የልጆች እንቅልፋምነት አሳሳቢ ችግር ሆኗልን?
የልጆች እንቅልፋምነት አሳሳቢ ችግር ሆኗልን?
ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በካናዳ የሚታተመው ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ እንቅልፍ ማጣት የማሰብና የማስታወስ ችሎታን እንደሚቀንስና የዚህ ችግር ተጠቂዎች አብዛኞቹ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች መሆናቸውን ዘግቧል። “ልጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በቂ እንቅልፍ ሳያገኙ ሲቀሩ ባሕርያቸው ይለወጣል፣ ነጭናጮችና ቁንጥንጦች ይሆናሉ።” ተመራማሪዎች 2, 200 የሚያህሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የእንቅልፍ ልማድ ካጠኑ በኋላ 47 በመቶ የሚሆኑት በየቀኑ ማግኘት ያለባቸውን የ8 ሰዓት እንቅልፍ እንደማያገኙ ደርሰውበታል።
አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች አኗኗራቸው የሚያስፈልጋቸውን እንቅልፍ እንዳያገኙ ቢያደርጋቸውም “አንዳንዶቹ ያልታወቀ የጤና ችግር ሊኖርባቸው ይችላል” በማለት ግሎብ ይናገራል። “ከ4 እስከ 18 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ልጆች መካከል 4 በመቶ የሚሆኑት በእንቅልፍ ላይ ሳሉ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የትንፋሽ መቋረጥ ችግር ያጋጥማቸዋል።” በእንቅልፍ ጊዜ በጉሮሮ በኩል የሚያልፈው የአየር ቱቦ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ይዘጋና አየር እንዳያልፍ ይከለክላል። ስለሆነም አእምሮ ሙሉ በሙሉ እረፍት ስለማያገኝ ልጆቹ ሲነቁ ድካም ድካም ይላቸዋል፣ እንዲሁም ነጭናጫ ይሆናሉ።
በእንቅልፍ ላይ እያሉ ማንኳረፍ፣ ማቃተት፣ ጠዋት ጠዋት የሚያጋጥም የራስ ምታት፣ የማስታወስና ትኩረትን የማሰባሰብ ችግሮች እንዲሁም ቀን ላይ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት ይህ ዓይነቱ የእንቅልፍ መዛባት እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸው ተኝተው እንቅልፍ ላይ እያሉ አልፎ አልፎ እንዲያዳምጧቸው ተመክረዋል። በሞንትሪያል የልጆች ሆስፒታል ከልጆች እንቅልፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ሮበርት ብሩየት እንዲህ ዓይነቱ ችግር ያለበት ልጅ በእንቅልፍ ላይ እያለ ደረቱ ቢንቀሳቀስም መተንፈስ ሊያቆም እንደሚችል ተናግረዋል። “ይህ ልጁን ከእንቅልፉ የሚቀሰቅሰው ሲሆን ሙሉ በሙሉም ወይም በከፊል ከነቃ በኋላ ትንፋሽ ይስብና ወዲያው ተመልሶ ይተኛል።” እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በየሌሊቱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት ሊያጋጥም የሚችል ሲሆን ይህም ልጁ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ የመጫጫን ስሜት ሊፈጥርበት ይችላል።
የአሜሪካ የእንቅልፍ መዛባት ችግሮች ማኅበር ቀዝቀዝና ጨለምለም ባለ እንዲሁም እንደ ቴሌቪዥን ወይም ኮምፒውተር ያሉ የሚያዘናጉ ነገሮች በሌሉበት የመኝታ ክፍል ውስጥ መተኛትን እንደ መፍትሔ አድርጎ ይጠቁማል። ልጆችና በአሥራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማታ የሚተኙበትና ጠዋት የሚነሱበት ቋሚ ሰዓት መመደባቸው ሌሊት ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። በእንቅልፍ ላይ የትንፋሽ መቋረጥ ችግር ያለባቸው አንዳንዶች በጉሮሯቸው በኩል የሚያልፈው የአየር ቱቦ እንዳይዘጋ በአፍንጫቸውና በአፋቸው አየር ያለማቋረጥ ወደ ውስጥ በሚገፋላቸው መሳሪያ ይጠቀማሉ። አንዲት የልጆች ሐኪም “እንቅልፍ ከምንመገበው ምግብ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግም ይበልጣል። እንቅልፍ ሆርሞኖቻችንን፣ ስሜታችንንና የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም ይቆጣጠራል” በማለት ተናግረዋል።