ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ለምንድን ነው?
ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ለምንድን ነው?
“ሕይወቱን የሚያጠፋ ሰው ሁሉ የራሱ የሆነ እጅግ ምሥጢራዊ፣ ድብቅና ከባድ ጭንቀት ውስጥ የሚከት ምክንያት አለው።”—ኬይ ሬድፊልድ ጄሚሰን፣ የሥነ አእምሮ ባለሙያ።
“በሕይወት መኖር መከራ ነው።” ይህ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖር የነበረ ሪዩኖሱኬ አኩታጋዋ የተባለ የታወቀ ደራሲ የራሱን ሕይወት ከማጥፋቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት የጻፈው ነው። ይሁንና ይህን ዐረፍተ ነገር የከፈተው “እርግጥ መሞት አልፈልግም፤ ግን . . .” በሚሉት ቃላት ነበር።
እንደ አኩታጋዋ ሁሉ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ብዙ ሰዎችም መሞት ባይፈልጉም እንኳ “እየደረሰባቸው ካለው ነገር መገላገል” እንደሚፈልጉ አንድ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር ገልጸዋል። የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች በአብዛኛው የሚተዉት ማስታወሻ ይህንኑ የሚጠቁም ነው። ‘በቃኝ’ ወይም ‘ከዚህ በኋላ የእኔ መኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?’ የሚሉት አባባሎች በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ አስከፊ ሁኔታዎች ለመገላገል ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት የሚያመለክቱ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ ባለሙያ እንደገለጹት የራስን ሕይወት ማጥፋት “የጉንፋን በሽታን በኑክሊየር ቦምብ ለማከም እንደ መሞከር ይቆጠራል።”
ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች የሚለያዩ ቢሆንም እንኳ ለዚህ ድርጊት የሚገፋፉ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ አንዳንድ የተለመዱ ሁኔታዎች አሉ።
የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱ ሁኔታዎች
ልጆች ለሌሎች ተራ መስለው ሊታዩ በሚችሉ ነገሮች ሳይቀር ተስፋ ቆርጠው የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋታቸው ያልተለመደ አይደለም። በደል እንደተፈጸመባቸውና ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደሌለ ሆኖ ከተሰማቸው የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት የበደሏቸውን ሰዎች መበቀል እንደሚችሉ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። በጃፓን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚነሳሱ ሰዎችን በመርዳት ሙያ ላይ የተሰማሩት ሂሮሺ ኢናሙራ “ልጆች የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት ሥቃይ
ያደረሰባቸውን ሰው መቅጣት ይፈልጋሉ” ሲሉ ጽፈዋል።በቅርቡ በብሪታንያ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ልጆች ከባድ በደል በሚደርስባቸው ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርጉበት አጋጣሚ በሰባት እጥፍ ገደማ ይጨምራል። በልጆቹ ስሜት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ቀላል አይደለም። ራሱን ሰቅሎ የሞተ አንድ የ13 ዓመት ልጅ በተወው ማስታወሻ ላይ ያሠቃዩትን አልፎ ተርፎም አስፈራርተው ገንዘቡን የወሰዱበትን አምስት ልጆች ስም የጠቀሰ ሲሆን “እባካችሁ ሌሎች ልጆችን ታደጓቸው” ሲል ጽፏል።
ሌሎች ደግሞ በትምህርት ቤት ወይም ሕግ በመተላለፋቸው የተነሳ ችግር ሲገጥማቸው፣ ከፍቅረኛቸው ሲለያዩ፣ ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጡ፣ የትምህርት ቤት ፈተና ጭንቀት ሲፈጥርባቸው ወይም የወደፊቱ ሕይወታቸው ተስፋ ሲያስቆርጣቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡና በሁሉ ነገር ፍጽምና የመጠበቅ ዝንባሌ የሚታይባቸው አንዳንድ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች አንድ ሳንካ ወይም እክል ሲገጥማቸው ወይም እንደገጠማቸው አድርገው ሲያስቡ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ።
