ሐዘን ላይ ላሉ የሚሆን ማጽናኛ
ሐዘን ላይ ላሉ የሚሆን ማጽናኛ
መስከረም 11, 2001 በኒው ዮርክና በዋሽንግተን ዲ ሲ ከተሞች የተፈጸመው የሽብርተኞች ጥቃት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦችን አስደንግጧል። በአንድ ቀን ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደፋር የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞችን፣ ፖሊሶችንና የህክምና እርዳታ ሰጪዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
ይህ አደጋ ከደረሰ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አሳዛኝ ገጠመኝ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሞት ያጡ ሰዎችን ለማጽናናት የተቀናጀ ጥረት አድርገዋል። ይህን ያደረጉት ‘ልባቸው የተሰበረውን ለመጠገን’ እና ‘የሚያለቅሱትን ለማጽናናት’ ነው።—ኢሳይያስ 61:1, 2
የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ብዙ ዓመታት ካገኙት ተሞክሮ የሚወዷቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከዚህ በታች የቀረቡት ጥያቄዎች እንደሚያሳስቧቸው ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱን ይሰጠናል። ጥቅሶቹን በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተህ ለምን አትመለከታቸውም?
አንድ ሰው የሚሞትበት ጊዜ አስቀድሞ ተወስኗል?
መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 9:11 ላይ “ጊዜና እድል” (“አጋጣሚ፣” ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) በማንኛውም ሰው ላይ ያልታሰበ ነገር ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራል። ሞት አስቀድሞ የተወሰነ ነገር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለደህንነታችን የሚበጁ ጥንቃቄዎችን እንድናደርግ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?—ለምሳሌ ዘዳግም 22:8ን ተመልከት።
የምንሞተው ለምንድን ነው?
የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች አዳምና ሔዋን በምድራዊ ገነት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ለአምላክ ታዛዥ ሆነው ቢቀጥሉ ኖሮ አይሞቱም ነበር። ሞት የሚመጣው ሰዎች አምላክን ካልታዘዙ ብቻ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15-17) የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን ፈጣሪያቸውን አልታዘዙም። በዚህም ምክንያት የኃጢአታቸው ዋጋ የሆነውን ሞትን ለመቀበል ተገደዱ። የሰው ልጆች ሁሉ የተገኙት ከአዳምና ከሔዋን ስለሆነ ሁሉም ኃጢአትንና ሞትን ወርሰዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ይገልጻል።—ሮሜ 5:12
ሙታን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
አዳም ካመፀ በኋላ አምላክ ‘ከምድር ስለ ተገኘህ ወደ ወጣህበት ምድር ትመለሳለህ . . . ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ’ ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:18-19 አ.መ.ት ) ስለዚህ ሞት ሙሉ በሙሉ ከህልውና ውጭ መሆን ወይም በሌላ አባባል አለመኖር ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:5፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ሲሞት “ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” በማለት ይናገራል።—መዝሙር 146:3, 4፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ሰው የማይሞት ነፍስ አለውን?
መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ አንተ ከሞትክ በኋላ መኖሯን የምትቀጥል ረቂቅ አካል ሳትሆን አንተ ራስህ ነፍስ እንደሆንክ በግልጽ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 2:7፤ ምሳሌ 2:10፤ ኤርምያስ 2:34 NW ) እንግዲያው አንድ ሰው ሲሞት ነፍስ ሞተ ማለት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ [ሰውዬው ማለት ነው] . . . ትሞታለች” በማለት በግልጽ ይናገራል።—ሕዝቅኤል 18:4
ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሙታንን በትንሣኤ አማካኝነት ወደ ሕይወት በመመለስ በሽታና ሞት ፈጽሞ በማይኖርባት ገነት የሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። ኢየሱስ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል . . . ይወጣሉና” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 21:1-4
ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በፊት ስለ ሞተው ወዳጁ ስለ አልዓዛር ሲናገር ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐንስ 11:11-13) አልዓዛርም ቢሆን ኢየሱስ ካስነሳው በኋላ ሞቶ በቆየበት አጭር ጊዜ ወደ ስቃይ ሥፍራም ሆነ ፍጹም ደስታ ወደሚገኝበት ቦታ ሄዶ እንደነበረ አልተናገረም። (ዮሐንስ 11:37-44) ሙታን ከህልውና ውጭ ስለሆኑ አልዓዛር ይህን በተመለከተ የሰነዘረው ሐሳብ አለመኖሩ ሊያስገርመን አይገባም። ሙታን የሚነሱበትን “ሰዓት” ይጠብቃሉ እንጂ ምንም ስቃይ አይደርስባቸውም። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ አልዓዛርን ማስነሳቱ ሙታን እንደገና በሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳያል። ኢየሱስ በዚህ ተአምር አማካኝነት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምን እንደሚፈጸም በትንሹ አሳይቷል ማለት ይቻላል። (ሥራ 24:15) ይህ በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች እንዴት ያለ ግሩም ማጽናኛ ነው!