በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጅ በገዛ እጁ ጉሮሮውን እየዘጋ ነውን?

የሰው ልጅ በገዛ እጁ ጉሮሮውን እየዘጋ ነውን?

የሰው ልጅ በገዛ እጁ ጉሮሮውን እየዘጋ ነውን?

“ዛሬ ፈታኝ የሆነብን ነገር ዕዳ እና የገንዘብ እጥረት ወይም ዓለም አቀፉ የገበያ ውድድር ሳይሆን የሕይወት ምሰሶ የሆነውን የፕላኔታችንን ሕይወት ክልል (biosphere) ሳንጎዳ የተሟላና አርኪ ሕይወት መኖር ነው። የሰው ዘር የዛሬውን ያህል ስጋት አንዣብቦበት አያውቅም። ለሕልውናችን ወሳኝ የሆኑት ንጥረ ነገሮች ሊጠፉ ተቃርበዋል።”​—⁠የጀነቲክስ ተመራማሪው ዴቪድ ሱዙኪ

በአንዳንድ ቦታዎች ፖም እንደ ልብ የሚገኝ በመሆኑ እምብዛም ትኩረት አይሰጠው ይሆናል። ፖም በብዛት በሚበቅልበት አካባቢ የምትኖር ከሆነ በፈለግህ ጊዜ እንደምታገኘው ታስብ ይሆናል። ይበልጥ ደስ የሚያሰኘው ደግሞ ከብዙ የፖም ዓይነቶች ማማረጥ የምትችል መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ዛሬ ያለህ ምርጫ ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ እንደሆነ ታውቃለህ?

ከ1804 እስከ 1905 ባሉት ዓመታት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 7,098 የፖም ዓይነቶች ይበቅሉ ነበር። ዛሬ ግን ከእነዚያ መካከል 6,121 የሚያክሉት ማለትም 86 በመቶዎቹ ጠፍተዋል። ፒር የተባለውም ፍሬ የገጠመው ዕጣ ተመሳሳይ ነው። በአንድ ወቅት ይበቅሉ ከነበሩት 2,683 የፒር ዓይነቶች መካከል 88 በመቶ የሚያክሉት ጠፍተዋል። ወደ አትክልቶች ስንመጣ ደግሞ ቁጥሩ ይበልጥ አስደንጋጭ ነው። ሕይወታዊ ሀብት (biodiversity) የሚባለውን ነገር እያጣን ነው። ይህ ሲባል እየጠፋ ያለው የሕያዋን ፍጥረታት ዝርያ ብቻ ሳይሆን በአንዱ ዝርያ ሥር ያሉ የተለያዩ ዓይነቶችም ጭምር ናቸው። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየአትክልት ዝርያው ሥር የነበሩት ዓይነቶች እየተመናመኑ መጥተው 97 በመቶ የሚያክሉት ከ80 ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጠፍተዋል! ይሁንና የዓይነት ልዩነት መኖሩ ይህን ያህል ለውጥ ያመጣልን?

ብዙ ሳይንቲስቶች ለውጥ እንደሚያመጣ ይናገራሉ። ሕይወታዊ ሀብት ያለው ሚና አሁን ድረስ አከራካሪ ቢሆንም በርካታ የአካባቢ ጥናት ባለሙያዎች በምድር ላይ ላለው ሕይወት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባሉ። በምድር ዙሪያ በየጫካው፣ በየዱሩና በየሜዳው ለሚበቅሉት ዕፅዋትም ሆነ ለምግብነት ለሚውሉት ዕፅዋት ጠቀሜታው እኩል መሆኑን ይናገራሉ። በአንድ ዝርያ ሥር የሚካተቱ ዓይነቶች መኖራቸውም ለውጥ ያመጣል። ለምሳሌ ያህል በርካታ የሩዝ ዓይነቶች መኖራቸው የተለመዱ ችግሮችን መቋቋም የሚችሉ የሩዝ ዓይነቶች የሚኖሩበትን አጋጣሚ ከፍ ያደርገዋል። በመሆኑም ወርልድ ዎች የተባለው ተቋም በቅርቡ ያወጣው አንድ ጽሑፍ እንደጠቆመው ምድራችን ላይ ያለው ሕይወታዊ ሀብት እንዲመናመን ማድረግ ያለውን አደገኛነት ለሰው ልጅ ከምንም ነገር በላይ የሚያስገነዝበው ነገር ይህ አድራጎት በምግብ እህሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው።