ዐዋቂ የሆኑ ሰዎችን ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከገንዘብ ወይም ከሥራ ጋር የተያያዙ ችግሮች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ያደርጓቸዋል። በጃፓን በርከት ላሉ ዓመታት ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ከመጣ ወዲህ በዓመት ውስጥ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ከ30, 000 በላይ ሆኗል። ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ የራሳቸውን ሕይወት ካጠፉት በመካከለኛ ዕድሜ ላይ ይገኙ ከነበሩ ወንዶች መካከል ሦስት አራተኛ ገደማ የሚሆኑት ይህን ድርጊት የፈጸሙት “ከዕዳ፣ በንግድ ሥራ ላይ ከሚደርስ ኪሳራ፣ ከድህነትና ከሥራ አጥነት ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ” ነው። ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮችም የራስን ሕይወት ለማጥፋት ሊያነሳሱ ይችላሉ። አንድ የፊንላንድ ጋዜጣ “ከትዳር ጓደኞቻቸው ከተፋቱ ብዙም ያልቆዩ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች” የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ያላቸው ዕድል በእጅጉ የሰፋ ነው ሲል ዘግቧል። በሀንጋሪ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት ከሚነሳሱት ልጃገረዶች መካከል አብዛኞቹ በተፋቱ ወላጆች ሥር ያደጉ ናቸው።
ጡረታ መውጣትና አካላዊ ሕመምም በተለይ አረጋውያን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። አንድ በሽታ የማይድን ዓይነት በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሕመምተኛው ሥቃዩን መቋቋም እንደማይችል አድርጎ በሚያስብበት ጊዜም የራሱን ሕይወት ማጥፋት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አድርጎ ሊያስብ ይችላል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች የገጠሙት ሰው ሁሉ የራሱን ሕይወት ለማጥፋት ይነሳሳል ማለት አይደለም። እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒ አብዛኞቹ ሰዎች ውጥረት ውስጥ የሚከቱ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት አያስቡም። አብዛኞቹ እንዲህ የማያስቡ ከሆነ ታዲያ አንዳንዶች መፍትሔው የራስን ሕይወት ማጥፋት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡት ለምንድን ነው?
ከበስተጀርባ ያሉት ምክንያቶች
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የሥነ አእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬይ ሬድፊልድ ጄሚሰን “ሰዎች በአብዛኛው ራሳቸውን ለመግደል እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው ላጋጠሟቸው ሁኔታዎች የሚሰጡት ትርጉም ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “አብዛኞቹ ጤናማ አእምሮ ያላቸው ሰዎች የገጠማቸው ሁኔታ ምንም ያህል አስከፊ ቢሆን የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያበቃ ምክንያት አድርገው አይመለከቱትም” ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኢቭ ኬ ሞሽቺትስኪ ከበስተጀርባ ያሉትን መንስኤዎች ጨምሮ በርካታ ምክንያቶች ተደራርበው አንድ ሰው ራሱን ለመግደል እንዲነሳሳ ያደርጉታል በማለት ተናግረዋል። እነዚህ ከበስተጀርባ ያሉ ምክንያቶች የአእምሮ ሕመምን፣ ከሱሰኝነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን፣ ጀነቲካዊ ቅንብርንና በአንጎል ውስጥ ያለውን ኬሚካላዊ አሠራር የሚያጠቃልሉ ናቸው። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።
ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ግንባር ቀደሞቹ እንደ የመንፈስ ጭንቀት፣ ባይፖላር ሙድ ዲስኦርደርስ፣ እና ስኪትሶፍሪኒያ ያሉ የአእምሮ ሕመሞችና አልኮልን አላግባብ የመጠጣት ወይም አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ ናቸው። በአውሮፓም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው ምርምር እንዳመለከተው የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሰዎች መካከል ከ90
