አምላክ የባሪያ ንግድን አቅልሎ ይመለከተዋልን?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ የባሪያ ንግድን አቅልሎ ይመለከተዋልን?
ሰውነታቸው በላብ የተጠመቀ ጥቁሮች ለሁለት የታጠፉ እስኪመስል ድረስ በከባድ የጥጥ ሸክም ጎብጠው ወደ መርከብ ሲወጡና ሲወርዱ ይታያል። ጨካኝ የሆኑ አሠሪዎቻቸው ካልለፋ ቆዳ በተሠራ ጅራፍ እየገረፉ ያጣድፏቸዋል። ጩኸት የሚያሰሙ ልጆች ሲቃ ይዟቸው ከሚያነቡ እናቶቻቸው ጉያ እየተነጠቁ ከፍተኛ ዋጋ ለጠሩ ተጫራቾች ይሸጣሉ። ስለ ባርነት ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጣው እንዲህ ያለው የከፋ የጭካኔ ድርጊት ይሆናል።
የሚያስገርመው ብዙዎቹ የባሪያ ነጋዴዎችና ባለቤቶች በጣም ሃይማኖታዊ ሰዎች እንደነበሩ ይነገራል። ታሪክ ጸሐፊው ጄምስ ዌልቪን እንዲህ ብለው ነበር:- “ባሪያዎቹን ለዚሁ ተብለው በተሠሩት መርከቦቻቸው ውስጥ በመጫን ባሕሩን አቋርጠው ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲጓዙ፣ አፍሪካ ውስጥ ይህን የመሰለ ትርፋማና አስተማማኝ የሆነ ንግድ በመስጠት ስለባረካቸው ጌታን የሚያመሰግኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ነበሩ።”
እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች አምላክ የባሪያ ንግድን አይቃወምም በማለት ተከራክረዋል። ለምሳሌ ያህል አሌክሳንደር መኬይን የሜቶዲስት ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን በ1842 ባደረገው አንድ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ በሰጡት ንግግር የባሪያ ንግድ “ራሱ አምላክ የፈቀደው ነገር ነው” በማለት ተናግረዋል። መኬይን ትክክል ነበሩን? አምላክ በመኬይን ዘመን የነበረውን የባሪያ ንግድ ለይተው የሚያሳውቁትን ሴቶችን አፍኖ እንደ መውሰድ፣ አስገድዶ እንደ መድፈር፣ ቤተሰብን ርህራሄ በጎደለው መንገድ እንደ መነጣጠልና ጭካኔ የተሞላበትን ድብደባ እንደ ማካሄድ የመሳሰሉትን ድርጊቶች ይደግፋልን? ዛሬስ ዘግናኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ልክ እንደ ባሪያ እየተገዙ ለመኖርና ለመሥራት ስለተገደዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ እንዲህ ያለውን ኢሰብዓዊ አያያዝ አቅልሎ ይመለከተዋልን?
ባርነትና እስራኤላውያን
መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 8:9 NW ) ምናልባትም የዚህን አባባል እውነተኛነት ጨቋኝ ከሆነው የባርነት ሥርዓት ይበልጥ የሚያረጋግጥ ነገር አይኖርም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይሖዋ አምላክ ባርነት በሰው ልጅ ላይ ያስከተለውን መከራ አቅልሎ አይመለከትም።
ለምሳሌ ያህል በእስራኤላውያን ላይ ደርሶ የነበረውን ሁኔታ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ግብፃውያን እስራኤላውያንን “በጽኑ ሥራ፣ በጭቃ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር” በማለት ይነግረናል። እስራኤላውያን “ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፣ ጮኹም፣ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ።” ይሖዋ ለጩኸታቸው ግድ የለሽ ነበርን? አልነበረም። ዘጸአት 1:14፤ 2:23, 24፤ 6:6-8
ከዚህ ይልቅ “የልቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፣ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ።” ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገራቸው:- “ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፣ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ።”—ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ጨቋኝ በሆነው የባርነት ሥርዓት ‘ሰው ሰውን እንዲገዛ’ አይፈልግም። ግን አምላክ ቆየት ብሎ በሕዝቡ መካከል ባርነት እንዲኖር ፈቅዶ የለምን? አዎን፣ ፈቅዷል። ይሁን እንጂ በእስራኤል የነበረው ባርነት በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከታዩት ጭካኔ የተሞላባቸው የባርነት ዓይነቶች ፈጽሞ የተለየ ነበር።
የአምላክ ሕግ ሰውን አፍኖ መውሰድም ሆነ መሸጥ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ ባሪያዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችሉ መመሪያዎች ሰጥቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ጌታው የአካል ጉዳተኛ ያደረገው ባሪያ በነፃ ይለቀቅ ነበር። አንድ ባሪያ ጌታው ደብድቦት ከሞተ ገዳዩ በሞት ይቀጣ ነበር። ሴት ምርኮኞችን ባሪያዎች አሊያም ሚስቶች ማድረግ ይቻል የነበረ ቢሆንም እንዲሁ የጾታ ፍላጎት ማርኪያ እንዲሆኑ ማድረግ ግን ፈጽሞ የተከለከለ ነበር። የሕጉ መንፈስ ቅን ልብ ያላቸው እስራኤላውያን ባሮቻቸውን ቅጥር ሠራተኞች እንደሆኑ አድርገው በመቁጠር በአክብሮትና በደግነት እንዲይዟቸው ገፋፍቷቸው መሆን አለበት።—ዘጸአት 20:10፤ 21:12, 16, 26, 27፤ ዘሌዋውያን 22:10, 11፤ ዘዳግም 21:10-14
