ማታቱ—በቀለማት ያሸበረቀ የኬንያ መጓጓዣ
ማታቱ—በቀለማት ያሸበረቀ የኬንያ መጓጓዣ
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ኬንያን የጎበኘ ሰው ስላደረገው ጉዞ አውርቶ እንደማይጠግብ የታወቀ ነው። መንጋውን የምትመራ ዝሆን፣ ባለግርማ አንበሳ እንዲሁም ፀሐይ ስትጠልቅ የምትፈጥረው ወደ ወይን ጠጅ ያደላ ቀይ ቀለም ከጎብኚው አእምሮ የማይጠፉ ጉልህ ምስሎች ናቸው። በዚያ የሚታየው ውበት ሰፊና ዓይነቱ የበዛ ነው። ይሁን እንጂ በአካባቢው በሚገኙ ብዙ ጎዳናዎች ላይ ትኩረት የሚስቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ። እነርሱም እንደልባቸው የሚከንፉት ማታቱዎች ናቸው። ይህ ስም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተወሰኑ መኪናዎች የሚጠሩበት ነው። ተለይተው የሚታወቁባቸው አስደናቂ ገጽታዎቻቸው በኬንያ ውስጥ በጣም ተወዳጅ የትራንስፖርት ዘዴ ለመሆን አብቅተዋቸዋል።
የማታቱ አጀማመር እንደ ሥራ ጠባያቸው ሁሉ አስደናቂ ነው። የመጀመሪያው ማታቱ ፎርድ ቴምስ ሞዴል የሆነ አሮጌ መኪና ሲሆን ይህ መኪና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ የነበሩ የብሪታንያ ወታደሮች ይጠቀሙባቸው ከነበሩ መኪኖች አንዱ ነው። በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ አንድ የናይሮቢ ነዋሪ ጥቂት ጓደኞቹን ወደ መሃል ከተማ ለማድረስ በዚህ አሮጌ መኪና ተጠቀመ። በዚያን ጊዜ እያንዳንዳቸው ለነዳጅ 30 ሳንቲም እንዲያዋጡ አድርጎ ነበር። * ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሌሎች ሰዎች አሮጌ መኪናዎች ትርፍ ሊያስገኙ እንደሚችሉ ተገለጠላቸው። ስለሆነም ብዙ አሮጌ መኪናዎች ለመቀመጫ የሚሆኑ ሦስት የእንጨት አግዳሚዎች ገብቶላቸው 21 ተሳፋሪዎች ወደሚይዝ ማጓጓዣነት ተለወጡ። እንዲህ ዓይነቱ ማጓጓዣ ከናይጄሪያው አሮጌ ቦሌኬጃስ ጋር ይመሳሰላል። እያንዳንዱ ሰው ለአንድ ጉዞ እንደ ቀድሞው ሦስት ባለ 10 ሳንቲሞችን እንዲከፍል ይደረግ ነበር። ይህ ሁኔታ መኪናዎቹ ማታቱ የሚለውን ስያሜ ያገኙበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል። ማታቱ በስዋሂሊ “ሦስት” የሚል ትርጉም ካለው ታቱ ከሚለው ቃል የተገኘ ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሰውን ይንጡ ከነበሩት የድሮ ሞዴል ማታቱዎች ተነስቶ ፍጹም ለውጥ በማድረግ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል። አዎን፣ የዛሬዎቹ ማታቱዎች ለዓይን የሚማርኩ መኪናዎች ሲሆኑ አንድ የኬንያ ዕለታዊ ጋዜጣ “እንደ ጀት ሾጠጥ ያሉና በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች” ሲል ገልጿቸዋል። እንዲህ የተባለው የ1960ዎቹ የጎጆ ኢንዱስትሪ ያፈራው ማታቱ አይደለም!