በመቶ በላይ የሚሆኑት እንዲህ ዓይነት ችግሮች ያሉባቸው ናቸው። እንዲያውም የስዊድን ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ ምርመራ ተደርጎላቸው እንዲህ ዓይነት ችግሮች ካልታዩባቸው 100, 000 ወንዶች መካከል የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉት 8.3 የሚያክሉት ሲሆኑ የመንፈስ ጭንቀት ካለባቸው 100, 000 ወንዶች መካከል ግን 650 የሚሆኑት የራሳቸውን ሕይወት ያጠፋሉ! በምሥራቃውያን አገሮችም ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ተመሳሳይ እንደሆኑ ጠበብት ይናገራሉ። ይህ ማለት ግን የመንፈስ ጭንቀትና የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚያነሳሱ ሁኔታዎች የተደራረቡበት ሰው ሁሉ ራሱን መግደሉ አይቀሬ ነው ማለት አይደለም።በአንድ ወቅት ራሳቸውም ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገው የነበሩት ፕሮፌሰር ጄሚሰን “ሰዎች ሁኔታዎች ይሻሻላሉ የሚል እምነት እስካላቸው ድረስ የመንፈስ ጭንቀትን የመቋቋም ወይም የመቻል አቅም ያላቸው ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ እያደር እየጨመረ የሚመጣው የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊሸከሙት የማይችሉት ደረጃ ላይ ሲደርስ አእምሮም የራስን ሕይወት ለማጥፋት የሚገፋፋውን ስሜት ለመዋጋት ያለው አቅም ቀስ በቀስ እየተዳከመ እንደሚሄድ ፕሮፌሰሯ አመልክተዋል። ሁኔታውን በተደጋጋሚ በሚደርስበት ጫና እየሳሳ ከሚሄድ የመኪና ፍሬን ሸራ ጋር አመሳስለውታል።
የመንፈስ ጭንቀት በሕክምና እርዳታ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነገር በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን አዝማሚያ ልብ ማለቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የተስፋ መቁረጥን ስሜት በአዎንታዊ አመለካከት መተካት ይቻላል። ከበስተጀርባ ያሉት መንስኤዎች ተለይተው ታውቀው መፍትሔ ሲፈለግላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ የሚያደርጓቸውን እጅግ አሳዛኝና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በተለየ መንገድ መመልከት ሊጀምሩ ይችላሉ።
አንዳንዶች ጀነቲካዊ ቅንብር ብዙዎች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ሊያደርግ የሚችል ስውር መንስኤ እንደሆነ ያምናሉ። እርግጥ ነው፣ ጂኖች የአንድን ሰው ባሕርይ በመወሰን ረገድ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ሲሆን የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት በአንዳንድ የዘር ሐረጎች ውስጥ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ ጥናቶች አመልክተዋል። ሆኖም “በጀነቲካዊ ቅንብር ሳቢያ የራስን ሕይወት ለማጥፋት ድርጊት የተጋለጡ ሰዎች ድርጊቱን ፈጽሞ ሊያስቀሩት አይችሉም ማለት እንዳልሆነ ሊስተዋል ይገባል” ይላሉ ጄሚሰን።
የአንጎል ኬሚካላዊ አሠራርም ስውር መንስኤ ሊሆን ይችላል። በአንጎል ውስጥ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሕዋሳተ ነርቭ ኤሌክትሮኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ግንኙነት ያደርጋሉ። ወደተለያየ አቅጣጫ ተዘርግተው በሚገኙት የነርቭ ቃጫዎች ጫፍ ጋጥሚያ ሕዋሳተ ነርቭ (synapses) በመባል የሚታወቁ ትናንሽ ክፍተቶች አሉ። ኒውሮትራንስሚተር የሚባሉት ንጥረ ነገሮች በእነዚህ ጋጥሚያ ሕዋሳተ ነርቭ በኩል መረጃውን ኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ያስተላልፋሉ። ሴሮቶኒን የሚባለው ኒውሮትራንስሚተር ያለው መጠን አንድ ሰው ከሥነ ሕይወት አኳያ የራስን ሕይወት ለማጥፋት ድርጊት የተጋለጠ እንዲሆን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ኢንሳይድ ዘ ብሬን የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሴሮቶኒን መጠን ማነስ . . . የሕይወትን ደስታ ሊሰርቅ፣ የሰውን የመኖር ፍላጎት ሊያጠፋ፣ ለመንፈስ ጭንቀት ይበልጥ ሊያጋልጥና የራስን ሕይወት ለማጥፋት ሊያነሳሳ ይችላል።”