አንዳንድ አይሁዳውያን እዳቸውን ለመክፈል ሲሉ በፈቃደኝነት የሌሎች አይሁዳውያን ባሪያ ይሆኑ ነበር። እንዲህ ያለው ልማድ ሰዎች እንዳይራቡ ከማድረጉም በላይ ብዙዎችን ከድህነት ቀንበር አላቅቋቸዋል። በተጨማሪም ባሪያዎች ከፈለጉ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር ጉልህ ስፍራ በሚሰጣቸው ዓመታት ነፃ ይለቀቁ ነበር። * (ዘጸአት 21:2፤ ዘሌዋውያን 25:10፤ ዘዳግም 15:12) አይሁዳዊው ምሁር ሞሰስ ሚልዚነር ባሪያዎችን አስመልክቶ በተሰጡት ሕጎች ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲገልጹ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ምንጊዜም ቢሆን አንድ ባሪያ እንደ ማንኛውም ሰው ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ባሪያው ሰብዓዊ መብቶች ያሉት ሰው ተደርጎ ይታይ የነበረ ከመሆኑም በላይ በዚህ ጉዳይ ጌታው እንኳ ጣልቃ መግባት አይችልም ነበር።” ይህ በታሪክ ገጾች ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው ካለፉት በጭካኔ የተሞሉ የባርነት ሥርዓቶች ምንኛ የተለየ ነው!
ባርነትና ክርስቲያኖች
ባርነት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይኖሩበት የነበረው የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ኢኮኖሚያዊ መዋቅር አካል ሆኖ ቆይቷል። ስለዚህ አንዳንድ ክርስቲያኖች ባሮች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ባሮች ነበሯቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:21, 22) ታዲያ ይህ ማለት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ባሮቻቸውን የሚጨቁኑ ጌቶች ነበሩ ማለት ነው? በፍጹም! የሮማ ሕግ ምንም ይበል ምን ክርስቲያኖች ባሪያዎቻቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንደማይዟቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ወደ ክርስትና የተለወጠውን አናሲሞስ የተባለ ባሪያውን እንደ ‘ወንድሙ’ አድርጎ እንዲይዘው ፊልሞናን አበረታትቶታል። *—ፊልሞና 10-17
ሰው ሰውን በባርነት መግዛቱ አምላክ ለሰው ልጅ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ክፍል እንደነበረ የሚጠቁም ምንም ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አናገኝም። ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች የሌሎች ሰዎች ባሪያዎች እንደሚሆኑ የሚያመለክት ጥቅስ የለም። ከዚህ ይልቅ በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ጻድቅ “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4
ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች በየትኛውም ዓይነት መንገድ እንግልት እንዲደርስባቸው አይፈቅድም። ከዚህ በተቃራኒ በሰዎች መካከል እኩልነትና አክብሮት እንዲሰፍን ያበረታታል። (ሥራ 10:34, 35) ሰዎች እነርሱ ሊያዙ በሚፈልጉበት መንገድ ሌሎችን እንዲይዙ አጥብቆ ያሳስባል። (ሉቃስ 6:31) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች የትህትና ባሕርይ በማዳበር ሌሎች ያሉበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ከእነርሱ እንደሚበልጡ አድርገው እንዲያስቡ ያበረታታል። (ፊልጵስዩስ 2:3) እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተለይ ከቅርብ መቶ ዓመታት ወዲህ በብዙ አገሮች ከታዩት ጭካኔ የተሞላባቸው የባርነት ዓይነቶች ጨርሶ ተቃራኒ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.11 አንዳንዶች ከፈለጉ ከጌቶቻቸው ጋር መኖራቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉ በእስራኤላውያን ዘንድ የነበረው ባርነት ጨቋኝ አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል።
^ አን.13 ዛሬም በተመሳሳይ አንዳንድ ክርስቲያኖች ቀጣሪዎች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ተቀጣሪዎች ናቸው። አንድ ክርስቲያን ቀጣሪ በሠራተኞቹ ላይ በደል እንደማያደርስ ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም በባሪያዎቻቸው ላይ ከክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓት ውጪ የሆነ ነገር እንደማያደርጉባቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴዎስ 7:12