መድኃኒቶችን በጥንቃቄ ተጠቀም
መድኃኒቶችን በጥንቃቄ ተጠቀም
ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
ሐኪምህ መድኃኒት የሚያዝልህ በምርመራ ውጤትህ፣ በሕክምና እውቀቱና ባካበተው ተሞክሮ ላይ ተመርኩዞ በቅን ልቦና እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ቢሆንም ሕመምተኛው ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ የሐኪሙ ኃላፊነት እንደሆነ ሊሰማው አይገባም። ወደ ሰውነቱ ለሚያስገባው ነገር ኃላፊነቱን የሚወስደው ሕመምተኛው ራሱ ነው።
የታዘዘልህን መድኃኒት በምትወስድበት ጊዜ አንድ የሕክምና ዶክተር የሰጧቸውን የሚከተሉትን ተግባራዊ መመሪያዎች ልብ በል:-
● ሁሉም መድኃኒቶች የራሳቸው የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ስለዚህ ምን ዓይነት መድኃኒት እንደታዘዘልህና መድኃኒቱ ሊያስከትል ስለሚችለው የጎንዮሽ ጉዳት የማወቅ መብት አለህ። ሐኪምህ ይህን ራሱ ካልነገረህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። አብዛኛውን ጊዜ ከመድኃኒቱ የሚገኘው ጥቅም ከጉዳቱ ያመዝናል። ቢሆንም ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ትችል ዘንድ በቂ መረጃ ሊኖርህ ይገባል።
● መድኃኒቶች የሚኖራቸው ውጤት ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ሐኪምህ አንድ መድኃኒት በአንተ ላይ ምን ዓይነት ውጤት ሊኖረው እንደሚችል በእርግጠኝነት ሊተነብይ አይችልም። መድኃኒቱ ያልተጠበቀ ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እያስከተለብህ እንዳለ ከተሰማህ ሐኪምህን አማክር።
● መድኃኒቱን ለምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንደሚያስፈልግህ እንዲሁም ሱስ የማስያዝ ባህርይ ያለው መሆን አለመሆኑን አጣራ።
● ተሽሎኛል ብለህ በራስህ ውሳኔ መድኃኒቱን መውሰድህን እንዳታቋርጥ ተጠንቀቅ። ያለጊዜው መድኃኒቱን ማቋረጥህ ሕመምህን ሊያባብሰው ይችላል። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ ሐኪምህን አማክር።
● ምንጊዜም የታዘዘልህን መድኃኒት ስትወስድ የሐኪም ክትትል አይለይህ።