ይሁን እንጂ የራሱን ሕይወት እንዲያጠፋ ተደርጎ የተፈጠረ ሰው እንደሌለ መታወቅ አለበት። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እጅግ አሳዛኝ የሆኑና ውጥረት ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ይኖራሉ። አንዳንዶች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ነገር ለሚያጋጥማቸው ጫና አእምሯቸውና ልባቸው ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ነው። ጎልተው የሚታዩት ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ ከበስተጀርባ ያሉት መንስኤዎችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።
እንግዲያው የመኖርን ፍላጎት መልሶ ሊያቀጣጥል የሚችል ይበልጥ አዎንታዊ የሆነ አመለካከት መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፆታና የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊት
በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ሴቶች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ ከወንዶቹ ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ሙከራቸው ተሳክቶ ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ወንዶች ቁጥር ግን ከሴቶቹ በአራት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል። በመንፈስ ጭንቀት የሚጠቁ ሴቶች ቁጥር ከወንዶቹ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት በሚያደርጉት ሙከራ ረገድ ከወንዶቹ በልጠው ሊገኙ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ይሁንና የሚያድርባቸው የመንፈስ ጭንቀት በጣም ከባድ ላይሆን ስለሚችል ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚጠቀሙበት ዘዴም ያን ያህል አደገኛ ላይሆን ይችላል። በአንጻሩ ግን ወንዶች ሙከራቸው ስኬታማ እንዲሆን ይበልጥ ኃይለኛና የማያዳግም እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ በቻይና ከወንዶቹ ይልቅ ሙከራቸው ይበልጥ የሚሳካላቸው ሴቶቹ ናቸው። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደጠቆመው በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሴቶች መካከል 56 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በቻይና በተለይ ደግሞ በገጠራማው ክፍል የሚኖሩ ናቸው። ሴቶቹ በግብታዊነት የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራ የሚሳካበት አንዱ ምክንያት ቀሳፊ የሆኑ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶች እንደ ልብ ስለሚገኙ እንደሆነ ይነገራል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊትና ብቸኝነት
ሰዎች የመንፈስ ጭንቀት እንዲይዛቸውና የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የብቸኝነት ስሜት ነው። በፊንላንድ በተፈጸሙ የራስን ሕይወት የማጥፋት ድርጊቶች ላይ የተካሄደውን ጥናት የመሩት ዮኡኮ ሎንክዊስት “[የራሳቸውን ሕይወት ካጠፉት ሰዎች መካከል] ብዙዎቹ የብቸኝነት ኑሮ ይኖሩ የነበሩ ናቸው። ብዙ ትርፍ ጊዜ የነበራቸው ቢሆንም ከሌሎች ጋር እምብዛም ማኅበራዊ ግንኙነት አልነበራቸውም” ሲሉ ተናግረዋል። በጃፓን በሃማማትሱ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የሥነ አእምሮ ባለሙያ የሆኑት ኬንሺሮ ኦሃራ በአገሪቱ የራሳቸውን ሕይወት የሚያጠፉ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶች ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ነገር “ብቸኝነት” እንደሆነ ገልጸዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙውን ጊዜ ዐዋቂ የሆኑ ሰዎችን ከገንዘብ ወይም ከሥራ ጋር የተያያዙ ችግሮች የራሳቸውን ሕይወት ለማጥፋት እንዲነሳሱ ያደርጓቸዋል