በማታቱ መጓዝ በተለይ ደግሞ በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚፈጠርበት ጊዜ ሾፌሩ እየተሹለከለከ ሲነዳ ልዩ ስሜት ይፈጥራል! እስቲ ናይሮቢ ውስጥ በማታቱ ተሳፍረን አጭር ጉዞ እናድርግና ምን ስሜት እንደሚፈጥር እንመልከት።
ማራኪ ውበት
ጉዞ የምንጀምረው በብዙ ደርዘን የሚቆጠሩ ማታቱዎች ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ለመሰማራት ቆመው በሚጠባበቁበት መናኸሪያ ውስጥ ነው። ጊዜው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን መናኸሪያው ወደሚፈልጉበት ቦታ የሚያደርሳቸውን ማታቱ ለማግኘት ወዲያና ወዲህ በሚተራመሱ ሰዎች ተጨናንቋል። አንዳንድ መንገደኞች ረጅም ርቀት ተጉዘው ወደ ክፍለ ሃገር የሚሄዱ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ከመሃል ከተማው ወጣ ብለው ምናልባትም ምሳቸውን ቶሎ በልተው መመለስ የሚፈልጉ ናቸው። ለዚህ ማታቱ የልብ አድርስ ነው።
አብዛኞቹ ማታቱዎች በደማቅ ቀለማት ያሸበረቁ መሆናቸውን አስተውለሃል? እንዲህ የሚደረገው እንዲያው መልካቸውን ለማሳመር ብቻ ሳይሆን በጣም በሚያምር ማታቱ ላይ መሳፈር የሚመርጡ ተሳፋሪዎች ስላሉ ነው። ማታቱዎችን ቀረብ ብለን ስናያቸው የተለያዩ ስሞች ተጽፎባቸው እንመለከታለን። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል አንዳንዶቹ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚገልጹ ናቸው። ለምሳሌ ያህል “ኤል ኒኞ፣” “ሚሌኒየም፣” “ዚ ዌብ ሳይት፣” “ኢንተርኔት” እንዲሁም “ዶት ኮም” የሚሉት ይገኙበታል። “ሚክ (የዋህ)” እና “ሚሽነሪ” እንደሚሉት ያሉት ደግሞ ተወዳጅ የሆኑ የሰው ባሕርያትን ወይም የሥራ ክንውኖችን የሚገልጹ ናቸው። በቀለማት በማሸብረቅ ረገድ ከማታቱ ጋር ይበልጥ የሚመሳሰለው የፊሊፒንሱ ጂፕኒ ነው። የሚገርመው ጂፕኒም የተመረተው በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ነው።
ተሳፋሪ ለማግኘት የሚደረገው ጥሪ አንድ ራሱን የቻለ ትእይንት ነው። በመኪናው የፊት መስታወት ላይ የሚቀመጠው ምልክት ማታቱው የሚሄድበትን መስመር የሚጠቁም ቢሆንም ረዳቶች ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ ይጮሃሉ እንዲሁም ሾፌሮች ሙዚቃውን ከፍ አድርገው ይከፍታሉ። በአንዳንድ ማታቱዎች ላይ “ኢየሩሳሌም” ወይም “ኢያሪኮ” የሚሉ ምልክቶችን ብታይ አይግረምህ። በእነዚህ ማታቱዎች ብትሳፈር መድረሻህ መካከለኛው ምሥራቅ ሳይሆን በምሥራቅ ናይሮቢ ወጣ ብለው የሚገኙ በእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስሞች የሚጠሩ ቦታዎች ይሆናል። ረዳቶች እያንዳንዱን ተሳፋሪ ወደ ራሳቸው ማታቱ ለማስገባት በሚያደርጉት ጥረት ብዙ ተሳፋሪዎች የትኛውን እንደሚሳፈሩ ግር ቢላቸው ምንም አያስገርምም!
እስቲ ስትሮውቤሪ (እንጆሪ) በተባለው ማታቱ እንሳፈር! ጉዞውም እንደ እንጆሪ ሁሉ አስደሳች ይሆንልናል ብለን እናምናለን። ብዙ ተሳፋሪዎች ይህን ማታቱ የሚመርጡት ቶሎ ስለሚሞላ ነው። ጣሪያው ላይ ከተገጠሙት አነስተኛ መጠን ያላቸው ድምፅ ማጉያዎች የሚሰማው ለስለስ ያለ ሙዚቃ ተሳፋሪው ዘና እንዲል ያደርጋል። ይሁን እንጂ በሁሉም ማታቱዎች ላይ የሚሰማው ሙዚቃ እንዲህ ነው ብለህ እንዳታስብ። አንዳንዶቹ መቀመጫዎቻቸው ሥር ጆሮ የሚጠልዝ ሙዚቃ የሚያሰሙ አንዳች
የሚያክሉ ድምፅ ማጉያዎች አሏቸው። ሁሉም ወንበሮች ከተያዙ አሥር ደቂቃ አልፎታል። የተሳፈርንበት ማታቱ ግን አንዲት ጋት ታክል እንኳ እልፍ አላለም። ቶሎ የማንሄደው ለምንድን ነው? በወንበሮች መካከል ያለው መተላለፊያ ቆመው በሚጓዙ ተሳፋሪዎች መሙላት ስላለበት ነው። ትንሽ ቆይቶ ለመላወስ እንኳን የሚያስችል ቦታ ማግኘት አይቻልም። እንዲያውም ማታቱው ገና በየመንገዱ እየቆመ ተጨማሪ መንገደኞችን ማሳፈሩ አይቀርም።በመጨረሻ ጉዞ ጀመርን። ከዚያ በፊት ፈጽሞ የማይተዋወቁ ተሳፋሪዎች በዕለቱ ለብዙዎች መነጋገሪያ በሆነ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሞቅ ያለ ጭውውት ማድረግ ጀመሩ። ቦታው የደራ ገበያ መሰለ። ሆኖም ጨዋታው እንዳያታልልህ ተጠንቀቅ። አንዳንዶች ሞቅ ያለ ጨዋታ ይይዙና የሚወርዱበትን ቦታ አልፈው ይሄዳሉ።