የዕጽዋት መጥፋት በምግብ እህል ላይ ቢያንስ በሁለት መንገድ ተጽዕኖ ይኖረዋል። አንደኛ በእርሻ የሚለሙትን አዝርዕት የዱር ዝርያዎች በማጥፋት ሲሆን (እነዚህ የዱር ዝርያዎች ወደፊት ሌሎች ዝርያዎችን ለማራባት የጂን ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ) ሁለተኛው ደግሞ በእርሻ በሚለሙት ዝርያዎች መካከል ያለውን ዓይነት በቁጥር በመቀነስ ነው። ለምሳሌ ያህል እስያ ውስጥ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በግምት ከ100, 000 የሚበልጡ የአካባቢው የሩዝ ዓይነቶች ጥቅም ላይ ውለው የነበረ ሲሆን በሕንድ ብቻ በትንሹ 30, 000 የሩዝ ዓይነቶች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን ከሕንድ የሰብል ምርት 75 በመቶ የሚሆነው በአሥር ዓይነቶች ብቻ የተወሰነ ነው። በስሪ ላንካ የነበሩት 2,000 የሩዝ ዓይነቶች በሙሉ ዛሬ ባሉት 5 የሩዝ ዓይነቶች ተተክተዋል። የበቆሎ አገር እንደሆነች የሚነገርላት ሜክሲኮ ዛሬ የምታበቅለው በ1930 ከነበሯት የበቆሎ ዓይነቶች መካከል 20 በመቶ የሚያክሉትን ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ አስጊ ሁኔታ ላይ ያለው የምግብ አቅርቦት ብቻ አይደለም። በመድኃኒት ፋብሪካዎች ከሚመረቱት መድኃኒቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት የሚቀመሙት ከዕጽዋት ሲሆን ለመድኃኒት ቅመማ የሚያገለግሉ ተጨማሪ ዕጽዋት እየተገኙ ነው። ይሁንና በየጊዜው የዕጽዋት ዝርያዎች እየጠፉ ነው። የተቀመጠበትን ቅርንጫፍ እንደሚገዘግዝ ሰው ሳንሆን ቀረን ብለህ ነው!

የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ድርጅት እንዳለው ከሆነ ጥናት ከተደረገባቸው 18,000 የዕጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች መካከል ከ11,000 በላይ የሚሆኑት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እንደ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያና ላቲን አሜሪካ ባሉት ለእርሻ ሲባል ስፋት ያለው ደን በሚመነጠርባቸው አካባቢዎች ተመራማሪዎች ምን ያህል ዝርያዎች ሊጠፉ እንደተቃረቡ ወይም እንደጠፉ በትክክል ለመናገር እንኳ ይቸገራሉ። ያም ሆኖ ዘ ዩኔስኮ ከሪየር እንደዘገበው አንዳንዶች ዝርያዎቹ የሚጠፉበት “ፍጥነት አስደንጋጭ” መሆኑን እየተናገሩ ነው።

እርግጥ ምድር አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው የእህል ምርት እየሰጠች ነው። ይሁን እንጂ ምድር ላይ ያለው ሕይወታዊ ሀብት እየተመናመነ ከሄደ ቁጥሩ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ያለው የሰው ልጅ በልቶ ማደር የሚችለው እስከ መቼ ድረስ ይሆን? የተለያዩ አገሮች የአንዳንድ አስፈላጊ ዕፅዋት ዝርያ እንዳይጠፋ ለመከላከል እንደ ዋስትና ይሆናል ያሉትን የዘር ማከማቻ ባንክ በማቋቋም ስጋታቸውን ለማቃለል ሞክረዋል። አንዳንድ የዕጽዋት መጠበቂያ የአትክልት ቦታዎች ዝርያዎች እንዳይጠፉ የመከላከሉን ተግባር እያከናወኑ ነው። ሳይንስ ደግሞ ጀነቲካዊ ምሕንድስና የተባለውን ለውጥ የማምጣት ኃይል ያለው አዲስ ዘዴ አበርክቷል። ይሁን እንጂ የዘር ማከማቻ ባንክና ሳይንስ ለችግሩ መፍትሔ ያመጣሉን? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጥያቄ የሚዳስስ ይሆናል።