴሌቪዥን ተቀርጸው ለተመልካቾች ይቀርባሉ። የቦክስ ውድድርና ሌሎች ዓመፅ የተሞሉ ስፖርቶች በብዙ አገሮች ውስጥ በጣም ተወዳጅ ናቸው። ይሁን እንጂ አምላክ የዓመፅ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከታቸዋል?
ዘመናት ያስቆጠረው የዓመፅ ታሪክ
የዓመፅ ድርጊቶች የጀመሩት ከረዥም ዘመናት በፊት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የኃይል ድርጊት እንደፈጸመ የሚገልጸው ዘገባ በዘፍጥረት 4:2-15 ላይ ይገኛል። የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ቅናት አደረበትና ወንድሙን ገደለው። አምላክ ምን አደረገ? ቃየን ወንድሙን በመግደሉ ምክንያት ይሖዋ አምላክ ከባድ ቅጣት እንደበየነበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።
ይህ ድርጊት ከተፈጸመ ከ1, 500 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ምድር ‘በዐመፅ እንደተሞላች’ በዘፍጥረት 6:11 (አ.መ.ት ) ላይ እናነባለን። በዚህ ጊዜስ አምላክ ምን አደረገ? ይሖዋ ጻድቁ ኖህና ቤተሰቡ በምድር ላይ ከሚመጣው የጥፋት ውኃ ለመዳን የሚያስችላቸውን መርከብ እንዲሠራ ለኖህ ከነገረው በኋላ ዓመፀኛውን ኅብረተሰብ ‘አጠፋው።’ (ዘፍጥረት 6:12-14, 17) ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ያን ያህል ዓመፀኛ የሆነው ለምን ነበር?
አጋንንት ያሳደሩት ተጽዕኖ
የዘፍጥረት ዘገባ የአምላክ ልጆች የነበሩ መላእክት በአምላክ ላይ በማመፅ ሰብዓዊ አካል ለብሰው ሚስቶች እንዳገቡና ልጆች እንደወለዱ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:1-4) ኔፍሊም በመባል የሚታወቁት ልጆቻቸው ከመጠን በላይ ግዙፎች ሲሆኑ ስማቸውም የገነነ ነበር። አጋንንት በሆኑት አባቶቻቸው ተጽዕኖ እነሱም ዓመፀኞች ሆኑ። የጥፋት ውኃው ምድርን ሲያጥለቀልቃት እነዚህ ዓመፀኞች ጠፉ። አጋንንቱ ግን ሰብዓዊ አካላቸውን ትተው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ሳይመለሱ አልቀሩም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ዓመፀኛ መላእክት በሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ኤፌሶን 6:12) መሪያቸው ሰይጣን የመጀመሪያው “ሐሰተኛ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 8:44) በመሆኑም በምድር ላይ የሚፈጸመው የዓመፅ ድርጊት አጋንንታዊ ወይም ሰይጣናዊ ተብሎ ሊጠራ ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፅ የማታለል ኃይል እንዳለው ይናገራል። ምሳሌ 16:29 “ግፈኛ [“ዓመፀኛ፣” NW ] ሰው ወዳጁን ያባብላል፣ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል” ይላል። ዛሬ ብዙዎች ሳያውቁት የዓመፅ ድርጊቶችን የሚደግፉና የሚያበረታቱ ከመሆኑም በላይ ድርጊቶቹን ይፈጽማሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም እንዲሁ ተታልለው የዓመፅ ድርጊቶችን በሚያወድሱ መዝናኛዎች ይካፈላሉ። በመዝሙር 73:6 (አ.መ.ት ) ላይ ያሉት ቃላት ዛሬ ያለውን ትውልድ በትክክል ይገልጹታል። መዝሙራዊው “ትዕቢት የአንገት ጌጣቸው ነው፤ ዐመፅንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈዋል” በማለት ተናግሯል።
አምላክ ዓመፅን ይጠላል
ክርስቲያኖች ዓመፀኛ በሆነ ዓለም ውስጥ መመላለስ ያለባቸው እንዴት ነው? የያዕቆብ ልጆች ስለሆኑት ስለ ስምዖንና ሌዊ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በዚህ ረገድ ጥሩ መመሪያ ይሰጠናል። እህታቸው ዲና ሥነ ምግባር ከጎደላቸው የሴኬም ሰዎች ጋር ጓደኝነት በመመሥረትዋ በአንድ ሴኬማዊ ሰው በጾታ ተነወረች። በአጸፋውም ስምዖንና ሌዊ የሴኬምን ወንዶች በሙሉ ያለ ርኅራኄ ገደሏቸው። ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹ ቁጣቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በመንፈስ ተነሳስቶ የሚከተለውን እርግማን ተናግሯል:- “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። በምክራቸው፣ ነፍሴ፣ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፣ ክብሬ፣ አትተባበር።”—ዘፍጥረት 49:5, 6
ከእነዚህ ቃላት ጋር በሚስማማ መልኩ ክርስቲያኖችም ዓመፅን ከሚያስፋፉ ወይም በዓመፅ ድርጊቶች ከሚካፈሉ ሰዎች ጋር ከመተባበር ይቆጠባሉ። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አምላክ ዓመፅን የሚያስፋፉ ሰዎችን ይጠላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 11:5) ክርስቲያኖች ስድብን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ እንዲያስወግዱ ተመክረዋል።—ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 4:31
ዓመፅ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
የጥንቱ ነቢይ ዕንባቆም “‘ግፍ በዛ’ ብዬ እየጮኽሁ፣ አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ለይሖዋ አምላክ አቅርቦ ነበር። (ዕንባቆም 1:2 አ.መ.ት ) ምናልባት አንተም ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቀህ ይሆናል። አምላክ ‘ኃጢአተኛውን’ እንደሚያጠፋ ቃል በመግባት ለዕንባቆም መልስ ሰጥቶታል። (ዕንባቆም 3:13) ትንቢታዊው የኢሳይያስ መጽሐፍም ተስፋ ይሰጣል። አምላክ እንዲህ የሚል ቃል ገብቷል:- “ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፣ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም።”—ኢሳይያስ 60:18
የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በቅርቡ ማንኛውንም ዓይነት ዓመፅና ዓመፅን የሚያስፋፉ ሰዎችን ከምድር ገጽ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ እርግጠኞች ናቸው። በዚያን ጊዜ ምድር በዓመፅ ሳይሆን “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን . . . የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለች።”—ዕንባቆም 2:14
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቃየን አቤልን በገደለው ጊዜ ዓመፅ ጀመረ