ማታቱዎች እንደልባቸው እንደሚከንፉ መጥቀሳችን አይዘነጋም። የሚፈልጉት ቦታ ለመድረስ እያቆራረጡ ይጓዛሉ። ሾፌሩ ቶሎ ደርሶ መመለስ ስለሚፈልግ በሚያገኘው ክፍት ቦታ ሁሉ እንዲያውም አንዳንዴ ሰዎችን ለጥቂት እየሳተ በእግረኛ መንገድ ላይ ይነዳል። በነገራችን ላይ የረዳቱ ሥራ እንዲህ ቀላል አይደለም። ከሚንጫጩ ተሳፋሪዎች ላይ ሒሳብ የሚቀበል ሲሆን አንዳንዶቹ ለመክፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። ሆኖም በትንሽ ትልቁ መነታረክ የሚፈልጉትን በመለማመጥ ጊዜ አያጠፋም። ወይ ተሳፋሪው ይከፍላል አለበለዚያ ማታቱው ወዲያው ይቆምና እንዲወርድ ይነገረዋል። አንዳንድ ጊዜ ማመናጨቅም ይኖራል! ወራጅ ሲኖር ረዳቱ ተሳፋሪ መኖሩን ለማጣራት ውጪ ውጪውን እየተመለከተ ለሾፌሩ ይነግረዋል። በፉጨት፣ ጣሪያውን መታ መታ በማድረግ ወይም እንዲያመች ተብሎ በሩ አካባቢ የተደረገውን ደወል በመጫን ለሾፌሩ ምልክት ይሰጠዋል። ለሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ መኪናዎች ተብሎ የተዘጋጁ መኪና ማቆሚያ ቦታዎች ቢኖሩም ማታቱዎች ለማሳፈርም ሆነ ተሳፋሪ ለማውረድ በፈለጉት ቦታና ጊዜ ይቆማሉ።
አሁን ከመሃል ከተማ ወጥተን አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ወደሚወርዱበት የከተማው ዳርቻ ደርሰናል። ማታቱው ወደ ተነሳበት መናኸሪያ ሊመለስ ነው። በየመንገዱ እየቆመ ሰው እያሳፈረ ይሄዳል። እነዚህም የእኛው ዓይነት ሁኔታ ይጠብቃቸዋል። ምቾት አይኑረው እንጂ በስትሮውቤሪ ማታቱ ያደረግነው ጉዞ አስደሳች ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
አገልግሎታቸው ይቀጥላል
በኬንያ በአማካኝ 30,000 መኪናዎች አገልግሎት የሚሰጡበት የማታቱ ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ከአሥርተ ዓመታት በፊት ከጦርነት ከተረፈ አንድ መኪና ተነስቶ ብዙ ሚልዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ሰፊ ተቋም ለመሆን በቅቷል። ይሁን እንጂ ማታቱዎች እንደልባቸው የመክነፋቸው
ጉዳይ አንዳንድ ችግሮች ማስከተሉ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል የማታቱ ሾፌሮች ሌሎች የመንገድ ተጠቃሚዎች የሚያከብሯቸውን የትራፊክ ሕጎች በተደጋጋሚ ይጥሳሉ የሚል ወቀሳ ስለሚሰነዘርባቸው ባለ ሥልጣኖች ይህን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሥርዓት ለማስያዝ የተለያዩ ደንቦችን ሥራ ላይ አውለዋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የወጣውን ደንብ ለመቃወም የሥራ ማቆም አድማ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም ምክንያት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በማታቱ ላይ የተመካው በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ችግር ላይ ሲወድቅ ይታያል። ምንም እንኳን ማታቱዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንገድ በሁሉም ዘንድ አድናቆት የሚቸረው ባይሆንም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ፈጣን የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ጥሩ አማራጭ ሆነዋል።[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 አንድ የኬንያ ሽልንግ በ100 የኬንያ ሳንቲም ይዘረዘራል። አንድ የአሜሪካ ዶላር በ78 ሽልንግ ገደማ ይመነዘራል።
[በገጽ 26 እና 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፎርድ ቴምስ ሞዴል
[ምንጭ]
Noor Khamis/The People Daily